Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጃሂሊያ

ጃሂሊያ
ይህ ስያሜ አረቦች ከነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መላክ በፊት የነበሩበትን የድንቁርና ዘመን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ዘመን አረቦችም ሆኑ አብዘሀኛው የአለም ህዝብ ከነብያት ሀይማኖት ራሱን ያገለለበት፣ በባእድ አምልኮ የተወጠረበት፣ በዘርና በጎሳ ወገንተኝነት የሚጋደልበት፣ ኩራትና አምባገነንነት የሰፈነበት ሰዎች የበደልና የጭካኔ ህይወት የሚገፉበት የጨለማ ትውልድ ነበር፡፡
ጃሂሊያ በኡለማዎች ዘንድ ጃሂሊያ አማ(ጠቅላይ ጃሂሊያ) እና ጃሂሊያ ኻሳ(የተናጠል ጃሂሊያ) በመባል ለሁለት ይከፈላል፡፡
1. ጃሂሊያ አማ፡- ይህ አለምን የሚያካልለው ከነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መላክ በፊት የነበረው የድንቁርናና የአላዋቂነት ዘመን ሲሆን በነቢዩ መላክ ሙሉ በሙሉ በኢስላም ጮራ ተገፎ ተወግዷል፡፡
2. ጃሂሊያ ኻሳ፡- ይህ በከፊል ሀገራት፣ ህዝቦች ወይም በከፊል ግለሰቦች የሚገኝ ሲሆን ይህ ቀጣይነት ያለውና በየዘመኑ ሊገኝ የሚችል ነው፡፡
ከዚህ እንደምንረዳው ሙሉ በሙሉ ሰዎችን የሚያካልለው ጃሂሊያ በነቢያችን(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) መላክ የተወገደ ሲሆን ከዛ በኋላ ግን ትከክለኛውን ጎዳና የያዙ አማኞች ከመኖራቸው ጋር በአንዳንድ ርእሶች ላይ የድንቁርና(ጃሂሊያ) መገለጫዎች የሚታዪባቸው ሰዎች፣ ህዝብ አሊያም ሀገር ሊኖር ይችላል፡፡
ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለው ነበር “አራት ነገሮች በኔ ኡማ ውስጥ ህዝቦቼ የማይተዋቸው የጃሂሊያ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በዘር መኮፈስ፣ በዘር መሳደብ፣ ከኮከብ ዝናብን መሻትና ሙሾ ማውረድ (ናቸው)” ሙስሊም ዘግቦታል
ይህ ሀዲስ አንዳንድ የጃሂሊያ ተግባራት በሙስሊሙ መካከል እንደሚታዩ የሚያሳይ ሲሆን ሙስሊሞች ከነኝህ መጥፎ መገለጫዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ጃሂሊያ ቢያንስም ቢበዛ ሁሉንም ሙስሊሞች ሊካለል ፈፅሞ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ዘመን ትክክለኛውን የኢስላም ግንዛቤ የያዙና ሀቅን የበላይ የሚያደርጉ ህዝቦች ቂያማ እስክትቆም እንደማይጠፉ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ በማለት ተናግረዋልና፡-
“ከኔ ኡማ የሚያዋርድም ሆነ የሚቃረን የማይጎዳት ሀቅን የበላይ በማድረግ የምትዘልቅ ጭፍራ የአላህ ትእዛዝ(ቂያማ) እስኪመጣ አትጠፋም” ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
ይሁንና ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ወዲህ የተነሱ አንዳንድ መጤ አስተሳሰብን ያዘሉ ፀሀፍት “በአላህ ሸሪዓ የሚፈርድ የለም፣ ምድር ላይ ፈሳድ ተስፋፍቷል፣ ሙስሊም መሪዎች ከፍረዋል” አና መሰል ክሶችን መነሻ በማድረግ ሙስሊም መሪዎችንና በስራቸው የሚገኘውንም ማህበረሰብ ጃሂሊያ ውስጥ ነው በማለት ያለአግባብ ሲደመድሙ ይስተዋላል፡፡ይህ አይነቱ ድምዳሜ ሙሉ በሙሉ ሙስሊሞችን የሚያከፍርና በምድር ላይ አንድም ሙስሊም እንደሌለ አድርጎ የሚያቀርብ አደገኛ ጥፋት ነው፡፡
ይህ ትውልድን በሙሉ በድንቁርና(ጃሂሊያ) መፈረጅ ቀስበቀስ የተክፊር አስተሳሰብን እያቀጣጠለ በዘመናችን እንደ ዳዒሽ(ISIS) ያሉ ሙስሊሞችን በጅምላ በማክፈር የነርሱን አስተሳሰብ ያልተከተለን ሁሉ የሚፈጁ አንጃዎች እንዲፈለፈሉ መሰረት ሆኗል፡፡ በመሆኑም እኛ ሙስሊሞች “ከኔ ወዲያ ሙስሊም” የሚሉ መፈክሮችን ወደ ጎን በማድረግ እርስበርስ በመመካከር፣ በመተራረምና በመዋደድ የጋራ ጠላቶቻችንን እየመከትን ልንቀጥል እንጂ ፈጽሞ ለዚህ መጨረሻው ዘግናኝ የሆነ እልቂትን የሚያስከትል አስተሳሰብ እጅ ልንሰጥ አይገባም፡፡ ወላሁ አዕለም
አላህ ሙስሊሞች ሁሉ አንድ ሁነን የምንዋደድና የምንፋቀር ያድርገን!

Post a Comment

0 Comments