"ትንሹ ዒድ(የሸዋል ዒድ)" የሚባለው በሸሪዓ እንዴት ይታያል?
ለርእሳችን መንደርደሪያ ይሆነን ዘንድ ዑለሞች የሸዋልን ስድስት ቀን ፆም በተመለከተ የሚያነሷቸውን የተለያዩ ሀሳቦች አጠር ባለ መልክ ለማየት እንሞክራለን።
👉ከሸዋል ወር ስድስት ቀናትን መፆምን በተመለከተ አብዛኞቹ ዑለማዎች የሚወደድ በመሆኑ ላይ የተስማሙ ቢሆንም ከአራቱ መዝሀብ ኢማሞች የሁለቱ የአቡ ሀኒፋ እና የማሊክ አቋም ግን ከዚህ በጣም ይለያል። ኢማሙ ማሊክ ሙወጣእ በተባለው ኪታባቸው ላይ በግልፅ እንደሚጠላ ሲገልፁ ከአቡ ሃኒፋም ተመሳሳይ አቋም ተንፀባርቋል።
አቡ ሃኒፋ ምክንያታቸው አላህ በደነገገው ፆም ላይ መጨመር ከአህለል ኪታቦች ጋር ያመሳስላል፤ ከነሱ ጋር መመሳሰል ደግሞ የተከለከለ ነው። የሚል ሲሆን በኢማሙ ማሊክ በኩል ደግሞ የቀረበው ምክንያት የእውቀት ባለቤቶች ሲፆሙት አላየሁም፤ ይልቁን መሀይማን እነሱ ሲፆሙት ቢያዩ ከረመዳን ያልሆነውን ፆም ከረመዳን አንደሆነ በማሰብ ቢደዓ ላይ ይወድቃሉ ብለው እንደሚፈሩ ገልፀዋል፤ በተጨማሪም ከሰለፎች ከአንዱም ይፆም እንደነበረ መረጃ አልደረሰኝም የሚል ነው። እዚህ ጋር አብሮ ተያይዞ መጠቀስ የሚገባው እነዚህ ዑለማዎች በሰሂህ ሙስሊም ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘውን እና ሌሎችንም የሸዋልን ስድስት ቀን መፆምን በተመለከተ የተዘገቡ ሀዲሶች እንዳልደረሷቸው ነው። ለዚህም ነው ከነሱ በኃላ ዘግይተው የመጡ የሀኒፍያ እና የማሊክያ መዝሀብ ዑለሞች በፊቅህ ኪታቦቻቸው ከተወደዱ የፆም አይነቶች መደዳ ያሰፈሩት በሌላ በኩል እነሱ ይሰጉት የነበረው ነገርም በመወገዱ መሆኑን የጠቀሱም አልጠፉም።
👉 በሌላ በኩል መፆሙ ይወዳዳል ያሉትን አል ኢማም አሻፊዒይ እና አህመድን ጨምሮ አብዛኞቹ (ጁምሁሮቹ) ዑለማዎችን አቋም ስንመለከት መቼ ይፆም በሚለው ላይ ከዒዱ ቀን ማግስት ጀምሮ ከሚለው ጀምሮ ከሸዋል ወር በኃላም ቢሆን እሰከሚለው የሀሳብ ልዩነትን አንፀባርቀዋል። ከፊሎቹ አከታትሎ ከወሩ መጀመሪያ ላይ መፆሙ ይወደዳል ሲሉ፤ ከፊሎቹ ደግሞ አይ ከዒድ በኃላ ወዲያው መፆም የለበትም ይልቁን ከአስራ ሶስተኛው ቀን በፊት ሶስት ቀን ይፆማል ይላሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በወሩ ውሰጥ በማነኛውም ጊዜ ከፆመው ፆሙን ባያከታትልም ቢያከታተልም ለውጥ የለውም ብለዋል።
👉 እንደጥቅል ከሸዋል ስድስት ቀናትን መፆም የሚወደድ መሆኑን የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም “ ረመዳንን ጾሞ ከዛም በኃላ ከሸዋል ወር ስድስት ቀናትን በመጾም ያስከተለው አንድ አመት የጾመ ያህል ነው። ” ማለታቸው የሚያመላክተው እንዲሁም የአብዛኞቹ ዑለማዎች አቋምም ቢሆንም። ነገር ግን አሁንም በዚህ ሀዲስ እና ሌሎች ተመሳሳይ ሀዲሶች አረዳድ ላይ የሸዋልን ስድስት ቀናት መፆም ይወደዳል የሚል አቋም የያዙት ዑለማዎች እራሳቸው ሌሎች ጥያቄዎችን አንስተዋል። ለምሳሌ ረመዳንን አሟልተው ያልፆሙ ሰዎች ቅድሚያ ቀዷእ ነው የሚፆሙት ወይስ ሸዋልን መፆም ይችላሉ? አይችሉም ካልንስ የሸዋል ወር ከወጣ በኃላ ቀዷቸውን ከጨረሱ የሸዋልን ሰድስት ቀን መፆም እንዴት ይታያል? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል።
👉 ይህንን ሀሳብ በመንደርደሪያዬ ላይ የጠቀስኩበትን ምክንያት ምን እንደሆነ ሳትረዱኝ የቀራችሁ አይመስለኝም። ምንም እንኳ እንደጥቅል በመልካም ስራ ላይ መቻኮል የተወደደ ስለሆነ በቶሎ መፆሙ አስፈላጊ እንደሆነ መምከሩ ተገቢ ቢሆንም ከርእሱ ጋር በተያያዘ ዑለማዎች ጋር ያለውንም ልዩነት ማወቁ አሁን ለምንነጋገርበት ርእስ ወሳኝ ነው። ያም እንኳን ለሸዋል ዒድ የሚባል ሊኖረው አይደለም ከጅምሩ ፆሙ የተወደደ ነው ወይስ አይደለም? የሚፆመው ከመቼ ጀምሮ እና እንዴት ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ አራቱ ኢማሞች እና ተከታዮቻቸው ያላቸውን ልዩነት ማወቁ በእርግጠኝነት "የሸዋል ዒድ" የሚባል ርእስ በነሱ ዘመን ያልነበረ መሆኑን በማያሻማ መልኩ ያስረዳል።
እንደውም ኢማሙ አቡ‐ሀኒፋ እና ማሊክ ዛሬ ሰዎች የወደቁበት ችግር ላይ ወይም እርሱን ተከትሎ ከሚመጣ ቢደዓ ላይ እንዳይወድቁ በመፍራት ነበር መፆሙኑም ይጠሉት የነበረው። ይህንንም በንግግራቸው ውስጥ እንረዳዋለን።
በኢስላም ስንት ዒድ አለ? በኢስላም ዒድ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቀናት የትኞቹ ናቸው? ትንሹ ዒድ ይኖርበት ይሆን?
عَنْ أَنَسٍ-رضي الله عنه- قَالَ: قَدِمَ رَسُولُ اللَّهِ -صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ- الْمَدِينَةَ، وَلَهُمْ يَوْمَانِ يَلْعَبُونَ فِيهِمَا فَقَالَ:(مَا هَذَانِ الْيَوْمَانِ؟) قَالُوا: كُنَّا نَلْعَبُ فِيهِمَا فِي الْجَاهِلِيَّةِ، فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ -صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ-: (إِنَّ اللَّهَ قَدْ أَبْدَلَكُمْ بِهِمَا خَيْرًا مِنْهُمَا يَوْمَ الْأَضْحَى وَيَوْمَ الْفِطْرِ) رواه أبو داود
አነስ ኢብኑ ማሊክ እንዲህ ይላሉ:- ‹‹የአላህ መልእክተኛ (ሰላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን) መዲና ከተማ ሲመጡ የመዲና ሰዎች በመሀይምነት ዘመን (ደስታቸውን የሚገልፁባቸው) የሚጫወቱባቸው ሁለት ክብረ-በዓላት ነበሯቸው። ይህንን ባዩ ጊዜ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ አሉ፡፡ "አላህ በእነዚህ በሁለቱ ምትክ ከእነርሱ የተሻሉ ሁለት ክብረ-በዓላትን ቀየረላችሁ፤ እነሱም "የፊጥር" እና "የአድሀ" በዓላት ናቸው፡፡" (አቡዳውድ እና አህመድ ዘግበውታል)
عن عقبة بن عامر قال: قال رسول الله صلى الله عليه وسلم "يومَ عرفةَ ويومَ النَّحرِ وأيَّامَ التَّشريقِ عيدُنا أَهْلَ الإسلامِ " رواه أبو داود والترمذي والنسائي.
ዑቅባ ኢብኑ ዓሚር(ረዲየላሁ ዓንሁ) እንዳስተላለፉት:- መልእክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል: - "የዓረፋ እና የእርዱ እለት እንዲሁም የተሽሪቅ ቀናት የእኛ የሙስሊሞች ዒዶች ናቸው።" ( አቡዳውድ ዘግበውታል አልባኒም ሰሂህ ብለውታል)
ከነዚህ እና መሰል ሌሎች ተመሳሳይ ሀዲሶች ዑለማዎች የተረዷቸዉን ቁም ነገሮች ልናስተውል ይገባል።
አንደኛ፡- ከእስልምና ውጭ ካሉ ማህበረሰቦች ጋር መመሳሰል የተከለከለ መሆኑን::
ሁለተኛ ፡- በኢስላም የተደነገጉ ክብረ-በዓላት ሁለት ብቻ መሆናቸውን ነው::
ሶስተኛ:- እነዚህ ክብረ በእላት ለሙስሊሞች አጠቃላይ እንደሆኑ:: ማለትም ለፆመውም እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ላልፆመውም፤ ቀዳእ ላለበትም ለሌበትም፤ ለድሀውም ለሀብታሙም፤ ለትንሹም ለትልቁም፤ በወቅቱ ሰላት ለሚሰግዱም ሰላት ላለመስገድ ምክንያት ያላቸውን ሴቶች ጨምር በአጠቃላይ ለሁሉም ሙስሊሞች ዒድ መሆኑን ያመለክታሉ::
በኢስላም የተደነገጉ ክብረ-በዓላት ሁለት ብቻ መሆናቸውን ነው:: ኢብኑ ሀዝም የዑለማዎች አጠቃላይ ስምምነት (ኢጅማዕ) እንዳለ እንዲህ በማለት ዘግበዋል:-
ኢብኑ ሀዝም (384-456 ሂጅሪይ) ረሂመሁ አላህ እንዲህ ይላሉ:- "የመጀመሪያው ዒድ ዒድል-ፊጥር ነው:: እሱም ከሸዋል ወር የመጀመሪያው እለት ነው:: ሁለተኛው ደግሞ ዒድ የአድሀ ቀን ነው:: እሱም ከዙል-ሂጃ ወር አስረኛው እለት የሚውለው ነው:: ለሙስሊሞች ከነዚህ ወጪ ዒድ የላቸውም የጁሙዓ እና ከአድሀ ቀን በኋላ ያሉ ሶስት ቀናት ቢሆኑ እንጂ:: ምክንያቱም አላህ እና መልእክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከነዚህ ቀናት ውጪ ዒድን አላደረጉላቸውምና:: በዚህ ጉዳይ በዑለማዎች መካከል ምንም አይነት ልዩነት የለም::"
ከላይ ያሳለፍናቸውን ሀዲሶች እና ይህንን ኢጅማዕ አንድ ላይ አድርገን ስንመለከተው ዒድን የመደንገግ መብት የአላህ እና የመልእክተኛው ብቻ እንደሆነና ኢስላም የተሟላ ስርአት ያለው ዲን ስለሆነም ከማንም ኩረጃም እንደማይፈልግ እንዲሁም እንደማይቀበል እንረዳለን:: በዲሶቹም ውስጥ አመታዊ በእሎች ሁለት ብቻ እንደሆኑ ዒደል-ፊጥር አንድ ቀን ብቻ እንደሆነ ዒድል-አድሀ ግን ከሱ በፊት ካለው የዓረፋ እለት እና እሱን ተከትለው ከሚመጡት ሶስት (የተሽሪቅ) ቀናት ውጪ ምንም አይነት አምት በእል እንደሌለ በግልፅ እንረዳለን::
ዲናችን ሙሉ መሆኑን አላህ በዚህ የቁርአን አንቀጽ ይነግረናል:-
الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا} المائدة 3
‹‹ዛሬ ሐይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ፀጋዬንም በእናንተ ላይ ፈፀምኩ፤ ከሀይማኖት በኩልም ለእናንተም ኢስላምን ወደደኩ...›› (አልማኢዳ፡ 3)
ከዚህም በመነሳት መጨመርንም ይሁን መቀነስን አይቀበልም እንዲሁም ከሌሎች መኮረጅንም ሆነ መመሳሰልን ይከለክላል፡፡
ይህንን እዉነታ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላምና ሰላት በርሳቸው ላይ ይሁን) በዚህ ሀዲሳቸው ይገልፁታል፡፡
قال رسول الله صلى الله عليه وسلم : ( من أحدث في أمرنا هذا ما ليس منه فهو رد ) رواه البخاري (2697) ومسلم (1718)
"በዚህ በዲናችን ላይ ከርሱ ያልሆንን ያመጣ (ሰው) ስራው ተመላሽ ነው፡፡ (ተቀባይነት አይኖረውም)" (ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውታል)
"ዒዱል አብራር" በመባል የሚታወቀውን "የሸዋል ዒድ" በተመለከተ ከዑለማዎች ፈትዋ አንዱን ብቻ ልጥቀስ በሱም ላብቃ::
ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ብለዋል:‐ "በሸሪዓ ያልተደነገጉ ጊዜያትን የበእላት ጊዜ አድርጎ መያዝን በተመለከተ እንደ የረቢዓል አወል(የመውሊድ)ና የረጀብ የተወሰኑ ለሊቶች፣ የየዙል ሂጃ ስምንተኛው ቀን ወይም ከረጀብ ወር የመጀመሪያውን ጁሙዓ አልያም ከሸዋል ስምንተኛውን ቀን የደጋጎች (ዒዱል‐አብራር) ዒድ ብለው መያዛቸው ከቢደዓ ነው:: ሰለፎችም አይወዱትም አልሰሩትምም::"
አላህ ቅኑን መንገድ ይምራን!
✍️ ጣሀ አህመድ - (1441 ሂ የተፃፈ)
0 Comments