Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እንደስራችሁ መሪ ይሾምባችኋል


=============================================
በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ እጅግ በጣም ሩህ ሩህ፡፡ የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብዩ ሙሃመድ፤ በቤተሰቦቻቸው፤ በሰሃባዎቻቸው እና ፈለጋቸውን እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን፡፡
ይህንን አስተማሪ የሆነ ቃለ ምልልስ ልብ ብለን እናንብበው፤ ውስጡ ያለውን መልክትም እንረዳው፡፡የበኒ ኡመያ መሪ ከሆኑት ውስጥ አብድመሊክ ኢብን መርዋን (ረሂመሁላህ) የተባሉት ማህበረሰቡ ስለስልጣናቸው እያወራ እንደሆነ ሰሙ፡፡ ከዛም የማህበረሰቡን ታላላቅ ሰዎች ጠሩና የሚከተለውን ጠየቁ
‹‹እኛ አቡበክር እና ኡመርን እንድንሆንላችሁ ትፈልጋላችሁ?››

እነሱም እንዲህ አሉ ‹‹አዎን አንተም ኸሊፋ ነህ እነሱም ኸሊፋ ናቸው፡፡››
አብድልመሊክ ኢብን መርዋን እንዲህ አሉ ‹‹እናንተ በአቡበክር እና ኡመር ዘመን እንደነበሩ ሰዎች 
ሁኑልን እኛም አቡበክር እና ኡመርን እንሆንላችኋለን››
የአብዱልመሊክ እና ህዝቦቻቸው ያደረጉት ንግግር እዚህ ላይ አበቃ
በመቀጠል የዛሪው አርዕስት መሪ እና ተመሪ የሚል ይሆናል፡፡ ዛሬ ሀይማኖታዊ እውቀት እየጠፋ እና ማሀይምነት እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ላይ፤ ከባድ መከራ እና ችግር እየደረሰ ይገኛል፡፡ ችግሩን የሚያከፋው ግን፤ በሽታው ወይንም ችግሩ በምን እንደመጣ አብዛኛው ሰው አለማወቁ ነው፡፡
አላሁ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) መለኮታዊ መፀሃፍትን አወረደ፤ መልክተኞችን እና ነብያትን ላከ፤ ለሰው ልጆች መመሪያ ይሆኑ ዘንድ፡፡
ብዙ ሰዎችም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች አለም ላይ እየተከሰተ ያለውን ችግር መሪዎች ላይ ብቻ አላከው ይገኛሉ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው፤ መሪ እንደህዝቡ ስራ እንደሚሾም መሆኑን አለማወቃቸው ነው፡፡
አላህም እንዲህ ይላል ‹‹ከፊል በዳዬችን በከፊል በዳዬች ላይ እንሾማለን››
ህዝቦች ለአላህ ታማኝ፤ የእርሱን ህግጋት በመሙላት የሚገባቸውን ያህል ሲያደርጉ፤ መሪዎቻቸውም ይስተካከላሉ፡፡ በተቃራኒው የአላህን ህግጋት ሁሉ ጥሰው ጥሩ መሪ ሲከጅሉ በጣም ገርሞ የሚገርም ነው፡፡
የነብያችንን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ዘመን ብናይ እሳቸውን ለነዛ ምርጥ ለተባሉት አላህ ዘንድ ለተወደዱት፤ እውነተኝነታቸው ለተረጋገጠላቸው፤ ሙሃጂር እና አንሷሮች አላህ መሪ አድርጎ ሾማቸው፡፡ ከዛም አቡበክር፤ ከዛም ኡመር፤ ከዛም ኡስማን፤ ከዛም አልይ (ሪድዋኑላሂ አለይሂም አጅመኢን)፡፡
ታድያ የአላህ ባሪያዎች ለምን ስራችንን በነፍስ ወከፍ አናስተካክልም፡፡ አለም ላይ እየደረሰ ያለው መከራ እኛ በሰራነው አይደለምን???
ምሳሌዎች ማንሳቱ ጥሩ ነው፡፡
1) ተውሂድን ትቶ በአላህ ላይ ማጋራት፡፡
ከአላህ ውጭ ያለን በመለመን፡፡ ለምሳሌ አብድል ቃድር ጀይላኔ፤ አልይ፤ ሁሴን፤ ነብያችንን፤ አህመድ በደዊ እና የመሳሰሉትን፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ ኑርሁሴን፤ አብሬት፤ ቃጥባሪ፤ አልከሲዬ፤ ዳንይ፤ ደግዬ፤ አሊ ጎንደር፤ አባድር፤ የዳንግላው፤ የቲጃንዬ እና የመሳሰሉት፡፡ ከአላህ ውጭ ያለን እየለመኑ፤ ክብረ ባዕል ብለው እየደገሱ፤ ከአላህ ውጭ ላሉ እያረዱ ጥሩ መሪ እና ድል ይከጀላልን፡፡
2) የነብያችንን ሱና ትቶ ቢድዐ መስራት
ከሰላት በኋላ ዱዓ፤ ሃሙስ ማታ፤ እሳቸው ያዘዙትን የሚተገበር ሱና ትቶ የከሃዲ ህዝቦችን ሱና መከተል፡፡
3) ሰሃባዎችን ከማክበር ይልቅ ሰሃባን ለሚጠሉ እና ለሚሳደቡ ሰዎች አድናቆትን መስጠት
ይሄ በግልፅ ያየነው እና በማስረጃ ከዚህ በፊት የመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰይድ ቁጡብ የተባለው ጋዜጠኛ ታላቁን ሰሃባ ኡስማን ኢብን አፋንን (ረድየላሁ አንሁም) ሲሳደብ እና ሲያዋርድ፤ ቡዙ የቢድዐ አራማጆች ለምን ተጋለጠ ብለው እዚሁ አገራችን ላይ ሲፎክሩ ታይተዋል፡፡ ሰሃባን እየሰደቡ እና እያሰደቡ ድል አለ???
4) የወላጆች ሃቅን ማጓደል
እናት እና አባት ልጆች ሲያሳድጉ ስንት መከራ አይተው ዛሬ ልጆች እናት እና አባቱን እያፈጠጠባቸው እና እየጨናነቃቸው፡፡ ልጆች ዛሪ ሰለጠን ብለው፤ ከአባት እና ከናታቸው ጋር አብሮ መሄድ የሚያሳፍራቸው ዘመን ላይ ተደርሶ፡፡ በልጅነቱ ስታሳድገው እንቅልፍ ያጣችው ላይበቃ፤ ዛሬ በተገላቢጦሽ ዲሽ ቤት ኳስ አይቶ መጥቶ ይረብሻታል
5)በሀይር አለማዘዝ ከመጥፎ አለመከልከል
አሁን ባለንበት ወቅት ስንት የጥመት ጀመዓዎች አሉ ይህንን ትልቅ የእስልምና ተግባር እንዳይተገበር እየጣሩ ያሉ፡፡ አንደኛው ተነስቶ ‹‹በተስማማንበት እንተጋገዝ በተለያየንበት (እንቻቻል) እንተላለፍ›› ይላል እንደ ኢህዋነል ሙስሊሚን አይነት፤ ነብያችን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ደግሞ ‹‹ከናንተ ውስጥ መጥፎ ሲሰራ ያየ በእጁ ያስቁመው፤ ያልቻለ በምላሱ፤ ያልቻለ በቀልቡ ይጥላ…….›› አላህ ደግሞ ‹‹በአንዳች ነገር ብትለያዩ ወደ አላህ(ቁርዓን) እና መልክተኛው(ሱና) መልሱት ይላል››፡፡ እንደ ጀመዓተ ተብሊግ አይነቱ ደግሞ ‹‹በአካባቢ ሀቅ አንገባም›› ብለው ሽርክ ሲሰራ ቢያዩም ምንም አይናገሩም፡፡
6)በወለድ መስራራት
ይሄ አለማችን ላይ በተግባር እየታየ ያለ ነው፡፡
7) የተፈጠሩለትን አላማ ረስቶ ጊዜን ማጥፋት
ፊልም፤ ዘፈን፤ ኳስ እና የመሳሰሉትን እያዩ ሰላት አለመስገድ፤ ማሳለፍ፤ ልብን ማድረቅ፡፡ ብሎም በነዚህ ነገሮች ለመርካት መሞከር በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡
ከነፍሴ ጀምሮ አላህን እንፍራ፤ ሀቁን እንወጣ፤ የነብያችንን ሱና እንከተል፤ ለሰሃባዎች ክብር እንስጥ ጠላታቸውን ጠላት አድርግን እንያዝ፤ ቤተሰቦቻችንን እናክብር፤ በኸይር እንዘዝ ከመጥፎ እንከልክል፡፡ አላህ የሚወደውን ሁሉ እንስራ አላህ የሚጠላውን ሁሉ እንራቅ፡፡ አላህ ሁለት አገር የድል ባለቤቶች ያደርገናል፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት ሁሉ መደምደሚያ አበል ቃሲም ላይ ይሁን፡፡ አላሁመ አሚን፡፡