Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ስለ ኡድሂያ አጭር ማብራሪያ



ኡድሂያ- በነዚህ አስር ቀናት ከተወደዱ ተግባሮች መካከል ኡድሂያን በማረድ ወደአላህ መቃረብ ነው።

የሚከተሉት ነጥቦች አጠር ያለ ግንዘቤን የሰጣሉ፤
- ኡድሂያ በጣም ከጠነከሩ የነብዩ ه ሱናዎች መካከል ነው።የነብዩ ኢብራሂምን ሱና ህያው ከማድረጉ በተጨማሪ ለድሆች እና ችግረኞች መድረስ ነው።
- ኡድሂያን በተመለከተ አላህ ከኛ የሚፈልገው ለእርሱ ያለንን ፍራቻ (ተቅዋ) ነው።
- ኡድሂያ የሚታረደው ከዒድ ሰላት በኋላ ነው። የአላህ መልዕክተኛ ከኢድ ሰላት በፊት ያረደ ሰው እንዲደግም አዘዋል።
- ሚዛን በሚደፋው የኡለማዎች አቋም መሰረት የዒድ ሰላትከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ የሶስተኛው ቀን ጸሀይ እስክትጠልቅ ድረስ ኡድሂያን ማረድ ይቻላል።
- ወንድም ይሁን ሴት ግመል፣ የቀንድ ከብቶች፣ በግና ፍየል ለኡድሂያ ይታረዱሉ።
- የአላህ መልዕክተኛ ه እንከን ያለባቸውን እንስሳት እንዳናርድ ከልክለዋል። አንድ አይኑ የታወረ፣ ስብራት ያለበት፣ የከሳና የደከመ፣ የታመመ እንስሳ ለኡድሂያ አይሆንም።
- ኡድሂያን ለብቻ ማረድ እንደሚቻለው ሁሉ ለሰባት ሆኖ አንድን ወይፈን ወይም በሬ መጋርትም ይቻላል።
- አንድ ሰው ኡድሂያ ሲያርድ ለራሱ እና በህይወት ላሉም ይሁን በህይወት ለሌሉ ለቤተሰቦቹ አስቦ ሊያርድ ይችላል።
- ኡድሂያውን ለራሱ፣ ለስጦታ እና ለሰደቃ አድርጎ መከፋፈሉ ሱና ነው። ይህ ማለት ግን እንደ አስፈላጊነቱ ለሶስቱም ያውለዋል ማለት እንጂ ሶስት እኩል ቦታዎች ይከፋፍለዋል ማለት አይደለም።
- በዒድ ቀን ኡድሂያን ለማረድ አስቦ የዙልሂጃ ወር ከገባ ጥፍሩንና ጸጉሩን አይቆርጥም። ቆዳውንም አይቀርፍም። ይህ በሀጅ ላይ ያሉ ሰዎችን የሚመሳሰልበት ነብያዊ ትዕዛዝ ነው። ይህ የሚመለከተው የሚያርደዉን ሰው ብቻ ነው። እያወቀ ጥፍሩን ወይም ጸጉሩን የቆረጠ ወንጀል ፈጽሟልና ወደ አላህ በተውበት ሊመለስ ይገባዋል፤ ኡድሂያው ግን አይበላሽም። የመልካም ስራ በሮች ብዙ ናቸውና የቻልነዉን ሁሉ በመፈጸም ወደ
አላህ መቃረብ ይገባል፤ የታሰረን ወይም የታመመን ሰው መጠየቅ፣ ዝምድናን መቀጠል፣ ሰደቃ ማብዛት፣ ሱና ሰላቶችን ማብዛት፣ ቁርዓን መቅራት፣ ዚክር ማብዛት፣ ዱዓን ማብዛት…ወዘተ ያስፈልጋል።
አላህ በነዚህ ወርቃማ ጊዜያት ከሚጠቀሙና አላህ ዘንድ መልካም ምንዳን ከሚያገኙ ጠንካራና ብልህ የአላህ ባሮች ያድርገን።
ዝግጅት- አቡጁነይድ ሳላህ አህመድ

Post a Comment

0 Comments