Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሸይኽ ሙቅቢል አልዋዲዒይ ማን ነበሩ? አቡጁነይድ ሳላህ አህመድ


ሸይኽ ሙቅቢል አልዋዲዒይ ማን ነበሩ?
አቡጁነይድ ሳላህ አህመድ
==================
የዋዲዓ ጎሳ አባል የሆኑት ሸይኽ ሙቅቢል በ1351ዓ.ሒ አካባቢ በደማጅ መንደር
ተወለዱ። በአካባቢው እንደተለመደው መሰረታዊ የንባብ እና የጽሁፍ እንዲሁ
የቁርዓን ትምህርት በልጅነታቸው የተማሩት ሸይኽ ሙቅቢል የቲም ሆነው ያደጉት። በወጣትነታቸው ወደ ሳዉዲ ሄደው ባደረጉት ቆይታ በብዙ ሸይኾች የተማረኩ ሲሆን፤
ከአንድ መምህር በተጠቆሙት መሰረት “ፈትሁልመጂድ” የተሰኘውን የኪታቡ ተዉሂድ
ማብራሪያ ካነበቡ በኋላ ወደ አካባቢያቸው ደማጅ ሲመለሱ ስህተቶችን በመጠቆምና
ሀቁን በመናገራቸው ሳዕዳ ከተማ ዉስጥ በመስጂደልሀዲ የዘይዲያን መዝሀብ
እንዲማሩ ተደረጉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የየመን አብዮት መፈንዳትን ተከትሎ
እንደገና ወደ ሳዉዲ አረቢያ ሄደው በመካ ዳሩልሐዲስ እና በመዲና ኢስላማዊ ዩኒቨርስቲ ትምህርት በመከታተል ከሸሪዓ ፋኩሊቲ በዲግሪ የተመረቁ ሲሆን
ትምህርታቸውን በመቀጠል በሀዲስ ጥናት የማስተርስ ዲግሪ አጊኝተዋል። ከረጅም
ጊዜ የትምህርት ቆይታ በኋላ ወደ ትውልድ ቀያቸው በመመለስ ስመ ጥር የዒልም
ማዕከል አድርገዋታል።
በየመን እና በሳዉዲ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ላይ የተማሩ ሲሆን፤ ካስተማሯቸው
መካከል፤ ሸይኽ ሙሀመድ ናሲሩዲን አል-አልባኒ፣ ሸይኽ አብዱልዓዚዝ ኢብኑ ባዝ፣ ሸይኽ አብደላህ ቢን ሁመይድ፣ ሸይኽ ሀማድ አል-አንሳሪይ፣ ሸይኽ ሙሀመድ
አልአሚን አሺንቂጢይ እና ሸይኽ አብዱልሙህሲን አልዓባድ ይገኙበታል። በተለያዩ
ኢስላማዊ የትምህርት ዘርፎች አርባ ሰባት የሚሆኑ መጽሀፍትን ያበረከቱ ሲሆን
“አሰሂህ አልሙስነድ ሊማ ለይሰ ፊሰሂሀይን” የተሰኘው መጽሀፋቸው በሀዲስ ዘርፍ
ለሙስሊሙ ኡማህ በዚህ ምዕተ አመት ከተበረከቱ መጻህፍት ታላቅ ቦታ ይይዛል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሏቸው። በተለየዩ የየመን ከተሞች የራሳቸዉን መርከዝ ለመክፈት የበቁም ብዙ ናቸው። በየመን ከታዋቂ ተማሪዎቻቸው መካከል፤
ሸይኽ ሙሀመድ አልዊሳቢይ፣ ሸይኽ ሙሀመድ አል-ኢማም፣ ሸይኽ አብዱልዓዚዝ
አልቡረዒይ፣ ሸይኽ አብዱላህ አዘማሪይ፣ ሸይኽ ያህያ አልሀጁሪይ ፣ ሸይኽ ሙሀመድ
ቢን ሳሊህ አሱመሊይ፣ ሸይኽ አብዱረህማን አልዓደኒይ እና ሸይኽ ሳሊህ አልበክሪይ
ይገኙበታል።
ወደሀገራቸው ሲመለሱ የነበረዉን ፈተና አስመልክተው እንዲህ ይላሉ። “ወደየመን እንደመጣሁ በኖርኩበት መንደር ልጆችን ቁርዓን አስቀራ ነበር። ሀገሬንና
መንግስትን እንዲሁም ዲንን ለማጥፋት የተነሳሁ ይመስል ሁሉም ያብርብኝ ጀመር።
በዚያን ጊዜ የጎሳ አለቃም ይሁን ባለስልጣኖችን አላዉቅም። “አላህ በቂዬ ነው፣
ምንኛ ያማረ መመኪያ” እላለሁ። በጣም ከተቸገርኩ ወደ ሰንዓ፣ ዘማር፣ ተዒዝ፣
ኢብ፣ ሁደይዳህ፣ ወይም ሀሺድ በመሄድ ለዳዕዋ ወንድሞችን ለመጠየቅ እሄድ
ነበር”። በአላህ እርዳታ የዋዲዓ ጎሳ ከጎናቸው በመቆሙ ከለላ እየሰጣቸው ዳእዋቸውን ቀጥለው ስኬታማ ሆነዋል።
ሸይኽ ሙቅቢል በዙህድ የታወቁ ነበር። ለዱንያ ጥቅማ ጥቅሞች አልተበገሩም።
ብዙዉን ጊዜ በራስ መብቅቃትን ያስተምሩ ነበር። ከየመን መንግስት የሸሪዓ ፍርድ
ቤቶች መጅሊስን እንዲመሩ ተጠይቀው ለመማር እና ለማስተማር ብቻ ጊዜያቸዉን ማዋል
እንደሚፈልጉ በመግለጽ መልሰዋል። በአንድ ወቅት ወደደቡባዊው የየመን ግዛቶች
ባደረጉት ጉዞ የየመን ፕሬዝደንት መኪና በስጦታ ቢያበረክትላቸዉም አልተቀበሉትም። ደጋግሞ ሲጠይቃቸው ግን መኪናዉን ለዚህ የዳእዋ ጉዟቸው
ተጠቅመው እንደሚመልሱ በመግለጽ ተጠቅመው አስረክበዋል። ከተልያዩ አቅጣጫዎች
የሚመጡላቸዉን ስጦታዎች ባለመቀበል ይታወቃሉ። ከመሞታቸው በፊት ለተማሪዎቻቸው
እና ለመላው አህሉሱና ጠቃሚ የሆኑ ምክሮችን ያዘለ ኑዛዜ አስተላልፈዋል። ወደ
ሀገሬ ስመጣ ምንም አልነበረኝም በማለት በመርከዙ የሚገኙ መኪናዎችና ንብረቶች
በሙሉ የእሳቸው እንዳልሆኑ ገልጸው ለተማሪዎች ግልጋሎት እንዲዉሉ አዘዋል። ለቤተሰብና ቅርብ ዘመዶቻቸው የተዉት ጠቃሚ እዉቀትን እና መጽሀፎቻቸውን ብቻ
ነው። ከሰባ አመት በላይ የኖሩት ሸይኽ ሙቅቢል አልዋዲዒይ በሳውድ አረቢያ
ህክምና ሲደረግላቸው ከቆየ በኋላ በረቢዕ አልኣኺር 30/1422 ዓ.ሒ
ህይወታቸው አልፏል። የአላህ እዝነት በእርሳቸው ላይ ይሁን።