Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

‹‹ሰርጎን በኢስላማዊ DJ›› ክፍል 1


‹‹ሰርጎን በኢስላማዊ DJ››
ክፍል 1
ማስታወቂያቸው ላይ ‹‹የደስታዎችን ቀን አላህን በመዘከር ያሳልፉ›› ይላል፡፡ በሸሪዓ እይታ ‹‹ሃላል››፤ ‹‹ዚክር›› የሚሉት ሽርክ አለው ወይ???
አዎን ታላቁ በደል ሽርክ አለው፡፡
ሙሉ ትምህርቱን ያንብቡ፡፡
ሙስሊም የሆነ ሁሉ የአርስቱን ክብደት አሁን ይገለፅለታል፡፡ ምክንያቱም እራሳቸውን ‹‹ኢስላማዊ DJ እና ኢስላማዊ ባንድ›› ብለው የሚጠሩ ሰዎች ታላቁን በደል ሽርክ የሚቀላቅሉ ሆነው ተሰምተዋል፡፡
እነሱንም በሸሪዓ የሚፈቀድ ነገር ነው የሚያደርጉት (የሚነሽዱት) ብለው የሚጠሯቸው ሰዎች የጉዳዩን ክብደት ያጤኑት ዘንድ ‹‹ኢስላማዊ DJ እና ኢስላማዊ ባንድ›› የሚሏቸው ላይ ታላቁ በደል፤ ለጀሃነም የሚዳርገውን፤ አላህ ንሰሃ ሳይገባ ለሞት ሰው ዘላለማዊ የሆነን ከባድ ቅጣትን የሚቀጣበት ሽርክ (በአላህ ላይ ማጋራት) መንዙማ እና ነሺዳ የሚሏቸው ውስጥ አካተዋል፡፡
ሽርክ ማለት ምን ማለት ነው?
አላህን እያመለኩ ከአላህ ጋር ያሉ አካላትን አብሮ ማምለክ፡፡ ለአላህ ብቻ የሚገቡትን አምልኮዎች (ዱዓ፤ ስግደት፤ መመካት፤ እርድ እና የመሳሰሉትን) ከአላህ ውጭ ላሉ አካላት ማድረግ፡፡ መላኢካን ይመስል፤ ነብይን ይመስል፤ ጂንን ይመስል፤ ሷሊሆችን ይመስል፤ ድንጋይ ዛፍን ይመስል፤ በአጠቃላይ ፈጣሪ አላህን ትቶ እሱ ከፈጠራቸው ፍጡራን አንዱንም ቢሆን የአላህን መብት አሳልፎ የሰጠው ሰው በአላህ ላይ አጋርቷል፡፡ ከሽርክ ንሰሃ ሳይገባ የሞተ ሰው ከጀሃነም አይወጣም እሳት ውስጥ ዘውታሪ ነው፡፡ ከሽርክ በታች ያለውን ወንጀል ለሚሻው ሰው ሲምር ሽርክን ግን ሳይቶብት ለሞተ በፍፁም አይምርም፡፡
አላሁ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) እንዲህ ይላል
إِنَّ ٱللَّهَ لَا يَغْفِرُ أَن يُشْرَكَ بِهِۦ وَيَغْفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَآءُ ۚ وَمَن يُشْرِكْ بِٱللَّهِ فَقَدِ ٱفْتَرَىٰٓ إِثْمًا عَظِيمًا
አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፡፡ ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢአት በእርግጥ ቀጠፈ፡፡
إِنَّهُۥ مَن يُشْرِكْ بِٱللَّهِ فَقَدْ حَرَّمَ ٱللَّهُ عَلَيْهِ ٱلْجَنَّةَ وَمَأْوَىٰهُ ٱلنَّارُ ۖ وَمَا لِلظَّٰلِمِينَ مِنْ أَنصَارٍ
እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡
ታድያ ከዚህ የባሰ ክስረት ምን አለ?
ጀነት እርም ተደርጎበት መኖርያው እሳት ውስጥ መሆን፡፡
ሉቅማንም ለልጃቸውን ሲመክሩት እንደሚከተለው ማለታቸው
وَإِذْ قَالَ لُقْمَٰنُ لِٱبْنِهِۦ وَهُوَ يَعِظُهُۥ يَٰبُنَىَّ لَا تُشْرِكْ بِٱللَّهِ ۖ إِنَّ ٱلشِّرْكَ لَظُلْمٌ عَظِيمٌ
ሉቅማንም ለልጁ እርሱ የሚገሥጸው ሲኾን «ልጄ ሆይ! በአላህ (ጣዖትን) አታጋራ፡፡ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና» ያለውን (አስታውስ)፡፡
አላህ መላክተኛውን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላቸዋል
وَلَقَدْ أُوحِىَ إِلَيْكَ وَإِلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِكَ لَئِنْ أَشْرَكْتَ لَيَحْبَطَنَّ عَمَلُكَ وَلَتَكُونَنَّ مِنَ ٱلْخَٰسِرِينَ
ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፡፡ በእርግጥም ከከሓዲዎቹ ትኾናለህ ማለት ወደ አንተም ወደእነዚያም ካንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል፡፡
ለእኛ መገሰጫ እንዲሆነን እንጂ እሳቸው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) የአላህ ምርጥ ባርያውን እና መልክተኛው ናቸው፡፡
የቱ ጋር ነው ‹‹ኢስላማዊ DJ እና ኢስላማዊ ባንድ›› ሽርክ የተገኘባቸው ይባል ይሆናል
1) ‹‹አሰላሙአለይኩም ያሰይዲና፤
አሰላሙአለይኩም ያሀቢቢና፤
ውሰዱን መካ መዴና››
ይህን ምድር ብቸኛው አስተናባሪ ህያው የሆነው አላህ ብቻ ሆኖ ሳለ የሞቱትን የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ማድረግ የማይችሉትን ነገር መጠየቅ ሽርክ ነው፡፡
‹‹ውሰዱን መካ መዲና›› የሚለው አባባል ሽርክ ነው፡፡ ሽርክ ደግሞ አንድ ናት ትዘለል የሚባል ነገር የለም፡፡ ከዛ በፊት የተሰራውን ስራ ሁሉ ውድቅ ታስደርገዋለች፡፡
2) ‹‹አላሁመሰሊ አላ ሙሃመዴ፤
ጀማሉል አለም፤
ካልጠሩኝ መዴና፤
የሚያሽረኝ የለም፤
ጀማሉል አለም››
- የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ማንንም መዲና መጥራት አይችሉም፡፡ መካም ይሁን መዲና እንዲወስደን የሚለመነው፤ የሚወስደንም አላህ ብቻ እና ብቻ ነው፡፡
- ‹‹የሚያሽረኝ የለም›› ያለውም ሽርክ ነው፡፡ የሚያሽረው አላህ ብቻ ነው፡፡ አላህ ፍፁም ወዳጅ አድርጎ የያዛቸው ኢብራሂም (አለይሂ ሰላም) ስለ ብቸኛው ተመላኪ ጌታ አላህ ሲናገሩ ምን እንዳሉ አላህ ቁርዓን ላይ እንዲህ ጠቅሶታል
وَإِذَا مَرِضْتُ فَهُوَ يَشْفِينِ
«በታመምኩም ጊዜ እርሱ (አላህ) ያሽረኛል፡፡
3) ‹‹ሰላቱላህ ዘይኑ በሉኝ አርሂቡ፤
አንቱ ቢሉኝ አርሂቡ፤
አልቀርም ወደኋላ››
- እሳቸው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሞተዋል፡፡ ህያው በሆነው አላህ ላይ ብቻ ነው በበካት፤ ህያው የሆነውን አላህ ብቻ ነው መጥራት፡፡
- የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እራሳቸው ካስተማሩን ከሰላት በኋላ ከሚባ ዚክሮች ውስጥ
اللَّهُمَّ لَا مَانِعَ لِمَا أَعْطَيْتَ، وَلَا مُعْطِيَ لِمَا مَنَعْتَ
አላህ ሆይ! አንተ ለሰጠኸው ከልካይ የለውም፡፡ አንተ ለከለከልከው ሰጪ የለውም፡፡
አላህ የሁሉ ነገር ባለቤት እሱን እንድንለምነው እንዲህ ይለናል
وَقَالَ رَبُّكُمُ ٱدْعُونِىٓ أَسْتَجِبْ لَكُمْ ۚ إِنَّ ٱلَّذِينَ يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِى سَيَدْخُلُونَ جَهَنَّمَ دَاخِرِينَ
ጌታችሁም አለ «ለምኑኝ፤ እቀበላችኋለሁና፡፡ እነዚያ እኔን ከመግገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ኾነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ፡፡
መልስ የሚሰጠውን አላህ ትቶ ለነፍሳቸውም ጭምር ምንም ማድረግ የማይችሉትን (መላእክቶችንም፤ ነብያትንም፤ ፍጡርን) ለአላህ የሚገባውን አምልኮ አሳልፎ የሰጠ ከከሳሪዎች ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ሽርኮች እያሉ እንዴት ነው ይህን ተግባራቸውን ‹‹የደስታዎችን ቀን አላህን በመዘከር ያሳልፉ›› ብለው የሚያስተዋውቁት?????
በአላህ ላይ ማጋራት ዚክር አይባልም፡፡ የሚያሳዝነው ቪድዬ ብለው የለቀቋቸው ላይ ዱንያዊ ትምህርትን ዲግሪ እና ማስትሬት ድረስም የደረሱ አይጠፉም ይሆናል ግን ሸሪዓዊ እውቀትን በተለይ የሃይማኖታችን መሰረት የሆነውን ተውሂድ አለማወቅ ምን ያህል ክስረት እንደሆነ ቪድዮው ላይ ባሉት ሰዎች ታይቷል፡፡
አንተ/ቺ የአላህ ባርያ ሆይ! ሃይማኖትህን ጠንቅቀህ እወቅ፡፡ ጭብጨባው፤ ድቤው፤ እና መሰል ነገሮች ሲደበላለቁ አንተ የሚባለውን ሳታውቅ እንዲህ አይነት ከባድ ዱንያ አኸይራ የሚያበላሽ ሽርክ ውስጥ እየወደቅክ ነው፡፡
ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው፡፡
በዚህ ፅሁፍ ሽርክ እንዳለበት አሳይተናል፡፡ ይህ ብቻ በቂ ነበር ከሽርክ የከፋ በደል ስለሌለ፡፡ ግን ሰዎች ያሉትን ሌሎች ጉዳቶች ያውቁ ዘንድ በቀጣይ ክፍሎች ኢንሻ አላህ እንመለሳለን፡፡
የአላህ ባርያዎች ሆይ! የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው ነው ነገሩ፡፡ የሰርግ ቀን ምን መምሰል እንዳለበት ሸሪዐው አስቀምጦታል:; በቀጣይ ትምህርቶች በአላህ ፈቃድ ይዳሰሳሉ፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት መደምደሚያ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረቦቻቸው፤ ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡