Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

‹‹አሰላቱ ኸይሩ ሚነ ነውም (ሰላት ከእንቅልፍ ይበልጣል)›› በጊዜ የተኛ በጊዜ ይነሳል

‹‹አሰላቱ ኸይሩ ሚነ ነውም (ሰላት ከእንቅልፍ ይበልጣል)››በጊዜ የተኛ በጊዜ ይነሳል 
Sadat Kemal Abu Nuh
የሰው ልጅ አላህ ሲፈጥረው ደካማ ነው፡፡ ግዴታ ማረፍ፤ መተኛት አለበት፡፡ ማንጎላጀትም ሆነ ማንቀላፋት የማያገኘው ብቸኛው ሃያል ፈጣሪ አላህ ብቻ ነው፡፡ አላህ 7 ሰማያትን 7 ምድሮችን በውስጣቸውም ያሉትን በ6 ቀናት ፈጥሮ ድካም የምትባል አላገኘችውም፡፡
ፍጡራኑን ጠንቅቆ የሚያውቀው አላህ፤ ለነፍሳቸውም፤ ለእርሱም፤ ለቤተሰቦቻቸም ግዜ እንዲሰጡ እና በዋነኝነት ደካማ መሆናቸውን አውቆ እረፍት እንዲያደርጉ እንዲህ ሲል ይናገራልوَجَعَلْنَا نَوْمَكُمْ سُبَاتًاእንቅልፋችሁንም ዕረፍት አደረግን፡፡
ታድያ የሰው ልጅ አላህ ያስቀመጠለትን ተፈጥሮዋዊ ሂደት ትቶ ትዕዛዝ ሲጥስ ሌሎች ነገሮቹም ግራ ይጋባሉ፡፡ ፍጡራንን የፈጠረው ፈጣሪ፤ ፍጡራኖቹ እንቅልፍ እንደሚያስፈልጋቸው ከላይ ባለው አንቀፅ ተናግሯል፡፡
ለፍጡራን እዝነት የተላኩት ነብዩ ሙሃመድ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ደግሞ ከኢሻ ሰላት በኋላ ወሬን ይጠሉ ነበር፡፡ በጊዜ ተኝተው ከዛም ተነስተው ጌታቸውን በሌሊቱ መጨረሻ ክፍል ይለምኑታል፤ ያለቅሱለታል፤ ያመሰግኑታል፤ ያመልኩታል፡፡
እስቲ ስራችንን እንፈትሽ፡፡ የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹‹ከኢሻ ሰላት በኋላ ወሬን ይጠሉ ነበር››፡፡
ዛሬ በተገላቢጦሹ- ‹‹አጅነቢ›› ዜና አንባቢ ሴት ወንዱ እያየ ፀጉሯን ተገልጣ ሲያፈጥባት እና ልቡን ሲያደርቅ ያመሻል፡፡ ሴቶችም በተገላቢጦሹ ‹‹አጅነቢ›› ወንድ ላይ ስያፈጡ ያመሻሉ- ወንዱ ኳስ ሲያይ ያመሻል- ሴቷ ሙሰልሰል ስታይ ታመሻለች- ሴት እና ወንድ በፊስቡክ እና መሰል ሚድያዎች ‹‹ቻት›› ሲደራረጉ ያመሻሉ- ወንድም ሴትም ጫት እየቃሙ፤ ፊልም እያዩ፤ ቡና አፍልተው ሰው ሲያሙ የሚያመሹም አልጠፉም፡፡
ከዛ የሰው ልጅ የሰው ነው፤ ቀን ሲለፋ ውሎ ማታ እንዲህ በማይረባ ነገር ጊዜውን አቃጥሎ አምሽቶ ሲተኛ፤ በድካም ላይ ድካም ተደራርቦበታል እና ሲያመሽም ልቡን በሚያጠቁር ነገር ነው ያመሸው ከዛም ‹‹አሰላቱ ኸይሩ ሚነ ነውም (ሰላት ከእንቅልፍ ይበልጣል)›› የሚለውን ከተለያየ መስጊዶች በዛ ፀጥ ባለ ለሌት ቢጠራም አይሰማውም/ አይሰማትም፤ ቢሰማውም/ቢሰማትም መነሳት ያቅተዋል/ ያቅታታል፡፡
የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹‹ከፈጅር ሰላት በፊት ያለችው ረከአተይን ዱንያ እና በውስጧ ከያዘችው ይበልጣሉ›› ነበር ያሉት፡፡ ዛሬ ሱናው ቀርቶ ፈርዱን አላህ ባዘዘው መልኩ በጀመዐ ሄዶ ፈጅርን መስገድ አይደለም፤ በሰዐቱ ቤቱም መስገድ ስንቱ እያቃተው ነው፡፡ አላህ ከገፍላ ይጠብቀን፡፡
አላህ ሆይ! አንተን በማውሳት፤ አንተንም ማመስገን ላይ፤ ያማረ አምልኮህን መፈፀምም ላይ አግዘን፡፡የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት ሁሉ መደምደሚያ ላይ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በሰሃባዎቻቸው እና ሃቅን በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡ አላሁመ አሚን፡፡