Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ድንበር ማለፍ ‹‹ኮሚቴው፤ አብሬት፤ ቃጥባሬ፤ አልከሶ››

ድንበር ማለፍ
‹‹ኮሚቴው፤ አብሬት፤ ቃጥባሬ፤ አልከሶ››
የአላህ ባርያዎች ሆይ! ፅሁፉን ስታነቡ የተፃፈውን ብቻ አንብቡ፡፡
ሃቅን ከማንም ይምጣ ከማን ቢመርህም ተቀበለው፡፡
የአላህ ባርያዎች ሆይ! አላህን እለምነዋለሁ ሃቅን በሃቅነቱ እንዲያሳየን የምንቀበለውም እንዲያደርገን፤ ባጢልን በባጢልነቱ እንዲያሳየን የምንርቀውም እንዲያደርገን፡፡ አላሁመ አሚን
ካስታወስን ነብየላህ ኑህ አለይሂ ሰላም የተላኩበት ዋናው ቁምነገር በዛ ወቅት የነበሩ 5 ደጋግ ሰዎች ሲሞቱ ህዝቦች በነሱ ላይ ድንበር አልፈው ስላመለኳቸው ነው፡፡ የማህበረሰቡ ቁንጮ የሚባሉት እንዲህ ሲሉ አዘዙ ‹‹አማልክቶቻችሁን እንዳትተዉ፤ ወድ፤ ሱዋእን፤ የጉስን፤የኡቅን እና ነስርንም›› ብለው የኑህ አለይሂ ሰላምን ዳእዋ አጣጣሉ፡፡ ይህ ድንበር ማለፋቸውን ልብ ብለን እንመልከት፡፡ የተመለኩት በአብደላህ ኢብን አባስ (ረድየላሁ አንሁም) አንደበት ደጋግ ባሪያዎች እንደነበሩ የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡

ኑህ አለይሂ ሰላም 950 አመት ዳእዋ አደረገበት፡፡ ግን ያመኑለት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው አንድ ጊዜ ድንበር ከታለፈ እና ስሜትን መከተል ከጀመረ በኋላ በነብይ አንደበት ይህን ያህል አመት ጥሪ ተደርጎ ያመኑት ጥቂት ሆኖ ተገኙ፡፡

ቀጥታ ወደ አገራችን ስንመለስ፡፡ አብሬት፤ ቃጥባሬ፤ አልከሶ፤ የወሎ መሻኢኾች እና ሌሎችም ‹‹ደጋጎች›› ነበሩ ይባልላቸዋል፡፡ ለምሳሌ የቃጥባሬ ሸይኽ ሰዉን ወደ ሰላት ተጣርተዋል ተብሎላቸዋል፡፡ ከዛም ድንበር ታልፎ ‹‹የቃጥባሬ ኮፍያ››፤ ‹‹የቃጥባሬ ሙሪዶች›› እና ‹‹የቃጥባሬ መውሊድ›› የሚባል እያየን ነው፡፡

አብሬቶች ጋር ስንሄድ ‹‹የአብሬት ሙሪዶች››፤ ‹‹የአብሬት መውሊድ››፤ ‹‹የአብሬት ቡና›› እና የመሳሰለውን እየተባለ፡፡ እንዲያውም የአብሬት ሙሪዶች በፊት የቃጥባሬን ኮፍያ ሲያገኙ እሳት ውስጥ ይከቱ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ እርስ በርስ ‹‹የአብሬት ሸይኽ ይበልጣሉ፤ የቃጥባሬ ሸይኽ ይበልጣሉ›› ሁለቱም በአላህ ስራ ገብተው እገሌ ከእገሌ ይበልጣል ሁሉ ይባባላሉ፡፡

ኑር ሁሴን ላይ ስንመጣ ‹‹ኑር ሁሴን ከናታቸው ማህፀን ሲወጡ ቁርዐን እየቀሩ ነው የወጡት›› ይላሉ፡፡ በጣም የሚገርመው አላህ እንዲህ እያለ ‹‹ምንም የማታውቁ ስትሆኑ ከናታችሁ ሆድ ውስጥ አወጣናችሁ››፡፡ ‹‹የኑር ሁሴን ቡና፤ የኑር ሁሴን መውሊድ እና የመሳሰለውን›› እየተባለ ይገኛል፡፡

ማንኛውም ድንበር ማለፍ ከጊዜ በኋላ መስተካከል የማይችልበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ባለፈው አብሬትን አስመልክቶ በፌስቡክም በሌላም ሚድያ ትምህርት ተሰጠ ይህም ሆኖ ብዙዎችን መግታት አልተቻለም፡፡ ስር ስለሰደደ ማለት ነው፡፡ ሌላው ሰሞኑን ደግሞ አልከሶ አለ፤ ያውም ከባባድ ሽርኮች ይዞ፡፡

ኮሚቴውን ለምን ከዚህ ፅሁፍ ጋር አገናኘሀው የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ ማንም የማይክደው እነአብሬት ላይ ድንበር እንደታለፈው ኮሚቴው ላይም ድንበር ታልፏል፡፡ ኮሚቴዎቹ ያሉትን ያልተቀበለ የኢስላም ጠላት እንደሆነ አድርጎ ማውራት፡፡ ሁሉ ነገር በምሳሌ ሲሆን ግልፅ ይሆናል

1) በድሩ ሁሴን ‹‹መውሊድ አይለያየንም›› ሲል፤ ሌሎች ወንድሞች ደግሞ የመውሊድን አስከፊነት፤ ውስጡ ያለውን ሽርክ ገላልፀው ለማህበረሰቡ ሲያብራሩ፤ ኮሚቴው ላይ ድንበር ያለፉ የሚከተሉትን ሲናገሩ እና ሲፅፉም ታይተዋል ‹‹እናንተ የይሁዳ ቅጥረኞች፤ የመንግስት ካድሬዎች፤ የኢስላም የውስጥ ጠላቶች፤ አትበታትኑን፤ አንድ ነን እና የመሳሰለውን››፡፡ ይህን አባባል ሽርክ ላይ የወደቁ ሰዎች ከሚሉት ጋር ይመሳሰላል፡፡ አላህን በብቸኝነት አምልኩ፤ አምልኮ ለአንድ አላህ ብቻ እንጂ ለነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምም) ይሁን ለአብድል ቃድር ጀይላኔ አይገባም ሲባሉ እነሱ የሚከተለውን ብለው ነበር ‹‹ወሃቢዬች፤ ነብዩን የማይወዱ፤ ሰለዋት የሚከለክሉ እና የመሳሰለውን››፡፡ ልብ ብሎ ያየ ሰው በድሩ ሁሴን እዚህ ቦታ ላይ ተሳስቷል፡፡ በማስረጃ መውሊድ የሚለያይ ውስጡ የሽርክ መናሃሪያ መሆኑን ሲጠቅስ አንድ ሰው፤ ሌላኛው አካል ያለውን መቀበል እንጂ ስሜቱን መከተል አይደለም፡፡ ፍጡራንን አላህ በሚታመፅበት ጉዳይ መታዘዝ የለም፡፡

ሌላው አንድ የሚባል አባባል አለ እሱም ‹‹ጠላት ሊያጠፋን ደርሶ እንደ መውሊድ አይነት ጥቃቅን አርስቶችን እያነሱ ኡማውን መበታተን እራስን አሳልፎ ለጠላት መስጠት ነው›› ይላሉ፡፡

መጀመሪያ እውነት መውሊድ ጥቃቅን አጀንዳ ነው???
በፍፁም፤ መውሊድ ማለት በውስጡ ታላላቅ ሽርኮች የያዘ፤ ታላቅ ቢድዐ ነው፡፡ ታድያ ሽርክ እና ቢድዐን ይዞ ከመከራ መውጣት ይቻላልን???

ሌላው ከመቼ ጀምሮ ነው አላህ በቁጥር ብዛት የሚረዳው??? አላህ አማኞችን ብቻ ነው የሚረዳው፤ በቁጥር ቢያንሱም፡፡ ስንት ፅሁፎች በፌስቡክ እና በበራሪ ወረቀት እናያለን ነገር ግን ስለ ሽርክ እና ቢድአ ብዙም አይታይም፡፡
አሁን ከዚህ አርስት ጋር የተያያዘ ድንበር ማለፍ የሚሆነው የሚከተለው ነው፡፡ አንድ ሰው ስለ መውሊድ ቢድአነት፤ ውስጡ ሽርክ እንዳለው ከተናገረ ከዚህ በፊት ፌስቡክ ላይ እንዳየነው ‹‹እኛ የአሚሮቻችንን ትዕዛዝ አንጥስም›› ብሎ አላህ በማንኛውም በተለያያችሁበት ጉዳይ ወደ ቁርዐን እና ሀዲስ ተመለሱ ሲል እዚህ ላይ እንዲህ ሲባል ታያለህ፡፡
እንዲያውም አንድ ወንድም ፌስቡክ ላይ እንዲህ ሲል ፃፈ ‹‹ከኮሚቴዎቹ ውጭ ማንንም አልሰማም፤ መስሚያ የለኝም›› ይሄም ድንበር ማለፍ ነው፡፡

2) የአቡበክር አህመድን ፎቶ ፌስቡክ ላይ ለጥፎ ‹‹የጀነት ሙሽራ›› ብሎ መፃፍ፡፡ ይህም ከባድ ድንበር ማለፍ ነው፡፡ ረሱል ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ኢማሙ ቡኻሪ ጂሃድ የሚለው ምእራፋቸው ላይ ‹‹እገሌ ሸሂድ ነው አይባልም›› ብለው በጠቀሱት አርስት ላይ፤ የረሱልን ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሃዲስ ጠቅሰዋል፡፡ ያም ሃዲስ አንድ ሰሃባ በጣም ጂሃድ ሲያደርግ ሰሃባዎች ‹‹እሱ የጀነት ነው፤ ሸሂድ ነው›› ሲሉ የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹‹(እሱ) የእሳት ነው›› አሉ፡፡ አንድ ሰሃባ የዛን ሰው ስራ ሲከታተል ጦርነት ላይ ቆስሎ እራሱን በሰይፍ ወግቶ ገደለ፡፡

ከዚህ ምን እናያለን አንድ ሰው የጀነት መሆኑን መመስከር የሚችሉት አላህ እና ወህይ የማይለያቸው የአላህ መላክተኛ ብቻ ናቸው፡፡ ልንል የሚገባው እገሌን ‹‹አላህ ወንጀሉን ይማረው፤ የጀነት ሰው ይበለው፤ እኛ ስናየው ከላይ ጥሩ ሰው ነው፤ የውስጡን አላህ ነው የሚያውቀው›› እንጂ መባል ያለበት፤ አንድን ሰው የጀነት ነው ብሎ መመስከር በአላህ ስልጣን መግባት ነው፡፡ ይህም ኮሚቴው ላይ የታለፈ ድንበር ነው፡፡ ይሄ ልክ አይደለም ተብሎ ሲሳፍ ከዚህ በፊት የሚከተሉትን ተባለ ‹‹ቅናት ነው፤ የአሚሮቻችን ጠላቶች፤ የመንግስት ቅጥረኞች እና የመሳሰለውን››፡፡ ታድያ ምኑ ላይ ነው ለቁርዐን እና ሃዲስ እጅ መስጠቱ???

ምንም እንኳን የሚከተለውን ያለው ጃሂል ቢሆንም አንድ ሰው ሃዲስ ሲናገር አቡበክር ሲዲቅ (ረድየላሁ አንህ) እንዲህ ብለው ብሎ ሲናገር፤ ቦታው ላይ የነበረ አንድ ሰው እንዲህ አለ ‹‹የታሰሩትን አቡበክር ናቸው››??? አለ፡፡

3) አንድ ሰው ቂሊንጦ ደርሶ መምጣቱን በፌስቡክ ካልፃፈ የሙስሊሞች ጉዳይ እንደማይመለከተው አድርጎ ማሰብ እና ሊሎችም ነገሮች ታዝበናል፡፡ አላህን እንፍራ
የታሰሩት ኮሚቴዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ተማሪዎችም፤ ኡለማዎችም ሌሎችም ታስረዋል፡፡

ሌላው እና በጣም አስገራሚው ደግሞ የሚከተለው አባባል ነው ‹‹እገሌ ሃቅ ላይ ቢሆን ኖሮ ይታሰር ነበር፡፡ ምን ደረሰበት??? መቼ ታሰረ??? ›› እና የመሳሰለውን እየሰማን ነው፡፡

ጥቂት መልሶች፡፡
1) ከተመረጡት ኮሚቴዎች ውስጥ ስንቶች ነው የታሰሩት??? እንደነዚህ ሰዎች አባባል ያልታሰሩት ኮሚቴ ተብለው የተመረጡት ሃቅ ላይ አይደሉምን???
2) ከታሰሩትም የተፈቱ አሉ፡፡ ታድያ የተፈቱት ሃቅ ላይ ስላልሆኑ ነው???
3) ስንት እና ስንት የኢትዬጵያ ዳኢዎችም ይሁኑ ህዝብ አልታሰረም፡፡ እንደነዚህ ሰዎች አባባል ይህ ሁሉ ሰው ሃቅ ላይ አይደለም???
4) አንድ ሰው ሃቅ ላይ መሆን እና አለመሆኑን የሚለካው በመታሰር እና ባለመታሰር ነውን???
አንድ ሰው ባላጠፋውም ይታሰራል፤ አጥፍቶም ይታሰራል፡፡ ለምሳሌ ሰው ገድሎ፤ ዘርፎ፤ የሚታሰር ሙስሊም አለ፡፡ ሙስሊም ስለሆነ ብቻ ሃቅ ላይ ነው ማለት ነው???

ስለዚህ ሚዛናችን ሸሪዐ ይሁን፡፡

አላህ ሆይ! ፈተናችንን በሃይማኖታችን ላይ አታድርግብን፡፡ ሰዎች ላይ ድንበር ከማለፍ እንቆጠብ፡፡ አላህ ሃቅን በሃቅነቱ ያሳየን የምንቀበለውም ያድርገን፤ ባጢልን በባጢልነቱ ያሳየን የምንርቀውም ያድርገን፡፡ አላሁመ አሚን፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት ሁሉ መደምደሚያ ላይ ይሁን፡፡