Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የአለም ሙስሊሞችን ለዚህ መከራ ምን ዳረጋቸው? ፓኪስታን እና አካባቢዋክፍል ሁለት



ሳንሸፋፍን እውነታውን እንነጋገር፤ በሽታውን ያልተናገረ መድሃኒት አይገኝለትምፓኪስታን እና አካባቢዋክፍል ሁለት===============================================በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ እጅግ በጣም ሩህ ሩህ፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብዩ ሙሃመድ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በሰሃባዎቻቸው እና ፈለጋቸውን እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡
ምስራና ሁሉ ለአላህ ነው የሁለት አገር ደስታን በኢማን፤ በዲን፤ አላህ እና መልክተኛውን በመታዘዝ ብቻ ያደረገ፡፡ 
የሚቀጥለውን አለም ምንም ጥርጥር የለውም የሚወርሷት የእምነት ባለቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ ምድራዊው አለም ላይስ ደስታ እና የተመቻቸ ህይወት፤ ስቃይ መከራ የሌለበት የተድላ ህይወት በምን ይገኝ?አላህ እንዲህ ይላልمَنْ عَمِلَ صَٰلِحًا مِّن ذَكَرٍ أَوْ أُنثَىٰ وَهُوَ مُؤْمِنٌ فَلَنُحْيِيَنَّهُۥ حَيَوٰةً طَيِّبَةً ۖ وَلَنَجْزِيَنَّهُمْ أَجْرَهُم بِأَحْسَنِ مَا كَانُوا۟ يَعْمَلُونَ <<ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሰራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፡፡ ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን፡፡ >>
የአላህ ቃል በግልፅ እንዳስቀመጠው፤ መልካም ኑሮ ለማግኘት አምኖ መልካም ስራ መስራት ብቻ ነው፡፡ መልካም ስራ ይሆን ዘንድ ማንኛውም ስራ ለአላህ ብቻ ተብሎ ሊሰራ እና የነብያችንን(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ፈለግ መከተል ግድ ይለዋል፡፡ ሀይማኖቱ እንዲመቻችለት፤ ሰላምን ማግኘት የፈለገ፤ የምድር ምትክ መሆን የፈለገ፤ በጠላት ላይ የበላይ ሆኖ ተከብሮ መኖር የፈለገ ምን ማድረግ እንዳለበት አላህ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
وَعَدَ ٱللَّهُ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ مِنكُمْ وَعَمِلُوا۟ ٱلصَّٰلِحَٰتِ لَيَسْتَخْلِفَنَّهُمْ فِى ٱلْأَرْضِ كَمَا ٱسْتَخْلَفَ ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِهِمْ وَلَيُمَكِّنَنَّ لَهُمْ دِينَهُمُ ٱلَّذِى ٱرْتَضَىٰ لَهُمْ وَلَيُبَدِّلَنَّهُم مِّنۢ بَعْدِ خَوْفِهِمْ أَمْنًا ۚ يَعْبُدُونَنِى لَا يُشْرِكُونَ بِى شَيْـًٔا ۚ وَمَن كَفَرَ بَعْدَ ذَٰلِكَ فَأُو۟لَٰٓئِكَ هُمُ ٱلْفَٰسِقُونَ 
‹‹አላህ እነዚያን ከእናንተ ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን እነዚያን ከእነሱ በፊት የነበሩትን እንደተካ በምድር ለይ በእርግጥ ሊተካቸው፣ ለእነሱም ያንን የወደደላቸውን ሃይማኖታቸውን ሊያደላድልላቸው፣ ከፍርሃታቸውም በኋላ ጸጥታን ሊለውጥላቸው ተስፋን ቃል ሰጥቷቸዋል፡፡ በእኔ ምንንም የማያጋሩ ኾነው ይግገዙኛል፡፡ ከዚያም በኋላ የካደ ሰው እነዚያ እነርሱ አመጸኞች ናቸው፡፡›› 
አላህ በሰጠን ንፁህ አእምሮ ስናየው አንቀፁ በግልፅ እንዳስቀመጠው፤ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁሉ ለማግኘት፤ አላህ እንደመስፈርት ያስቀመጠው ‹‹በእኔ ምንንም የማያጋሩ ኾነው ያምልኩኝ ይገዙኝ›› ይላል አላህ፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፤ አላህ ካዘነላቸው ባሪያዎች ውጭ፡፡ ወደ አላህ መንገድ የሚጣሩ፤ ነብያትን እና የነሱን ተከታዬች፤ የእውቀት ባለቤቶች ኡለማዎችም ይሁን ዱዓቶች የታዘዙት ይህንን መሰረታዊ እና ግዴታ የሆነ ትምህርት ማህበረሰቡ ውስጥ እንዲያሰርፁ ነበር፡፡ ነገር ግን አላህ ካዘነላቸው ውጭ አብዛኛዎቹ የአለማችን ዱዓት የተባሉት ባለንበት ጌዜ ይህንን ታላቅ አጀንዳ ትተው ግማሹ ቀን እና ሌሊት ፖለቲካ እና ስልጣን ይላል፤ ግባሹ ተውሂድ ካልተስተካከለ ምንም ጥቅም የሌላቸውን አምልኮዎች ሰውን ተግብር ይሉታል፡፡ 
ፓኪስታን እና አካባቢዋ ህንድን፤ ባንግላዲሽን የመሳሰሉት ከባድ የሆነ ባዕድ አምልኮ ይካሄድባቸዋል፡፡ ከአላህ ውጭ ሙታንን መለመን፤ ‹‹ወልይ›› ብለው ለሚገምቷቸው ሰዎች ስግደት ማድረግ እና የመሳሰለው፡፡ በብዛት ፖለቲከኞች እንዲህ ሲሉ ይደመጣሉ ‹‹ምእራቡ አለም ፓኪስታን፤ አፍጋኒስታን እና የመሳሰሉ የሙስሊም አገሮች ላይ ከባድ በደል እያደረሱ ነው›› ይባላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አገራት ውስጥ የሚሰሩትን በአላህ ላይ ማጋራት እና አላህ ላይ ማማፅ እስቲ እንይ፡፡ እስቲ ፓኪስታን ውስጥ የሚሰራውን አላህ የጠላቸውን ስራዎች በግልፅ ዘርዘር አድርገን እንያቸው፡፡
1) ሽርክ ቀብር አምልኮ1 ሚሊዬን ህዝብ በላይ በአመት የሚያመልከው ‹‹የባባ ፈሪዱ ዲን›› ቀብር፡፡ ፓኪስታ ውስጥ ከሚመለኩ ታላላቅ ቀብሮች ውስጥ ‹‹የባባ ፈሪዱ ዲን›› ብለው የሚጠሩት ታላቁ ነው፡፡ ለዚያራ ብለው የሚሄዱት ሰዎች እርስ በርስ ተጨፍልቀው እየሞቱ ሲያስቸግሩ፤ መንግስት ፖሊስ መድቦ ቦታው ላይ፤ ይህን ቀብር ነክተውት ያልፋሉ፡፡ከሚሏቸው አስከፊ ንግግሮች ውስጥ- ‹‹የባባ ፈሪዱ ዲንን›› ቀብር የዘየረ ‹‹ከጀሃነም ቅጣት ይጠበቃል››- ‹‹በባባ ፈሪዱዲን›› ቀብር በር በኩል ያለፈ ‹‹የጀነተል ፊርደውስ በር ገባ ማለት ነው›› ይላሉ፡፡ከዚህ የበለጠ የከፋ ጉድ አለን የአላህ ባሪያዎች???ስለ ቀብር አምልኮው አፈፃፀም እንደሚከተለው ነው፡- የሚከፈተው ለአምስት ቀናት ነው፡፡ የመጀመሪያው ቀናት የቅርብ ዘመዶች፤ ከዛም ባለስልጣናት፤ ከዛም ተራው ሰው፡፡ መግቢያ በር አለው፤ መውጫ በር አለው፡፡ ቀብሩን ነክቶ ማለፍ ብቻ ነው፡፡ ፖሊሶች እለፍ እለፍ እያሉ ያባሯቸዋል፡፡ ይህ አንዱ ብቻ የቀብር አምልኮ ነው፡፡ በተለያየ ከተማ የሚሰሩትን ቤት ይቁጠረው እንደሚባለው….፡፡አላህ ሽርክን አስመልክቶ፤ ተውበት እስካልተደረገ ድረስ ከሞት በፊት፤ ዘላለሙን ጀሃነም እንደሚያስገባ፤ ይህ የተሰራው ሽርክ አንድም ቢሆን የተሰራውን ስራ ሁሉ ገደል እንደሚያስገባ ተገልጧል፡፡ ታድያ….. 
2) ሽርክ ኢልመል ገይብ (የሩቅን ሚስጥር….)ፓኪስታን ውስጥ በየመንገዱ ልክ እንደ ሱፐር ማርኬት እና ሱቅ ማስታወቂያ፤ ‹‹የመዳፍ ስእል›› ያለበት ማስታወቂያዎች አሉ፡፡ ይህም ከባድ ከሚባሉት ሽርኮች ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ መዳፍ አንባቢ የሚባሉት ጠንቋዬች፤ ሰው የሚያጋጥመውን እጅ አይተን እናነባለን ብለው፤ ማስታወቂያ የለጠፉ መሆናቸው ነው፡፡የአላህ መልክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ነብያችን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) የነገን አውቃለሁ ስለሚል ሰው የሚከተለውን ተናግረዋል፡፡የነገን የሚያውቀው አላህ ብቻ ነው፡፡ ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ ‹‹የነገን እውቃለሁ ባይ ዘንድ የሄደ እና እሱን የጠየቀ የ40 ሌሊት ሰላቱን አይቀበለውም፡፡›› ሙስሊም ዘግበውታል
ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ ‹‹የነገን እውቃለሁ ባይ ዘንድ የሄደ እና እሱን የጠየቀ የ40 ለሊት ሰላቱን አይቀበለውም፡፡›› አልባኒ ሰሂህ አ-ተርጊብ ወተርሂብ
አቡ ሑረይሪ እንደተላለፈው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ‹‹ወደ ጠንቋይ በመሄድ የሚለው የተቀበለ ሙሐመድ ላይ በወረደው ክዷል›› አቡ ዳውድ አህመድና ሃኪም
3) የቢድዓ ዚክር ጠሪቃዎች‹‹ዚክር›› እንደሚታወቀው ኢባዳ አምልኮ ነው፡፡ አምልኮ ደግሞ ደንጋጊው አላህ ነው፡፡ በተግባር ደግሞ የሚያሳዩን የአላህ መላክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ናቸው፡፡ ፓኪስታን እና አካባቢዋ ላይ፤ ‹‹ጠሪቃ›› በሚል ስም፤ የዚክሩን ብዛትም ይሁን አይነቱን ከአላህ መልክተኛ ውጭ የሚደነግጉላቸው አሉ፡፡ በጣም መወዛወዝ፤ መደነስ፤ አንዳንዲም አልፎ ‹‹ሽርክ›› የቀላቀሉ ዚክሮችን ይላሉ፡፡ አላህ ይጠብቀን፡፡ ጠሪቃ ከሚሏቸው ውስጥ፤ ‹‹ነቅሸበንዲያ፤ ሻዚሊያ፤ ቃዲሪያ….›› ልብ በሉ ሁሉንም ዚክር ደንጋጊ አካል አለው፤ ሁኔታውንም ይሁን ቁጥሩን፤ ከአላህ እና መልክተኛው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ውጭ፤ እነዚህ ሰዎች ዘንድ ማለት ነው፡፡
4) ሴቶች ተገላልጠው መሄድ እና ኢኽቲላጥየሴቶች አለባበስ ‹‹ፓኪስታኒ›› እየተባለ ፀጉራቸውን በቅጡ ሳይሸፍኑ፤ ሱሪ ቢጤ ለብሰው፤ ከላዩ ጉልበታቸው ድረስ ደረብ የሚል ነገር ታል ያደርጉበታል፡፡ የህንድ ፊልም እየተባለ አለምን አጥለቅልቋል፡፡ እና የመሳሰለውን
ፓኪስታን እና አካባቢዋ ያሉ የሚንቀሳቀሱ ጀመዓዎች ‹‹ጀመዓተል ኢስላሚያ እና ጀመዓተ ተብሊግ›› ናቸው፡፡‹‹ጀመዓተል ኢስላሚያ››፤ በአቡል አላአልመውዱዲ የተመሰረተ ሲሆን፤ የሚያተኩረው እንደ ግብፁ ‹‹ኢኽዋንል ሙስሊሚን›› ፖለቲካ ላይ ነው፡፡ ‹‹ጀመዓተ ተብሊግ›› ደግሞ እንደሚታወቀው፤ ‹‹አቂዳ (እምነት)›› ላይ ሳይሆን ጥሪያቸው፤ ሰዎችን ‹‹ኹሩጅ›› ውጡ፤ ‹‹ሰላት ስገዱ›› ማለት ብቻ ነው፡፡ ግን አንድ ሰዉ የሚሰግድለትን ጌታ ጠንቅቆ ካላወቀው፤ ማለትም ‹‹አቂዳ›› ካልተማረ አላህን በአግባቡ ያመልካል ተብሎ አይጠበቀም፡፡‹‹ጀመዓተ ተብሊግ›› ከሚታወቁበት መርሆ አንዱ ‹‹በአካባቢ ሃቅ አንገባም›› የሚሉት ነው፡፡ ይህ በጣም አስገራሚ እና ከባድ የስህተት ንግግር ነው፡፡ ምክንያቱም እራሳቸውን የዳእ ሰዎች በለው የሚጠሩ ሰዎች፤ በአካባቢ ሃቅ ገብተው፤ የነብያትን ፈለግ ተከትለው ‹‹ይህ ሽርክ ነው፤ ይህ ቢድዓ ነው›› ማለት ካልቻሉ፤ ታድያ ምኑ ላይ ነው የነሱ የዳእዋ ሰውነት???‹‹ጀመዓተ ተብሊግ›› ትልቅ የእውቀት ችግር ስላለባቸው፤ ነብያት ሁሉ (አለይሂሙ ሰለዋት ወሰላም) የሄዱበትን መንገድ እነሱ ዘንድ ሂክማ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሽርክን አስከፊነት ካስተማርን ‹‹ሰዎች ይሸሻሉ›› ብለው ስለሚያስቡ፤ ‹‹በአካባቢ ሃቅ አንገባም›› ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሰዎች ተብሊጎች ‹‹ኹሩጅ›› የሚሉትን ሰው እስከወጣ ድረስ፤ ሽርክ ሲሰራ ቢያዩም፤ በአካባቢ ሃቅ አይገቡም፡፡‹‹የጀመኣተ ተብሊግ›› መስራች ‹‹ኢልያስ መውላና›› ቀብር ይመለካል፡፡ አደለም ከሽርክ ሊያስጠነቅቁ……. አላህ ይድረስልን፡፡ልብ ሊባል የማይረሳው የትም ቦታ ይሁን የሃቅ ተጣሪዎች፤ የአላህ ባሪያዎች እንዳሉት ነው፡፡ አላህ ከእነርሱ ያድርገን፡፡ 
መሬዎች ላይ ጣቱን በመቀሰር ነብያት የተላኩበትን ተውሂድ የዘነጋውን ‹‹ጀመዓተል ኢስላሚያ›› ብሎ እራሱን ለሚጠራው ቡድን የሚከተለውን የአላህ መልክተኛ ንግግር መታረሚያ ይሆነው ዘንድ እንጥቀሰው፡፡ የሙስሊም መሬዎችን አስመልክቶ የሚከተለውን ይላሉ ‹‹ከእኔ በኋላ በሪዎች ይመጣሉ ለናንተ የማያዝኑላችሁ፤ እኔን ሃውድ ላይ እስክታገኙኝ ድረስ ታገሱ›› ይህ ነበር የነብያችን ትዕዛዝ፡፡ 
ሁላችንም ልብ ልንለው የሚገባው አላሁ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) ነብዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምን) የላከበት ዲን ሙሉ ነው፡፡ እስከ ቂያማ ድረስ የሳቸውን መንገድ ብቻ የተከተሉ ሰዎች ናቸው ለድልም የሚበቁት፡፡ ሰዎች ፊትና ሲመጣባቸው ከፊትናው እና ከጠላቶቻቸው የሚጠበቁት የነብዩን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱና አጥብቆ መያዝ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢማሙ አህመድ ኢብን ሀንበል፤ ‹‹ሙእተዚላዎች›› ፊትና አመጡ በዛ ዘመን፤ ኢማሙ አህመድም በሱና ከትግስት ጋር አሸናፊ ሆኑ፡፡ ኢብኑ ተይሚያ ‹‹ታታሮችን፤ ሺኣዎችን፤ ሱፊዮችን›› እናም ሌሎች ምንገድ የሳቱትን በእውቀት የነብዩን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱና አጥብቆ በመያዝ፤ ኢስላምን ከቢድዓ ሰሪዎች በአላህ ፈቃድ ታድጓል፡፡ ካፈራቸው ታላላቅ ኡለማዎች ውስጥ ‹‹ኢብነል ቀይም፤ ኢብን ከሲር እና ሌሎችም ይገኛሉ››፡፡
ሙሃመድ አብድል ወሃብም፤ ሳውዲ ተበታትነው እና ሽርክ ተንሰራፍቶ እያለ፤ በአላህ ፈቃድ የነብያችንን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሱና ተከትሎ ህዝቦችን ‹‹ከፍጡራን አንላኪነት ወደ ብቸኛው ተመላኪ ፈጣሪ አላህ›› የተጣራ እና አላህም በዳእዋው ፍሬን ለግሶት የተበታተኑትን መልሶ በአላህ ፍቃድ አንድ ያደረገ ነው፡፡
ተውሂድ የሁለት አገር የድል እና የበላይነት ምንጭ ነው፡፡ ተውሂድን ወደ ኋላ ብሎ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በሽታው አቂዳ ላይ ለሆነ ሰው፤ ሰላት ስገድ ቢሉት ምን ይፈይደዋል፡፡ አህለል ኪታቦችም ይሰግዳሉ፤ ይፆማሉ፤ ሰደቃ ይሰጣሉ፤ ነገር ግን አቂዳቸው ላይ እግር አለ፤ ከአቂዳም አልፎ የነብያችንን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ነብይነት አይቀበሉም፡፡
ዛሬ ግን በጣም የሚያሳዝነው፤ የአላህን መብት ሳያከብሩ እና ሳያስከብሩ፤ ከመሪዎች ፍትህን ይጠብቃሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ፈተና የዳረገን፤ ‹‹ሽርክ፤ ቢድዓ፤ ወንጀል በጠቅላላ፤ በኸይር አለማዘዝ እና ከመጥፎ አለመከልከል›› ናቸው፡፡
መድሃኒቱም አላህን በብቸኝነት ማምለክ፤ የነብያችንን ሱና መከተል፤ ከወንጀል ሁሉ በቻሉት መጥራት፤ ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለም ሲሳሳቱ ወዲያው በንሰሃ መመለስ፤ በጥሩ ማዘዝ ከመጥፎ መከልከል እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የእውነተኛ የሙስሊሞች ጉዳይ የሚያስጨንቀው፤ ሙስሊሞችን ሙስሊም ያስባላቸውን፤ ነብያት ሁሉ የተላኩበትን ተውሂድ ወደሱ ይጣራ፤ አላህ እና መልክተኞቹ ሁሉ በመጀመሪያነት የከለከሉትን ‹‹ሽርክ›› ይከልክል፡፡ በቁጥር 3 ኢንሻአላህ ስለ ኢራቅ እናነሳለን፡፡ አላህ የኢህላስ ባለቤቶች ያድርገን፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት ሁሉ መደምደሚያ በነብዩ ሙሃመድ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በባልደረባዎቻቸው፤ ሃቅን በተከተሉ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡