(አጠር ያለ የሐጅና ዑምራ አፈጻጸም)
ሐጅና ዑምራ ማድረግ በህይወት አንድ ጊዜ ብቻ ነው ግዴታ የሚሆነው ከዛ በተረፈ ያለው ሱናና ወንጀል ማራገፊያ ነው ሐጅ ከእስልምና መእዘናት አንዱ በመሆኑ ግዴታነቱን ያስተባበለ ከዲነል ኢስላም ይወጣል ግዴታ መሆኑን ከማመን ጋር ማድረግ እየቻለ በግዴለሽነት ሳያደርግ የሞተ አሏህ ዘንድ ይጠየቃል ከፍተኛ ቅጣትም ይጠብቀዋል::
ሐጅ ግዴታ የሚሆነው፥ የሚከተሉት መስፈርቶች ሲሟሉ ነው
1ኛ: ሙስሊም መሆን , ካፊር ቢያደርግ እንኳ ተቀባይነት አይኖረውም
2ኛ: ለአካለ መጠን መድረስ, ህጻናት ግዴታ አይሆንባቸውም ቢያደርጉ ተቀባይነት ይኖረዋል ነገር ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ በድጋሜ ማድረግ አይቀርላችውም
3ኛ: ከባርነት ነጻ መሆን, ባሪያ እራሱም ንብረቱም የአለቃው በመሆኑ ነጻ እስካልወጣ ወይም አለቃው እስካልፈቃደለት ሀጅ ግዴታ አይሆንበትም
4ኛ: አቅም መኖር, አቅም ያሌለው ሰው ግዴታ አይሆንበትም አቅም ማለት ጤና ገንዘብ እና የመንገድን ጸጥታና ሰላም ያካትታል
5ኛ: ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱንም ጾታዎች የሚመለከቱ ሲሆን ሴት ልጅ በተጨማሪ, መሕረም (አብሯት የሚጓዝ የቅርብ የስጋ ዘመድ ለምሳሌ፥ አባት፣ ባል፣ ልጅ፣ ወንድም፣ አጎት ወዘተ) ሊኖራት ይገባል:: መሕረም ካሌላት እርሷ ላይ ሀጅ ግዴታ አይሆንም ያለ መሕረም የተጓዘች እንደሆነም ወንጀለኛ ትሆናለች:: ጉዞው በባህር ላይም ይሁን በየብስ፣ በሰዓታት የሚጠናቀቅም ይሁን በቀናት፣ ከሷ ጋር ብዙና ታማኝ ወንዶችና ሴቶችም ይኑሩ ብቻዋን ሁሉም ያውነው አይቻልም:: ይቻላል ያለ ሰው ከነቢዩ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም አንደበት ወይም ከቀደምት ዑለሞቻችን የጋራ ስምምነት ማስረጃ ማምጣት ይኖርበታል መቼም አያገኝም!
በርግጥ አንዳንድ ዑለሞች "ግዴታ ለሆነው (ለመጀመሪያ ዙር ለሚደረገው) ሐጅ ሴት ልጅ ለደህንነቷ ምንም ካልሰጋች እና መንገድ ሰላም ከሆነ እንዲሁም ከሷ ጋር አሏህን የሚፈሩ ሴቶች ካሉ መሄድ ትችላለች" በለዋል ይህም ከላይ እንደተገለጸው ሶስት መስፈርቶችን አስቀምጠው ነው 1ኛ: ግዴታ ለሆነው ሀጅ ከሆነ 2ኛ: ክብሯ ይነካል ብላ ካልሰጋች 3:ኛ ከሷ ጋር አሏህን የሚፈሩና ታማኝ ሴቶች ካሉ ነው ይህ የተወሰኑ ፉቀሃዎች አስተያየት ሲሆን አንድም ጠንካራና ግልጽ ማስረጃ የለውም:: ይሄን ማስረጃ አልባ አስተያየት ተንተርሰው በየአመቱ ለሀጅና ዑምራ ያለ መህረም የሚጓዙ እህቶች አሏህን ሊፈሩ ይገባል!
እንዲሁም ሴቶች ተስብስበው በጋራ መሄድ ይችላሉ እያሉ በዚህ ፊትናና የቀልብ ድርቀት በበዛበት ዘመን ፈትዋ የሚሰጡ ሰዎችም ይሄንን ማድረግ ይቻላል ያሉ ፉቀሃዎች ይሄን ሲፈቅዱ ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች ከግምት ውስጥ ሊያስገቡና ልብ ሊሉ ይገባል እላለሁ
የሐጅ መስፈርቶች ከተሟሉና ወቅቱም ከደረሰ ባጠገቡ ወይም በአቅጣጫው ከሚያልፉበት ሚቃት የሚፈልጉትን የሐጅ አይነት መርጦ በመሀረም መካ ሲዘልቁ መስጂደል ሀራም በመግባት ከከዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ይጀምሩ ልክ ጠዋፉን ሲጀምሩ ወንዶች የቀኝ ተከሻቸውን መግለጥ ይኖርባቸዋል ይህም የሚደረገው ጠዋፍ ላይ ብቻ ነው ከዛ በፊትም ይሁን ከዛ በኋላም ተከሻን መግለጥ አይቻልም:: ብዙሃን የሚያደርጉት ባለማወቅ ነው ጠዋፍ የሚጀመረው በሀጀረል አስወድ ሲሆን መንካትና መሳም ከተቻል ጥሩ ነው ካልሆነ ከርቀት እጅን በማንሳት ቢስሚላህ አሏሁ አክበር በማለት ጠዋፍ ይጀመራል እሱን ለመንካትና ለመሳም በሚል መጋፋትና ሰዎችን አዛ ማድረግ በጥብቅ ይከለከላልል በተለይም ለሴቶች ጠዋፍ የሚደረገው ሰባት ጊዜ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ 3 ዙሮች ላይ ለወንዶች ፈጠን ብሎ መራመድ ሱና ነው ለሴቶች አይቻልም ይህንን ማድረግ ያልቻለ ሰው ወይም ደግሞ ከሱ ጋር ህጻናትና ሴቶች ያሉበት ሰው ቢተወው ይመረጣል ጠዋፍ ላይ ዱዓና ዚክር ማብዛት ሱና ሲሆን ጠዋፍ ላይ የሚባል እራሱን የቻለ ዱዓም ይሁን ዚክር የለም ከሀጀረል አስወድ በፊት ካለው ሩክን (ኮርነር) እስከ ሀጀረል አስወድ ድረስ ባለው ቦታ ብቻ የሚከተለው ዱዓ እንዲሚደረግ ሐዲስ ላይ ተዘግቧል { ረበና ኣቲና ፊዱኒያ ሐሰነተን ወፊል ኣኺረቲ ሐሰነተን ወቂና ዐዛበንናር}
ጠዋፍ እንደተጠናቀቀ ከተቻለ ከመቃሙ ኢብራሂም በስተጀርባ ካልተቻለም የትኛውም ቦታ ላይ ሁለት ረካ ሰላት ይሰገዳል
ከዛም ወደ ሰፋ ይኬድና ከፍታው ላይ ይወጣል ካልተቻለም ጠጋ ተብሎ ፊትን ወደ ከዕባ በማዞር ይቆምና የሚከተለው አንቀጽ እና ዚክር ይነበባል
(إِنَّ الصَّفَا وَالْمَرْوَةَ مِنْ شَعَائِرِ اللَّهِ فَمَنْ حَجَّ الْبَيْتَ أَوِ اعْتَمَرَ فَلَا جُنَاحَ عَلَيْهِ أَنْ يَطَّوَّفَ بِهِمَا وَمَنْ تَطَوَّعَ خَيْرًا فَإِنَّ اللَّهَ شَاكِرٌ عَلِيمٌ) البقرة 185
لا إله إلا الله وحده، صدق وعده ونصر عبده، وهزم الأحزاب وحده،
ከዛም ወደ መርዋ ጉዞ ይደረጋል እዛም ሰፋ ላይ የተደረገው በሙሉ ይደረጋል የቁርኣን አያውን ማንበብ ሲቀር ከሰፋ ወደ መርዋ መሄድ አንድ መመለሱ ሁለት እየተባለ ሰባት ጊዜ እንመላለሳለን መሀል አካባቢ ላይ አረንጓዲ መብራት ያለበት ቦታ ላይ ሲደረስ ለወንዶች መሮጥ ሱና ነው ለሴቶች ግን ይከለከላል:: ከዛም ሐጅ እና ዑምራን በተመቱዕ መልኩ ነይቶ የመጣ ሰው ጸጉሩን ያሳጥራል በዚህም ዑምራው ይጠናቀቃል እስከ ዙልሂጃ 8 ድረስም የሀጅና ዑምራ ኢህራም ላይ ያለ ሰው የሚከለከላቸው ነገሮች በሙሉም ይፈቀዱለታል ያለተመቱዕ ሐጅና ዑምራን አቆራኝቶ የነየተ ሰው ደግሞ ከሰዕይ በኋላ ምንም ማድረግ አይችልም እንደዛው ባለበት እስከ ዙልሂጃ 8 ድረስ ይቆያል ====ኢን ሻ አሏህ ይቀጥላል===
///አሕመድ ኣደም///