Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እንዳያመልጦት!!! ይሳተፉ ይሸለማሉ!!! በጥቂት ቀናት ውስጥ አስደማሚ ሽልማቶች!!



እንዳያመልጦት!!!
ይሳተፉ ይሸለማሉ!!!
በጥቂት ቀናት ውስጥ አስደማሚ ሽልማቶች!!

ዛሬ ዱንያ እስከ ደም ስራችን ገብታ ሁለ-ነገራችንን ተቆጣጥራዋለች፡፡ ቆመን ተቀምጠን የምናስበው ስለዱንያ ነው፡፡ አብዛሃኛው ግንኙነታችን የተመሰረተው ዱንያ ላይ ነው፡፡ ለአላህ ስንል ተዋደናል የሚሉት እንኳን ለመጥቀስ በሚያሳፍሩ ርካሽ ዱንያዊ ጥቅሞች ሲራራቁ ይታያሉ፡፡ መነፅራችን ዱንያ ነው፡፡ ልብሳቸውን ብቻ አይተን ለሰዎች የተራራቁ ደራጃዎችን እንሰጣለን፡፡ ነጭ ለባሹን እናስቀድማለን፡፡ የኔ ብጤውን ዝቅ እናደርጋለን፡፡ ለዱንያ ስንል እንወዳለን ለዱንያ ስንል እንጠላለን፡፡ ለዱንያ ስንል ባህር በረሃውን እናቋርጣለን፣ ለዱንያ ስንል እንዘምታለን፡፡ እርግጥ ነው ጌታችን (ከዱንያም ድርሻህን አትርሳ) ብሎናልና ጭራሽ ለልመና ጎዳና እስከምንወጣ እንቀመጥ ወይም አለም በቃኝ እንመንን አይባልም፡፡ አኺራችንን ግን ልታስረሳን አይገባም ነበር፡፡ ዛሬ ሶላታችን የጠፋ እቃ ማግኛ ወይም የተረሳ ነገር ማስታወሻ ሆኗል፡፡ “አላሁ አክበር” ብለን ሶላት ከገባን በኋላ ያለቪሳ ስንቱን አለም ቃኝተን፣ ያለ ሂሳብ ስንት አለም ተጉዘን “አሰላሙ ዐለይኩም” ሲባል ወደ ሀገር ቤት የምንመለሰው ስንቶች ነን? ኢማሙ ስንት እንደሰገደ አናውቀው፣ ምን እንደቀራ አናውቀው ሱብሓነላህ!! ዱንያ የት እንዳደረሰችን ተመልከቱ!! ((ተከልከሉ!!! ይልቅ ፈጣኒቱን (በፍጥነት የምታልፈዋን ህይወት ዱንያን) ትወዳላችሁ፡፡ መጨረሻይቱንም (አኺራንም) ትተዋላችሁ፡፡ (አትዘጋጁላትም))) (አልቂያማህ፡20-21)
እዚህ ላይ ነው ችግሩ፡፡ ሰው ከአኺራው ይልቅ ለዱንያው ቅድሚያ መስጠቱ፡፡ ለዱንያ ሲባል አቤት ትጋቱ! አቤት እውቀቱ! ግን ተስፈኛ ነው፡፡ ጀነትንም ይመኛል፡፡ ቢመኝስ? ሰው የተመኘውን ሁሉ ያገኛልን? መመኘት ባልከፋ፡፡ ግን በከንቱ? ወደ ደቡብ እየተጓዙ ሰሜን መድረስ ይቻላል እንዴ?! አኺራ ቀልድ አይደለም፡፡ ጤፍ ዘርቶ ባቄላ የሚጠብቅ ካለ የዋህ መሆን አለበት፡፡ ማለቴ ንክ መሆን አለበት- ትንሽ የህሊናው ቡሎን የላላበት፡፡ አንዳንዱማ ጭራሽኑ በጣም ያልፋል፡፡ የተቅዋ ታኮ ቢደረግለት እንኳ እየዘለለ ያስቸግራል፡፡ “ጀነቱን አህያ አያስርበት” እያለ እሱ ካልገባ ጀነት ባዶ እንዳትቀር “ያስፈራራል፡፡” አጉል የዋህነት!!! ለአላህ ስንት ባሮች አሉ? ዱንያን የፈቱ ለህጉ ያደሩ?! ወዳጆቼ! ጀሀነሙስ ምንድነው የሚታሰርበትና ነው እንዲህ የሚባለው? ማገዶው ሰውና ድንጋይ መሆኑ ተዘነጋ እንዴ? ያ ረቢ አንተ ከጀሀነም እሳት ጠብቀን፡፡ አንተ ካልጠበቅከን ማ ይጠብቀናል?
ወደ ርእሴ ልመለስ፡፡ ለጋሱ፣ አዛኙ፣ ቸሩ ጌታችን ትልቅ ሽልማት አዘጋጅቷል፡፡ አትጠራጠሩ፡፡ ዜናውን ያደረሰን ቢቢሲ አይደለም፡፡ ዜናውን ያደረሰን ቪ ኦ ኤም አይደለም፡፡ ዜናውን ያደረሰን አልጀዚራም አይደለም፡፡ … ውይ ረስቸው! ዜናውን ያደረሰን ኢቲቪም አይደለም! ይልቁንስ ዜናውን ያደረሰን የማይዋሸው ነብይ ነው- ሙሐመዱል አሚን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ ይሄውና የብስራቱ አዋጅ፡- “በነዚህ (የዙልሒጃ ወር)አስር ቀናቶች ውስጥ ከሚፈፀም መልካም ስራዎች በበለጠ፣ መልካም ስራዎች አላህ ዘንድ የተወደዱ የሚሆኑባቸው ቀናት የሉም” “በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ጂሀድም ጭምር?” ሲባሉ፤ “ራሱንና ንብረቱን ይዞ ወጥቶ ምንም ያልተመለሰለት ሰው ሲቀር ጂሀድም ከዚህ አይበልጥም” አሉ። ታዲያ የዘገበው ዋልታ እንዳይመስልህ፡፡ ቡኻሪ እንጂ፡፡ አከሉም “ከዱንያ ቀናት ሁሉ ብልጫ ያላቸው አስርቱ የዙልሂጃ ቀናት ናቸው፡፡” አልበዛር እና አልሐይሰሚይ ዘግበዉታል፡፡ አልባኒም ሰሂህ ብለዉታል፡፡ አከሉም፡- “ከእነዚህ አስር ቀናት በበለጠ አላህ ዘንድ ታላቅ የሆኑና መልካም ስራ እጅግ የተወደደባቸው ቀናት የሉም፡፡ ስለዚህ ተህሊል (ላኢላሀ አለላህ)፣ ተክቢር (አላሁ አክበር) እና ተሕሚድ (አልሐምዱሊላህ) (ማለትን) አብዙ” አሉ፡፡ ኢማም አህመድ ዘግበውታል፡፡ ታላቁ ሙሐዲሥ አህመድ ሻኪርም ሰሂህነቱን አረጋግጠዋል- ረሒመሁላህ።
አስተውሉ! ስለዚህ እነኚህ አስሩ የዚልሒጃ ቀናት ከአስሩ የረመዷን የመጨረሻ ቀናት እንኳ የከበሩ የሚበልጡ እንቁ ቀናት ናቸው፡፡ ማስረጃው ከላይ አልፏል፡፡ ለቀጣይ አመት መድረሳችንን አናውቅምና ይሄ እድል ሊያመልጠን አይገባም፡፡ በሶላት፣ በፆም፣ ቁርኣን በመቅራት፣ በዚክር፣ በሰደቃ፣ በማስተማር፣ … ባጠቃላይ በሚመስጠን፣ በምንችለው የዒባዳ ዓይነት ትጥቅን ጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ “በቀጣዮቹ 10 ቀናት ውስጥ በርትቶ የሰራ ሰው በየቀኑ አንድ ሺህ ዶላር ይታሰብለታል፡፡ እንደ ሰውየው ብርታትም ክፍያው ከፍ ሊል ይችላል” ቢባል ምን እንጠብቃለን? ተአምር አናይም? ተአምር አንሰማም? ወሬውን ያደረሰን ለምን ኢቲቪ አይሆንም፣ ያለወትሯችን አምነነው ወይም ተስፋችን አድልቶ ብዙ እንጥራለን፡፡ ለአኺራስ ሲሆን? አቤት የየቂን ድክመት!!! ((ከጌታችሁ ወደ ሆነች ምህረት፣ ወርዷ እንደ ሰማይና ምድር ወርድ ወደ ሆነችም ጀነት ተሸቀዳደሙ፡፡ ለነዚያ በአላህና በመልእክተኞቹ ላመኑት ተዘጋጅታለች፡፡ ይህ የአላህ ችሮታ ነው፤ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፡፡ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነውና)) (አልሐዲድ፡ 21)

ማሳሰቢያ፡
ዙልሒጃህ የሚጀምረው ከነገ ወዲያ ሀሙስ ወይም ጁሙዐ ነው፡፡ እንዳያመልጦ! ይህን የመሰለ ድግስ ደንታ ሳይሰጡት አሳልፈው ኋላ እንዳይቆጩ፡፡

ሙእሚን ለራሱ የሚወደውን ለወንድሙ የሚወድ ነው፡፡ ስለሆነም ስራዎትን ይህን መልእክት በማዳረስ ሌሎችም የኸይሩ ተካፋይ እንዲሆኑ ያድርጉ፡፡