Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ለፍትህ ናፋቂው የኢትዬጵያ ሙስሊም!!!

ለፍትህ ናፋቂው የኢትዬጵያ ሙስሊም!!!

 
ለፍትህ ናፋቂው የኢትዬጵያ ሙስሊም!!!
====================
ሰው የዘራውን ያጭዳል

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ፡፡
እንደሚታወቀው አላህ ባርያዎቹን ይፈትናል፡፡ አምነው እውነተኛውን ከውሸታሙ ለመለየት ይፈተናሉ፡፡ ሌላው ደግሞ አላህን አምፀው ታላቁንም ይሁን ሌሎች ወንጀሎችን ሰርተው ይፈተናሉ፤ በንሰሃ ይመለሱ ዘንድ ይከጀላል እና፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡፡
 ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ وَلَمْ يَلْبِسُوٓا۟ إِيمَٰنَهُم بِظُلْمٍ أُو۟لَٰٓئِكَ لَهُمُ ٱلْأَمْنُ وَهُم مُّهْتَدُونَ
እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ እነዚያ ለእነርሱ ጸጥታ (ደህንነት) አላቸው፡፡ እነሱም የተመሩ ናቸው፡፡
ሙሉ ፀጥታ፤ ደህንነት፤ መመራት የፈለገ ሁሉ ከላይ ያለውን አንቀፅ ጠንቅቆ ሊተገብር ይገባዋል፡፡
አንቀፁ ሲወርድ ሰሃባዎችን ከበዳቸው እና የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ጋር መጥተው ‹‹የአላህ መላክተኛ ሆይ! ማን ነው ከእኛ ውስጥ ነፍሱን ያልበደለ›› ብለው ጠየቁ
እሳቸውም ‹‹እናንተ እንደተረዳችሁት አይደለም፤ የአላህ ባርያ ሉቅማንን አልሰማችሁትም
 وَإِذْ قَالَ لُقْمَٰنُ لِٱبْنِهِۦ وَهُوَ يَعِظُهُۥ يَٰبُنَىَّ لَا تُشْرِكْ بِٱللَّهِ ۖ إِنَّ ٱلشِّرْكَ لَظُلْمٌ عَظِيمٌ
ሉቅማንም ለልጁ እርሱ የሚገሥጸው ሲኾን «ልጄ ሆይ! በአላህ አታጋራ፡፡ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና» ያለውን (አስታውስ)፡፡
አሁንም አላህ እንዲህ ይላል፡፡
 وَلَقَدْ أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ رُسُلًا إِلَىٰ قَوْمِهِمْ فَجَآءُوهُم بِٱلْبَيِّنَٰتِ فَٱنتَقَمْنَا مِنَ ٱلَّذِينَ أَجْرَمُوا۟ ۖ وَكَانَ حَقًّا عَلَيْنَا نَصْرُ ٱلْمُؤْمِنِينَ
ከአንተ በፊትም መልክተኞችን ወደየሕዝቦቻቸው በእርግጥ ላክን፡፡  በግልጽ ማስረጃዎችም መጡባቸው፡፡ ከእነዚያ ካመጹትም ተበቀልን፡፡ ምእመኖቹንም መርዳት በእኛ ላይ ተገቢ ሆነ፡፡
መልክተኞቹ ይዘውት የመጡትን የካዱ እና ያመፁትን አላህ ተበቀላቸው፤ ምዕመናኑንም ከመልክተኞቹ ጋር ረዳቸው፡፡ የአላህም እርዳታ በአማኞች ላይ ተገቢ ነው፡፡
አሁንም አላህ እንዲህ ይላል
إِنَّ ٱللَّهَ يُدَٰفِعُ عَنِ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓا۟ ۗ إِنَّ ٱللَّهَ لَا يُحِبُّ كُلَّ خَوَّانٍ كَفُورٍ
አላህ ከእነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡ አላህ ከዳተኛን ውለታቢስን ሁሉ አይወድም፡፡
 وَلَن يَجْعَلَ ٱللَّهُ لِلْكَٰفِرِينَ عَلَى ٱلْمُؤْمِنِينَ سَبِيلًا
አላህም ለከሓዲዎች በምእምናን ላይ መንገድን በፍጹም አያደርግም፡፡
አማኞች እምነታቸውን በሽርክ እስካልቀላቀሉ፤ አማኝ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ለካሃዲያን በአማኞች ላይ መንገድን አያደርግላቸውም፡፡

እንግዲህ ይህ ከሆነ በነዚህ አንቀፆች ላይ ያለው መልክት ወደ አገራችን መጥተን፤ ችግራችንን ልናክም ይገባናል፡፡ አንድ ሰው እምነቱ ለአላህ በጠራ ቁጥር እና ከሽርክ በራቀ ቁጥር በዱንያም በአኸይራም ፀጥታን፤ መመራትን፤ የአላህን ጥበቃ አላህ ይለግሰዋል፡፡ የአላህ ባርያዎች ከእምነታቸው ባሟሉት ቁጥር ከላይ የተዘረዘሩትን ሲያገኙ፤ በተገላቢጦሽ ከእምነታቸው ባጓደሉት ቁጥር ውርደታቸውም እንደዛው ይጨምራል፡፡

አገራችን ላይ ያሉትን ወንጀሎች በተራ ቁጥር እንደ ግዝፈታቸው እናያለን፡፡ በአላህ ፍቃድ መፍትሄው ምን መሆን እንዳለበትም እንማከራለን፡፡

1) ሽርክ፡- ይህ ታላቅ በደል ነው፡፡ ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹‹ከወንጀሎች ሁሉ ታላቁ በደል በአላህ ላይ ማጋራት ነው እሱ ፈጥሮህ ሲያበቃ››፡፡ የተፈጠርነው እሱን ለማምለክ ብቻ ሲሆን፤ ፈጣሪውም እሱ ብቻ ሆኖ ሳለ፤ እንዴት ከእርሱ ውጭ ፍጡራን ይመለካሉ? ይህ ታላቅ በደል ነው፡፡ ማንም ይሁኑ ማን ለአላህ ብቻ የሚገቡትን መብቶች ‹‹ዱዓ፤ ሰላት፤ ጠዋፍ፤ መመካት፤ መታገዝ፤ አምልኳዊ ፍራቻ፤ እርድ፤ እና የመሳሰሉትን›› ከአላህ ውጭ ላለ ማድረግ ሽርክ ነው፡፡ ሽርክን ከሌሎች ወንጀሎች የሚያከፋው ስራን ሁሉ ከዚህ በፊት የተሰራውንም አፈር ከድሜ ማብላቱ ነው፡፡

ወደ አገራችን ስንመለስ
-) ለአላህ ብቻ የሚገባውን ሱጁድ ቃጥባሬ ቀብር ላይ ይፈፀማል
-) ካዕባ ላይ ብቻ የሚፈፀመውን ጠዋፍ፤ ኑርሁሴን ቀብር ላይ ከአላህ ውጭ ላለ ይፈፀማል፡፡ እንዲያውም ‹‹ትልቁን ሃጅ ከመሄድ በፊት ትንሹን ሃጅ አናጂና መሄድ ነው›› ሁሉ እስከማለት ደርሰዋል፡፡
-) እርድ ለአላህ ብቻ ሲገባው ለአልከሶ ሸይኽ፤ ‹‹ጌቶች ደዋም›› ብለው እስከማረድ መድረስ፡፡
-) እርዳታ ከአላህ ብቻ የሚጠየቀውን ‹‹የቦረናው ደግዬ እርዱኝ አባብዬ›› ይላሉ
-) በሽርክ የተጥለቀለቁ መንዙማዎችን ቀን ሌት ቁርዓን እንደሚደመጠው ማዳመጥ ብሎ መጨፈር
-) አንዳንድ መስጂዶች ረመዳን ላይ ከአፍጥር በፊት ቀኑን ሙሉ ፆመው ውለው የሽርክ ስንኝ በጀመዓ እያሉ ስራን ማበላሸት 
-) ዱዓ አድራጊ ናቸው እየተባለ ‹‹መጋረጃ ጋርደው›› የሚቀመጡ ጠንቋዬች፤
-) ሰይፉ ጨንገሬ፤ አዳል ሞቴ፤ ወሰን ጋሎ፤ እና የመሳሰሉትን ጂኖች ማምለክ፤ ምስዋትንም ለጂኖች ማቅረብ
-) ፍርድ ይፈርዳሉ እየተባለ የነገን እናውቃለን የሚሉ ጠንቋዬች ጋር መሄድ
ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ ‹‹የነገን እውቃለሁ ባይ ዘንድ የሄደ እና እሱን የጠየቀ የ40 ሌሊት ሰላቱን አይቀበለውም፡፡›› ሙስሊም ዘግበውታል
አቡ ሑረይሪ እንደተላለፈው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ‹‹ወደ ጠንቋይ በመሄድ የሚለው የተቀበለ ሙሐመድ ላይ በወረደው ክዷል›› አቡ ዳውድ አህመድና ሃኪም
-) ባል እና ሚስትን የሚያፋታ እና የሚያጋጭ ድግምት
-) እና በጣም ብዙ ሌሎችንም አይነተቶች የሽርክ ተግባሮች

ሀይማኖቱ እንዲመቻችለት፤ ሰላምን ማግኘት የፈለገ፤ የምድር ምትክ መሆን የፈለገ፤ በጠላት ላይ የበላይ ሆኖ ተከብሮ መኖር የፈለገ ምን ማድረግ እንዳለበት አላህ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
وَعَدَ ٱللَّهُ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ مِنكُمْ وَعَمِلُوا۟ ٱلصَّٰلِحَٰتِ لَيَسْتَخْلِفَنَّهُمْ فِى ٱلْأَرْضِ كَمَا ٱسْتَخْلَفَ ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِهِمْ وَلَيُمَكِّنَنَّ لَهُمْ دِينَهُمُ ٱلَّذِى ٱرْتَضَىٰ لَهُمْ وَلَيُبَدِّلَنَّهُم مِّنۢ بَعْدِ خَوْفِهِمْ أَمْنًا ۚ يَعْبُدُونَنِى لَا يُشْرِكُونَ بِى شَيْـًٔا ۚ وَمَن كَفَرَ بَعْدَ ذَٰلِكَ فَأُو۟لَٰٓئِكَ هُمُ ٱلْفَٰسِقُونَ
‹‹አላህ እነዚያን ከእናንተ ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን እነዚያን ከእነሱ በፊት የነበሩትን እንደተካ በምድር ለይ በእርግጥ ሊተካቸው፣ ለእነሱም ያንን የወደደላቸውን ሃይማኖታቸውን ሊያደላድልላቸው፣ ከፍርሃታቸውም በኋላ ጸጥታን ሊለውጥላቸው ተስፋን ቃል ሰጥቷቸዋል፡፡ በእኔ ምንንም የማያጋሩ ኾነው ይግገዙኛል፡፡ ከዚያም በኋላ የካደ ሰው እነዚያ እነርሱ አመጸኞች ናቸው፡፡››

አላህ በሰጠን ንፁህ አእምሮ ስናየው አንቀፁ በግልፅ እንዳስቀመጠው፤ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁሉ ለማግኘት፤ አላህ እንደመስፈርት ያስቀመጠው ‹‹በእኔ ምንንም የማያጋሩ ኾነው ያምልኩኝ ይገዙኛል›› ይላል አላህ፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፤ አላህ ካዘነላቸው ባሪያዎች ውጭ፡፡ መቼም ሽርክ ተነንሰራፍቶ የአላህን እርዳታ መከጀል እላይ ባሉ አንቀፆች መሰረት አይታሰብም፡፡ አሳዛኙ ይህ አርስት እንዳይነሳ እና ሰው እንዳይነቃ ካለበት ሽርክ እና ቢድዐ ‹‹ሂክማ፤ ወቅቱ አይደለም፤ አንድነታችን....›› እና የመሳሰሉትን በመደርደር ሰውን ባለበት ጥመት ላይ እንዳይነቃ መሰናክል የሆኑት አሉ፡፡ ሊረሳ የማይገባው ግን ሰው ቢታሰር፤ ቢገረፍ፤ ቢደበደብ፤ ብሎም ቢገደል ተውሂድ እና ሱናውን አሟልቶ ከሄደ ጀነትን በአላህ ፍቃድ ሲወርስ ሽርኩን ታቅፎ ቢገደል የሚቀጥለው አለም ላይ አላህ (ጀነትን እርም አድርጎበት፤ ጀሃነም ላይ ነው መኖርያው) ታድያ ከዚህ በላይ የከፋ አለ? “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

2) ቢድዓ፡- (በዲን ላይ የተደረገ አዲስ ፈጠራ)፡፡ አንድ ኢባዳ ለአላህ ብቻ ብሎ መሰራት ሳይሆን ያለበት የነብዩንም (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱና ገጥሞ መገኘት ግድ ይለዋል፡፡

የቢድዓ ሸርነቱ በዋነኝነት ኡማውን መበታተኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ረሱል ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሰሃባዎችን በእሳቸው ሱና አንድ ካደረጉ በኋላ መልሰው ለሰሃባዎቻቸው የሚከተለውን መከሩ ‹‹ከናንተ ውስጥ የቆየ ብዙ መለያየትን ያያል፡፡ (ይህ መለያየት ሲከሰት) አደራችሁን የእኔን እና የተቀኑ ምትኮቼን (አቡበክር፤ ኡመር፤ ኡስማን፤ አልይ) ፈለግ አጥብቃችሁ ያዙ፡፡ አስጠነቅቃችኋለሁ ከአዳዲስ ነገሮች፤ እያንዳንዱ አዲስ ፈጠራ ጥመት ነው...››
-) የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ይሁኑ ቅን ምትኮቻቸው (አቡበክር፤ ኡመር፤ ኡስማን፤ አልይ) አንድም ቀን የልደት በዓልን አክብረው አያውቁም፡፡ ዛሬ መውሊድ እየተባለ ያውም ውስጡ ሰለዋት ብለው ሽርክ መንዙማ የሚሉበት፡፡ የነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) መውሊድ ብቻ ብለው አይቆሙም፤ የበደዊ፤ አገራችን ላይ ሲመጣ የአብሬት፤ የቃጥባሬ፤ አሊ ጎንደር፤ የሚዕራጅ፤ የኡለማዎች፤ የቃጥባሬ እና የመሳሰለውን ይላሉ፡፡
-) የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ይሁኑ ቅን ምትኮቻቸው (አቡበክር፤ ኡመር፤ ኡስማን፤ አልይ) አንድም ቀን ሰላት አሰግደው ሲያበቁ ወደ ህዝቡ ዞረው ዱዓ አድርገው አያውቁም፡፡ ዛሬ አብዛኛው መስጂድ ላይ ተከታዬች ከነብያችን የተላለፉ ዚክሮችን በስርዓቱ እንዳይል ኢማሙ ዱዓ ሲያደርግ ህዝቡ አሚን ብሎ የሱና ዚክሩን ይተዋል ወይንም ያጓድላል፡፡
“ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም
-) ጠሪቃ እየተባለ ቁጥር ያልተገደበባቸውን ዚክሮች ጨምሮ፤ ቀንሶ፤ ቆርጦ ቀጥሎ ከእገሌ ሸህ የተቀበልነው በማለት ሸሆቹን ዚክር ደንጋጊ ማድረግ እና ያንንም ምንም ቢመጣ እንደ ግዴታ በመውሰድ መተግበር፡፡ እና የመሳሰሉት
“ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

3) በዲን እና ዲንን በተሸከሙ ላይ ማላገጥ እና ማሾፍ፡፡
አላህ እንዲህ ይላል
  قُلْ أَبِٱللَّهِ وَءَايَٰتِهِۦ وَرَسُولِهِۦ كُنتُمْ تَسْتَهْزِءُونَ
«በአላህና በአንቀጾቹ፣ በመልክተኛውም ታላግጡ ነበራችሁን?» በላቸው፡፡
ይህ የወረደው መንገድ እንዲገፋልን ብለው ሰሃባዎች ላይ ሲቀልዱ የነበሩ ሰዎች ላይ ነው፡፡ አስገራሚው ሰዎቹ ጀሃድን የሚያክል ከባድ ኢባዳ ለመፈፀም አብረው ዘምተው አላህ ግን በዚህ ተግባራቸው የሚከተለውን አላቸው፡፡
 لَا تَعْتَذِرُوا۟ قَدْ كَفَرْتُم بَعْدَ إِيمَٰنِكُمْ ۚ
አታመካኙ፤ ከእምነታችሁ በኋላ በእርግጥ ካዳችሁ፡፡

የአላህን ብቸኛ ተመላኪነት ተውሂድ እንዲህ እያሉ ያላግጡበታል፡፡
-) ‹‹ተው እና ሂድ››
-) ‹‹ተው!›› ‹‹ሂድ!››
-) ‹‹ቅድሚያ ለእግረኛ›› እና የመሳሰለውን፡፡ 
በዘመናችን ደረሳን ሞኝ አስመስሎ ድራማ መስራት፡፡ በየጫት ቂምሃው እና ለቅሶ ቤቱ በማይቀለድባቸው ሃይማኖታዊ ጉዳዮች መቀለድ፤ ማስካካት ምን ይሆን ቅጣቱ??? “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

4) የወላጅ ሃቅ እና ዝምድናን መቁረጥ፡-
እንደሚታወቀው አላህ እና መልክተኛው በወላጅ ላይ በጎን በመዋል አዘዋል፡፡ ይህ ተረስቶ ወላጆችን መጨቃጨቅ፤ በነሱ ማፈር፤ ከነሱ ጋር መታየትን እንደ ነውር መቁጠር እና በተጨባጭ የተረጋገጠ ወሬ ደግሞ አንድ ልጅ እናቱን እደበድባለሁ ብሎ ሰው ገላግሎት ፖሊስ መጥቶ ይዞት ከቤት ወጥቷል፡፡ ልብ በሉ ስለ ሙስሊም ነው የማወራው፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

5) ሰሃባዎች የሚሰደቡበት ኪታብ እኛው ኢትዬጵያ ውስጥ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሰራጨት፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

6) በወለድ መስራት፡-
ወለድ ከአላህ ጋር ሰይፍ መማዘዝ ነው የተባለለት የወንጀሉ ክብደት፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

7) የዘረኝነት መበራከት፡-
የአላህ መላክተኛ ‹‹ጥምብ ናት ተዋት›› ይላሉ ዛሬ ‹‹የእኛ ዘር ይበልጣል እያሉ አንጋባም እስከማለት የደረሱም አሉ››፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

8) ኳስ፡-
በተለይ የኢትዬጵያ ሙስሊም ኳስ እና ፊልም የሚያይበት ጊዜ አልነበረም፡፡ የአላህ መላክተኛ ‹‹በፈተና ዘመን አላህን መገዛት ወደ እኔ ስደት እንደማድረግ ነው›› ማንም ሰው የሚያውቀው ፈተና ላይ ነን፡፡ ታድያ በዲኑ እየተፈተነ ያለ ሰው ኳስ፤ ፊልም፤ ድራማ ነው የሚያየው፤ የሽርክ መንዙማ፤ ድንበር ማለፍ ያለባቸው ነሺዳዎች ነው የሚሰማው፤ ወይንስ ቁርዓን እየቀራ እያለቀሰ አላህ ሆይ! ፈተናችንን በሃይማኖታችን ላይ አታድርገው ይላል???

ትዝብት
=====
ኢትዬጵያ ከቡርኪና ፋሶ ጨዋታ የነበራት ቀን ሽማግሌዎች ይመስክሩ መስጊዶች ጭር ብለው ነበር፡፡ ታድያ ወንድ ልጅ ጀመዓ መስገድ ግዴታው እንደሆነ እና ጀመዓ መቅረት የሙናፊቅነት ምልክት እንደሆነ አላወቀምን??? ድል ፈላጊ እና ከመከራ መውጣት የፈለገ የአላህ ባርያ ሆኖ መገኘት ግድ ይለዋል፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

9) ‹‹ኢስላማዊ›› ፊልም እና ድራማ እየተባለ ነብያትን፤ ሰሃባዎችን፤ ኡለማዎችን ክብራቸውን የሚያጎድፍ ፊልሞች ይሰራሉ፡፡ በኢስላም የሌለን ድራማ ‹‹ኢስላማዊ ቻናሎች›› ላይ ይለቀቃል፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

10) አላህ እና መልክተኛው የረገሟቸውን ሴቶች ተግባራት የሙስሊም ሴቶች ይፈፅማሉ የሚከተሉትን ይመስል
-) ቅንድብ አስቀንዳቢ
-) ቅንድብ ቀንዳቢ
-) ዊግ (አርቴፊሻል ፀጉር) ቀጣይ
-) ዊግ አስቀጣይ
-) ንቅሳት ተነቃሽ
-) ንቅሳት ነቃሽ
“ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

11) ወንዶች በየጫት ቤቱ እየተቀመጡ ገንዘባቸውን እየጨረሱ ትዳራቸውን የሚጎዱ ብሎም የሚበትኑት አሉ፡፡ ለሴት ልጅ ሊሰጡ የሚገባቸውን ወንዳዊ ስሜት በጫት አደንዝዘው እና ገድለው የስንት ባለ ትዳር ሴቶች ደስታ አጥተው የስንቶች ትዳር ተበትኗል፡፡ በጫት መርቅነው፤ ከምርቃና መነሳት ተራራ የመግፋት ያህል የሆነባቸው ስንት ወንድሞች አዛን እየሰሙ ጀመዓ ሰላት መሄድ አቅቷቸዋል፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

13) የሙስሊም ሴቶች አለባበስ ከእለት እለት እየከፋ መምጣቱ፡፡ የአላህ መላክተኛ ‹‹ለብሰው ያለበሱ›› ያሉዋቸውን ይመስል፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

14) ጫት፤ ሺሻ፤ ሲጋራ፤ አደንዛዥ እፅ የሙስሊም መገለጫ እስኪመስል ድረስ
- ነብያችን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰልመ) ጊዜን አስመልክቶ የውመል ቂያማ ትጠየቃላችሁ እያሉ፡፡ እድሜውን በምን እንዳሳለፈ እና ወጣትነቱን በምን እንዳሳለፈ ሁሉም ሰው ይጠየቃል፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

15) ሙሰልሰል እየተባለ የቱርክ፤ የግብፅ እና የተለያዩ አረብ አገራትን አክተሮች ላይ ሲያፈጡ ማምሸት፡፡ አጅነቢ ሴት እና ወንድን እያዩ ልብን ሲያደርቁ ጫት ሲቅሙ አምሽቶ ፈጅር ሰላት ማሳለፍ፡፡ ይህ አብዛኛው ሴቶች ላይ ይበረታል፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

- ኒካህን እያወገዙ ዝሙትን ....
16) አንድ አጅነቢ ወንድ እና ሴት ቦይ ፍሪንድ ገርል ፍሪንድ ተባብለው አስፋልት ለአስፋት ተቃቅፈው ሲሄዱ፤ ልጅቷን ቤት ድረስ ሲሸኛት ማንም ምንም አይናገረውም፤ ብሎም አንዳንዴ ወንድሟ ልጁን ሰላም ሊለው ሁሉ ይችላል፡፡ ልክ እንዚህ ልጆች ኒካህ እናድርግ ካሉ የሚከተለውን ትሰማለህ ‹‹እድሜዋ አልደረሰም፤ ትምህርቷን ትጨርስ፤ ቤተሰብ ታክረን……›› ዝሙቱን እና ሌላ አላህ የተላውን ሲሰሩ ይህ አባባላቸው አይደመጥም ትዳር ካሉ፤ የመሀር እና የጥሎሽ መዓት ይደረደርለታል፡፡ ወጣቱም ይህን ፈርቶ አላህ የጠላው ወንጀል ላይ የሚወድቅም አለ፡፡ “ውርደትና ክብረ ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ሆነ” ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም

ወደ ጨብጡ ልመለስ ሽርክ የሚባለው አደጋ በጣም ከባድ፤ እየሰራው ለሞተ ሰው መቼም ቢሆን ጀነት የመግባት እድል እንዳይኖረው የሚያረደርግ ነው፡፡ ከሽርክ በታች ያሉት ወንጀሎች አላህ ከፈለገ ይምራቸዋል፤ ካልሆነ ባሪያው ይቀጣበታል፤ ሲቀጣ ግን የወንጀሉን ብቻ ተቀጥቶ ወደ ጀነት ይመለሳል፡፡
ነብያችን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰልም) ሙዓዝም (ረድየላሁ አንሁም) ወደ የመን ሲልኩት እንዲህ አሉት ‹‹አንተ የምታገኛቸው አህለል ኪታቦች ናቸው፤ የመጀመሪያጥሪህ ሸሃደቱ አላኢላሃ ኢለላህ፤ ወአኒ ረሱለላህ፤ ይህን እሺ ካሉህ በቀን እና በሌሊት 5 ወቅት ሰላት አላህ አዟቸዋል……….›› ሀዲሱ በግልፅ እንደሚያሳየው

-)  አህለል ኪታቦች የአላህ ውዶች ነን ከማለታቸውም ጋር ሽርክ ውስጥ በመውደቃቸው ምክንያት የመጀመሪያ ጥሪ ተውሂድ እንዲደረግላቸው የአላህ መላክተኛ ለሙዐዝ አዘዙት፡፡
ይሄ ለኡለማዎች እና ወደ አላህ መንገድ እንጣራለን ለሚሉ ሁሉ ሽርክ ያለበት ቦታ ሁሉ መጣራት መጀመር ያለባቸው ከተውሂድ ብቻ እና ብቻ ለመሆኑ ማስረጃ ነው፡፡

-) ‹‹ይህን እሺ ካሉህ›› የሚለው ትዕዛዝ ለማንም ዳእዋ አድራጊ የተውሂድን ጉዳይ እሺ ላላሉ ሰዎች ስለ ሰላት፤ ወንድማማችነት፤ አኽላቅ እና የመሳሰሉት አይጠሩም፡፡

አንድ ኢንጂነር 10 ፎቅ ያለው ከሰራሁ በኋላ መሰረቱን እሰራዋለሁ ቢል አምኖ ገንዘቡን የሚሰጠው የለም፡፡ ምክንያቱም ያለ መሰረቱ ፎቁ ሊቆም አይችልምና፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ወደ አላህ መንገድ የሚጣራው ተጣሪ መሰረቱን (ተውሂድን እና አቂዳን) ቀድሞ ሳይጣራ እና ሰዎች ላይ ሳያስተካክል ወደ ሌላ አርስቶች የለፋውን ቢለፋ ከንቱ ልፋት ሆኖ ብቻ ነው የሚቀረው፡፡ ያለ መሰረት የሚሰራው ፎቅ ፈራሽ እንደሚሆነው ሁሉ ያለ ተውሂድ እና ሱና መሰረት የተሰራው ስራ ሁሉ ወዳቂ፤ ትቢያ ብቻ ነው ውጤቱ፡፡ ወደ አላህ መንገድ የሚጣሩ ሰዎች ሁሉ ይህን ልብ ሊሉ ይገባቸዋል፡፡

ወደ ማጠቃለያው ስንመጣ ለአላህ በተውሂድ ፍትሃዊ ሳንሆን ፍጡራን ለእኛ ፍትሃዊ ይሆኑልናል ማለት ዘበት ነው፡፡
‹‹ከ 40ሚሊዬን ሙሰሊም ውስጥ 0.01% የሚሆነው እንኳን ፌስቡክ ተጠቃሚ ባልሆነበት ሃገር ተውሂድን በፌስቡክ›› የሚል ልክ ያልሆነ አባባል እዚሁ facebook ላይ ተፅፎ ነበር፤ ሲጀምር ሰላማዊ ሰለፍ እና ሌሎችን ጥሪዎች እዚሁ በfacebook አይደል እንዴ የሚለቀቁት??? ታድያ ምን ነው ተውሂድን በፌስቡክ የሚለው ከፋቸው??? ምድር ላይ ተወርዶ በአቅም ልክ የሚሰራውን ደግሞ ፌስቡክ ላይ ሪፖርት መቅረብ የለበተትም፡፡ ቁጥር አሃዙም በጣም የተጋነነ እና ውሸት የተሞላበት ነው፡፡ የ40 ሚሊዬን 0.01% የሚመጣው 4000 ብቻ ነው፡፡ ታድያ እውነት ከኢትዬጵያ ሙስሊም 4000 ብቻ ነው ፌስቡክ የሚጠቀመው??? አላህ ሃቅን በባጢል ከመሸፋፈን ይጠብቀን፡፡ ዛሬ አብሬት እና ቃጥባሬ መውሊዳቸውን በፌስቡክ ያስተዋውቃሉ፤ ወደ ሽርካቸው በዚሁ ሚድያ ይጣራሉ፤ አህባሽ ማደናገሬያውን በዚሁ በፌስቡክ ይለቃል፡፡ ታድያ ወረድ ብላችሁ አስተምሩ የሚሉት ሰዎች እነሱስ ወረድ ብለው ለምን ማስተማሩ ከበዳቸው???

አለ በሚባል ሚድያ ሙስሊሞች ተጠቅመው ከምንም ነገር በላይ እና በፊት አንገብጋቢውን የአላህ መብት በባሪያዎቹ ላይ (ተውሂድ) ማወቅ እና ማሳወቅ ግድ ይላቸዋል፡፡ ስንት እና ስንት ገንዘብ ለኢስላማዊ ሚድያዎች (ቻናሎች፤ ሬድዬ ጣቢያዎች፤ በራሪ ወረቀቶች፤ ካሴቶች) ሲወጣ ይታያል፡፡ ግን ካለው የሽርክ እና ቢድዐ ችግር አኳያ የሚገባውን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠበት መስካሪም አይፈልግም፡፡ ሽርክ እና ቢድዐ ባለበት አገር ላይ ድራማ፤ ፊልም እያሉ የሰው አእምሮ ላይ መጫወት አላህ ዘንድ ያስወቅሳል፡፡ ይህ ሃላፍትና የጥቂት ሰዎች ሳይሆን ከምንም ነገር በፊት ጥሪው ልክ የአላህ መላክተኛ ሙዐዝን እንዳዘዙት ከተውሂድ መጀመር አለበት፡፡ እውቀት ያለው በእውቀቱ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፤ ሚድያ ያላቸው ሚድያን ተጠቅመው ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ ይህንን ታላቅ ሃላፍትና ማድረስ ግዴታ የሁሉም ነው እላለሁ፡፡

ሀይማኖቱ እንዲመቻችለት፤ ሰላምን ማግኘት የፈለገ፤ የምድር ምትክ መሆን የፈለገ፤ በጠላት ላይ የበላይ ሆኖ ተከብሮ መኖር የፈለገ ምን ማድረግ እንዳለበት አላህ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
وَعَدَ ٱللَّهُ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ مِنكُمْ وَعَمِلُوا۟ ٱلصَّٰلِحَٰتِ لَيَسْتَخْلِفَنَّهُمْ فِى ٱلْأَرْضِ كَمَا ٱسْتَخْلَفَ ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِهِمْ وَلَيُمَكِّنَنَّ لَهُمْ دِينَهُمُ ٱلَّذِى ٱرْتَضَىٰ لَهُمْ وَلَيُبَدِّلَنَّهُم مِّنۢ بَعْدِ خَوْفِهِمْ أَمْنًا ۚ يَعْبُدُونَنِى لَا يُشْرِكُونَ بِى شَيْـًٔا ۚ وَمَن كَفَرَ بَعْدَ ذَٰلِكَ فَأُو۟لَٰٓئِكَ هُمُ ٱلْفَٰسِقُونَ
‹‹አላህ እነዚያን ከእናንተ ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን እነዚያን ከእነሱ በፊት የነበሩትን እንደተካ በምድር ለይ በእርግጥ ሊተካቸው፣ ለእነሱም ያንን የወደደላቸውን ሃይማኖታቸውን ሊያደላድልላቸው፣ ከፍርሃታቸውም በኋላ ጸጥታን ሊለውጥላቸው ተስፋን ቃል ሰጥቷቸዋል፡፡ በእኔ ምንንም የማያጋሩ ኾነው ይግገዙኛል፡፡ ከዚያም በኋላ የካደ ሰው እነዚያ እነርሱ አመጸኞች ናቸው፡፡››

አላህ ሃቁን ይምራን፡፡ አላህ ሆይ! ሃቅን በሃቅነቱ አሳየን የምንቀበለውም አድርገን፤ ባጢልን በባጢልነቱ አሳየን የምንርቀውም አድርገን፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት ሁሉ መደምደሚያ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረቦቻቸው፤ ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡