Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

መውሊድን በማስመልከት ማስረጃ እያሉ ከሚያቀርቧቸው መሞገቻዎች መካከል ለ33 ያክሉ መልስ የተሰጠበት መጠነኛ ፅሁፍ

       


  ምስጋና ለአላህ ይገባው ፡፡ በእርሱ እመካለሁ ፣ ወደርሱ ተጸጽቸ እመለሳለሁ ፡፡ ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የሌለ መሆኑን ፣ ነብዩ ሙሐመድ ﷺ የአላህ አገልጋይና መልክተኛ መሆናቸውን ፣ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ህዝብን በትክክል የመከሩና የተሰጣቸውን አደራ በአግባቡ የተወጡ መሆናቸውን ፤ መልካም ነገር ኖሮ የተውት ፣ መጥፎ ነገር ኖሮ ያላስጠነቀቁት አንድም ነገር የለም ብየ በእርግጠኝነት እመሰክራለሁ፡፡ በእርሳቸው ፣ በቤተሰቦቻቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ የአላህ ሶላትና ሰላምታ ይስፈን፡፡ 

ከዚህ በመቀጠል፡
      ሶሃቦቹ - ረዲዬሏሁ ዓንሁም - የረሡልን ﷺ የትውልድ ዘመን ከታሪካቸው አንዱ ምዕራፍ በማድረግ እርሳቸው ያዘዟቸውን ትዕዛዛት ተፈጻሚ ለማድረግ ፤ የከለከሏቸውን ደግሞ ለመራቅ ታሪካቸውን በመማር ልጆቻቸውን በማስተማር የተጠመዱ ነበሩ፡፡ አላህ ለረሡል ﷺ የለገሳቸውን ምርጥ ስነ-ምግባር ወደራሳቸው ለማምጣትም ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡
    የረሡልን ﷺ ምርጥ ስነ-ምግባር አስመልክቶ አላህ - ሱብሃነሁ ወተዓላ - በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡- 
"وَإِنَّ لَكَ لَأَجْرًا غَيْرَ مَمْنُونٍ (٣)" القلم ٦٨:٣
"وَإِنَّ لَكَ لَأجْرًا غَيْرَ مَمْنُونٍ (٣)" القلم ٦٨:٣
 “አንተም በታላቅ ጸባይ ላይ ነህ፡፡” (አል ቀለም፡4)
 
      በነብዩ ﷺ ታሪክ ዙሪያ የተጻፉ በርካታ መጽሐፍት በቅጥፈት ፣ በፈጠራና በውሸት የታጨቁ ፤ በቅድሚያ የረሡልን  ﷺ ስብዕና ከዚያም የእስልምናን ሐይማኖት ገጽታ የሚያጠለሹ በመሆናቸው ቀደምቶችም ይሁን በወቅታችን የሚገኙ የአህለሱና ዑለሞች በጻፏቸው የታሪክ መጽሐፍት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ማንኛውም ሙስሊም በውሸት ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ፤ ከቁርኣንና ከሐዲስ ጋር የሚፋለሱ መጽሐፍትን ለዲኑ መሰረት ሊያደርግ በፍጹም አይገባም፡፡ ቅድሚያ ማንኛውም ታሪክ ወደቁርኣንና ወደሐዲስ ቀርቦ ሊመዘን ይገባዋል፡፡ ከሐቁ ጋር ገጥሞ ከተገኘ መቀበል ግዴታ ሲሆን ከእውነታው የራቀ ከሆነ ደግሞ አሽቀንጥሮ መጣል ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡ 
    የመውሊድ ባለቤቶች በታሪክ ግድፈት ውድቅ በሆኑና ከሸረሪት ድር በደከሙ ማስረጃዎች ላይ ተንጠልጥለው ይገኛሉ፡፡ በማንኛውም መንገድ በቅርብም ይሁን በሩቅ መውሊድ በእስልምና ሐያማኖት መፈቀዱን የሚጠቁም የቁርኣንም ይሁን የሐዲስ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም፡፡ ስሜት የሰው ልጅን ወደጥመት እንደማግኔት የሚስብ መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በዘመናችን ሳያስተነትኑ ተቃራኒ ንግግሮችን የሚናገሩ ሰዎች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ለምን አላህን አይፈሩም? ነብዩን ﷺ መውደድ እርሳቸውን በመከተል እንጅ አዳዲስ ሰርጎ ገብ አምልኮቶችን በሸሪዓው ላይ በመጨመርና በመፍጠር አይደለም፡፡
     በመሆኑም ሙስሊሙ ሕብረተሰብ በዚህ አወዛጋቢ አጀንዳ ዙሪያ የማያወላዳ ግንዛቤ ይጨብጥ ዘንድ ለቀረቡ ብዥታዎች ምላሽ ከሰጡ የተለያዩ መጽሐፍት ሰላሳ ሶስት የሚሆኑትን ብቻ በመምረጥ “በኢስላም ውስጥ ሰርጎ ገብ የሆነው መውሊድ ብዥታዎቹና መልሶቻቸው” በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ግልጽ በሚሆን መልኩ በዚህ የትምህርት ክፍል በአላህ ፈቃድ አጠር አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ 

አላህን በመፍራት ላይ እኔንም እናንተንም አደራ እላለሁ ፤ አላህን የፈራ ሰው ከክፉ ነገር ይጠበቃል ፤ መልካም ለሆነው ጎዳና አላህ ይመራዋል፡፡

ብዥታ 1፡

የመውሊድ ባለቤቶች መውሊድን ሐይማኖታዊ በዓል አድርገው ለማክበር የሚከተለውን የቁርኣን አንቀጽ ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ፡-

"قُلْ بِفَضْلِ ٱللَّهِ وَبِرَحْمَتِهِۦ فَبِذَٰلِكَ فَلْيَفْرَحُوا۟ هُوَ خَيْرٌ مِّمَّا يَجْمَعُونَ (٥٨)" يونس ١٠:٥٨
 “በአላህ ችሮታና በእዝነቱ (ይደሰቱ) ፤ በዚህም ምክንያት ይደሰቱ ፤ እርሱ ከሚሰበስቡት ሀብት በላጭ ነው” በላቸው፡፡” (ዩኑስ፡58)

 “አላህ በረህመቱ እንድንደሰት አዞናል ፤ ነብዩ ﷺ ደግሞ ትልቁ ረህመት (እዝነት) ናቸው፡፡ ምክንያቱም ይህን አስመልክቶ አላህ የሚከተለውን ቁርኣን አውርዷል፡፡” ይላሉ፡፡
"وَمَآ أَرْسَلْنَٰكَ إِلَّا رَحْمَةً لِّلْعَٰلَمِينَ " الأنبياء ٢١:١٠٧
 
“(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡” (አል አንቢያእ፡107) 

   መልስ 1

ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን የቁርኣን አንቀጾች መውሊድን ለማክበር ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ትክክል አይደለም፡፡ አንድን የቁርኣን አንቀጽ ባልተፈለገ መልኩ ቆልምሞ መተርጎም ከዓሊሞች ዘንድ ያልተረጋገጠ ፤ ከሰለፎች ግንዛቤ የወጣና ፤ የሸሪዓውን ህግ የተጻረረ ነው፡፡ 
    የመውሊድ ባለቤቶች ከስሜታቸው ጋር ለማጣጣም ሲሉ የሚያቀርቧቸው መረጃዎች የዚህ ማህበረሰብ የቁርኣን ተንታኞች ከተጓዙበት ትርጉም አንጻር ቆቅ ወዲህ ቅዥምዥም ወዲያ ናቸው፡፡ የቁርኣን ተንታኞች የአላህ ችሮታ እና እዝነት የሚለው የቁርኣን ቃል ጽንሰ ሐሳብ በምን አይነት መልኩ ተገነዘቡት የሚለውን በተወሰነ መልኩ መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ 
ኢማም አጥጦበሪ - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡- ((“አላህ ለነብዩ ﷺ የሚከተለውን ተናግሯል፡- አንተ ሙሀመድ ሆይ! ለእነዚያ በአንተና በአንተ ላይ በተወረደው ለካዱ አጋሪዎች የሚከተለውን ንገራቸው፡- እናንተ ሰዎች ሆይ! አላህ በችሮታው በእናነተ ላይ ጸጋን ለገሳችሁ ፤ እርሱም ኢስላም ነው ፤ እርሱንም ለእናንተ ግልጽ አደረገ ፤ ወደርሱም ቅስቀሳ አደረገ ፤ በእዝነቱም ለእናንተ አዘነላችሁ ፤ መጽሐፉን በማውረድ ከዚህ በፊት የማታውቁትን አሳወቀ ፤ የዲናችሁን መለያ ምልክት በእርሱ አስገነዘባችሁ ፤ እርሱም ቁርኣን ነው፡፡” 

አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናገረ፡ - “በአላህ ችሮታና በእዝነቱ (ይደሰቱ) ፤ በዚህም ምክንያት ይደሰቱ ፤ እርሱ ከሚሰበስቡት ሀብት ሁሉ በላጭ ነው” በላቸው፡፡” (ዩኑስ፡58) 
ወደርሱ ጥሪ ያደረገላችሁ ኢስላም ፤ በእነርሱ ላይ ያወረደው ቁርኣን ፤ ከሚሰበስቡት ገንዘብ እና ድልብ ሐብቶች ሁሉ በላጭ ነው በላቸው፡፡”)) (ተፍሲር አጥ ጦበሪይ፡15/105)

 ኢብን ከሲር - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናገሩ፡- ((“አላህ በረሡል ﷺ ላይ ባወረደው ቁርኣን በፍጡራኖች ላይ በመመጻደቅ የሚከተለውን ተናገረ፡- “እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ግሳጼ በርግጥ መጣላችሁ” ማለትም ከጸያፍ ነገር የሚገስጽ ማለት ነው፡፡ “በደረቶች ውስጥ ላለውም የመጠራጠር በሽታ መድሃኒት (በእርግጥ መጣላችሁ)” ማለትም ለብዥታዎችና ለጥርጣሬዎች መድሐኒት የሆነ ማለት ነው ፤ (ወሁደን ወረህመተን) ማለት ደግሞ በእርሱ ወደቅኑ ጎዳና የሚመሩበት እና አላህ በእርሱ የሚያዝንበት ማለት ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ለአማኞች፣ ለአረጋጋጮች እና ቁርኣንን እውነት ብለው ለተቀበሉት ብቻ ነው…)) (ተፍሲር ኢብኑ ከሲር፡2/1131) 

 ኢብን አልቀይም - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡- “ፈድሉሏህ” (የአላህ ችሮታ) እና “ወረህመቱሁ” (እዝነቱ) ለሚሉት የቁርኣን ቃላቶች የሰለፎች ትርጉም የሚሽከረከረው (ኢስላም እና ሱና) በሚሉት ትርጉሞች ዙሪያ ነው፡፡ (ኢጅቲማዑል ጁዩሺል ኢስላሚያ፡ ገፅ፡6 )
በእነዚህ ሁለት ጸጋዎች ልቦና ህያው ከሆነ ደስታ ይጨምራል ፤ ግንዛቤው ከፍ ካለ ደግሞ በሐሴት የተሞላ ይሆናል ….”      በዚህ የቁርኣን አንቀጽ ሙብተዲዖች ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው ማንኛውም ሐቅ ፈላጊ ሁሉ ያረጋግጣል ማለት ነው፡፡ ሙብተዲዖች የሰለፎችን ትርጉም የሚቃረን እንኳ ቢሆን መረጃዎችን ከስሜታቸውና ከልብ ወለዳቸው ጋር ለማጣጣም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ 

ብዥታ 2 

ነብዩ ﷺ የዓሹራን ጾም ጹመውታል፡፡ ተከታዮቻቸው እንዲጾሙትም አዘዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ “ይህ ሙሳን እና ህዝቦቹን ነጻ ያወጣበት ፊርዓውን እና ተከታዮቹን ደግሞ ያሰመጠበት ቀን በመሆኑ ታላቅ ቀን ነው፡፡ ሙሳ ﷺ አላህን ለማመስገን ይህን ቀን ጾሙት እኛም እንጾመዋለን፡፡” (ቡኻሪ፡2004 ሙስሊም፡1130) በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ረሡል ﷺ ሙሳን እና ህዝቦቹን ከፊርዓውን ነጻ በማድረጉ አላህን ለማመስገን ጾመውታል ፤ እኛም ነብዩ ﷺ የተወለዱበትን ቀን የምስጋና ፣ የደስታ እና የዒድ ቀን በማድረግ እናከብረዋለን፡፡” ይላሉ፡፡

 መልስ 2

ጸጋ በመገኘቱ ምክንያት ከዓሹራእ ጾም ጋር ተያያዥ የሆኑ ሐዲሶችን መውሊድ ለማክበር በንጽጽር ማምጣት ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም በሁለቱም ምስጋናን ይፋ የምናደርግባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው፡፡ በዓሹራ ቀን ጾም ይጾማል ፤ በመውሊድ ቀን ደግሞ ድግስ ተደግሶ ምግብ ይበላል፡፡ በዚህም ንጽጽሩ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ምንም እንኳ ረሡል ﷺ ተወልደውበታል በሚባለው ረቢዑል አወል 12ኛው ቀን መጾም በሸሪዓ ያልተደነገገ መሰረተ ቢስ ተግባር ቢሆንም በመውሊዱ ቀን ጾም ቢጾሙ ንጽጽራቸው የተቀራረበ ይሆንላቸው ነበር፡፡
 
    ከዚህ ላይ መታወቅ የሚገባው ወደአላህ የምንቃረብበት ተግባር ሁሉ በቂያስ ወይም በንጽጽር የሚጸድቅ አለመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የአምልኮት መሰረቱ አላህ የደነገገው እንጅ እኛ የምንፈጥረው ባለመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን አምልኮት ያልሆኑ ነገሮች አላህ ካላስጠነቀቀ በቀር መሰረታቸው የተፈቀዱ ናቸው፡፡ 
    ነብዩ ﷺ የዓሹራን ቀን ጾመው አሳይተዋል ፤ ተከታዮቻቸውም እንዲጾሙ አዘዋል፡፡ ታዲያ እኛ ረሡልን ﷺ እንዎዳለን የምንል ከሆነ ለምንድን ነው ረሡልን ﷺ የማንከተለው? እርሳቸው የሰሩትን ለምን አንሰራም? እርሳቸው የተውትን ለምን አንተውም? ለምንድን ነው ነብዩ ﷺ የተወለዱበትን ቀን ጫት እየቃምን ፣ የተለያዩ የሽርክ መንዙማዎችን እያቀነቀንን በነብዩ ﷺ ላይ ወሰን የምናልፈው? ለምንድን ነው ነብዩን ﷺ ከአላህ ውጭ የምንማጸናቸው? ለምን ወንዶችን እና ሴቶችን በመቀላቀል ሀራም የሆኑ ተግባራቶችን እንፈጽማለን? 

ሐፊዝ ብን ሐጀር - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡- የመውሊድ ተግባር ከቀደምት ደጋጎች ከአንዱም ያልተነቀለ መሰረት የሌለው የቢድዓ ተግባር ነው፡፡” (ሐዊ 1/196) 

ኢብን አል’ሐጅ - ረሂመሁሏህ - ከመውሊድ ጋር የተቆራኙ አስቀያሚ ነገሮችን ከጠቀሱ በኋላ የሚከተለውን ተናግረዋል፡- 
  “እነዚህ ብልሹ አመለካከቶችና እምነቶች የሚሰራጩት በመውሊዱ ውስጥ የተለያዩ ግጥሞች፣ መንዙማዎች እና ድቤዎች ሲኖሩ ነው፡፡ ከእነዚህ ነገሮች የጸዳ እንኳ ቢሆን ለምሳሌ መውሊድ በሚል ሐሳብ ምግብ ብቻ ተዘጋጅቶ ሰዎችን አብልተው ቢሸኙ እንኳ ይህ ተግባር ከተዘጋጀበት ዓላማ አንጻር ብቻ በዲን ላይ የተጨመረ ቢድዓ ይሆን ነበር፡፡ ሰለፎቹ የረሡልን ﷺ ሱና በመከተል ፤ ሱናቸውን በማላቅ ብርቱዎች ፤ እርሳቸው የሰሩትን ለመስራት ተሸቀዳዳሚዎች በመሆናቸው እነርሱን መከተል ለእኛ በላጭና ግዴታ የሆነ ተግባር ይሆናል፡፡ ሰለፎቹ መውሊድን ለማውጣት ሐሳብ ነበራቸው የሚል አንድም ዘገባ ወደእኛ አልመጣም፡፡ እኛ የእነርሱ ተከታይ ነን ፤ ታዲያ ለእነርሱ የበቃቸው ለእኛም ለምን አይበቃንም?” (አል መድኸል ሊብን አል ሐጅ ፡2/110)

ብዥታ 3   

 ነብዩ ﷺ ስለ ሰኞ ቀን ሲጠየቁ የሚከተለውን መልስ ሰጠዋል፡- “ይህ ቀን እኔ የተወለድኩበት ቀን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ (ሙስሊም፡1162) ይህ ደግሞ ነብዩ ﷺ ከሌሎች ቀናቶች የተወለዱበትን ቀን በተለየ ሁኔታ እንደሚያልቁት ነው የሚጠቁመው፡፡ እርሳቸው አክብሮታቸውን የገለጹት በጾም ቢሆንም እኛ ደግሞ በክብረ በዓል መግለጽ እንችላለን፡፡ አክብሮትን በጾምም ይሁን በምግብ መግለጽ ተመሳሳይ ነው ይላሉ፡፡

 መልስ 3

ረቢዑል አወል 12ኛው ቀን ረሡል ﷺ በትክክል የተወለዱበት ቀን ከሆነም ይህን ቀን በጾም ሲያሳልፉት አልታየም፡፡ ጾም የጾሙት ሁሌም በየወሩ አራት ጊዜ ተደጋግሞ የሚመጣውን ሰኞ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ እናንተ የእርሳቸው ትክክለኛ ተከታይ ከሆናችሁ እርሳቸው የሰሩትን እንጅ በዒባዳ (አምልኮት) ላይ አዲስ ነገር ለምን ትፈጥራላችሁ? የሚል መልስ እንሰጣቸዋለን፡፡
 በዚህ መሰረት በየሳምንቱ ከሚደጋገመው ሰኞ ቀን ውጭ በረቢኡል አወል 12ኛው ቀን በሸሪዓ ትዕዛዝ የሌለበትን ተግባር መፈጸም ከረሡል ﷺ እኔ እበልጣለሁ ፤ የእርሳቸው ስራ ትክክል አልነበረምና እናስተካክለው የሚል አንድምታ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ 
ሌላው ረሡል ﷺ የሰኞን ቀን ብቻ ሳይሆን ሐሙስንም ጭምር ይጾሙ እንደነበር መታወቅ አለበት፡፡ የአላህ መልክተኛ ﷺ የሚከተለውን ሐዲስ ተናግረዋል፡- 
"تعرض األعمال يوم اإلثنين والخميس ، فأحب أن يعرض عملي وأنا صائم" 
“ሰኞ እና ሐሙስ ቀን ስራዎች (ከአላህ) ይቀረባሉ ፤ እኔ ጾመኛ ሆኘ ስራየ እንዲቀረብልኝ እወዳለሁ፡፡” (ሙስሊም፡2565) 

ሰኞና ሐሙስ ስራዎች ይቀረባሉ፡፡ ሰኞ ቀን በትክክለኛ ሐዲስ እንደተረጋገጠው የተወለዱበት ቀን ብቻ ሳይሆን በእርሳቸው ላይ ቁርኣን የተወረደበት (የተላኩበት) ቀን መሆኑም መታዎቅ አለበት፡፡ በሰኞ ቀን ጾምን ንጽጽር አድርጎ የመውሊድን በዓል ማክበር ከእውነታው የራቀ ነው፡፡ 
    ስለዚህ በዚህ ቀን የተለያዩ ቢድዓ ተግባራትን በመፈጸም ድቤ እየደበደቡ ፤ የተለያዩ የሽርክ መንዙማዎችን እያቀነቀኑ ፤ በመጨፈር ወይም ወንድና ሴት ተቀላቅሎ በመብላትና በመጠጣት ማሳለፍ ሳይሆን ረሡል ﷺ የተወለዱበትን ሰኞ ቀን ተጠባብቀን በመጾም ምስጋናችንን ልንገልጽ ይገባል፡፡ 
    አንዳንድ የመውሊድ ሰዎች ረቢዑል አወል 12ኛውን ቀን ገጥሞ የመጣውን ሰኞ ቀን በጭፈራ በመብላት በመጠጣት ማሳለፍ እንጅ መጾም የተጠላ ነው በማለት ወሰን ያለፈ ንግግር ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ 

ብዥታ 4

ኢብን አልጀዘሪ - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡-  
አቡለሐብ በህልም ታየ “ሁኔታህ እንዴት ነው?” ተብሎ ተጠየቀ ፤ “በእሳት ውስጥ ነኝ ፤ ነገር ግን በረሡል ﷺ መወለድ በመደሰት አገልጋየ የነበረችውን ሱወይባ ነጻ በማድረጌ ሰኞ ሰኞ ሌሊት እሳት ከእኔ ላይ ይቃለልልኛል፡፡” 
 ከሐዲ የሆነ ሰው በረሡል ﷺ መወለድ ተደስቶ እንዲህ አይነት ጥቅም የሚያገኝ ከሆነ አላህን የሚገዛ ሙስሊም በየአመቱ መውሊድ ደግሶ ቢያበላና ቢደሰት ምን ችግር አለው? ይላሉ፡፡ 

መልስ 4

 ከዚህ መረጃ የበለጠ ደካማ መረጃ የለም፡፡ ህልሙን የተመለከተው ሰው ማን እንደሆነ አይታወቅም ፤ በህልም የታየው አላህ የረገመው ከሀዲ ነው ፤ ከመቼ ወዲህ ነው ህልም ለሸሪዓ መረጃ ሆኖ የሚቀርበው? አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡-
"بِسْمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحْمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ تَبَّتْ يَدَآ أَبِى لَهَبٍ وَتَبَّ " المسد ١١١:١ 
“የአቡ ለሀብ ሁለት እጆቹ ከሰሩ፡፡ (ጠፉ፤ እርሱ) ከሰረም፡፡” (አል መሰድ፡1) 
ለዚህ ብዥታ ከብዙ አቅጣጫ መልስ መስጠት ይቻላል፡፡ 
1. የኡርዋ ሐዲስ “ሙርሰል” (ሰንሰለት የሌለው) ሐዲስ ነው፡፡
2. የኡርዋ ሐዲስ “መውሱል” (ሰንሰለት ያለው ሐዲስ) እንኳ ቢሆን የህልም እይታ በመሆኑ ለመረጃነት አያገለግልም፡፡ 3. የኡርዋ (ሙርሰል) ሐዲስ አቡለሀብ ሱወይባን ነጻ ያደረጋት ነብዩን ﷺ ከማጥባቷ በፊት መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ኢብን ሐጀር - ረሂመሁሏህ - ፈትህ በሚባለው ኪታባቸው ላይ ግልጽ እንዳደረጉት ከታሪክ ባለቤቶች ዘንድ ከተወሳው ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቡለሀብ ሱወይባን ነጻ ያደረጋት ረሡልን ﷺ ካጠባች ከብዙ ዘመን በኋላ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ (ፈትሁ አል ባሪ፡ 4/250)
4. የኡርዋ ሙርሰል ሐዲስ ከቁርኣን ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ነው፡፡ ሀፊዝ ብን ሐጀር - ረሂመሁሏህ - ፈትሁ አል’ባሪ በሚባለው ኪታባቸው እንዳብራሩት የኡርዋ ሙርሰል ሐዲስ ካፊር መልካም ስራው ለአኼራ እንደሚጠቅመው የሚጠቁም ሲሆን አላህ - ሱብሃነሁ ወተዓላ - በቁርኣኑ ደግሞ ከሐዲዎች በዱንያ ላይ የሰሩት መልካም ስራ እንደትቢያ ተበትኖ የሚቀርና የማይጠቅማቸው መሆኑን ይገልጻል፡፡
 ﴿ َوقَد ْمنَا إَل ما ِ َُعلوإ من ََعل فَجعلْنَا ُه ه َباء منوُو ًرإ﴾ 
“ከስራም ወደሰሩት እናስባለን፡፡ የተበተነ ትቢያም እናደርገዋለን፡፡” (አል ፉርቃን፡23) (ፈትሁ አል ባሪ፡ 9/167)

 ብዥታ 5

 “መውሊድ የነብዩን ﷺ ታሪክ ለመማርና ለማወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡” ይላሉ፡፡ 

 መልስ 5

 ነብዩን ﷺ ባህሪያቸውን ፣ ተኣምራቶቻቸውን እና ታሪካቸውን ለማወቅ የፈለገ ሰው በማንኛውም ጊዜ የተመቻቸ ነው፡፡ የረሡልን ﷺ ታሪክ ለማወቅ በተለየ ወቅት ፤ በተለየ አኳኋን ፤ መሰረተ ቢስ በሆነ ስብስብ የሚገደብ አይደለም፡፡

 ብዥታ 6

 “በይሐቅይ የዘገቡት አነስ 4 ያስተላለፉት የሚከተለው ሐዲስ መውሊድ ለማውጣት ማስረጃችን ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 
(أن النبي صلى هللا عليه وسلم عق عن نفسه بعد النبوة مع أن جده عبد المطلب )والدته سابع في عنه عق 
የነብዩ አያት (ዓብደል ሙጦሊብ) ረሡል ﷺ በተወለዱ በሰባት አመታቸው አቂቃ አውጥቶላቸው ሲያበቃ ነብይ ከሆኑ በኋላ ደግሞ በራሳቸው አቂቃ አውጥተዋል፡፡” (አስ ሱነን አል ኩብራ፡9/300)
 ((ነብዩ ﷺ በተደጋጋሚ ይህን ተግባር የፈጸሙት አላህ እርሳቸውን ለዓለማት እዝነት በማስገኘቱ የአላህን ምስጋና ይፋ ለማድረግና ከእርሳቸው በኋላ ለሚመጣው ትውልድ ሱና ሆኖ እንዲቀጥል በማሰብ ነው፡፡)) ይላሉ፡፡

 መልስ 6

 ኢማም ማሊክ - ረሂመሁሏህ - ይህን ሐዲስ ውድቅ አድርገውታል፡፡ ዓብደላህ ብን ሂዋር በተባለው ዘጋቢ አማካኝነት አቡዳውድ ፣ አህመድ፣ ኢብን ሂባን ፣ በዛር፣ ኢብን ሐጀር፣ ኢብን አልቀይም ፣ ዘህብይና ሌሎችም የዲን መሪዎች ይህን ሐዲስ ደካማ ነው ብለውታል፡፡ (ፈትሁ አል ባሪ፡9/595 መጅሙዕ አል ፈታዋ፡8/431-432) ሐዲሱ ትክክል እንኳ ቢሆን ከመውሊድ ጋር የሚያገናኘው አንድም ነገር የለም፡፡ መረጃ እናድርግ እንኳ ቢሉ አንድ ሰው ለአቅመ አደም ከደረሰ በኋላ አቂቃውን ማውጣት እንደሚችል ማስረጃ ሊሆናቸው ይችል ነበር፡፡ 

ብዥታ 7

“መውሊድን በርካታው ሙስሊም መልካም ብሎታል ፤ እርሱን መቃወም አብዛኛው ሰው መልካም ያለውን እንደመቃወም ይቆጠራል፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 7

 ታላቁ ሶሃባ ዓብዱሏህ ብን ዑመር 4 የሚከተለውን ተናግረዋል፡- 
 : "وإنما الجماعة ما وافق ، وفي رواية (كل بدعة ضاللة وإن رآها الناس حسنة) طاعة هللا وإن كنت وحدك"
 (ሰዎች መልካም ነው ብለው ቢመለከቱት እንኳ ፤ ማንኛውም ፈጠራ ጥመት ነው፡፡) (አል ላለካኢይ፡1/92 ኢብኑ በጣህ፡205 አል በይሓቂዩ ፊ አል መድኸል፡191) 
በሌላ ዘገባ፡ (ብቻህን እንኳ ብትሆን ጀማዓ ማለት ከአላህ ትዕዛዝ ጋር የተስማማ ነው፡፡) (አል ላለካኢይ፡1/160)      
وقال ابن مسعود رضي هللا عنه : "الجماعة ما وافق الحق وإن كنت وحدك" 
ኢብን መስዑድ 4 የሚከተለውን ተናግረዋል፡-  “ጀማዓ የሚባለው ብቻህን እንኳ ብትሆን ከሐቅ ጋር የተስማማ ነው፡፡” አል ሃዋዲሱ ወልቢደዕ፡ ገፅ መሸካቱ አል መሳቢህ፡

 يقول صلى هللا عليه وسلم : "إن اإلسالم بدأ غريبا وسيعود غريبا كما بدأ فطوبى : "هم الذين : من هم يا رسول هللا ؟ قال صلى هللا عليه وسلم قيل للغرباء" يصلحون إذا فسد الناس" 
ረሡል ﷺ የሚከተለውን ሐዲስ ተናግረዋል፡- “ኢስላም እንግዳ ሆኖ ጀመረ ፤ እንዳጀማመሩ እንደገና እንግዳ ሆኖ ይመለሳል ፤ ብቸኛ ለሆኑት አማረላቸው፡፡” (ሙስሊም፡145) በማለት ረሡል ﷺ ተናገሩ፡፡ “የአላህ መልክተኛ ሆይ! እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡ “ሰዎች ሲበላሹ የሚያስተካክሉ ናቸው፡፡” በማለት ምላሽ ሰጡ፡፡ (ኢብኑ ማጀህ፡3986 ሐዲሱን አልባኒ ሶሂህ ብለውታል አስ ሲልሲለቱ አስ ሶሂህ፡3/1273) 
ሐቅ በተከታዮች ብዛት እንደማይለካ አላህ በሚከተሉት የቁርኣን አንቀጾች ነግሮናል፡-
 ﴿ َوإن تُط ْع أك ََث من ِف إأل ْرض يُضلُّوك عن س ِبيل إ ِّلل﴾
 “በምድርም ካሉት ሰዎች አብዛኞቹን ብትከተል ከአላህ መንገድ ያሳስቱሃ፡፡” (አል አንዓም፡116)
 ﴿ َو َما أك َُث إلنَّاس ولَ ْو ح َر ْصت ب ُمؤ ِم ِني﴾ 
አብዛኞችም ሰዎች (ለማመናቸው) ብትጓጓም የሚያምኑ አይደሉም፡፡” (ዩሱፍ፡103)   
" وَقَلِيلٌ مِّنْ عِبَادِىَ ٱلشَّكُورُ (١٣)" سبإ ٣٤:١٣

“ከባሮቼ በጣም አመስጋኞቹም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡” (አስ ሰበእ ፡ 13)

ብዥታ 8 

 “የመውሊድ በዓል በበርካታ አገሮች የሚፈጸም የአብዛኛው ሙስሊም ማህበረሰብ ተግባር ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 8

 ማስረጃ ማለት ከቁርኣን እና ከነብዩ ﷺ በትክክለኛ ሐዲስ ወይም ሱና የጸደቀው ነው፡፡ በቁርኣንና በትክክለኛ ሐዲስ ከነብዩ ﷺ የጸደቀው ደግሞ በዲን ላይ የሚፈጠሩ ፈጠራዎች በጥቅሉ ክልክልና ወደጥመት ጎዳና የሚመሩ መሆናቸው ነው፡፡ መውሊድ ደግሞ ከቢድዓዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የሰዎች ተግባር ከመረጃ ጋር ከተቃረነ የሰዎቹ ቁጥር በርካታ እንኳ ቢሆን ማስረጃ ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡-
 "وَإِن تُطِعْ أَكْثَرَ مَن فِى ٱلْأَرْضِ يُضِلُّوكَ عَن سَبِيلِ ٱللَّهِ " الأنعام ٦:١١٦ 
“በምድርም ካሉት ሰዎች አብዛኞቹን ብትከተል ከአላህ መንገድ ያሳስቱሃ፡፡” (አል አንዓም፡116)
 ሸይኽ ሙሐመድ ብን ሷሊህ አልዑሰይሚን - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡-
“ሰዎች ረሡልን ﷺ እንዎዳለን ወይም እናስታውሳለን በሚል ሙውሊድን ያከብሩታል፡፡ እኛ ደግሞ እንላቸዋለን ፡ - ረሡልን ﷺ ከወደዳችሁ መልካም ነው ፤ ረሡልን ﷺ ለማስታወስም ከሆነ መልካም ነው ፤ ነገር ግን የዳኞች ዳኛ የሆነው አላህ - ሱብሃነሁ ወተዓላ - ያስቀመጠው ሚዛን አለ፡፡ እርሱም ፡-
"قُلْ إِن كُنتُمْ تُحِبُّونَ ٱللَّهَ فَٱتَّبِعُونِى يُحْبِبْكُمُ ٱللَّهُ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ذُنُوبَكُمْ وَٱللَّهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ " آل عمران ٣:٣١ 
 “በላቸው፡- “አላህን የምትወዱ እንደሆናችሁ ተከተሉኝ ፤ አላህ ይወዳችኋልና ፤ ሃጢአቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና ፤ አላህም መሃሪ አዛኝ ነው፡፡” (አል ኢምራን፡31) 
አንድ ሰው አላህን እና ረሡልን ﷺ እወዳለሁ ማለቱ ትክክል ከሆነ ለአላህ ሸሪዓ እንዲሁም ረሡል ﷺ የመጡበትን ተከታይ ይሁን ፤ እርሳቸውን ተከታይ ካልሆነ ረሡልን ﷺ እወዳለሁ የሚለው ሙግት ውሸት ይሆናል ማለት ነው፡፡ እስኪ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናቅርብ፡፡ ረሡል ﷺ የተወለዱበት ቀን ነው በማለት ሌሊትን ክብረ በዓል አድርጎ ማክበር ከአላህ ሸሪዓ የሚቆጠር ነውን? ነብዩ ﷺ ፈጽመውታልን? እነዚያ ቅን የነበሩት የረሡል ﷺ ምክትሎች እንዲሁም ሶሃቦችና ተከታዮቻቸው - አላህ ስራቸውን ይውደድላቸው - ሰርተውታልን? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ አልሰሩትም የሚል ነው፡፡ በዚህ ተቃራኒ አለኝ የሚል ካለ መልሱን ባፋጣኝ ሊያቀርብ ይገባል፡፡ አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡-
" قُلْ هَاتُوا۟ بُرْهَٰنَكُمْ إِن كُنتُمْ صَٰدِقِينَ " البقرة ٢:١١١
“እውነተኞች እንደሆናችሁ ማስረጃችሁን አምጡ” በላቸው፡፡ (አል በቀራህ፡111) 

ብዥታ 9 

 በመውሊድ ባለቤቶች ላይ ተቃውሞ የምታቀርብ ከሆነ “አላህ ከፈጠረን ጊዜ ጀምሮ አላህን የምንገዛበት ፤ አባቶቻችን አያቶቻችን ሸኾቻችን የነበሩበትን ሱና (ጎዳና) እንዴት ትቃዎማለህ? የእነርሱን ሱና ትቀይራለህ እንዴ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ 

 መልስ 9

 ሱብሃን አላህ! የትኛውን የአባቶችና የአያቶች ሱና ነው የቀየርነው? የእነርሱ ስራ ማስረጃ ይሆናል እንዴ? ወይስ አላህ ያወገዘው የሆነውን የሙሽሪኮች አባባል ነው የምትናገሩት? አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡-
 " حَسْبُنَا مَا وَجَدْنَا عَلَيْهِ ءَابَآءَنَآ " المائدة ٥:١٠٤

“አባቶቻችንን በእርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር ይበቃናል፡፡” (አል ማኢዳ፡104)   
"بَلْ قَالُوٓا۟ إِنَّا وَجَدْنَآ ءَابَآءَنَا عَلَىٰٓ أُمَّةٍ وَإِنَّا عَلَىٰٓ ءَاثَٰرِهِم مُّهْتَدُونَ" الزخرف ٤٣:٢٢
 “ከቶውንም እኛ አባቶቻችንን ከሃይማኖት ላይ አገኘናቸው፡፡ እኛም ከፈለጎቻቸው ላይ ተመሪዎች ነን አሉ፡፡” አዝ ዙኽሩፍ፡22

 ብዥታ 10

“ሸሪዓዊ ያልሆነ ተግባር ከሰዎች ዘንድ በብዛት ከተሰራ ወደሸሪዓዊ ተግባር ይቀየራል” ፤ “አንተ እያከረርከው ነው እንጅ ይህ ጉዳይ የቆየ በጣም ቀላልና ገር የሆነ በሰዎች መካከል የተሰራጨ ፤ በዚህ ላይ አባቶቻችንን ያገኘንበት ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 10

 አብዛኛው ሰው ስህተት ላይ መውደቁ ተግባሩ ወደትክክል ይቀየራል ማለት ይህ በዲን ላይ ሸፍጥ ነው፡፡ ፉዶይል ብን ዒያድ - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡-
 "اتبع طرق الهدى وال يضرك قلة الشاكرين ، وإياك وطرق الضاللة ، وال تغتر بكثرة الهالكين" 
“ትክክለኛውን መንገድ ተከተል ፤ የአመስጋኞች ቁጥር ቢያንስም አይጎዳህም ፤ የጥመትን መንገድ ተጠንቀቅ የጠፊዎች ቁጥር መብዛት አይሸውድህ፡፡” (አል ኢዕቲሷም ሊሻጢቢይ፡1/183)

 ብዥታ 11

 ከጭቃው ላይ የበለጠ ርጥበትን የሚጨምር አስቀያሚ ንግግር ደግሞ የሚከተለው ነው፡- 
(خطأ مشهور خير من صواب مهجور) 
(የታወቀ ስህተት ከተተወ ሐቅ ይሻላል፡፡) 

መልስ 11 

ይህ ንግግር ትክክል የሆነውን ንግግር እንድንተው የሚቀሰቅስ አደገኛ ንግግር ነው፡፡ በዲን ጉዳይ በርካታ ስህተቶች ተከስተዋል ፤ እነዚህ ስህተቶች ደግሞ ከሰው ዘንድ ተስፋፍተዋል ፤ ታዲያ ከሰዎች ዘንድ ሐቁ ስለተተወ ብቻ ስህተቱን ይከተላሉ እንዴ? ይህን ከሰሩ ግልጽ የሆነ ጥመት ጠመሙ ማለት ነው፡፡ 

 ብዥታ 12

 የመውሊድ ባለቤቶች ከሚያቀርቡት ብዥታ መካከል አንዱ “ማንኛውም ልዩነት ቢከሰት ከስህተቱ ነጻ ለማውጣት ምክንያት መስጠት፡፡” የሚል ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚያደርጉት የሚከተለውን አባባል ነው፡፡ (اختالف أمتي رحمة) (የህዝቦቸ ልዩነት እዝነት ነው፡፡) ሚዛኑ አል ኢዕቲዳል ሊዘሐቢይ፡ ሐዲሱን አልባኒ ዶዒፍ ብለውታል አስ ሲልሲለቱ አድ ሮዒፍ፡ ከእነርሱ ዘንድ መረጃን መሰረት አድርጎ የሚቃወምን ሰው እንደአክራሪ መመልከት የተለመደ ባህሪያቸው ነው፡፡ አንድ ሙፍቲ በአንድ ጉዳይ ፈትዋ ከሰጠ “ልዩነት እዝነት ሆኖ እያለ ለምን ልዩነት ባለባቸው የዲን ጉዳዮች ፈትዋ ይሰጣል?” በማለት ተቃውሟቸውን ይገልጻሉ፡፡ “በዑለሞች መካከል ልዩነት መስፋቱ እዝነት ነው፡፡” የሚሉም ሌሎች ጽንፎችም አልጠፉም፡፡ “በዲኑ ውስጥ ችግር የለም ፤ ዲኑ ሰፊ ሆኖ እያለ ሰዎችን ችግር ላይ ለመጣል አትፈልጉ፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 12 

 ከላይ የተጠቀሰው አባባል ሁሉ ስህተትና ሸሪዓው የመጣበትን አላማ አለመገንዘብ ነው፡፡ በዑለሞች መካከል ልዩነት ከተከሰተ መረጃው አመዛኝ የሆነውን መርጦ መያዝ እንጅ ያለምንም ጥናትና ማረጋገጫ ከሁለቱ ንግግሮች የፈለገውን መያዝ ይችላል የሚለው አባባልም ትክክል አይደለም፡፡
 ሸይኽ ሙሐመድ ብን ሷሊህ አልዑሰይሚን - ረሂመሁሏህ - “ኪታቡል ዒልም” በሚባለው ኪታባቸው የሚከተለውን ተናግረዋል፡- “በዑለሞች መካከል የተከሰተ ልዩነት እንጅ ፤ ገና ጀማሪ በሆኑ ተማሪዎች ወይም ጥልቅ ግንዛቤው በሌላቸው ሰዎች መካከል የተከሰተ ልዩነት ፍጹም ቦታ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፡፡” (ኪታቡ አል ዒልም፡187) ረህመት (እዝነት) ማለት መስማማት እንጅ መለያየት ረህመት (እዝነት) ሆኖ አያውቅም፡፡ በመሆኑም “የህዝቦቸ መለያየት ረህመት ነው” የሚለው አባባል መሰረተ ቢስ አባባል ነው፡፡

ብዥታ 13

 የመውሊድ ባለቤቶች የሚከተለውን ጥቅስ እንደማስረጃ ያቀርባሉ፡-  
(صيب مجتهد كل)
“ማንኛውም (የኢስላምን ህግጋት ለመረዳት) ጥረት የሚያደርግ ሁሉ ሐቀኛ ነው፡፡” በዚህ ህግና መርሆ ላይ ተንተርሰው “ማንኛውም በዲኑ ዙሪያ ጥረት የሚያደርግ አካል የፈጠረውን ልዩነት ሁሉ መያዝ ችግር የለውም፡፡” ይላሉ፡፡

መልስ 13

 እነርሱ እንደሚሉት ሳይሆን ማንኛውም በዲኑ ላይ ጥረት የሚያደርግ ሁሉ የራሱ የሆነ ድርሻ ሊኖረው ይችላል ፤ ነገር ግን ሁሉም ጥረት አድራጊ ትክክለኛውን ያገኛል ማለት አይደለም፤ ትክክለኛው አንድ ብቻ እንጅ ብዙ ቁጥር ሊኖረው አይችልም፡፡

 ብዥታ 14

 “መውሊድ ቢድዓ ፣ የጃሂልያ ተግባርና ስህተት ከሆነ ከበርካታ ዘመናት ጀምሮ ሙስሊሞች ለምን ሊሰሩት ቻሉ?” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ 

መልስ 14 

ለበርካታ አመታት ሙስሊሞች መውሊድን ማክበራቸው ልክ እንደ ሸሪዓዊ ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ መውሊድ ሸሪዓዊ መሰረት ኖሮት ሳይሆን ትውልድ ከትውልድ ሲረከበው የኖረ የጃሂልያ እምነት ነው፡፡ አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡-
  " حَسْبُنَا مَا وَجَدْنَا عَلَيْهِ ءَابَآءَنَآ " المائدة ٥:١٠٤ 
“አባቶቻችንን በእርሱ ላይ ያገኘንበት ነገር ይበቃናል፡፡” (አል ማኢዳ፡104)

 ብዥታ 15

 ስለመውሊድ ታሪክ የጻፈ አንድ ግለሰብ የሚከተለውን ተናግሯል፡- ((የነብዩ ﷺ ምክትሎች አቡበክር ፣ ዑመር፣ ዑስማን እና ዓልይ - ረዲዬሏሁ ዓንሁም - የዲን መሰረቶችን ለማስፋፋት አገሮችን ለመክፈት በመጠመዳቸው መውሊድን ለማክበር ጊዜ አላገኙም …)) 

መልስ 15

 በኹለፋኡ ራሽዲኖች ላይ የተናገረው ንግግር ከመሰረቱ ውድቅ የሆነ ንግግር ነው፡፡ ሸይኹል ኢስላም ብን ተይሚያ - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡- “ይህን የቢድዓ ተግባር ሸሪዓውንና ሱናውን ያቃለሉ ሐራሙን ሐላል ፤ ሐላሉን ሐራም ፣ ቢድዓውን ሱና ፤ ከሐዲዎችን ወዳጅ ያደረጉ የዑበይድያዎች ግዛት እስኪመሰረት ድረስ ከተከበረው ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩ ሙስሊሞችም ይሁን ከእነርሱ በኋላ የመጡት በፍጹም አልሰሩትም ….” 

ብዥታ 16

 “የመውሊድ በዓል መልካም ሱና ነው ፡፡ ለዚህ ማስረጃችን ደግሞ የሚከተለው የነብዩ ﷺ ሐዲስ ነው፡፡” በማለት የመውሊድ ባለቤቶች ይሞግታሉ፡፡ “በኢስላም ውስጥ መልካም ሱናን (ህያው) ያደረገ ፤ ለእርሱ ምንዳዋ አለው ፤ ከእርሱ በኋላ የፈጸሟትም ሰዎች ከምንዳቸው አንድም ሳይቀነስ ምንዳዋ አለው…” (ሙስሊም፡1017)

መልስ 16

 መልካም ሱና የሚባለው ሸሪዓዊ መሰረት ሲኖረው ነው፡፡ ይህ ሐዲስ የተነገረበትን ምክንያት ብናስተውል እንኳ ሸሪዓዊ መሰረት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እርሱም ሶደቃን አስመልክቶ ነው፡፡ የመውሊድ በዓል ግን ምርጡ ክፍለ ዘመን ካለፈ በኋላ ሙብተዲዖች የፈጠሩት በመሆኑ በሸሪዓ ምንም አይነት መሰረት የለውም፡፡ 

ብዥታ 17

 “የመውሊድን በዓል የምናከብረው ረሡልን ﷺ ለማላቅና ለማክበር ነው፡፡” ይላሉ፡፡

መልስ 17

 ረሡልን ﷺ የምናልቃቸው እርሳቸውን በመታዘዝ ፤ እርሳቸው የፈጸሙትን በመፈጸም ፤ የከለከሉትን በመራቅ እንጅ በቢድዓ ተግባር አይደለም፡፡ ውዴታቸው መሰረተ ቢስ በሆኑ የቢድዓ ተግባራትና በወንጀል አይገለጽም፡፡ ረሡልን ﷺክብር በመስጠት ቁጥር አንድ የሚታወቁት ሶሃቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ፍቅራቸውንና ክብራቸውን ቢድዓ በሆነው የመውሊድ በዓል አልገለጹም፡፡ የመውሊድ በዓል ሸሪዓዊ ቢሆን ኖሮ ሶሃቦቹ ፍጹም አይተውትም ነበር፡፡ 

ብዥታ 18

 “መውሊድ ማክበር ረሡልን ﷺ ለመውደድ ትልቁ ምልክትና መገለጫ ነው ፤ ፍቅራቸውን ይፋ ማድረግ ደግሞ ሸሪዓዊ ነው ፤ መውሊድ ያላከበረ ረሱልን የሚጠላ ሰው ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 18

 ሱብሃን አላህ! ሱብሃን አላህ! አንተ የመውሊድ ባለቤት ረሡልን ﷺ ከአቡበክር፣ ከዑመር፣ ከዑስማን፣ ከዓልይ፣ ከዓኢሻ እና ከሌሎችም የረሡል ሚስቶች - ረዲዬሏሁ ዓንሁም ጀሚዓን - እውነት አብልጠህ ትወዳለህ? መውሊድን በየአመቱ የሚያከብር ከሶሃቦች በጣም የተመራ ፤ የረሡል ﷺ በጣም ወዳጅ ነው ብለህ ታስባለህ? ምንም ጥርጥር የለውም መልሱ አይደለም የሚል ነው፡፡ የመውሊድን በዓል ሌሊት ተነስቶ ማክበር ረሡልን ﷺ ለመውደድ ምልክት ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ መውሊድን የሚያከብሩ ነገር ግን ከረሡል ﷺ መንገድ የወጡ ስንት ሰዎች አሉ? መውሊድ የሚያከብሩ ነገር ግን በአራጣ የሚተዳደሩ ፣ ሶላትን የማይሰግዱ ፣ የነብዩን ﷺ ሱና ያጠፉ ስንት ፋሲቆች ወይም አመጾኞች አሉ፡፡

ብዥታ 19

 “ከሐዲዎች ለአለቆቻቸው ፣ ለመሪዎቻቸው እና ታላላቅ ለሚባሉ ሰዎች የልደት በአል የሚያከብሩ ከሆነ ከሁሉም አካል ለተላቁት ረሡላችን ﷺየተወለዱበትን ቀን ማክበር ደግሞ በጣም በላጭ ይሆናል፡፡” የሚል ብዥታ ያቀርባሉ፡፡ ከመውሊድ አክባሪዎች መካከል አንዱ የሚከተለውን ብዥታ አሰራጭቷል፡-
 (إذا كان أهل الصليب اتخذوا ليلة مولد نبيهم عيدا أكبر ، فأهل اإلسالم أولى )وأجدر بالتكريم 
((የመስቀል ባለቤቶች ነብያቸው የተወለዱበትን ሌሊት ታላቅ ክብረ በዓል አድርገው ከያዙ ፤ የኢስላም ባለቤቶች (የነብያቸውን ልደት በዓል) በማክበር ቀዳሚዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡)) 

መልስ 19

 ይህን አዕምሯዊ ብዥታ የፈጠሩት የቢድዓ ተጣሪና ረዳቶች ናቸው ፡፡ መውሊድ የሸሪዓ ተቃራኒ ሆኖ እያለ አእምሯቸው መልካም አስመስሎ አሳያቸው ፤ ከዚያም ልቦቻቸው ተቀበሉት፡፡ 
አንደኛ፡- እኛ ካፊሮችን እና ሙሽሪኮችን በኢባዳም ይሁን በበዓል በመቃረን ታዘናል፡፡ እንደውም ሸይኹል ኢስላም ብን ተይሚያህ - ረሂመሁሏህ - “ኢቅቲዷኡ ሲራጦል ሙስተቂም” በተባለው ኪታባቸው በአላት ከዚህ ቀደም የነበሩ እምነቶች መገለጫ እንደሆነ ፤ ውጫዊ መመሳሰል የውስጥ መመሳሰልን እንደሚያመጣ ፤ ሸሪዓውም ይሁን አዕምሮ እንዲሁም ተጨባጩ የሚያስረዳው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 
ሁለተኛ፡ - ከዚህ ማህበረሰብ የአህለል ኪታቦችን መንገድ በተግባርም ይሁን በንግግር የሚከተል እንደሚመጣ ነብዩ ﷺ ተናግረዋል፡፡ 

عن أبي سعيد رضي الله عنه، أنَّ النبي صلى الله عليه وسلم قال: ((لَتَتَّبِعُنَّ سَنَنَ مَنْ قَبْلَكُم شِبْرًا بشبْر، وذراعًا بذراع، حتَّى لو سَلَكُوا جُحْر ضَبٍّ لَسَلَكْتُمُوهُ))؛ قلنا: يا رسول الله؛ اليهودُ والنَّصارى[1]؟ قال النَّبيُّ صلى الله عليه وسلم: ((فَمَن؟!))؛ متفق عليه.


ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሐዲስ አቡሰኢድ አልኹድርይ 4 የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡-
 “ክንድ በክንድ ስንዝር በስንዝር ከዚህ በፊት የነበሩ ሰዎችን መንገድ በእርግጥ ትከተላላችሁ፡፡ የአርጃኖ ጉድጓድ ቢገቡ እንኳ በእርግጥ ትገባላችሁ፡፡” የአላህ መልክተኛ ሆይ! አይሁድና ነሷራ ናቸውን?” በማለት ጠየቅናቸው፡፡ “እንግዲያ እነማን ናቸው?” በማለት መልስ ሰጡን፡፡ (ቡኻሪ፡3456 ሙስሊም፡2669) መውሊድ አክባሪዎች ይህን ሐዲስ ዘነጉት እንዴ? 

ብዥታ 20

 “መውሊድን በመሰሉ ክብረ በዓላት ታላላቆቻችንን ማክበርና ማላቅ የተለመደ ባህላችን ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 20

 አዎ ሰይጣን መልካም ባህላችሁ እያለ የተለያዩ ጣዖታት አምላኪዎች በማድረግ ከሽርክ አረንቋ ውስጥ እንድትገቡ አደረጋችሁ፡፡ ነብዩ ﷺ ልክ እንደናንተ አለቆች ዓይነት አይደሉም፡፡ የአላህን ዲን በልማዳችሁ በባህላችሁ ልትወስኑ ትፈልጋላችሁን? እንደውም ረሡል ﷺ ከሁሉ በላይ ታላቅ ፤ የነብያቶች ሁሉ መደምደሚያ የዲን መሪ ናቸው፡፡ እርሳቸውን በመታዘዝ በእርሳቸው ላይ ሶላትና ሰላምታ በማውረድ አልቋቸዋል፡፡ ወደቀኝም ወደግራም ሳትሉ አላህ ባዘዘው ላይ ቀጥ በሉ፡፡

 ብዥታ 21

 የመውሊድ ባለቤቶች ከሚያቀርቡት ብዥታ መካከል ኢብን መስዑድ 4 ተናግረውታል ተብሎ የሚወራው የሚከተለው ንግግር ነው፡፡ (ما رآه المسلمون حسنا فهو عند هللا حسن) (ሙስሊሞች መልካም ነው ብለው የተመለከቱት ፤ ከአላህም ዘንድ መልካም ነው፡፡) (መቃሲድ፡959    አልቢዳያ ወኒሃያ፡10/327 ሐዲሱን አልባኒ ዶዒፍ ብለውታል አስ ሲልሲለቱ አድ ዶዒፋ፡2/17)

 መልስ 21

ይህ አነጋገር የሸሪዓ ማስረጃ ሊሆን ዘንድ ከመሰረቱ የነብዩ ﷺ ሐዲስ አይደለም፡፡ ከኢብን መስኡድ 4 ንግግሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢብን መስዑድ ይህን የተናገሩት አቡበክር 4 የረሡል ﷺ ምክትል ሆነው በተመረጡበት ወቅት ነው፡፡ እንደ ሐዲስ ብንወስደው እንኳ የንግግሩ ጽንሰ ሐሳብ ከፊሉ መልካም ፤ ከፊሉ ደግሞ እንደመጥፎ የተመለከተው ማለት ሳይሆን ሙስሊሞች የተስማሙበትና መልካም ነው ብለው የተመለከቱት ማለት ነው፡፡ መውሊድን መልካም በማለት ሁሉም ሙስሊም ተስማምቷል እንዴ? በመውሊድ ላይ ሁሉም ሙስሊም በአንድ ድምጽ ተስማምቷል የምትሉ ከሆነ በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ የትኛው የማህበረሰብ ክፍል ነው መውሊድ ይበቃል ብሎ በአንድ ድምጽ የተስማማው? ምናልባት የሱፍያ ፣ የራፊዷ ፣ የአህባሽ እና እነርሱን በቢድዓ ተግባር የተከተለ ማህበረሰብ ካልሆነ በቀር? ተራው ማህበረሰብ ወዶት ተቀብሎትም ከሆነ አላህ እንደነገረን ነው፡፡ አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡-
"وَإِن تُطِعْ أَكْثَرَ مَن فِى ٱلْأَرْضِ يُضِلُّوكَ عَن سَبِيلِ ٱللَّهِ إِن يَتَّبِعُونَ إِلَّا ٱلظَّنَّ وَإِنْ هُمْ إِلَّا يَخْرُصُونَ " الأنعام ٦:١١٦
“በምድርም ካሉት ሰዎች አብዛኞቹን ብትከተል ከአላህ መንገድ ያሳስቱሃ፡፡” (አል አንዓም፡116)  

ብዥታ 22

 “የመውሊድ ባለቤቶች መውሊድን እየፈጸሙ የሚገኙት በመልካም ሐሳብና አላማ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 22

 መልካም ሐሳብ ወይም አላማ በዲን ውስጥ የሚፈጠሩ ፈጠራዎችን የተፈቀዱ አያደርግም፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ማህበረሰቦች በዲናቸው ውስጥ ታላላቅ ፈጠራዎችን የፈጠሩ ሩሡሎች ከተላኩበት ጋር ሙሉ በሙሉ እስከሚጋጭ ድረስ የጨመሩ የቀነሱ ከመልካም ሐሳብ ተነስተው መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ መልካም ሐሳብ ሀራምን ሀላል ፤ ሀላሉን ሀራም አያደርግም፡፡ የዲን ጉዳይን አስመልክቶ መመለሻችን የአላህ ኪታብና የረሡል ﷺ ሱና ብቻ ነው፡፡ ሙስሊሞች መጨረሻው የማያምር መንሸራተት ላይ እንዳይወድቁ ይህን መርሆና ደንብ መጠበቅ አለባቸው ፡፡ ሙስሊሞች አንድን ተግባር ከመፈጸማቸው በፊት ወደአላህ የሚያቃርብ ተግባር መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡- 
 لَا تُقَدِّمُوا۟ بَيْنَ يَدَىِ ٱللَّهِ وَرَسُولِهِۦ " الحجرات ٤٩:١
 “በአላህና በመልክተኛው ፊት (ነፍሶቻችሁን) አታስቀድሙ፡፡” (አል ሑጁራት፡1)

 ብዥታ 23

 “ከመልካም አላማ ተነስቶ መውሊድን የጀመረው ፍትሃዊና አሊም የሆነ ንጉስ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 23

 በዲን ውስጥ ቢድዓን የፈጠረ ማንም የሁን ማን የተወገዘ ነው፡፡ ከአላህ ዘንድ ምንም አይነት ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዴውም ስራው ወደ ሰውየው ተመላሽ እንደሚሆንበት ነብዩ ﷺ በሐዲሳቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪ መውሊድን የፈጠረው ንጉስ ነው መባሉ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ የመውሊድን በዓል ወይም ቢድዓ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰራጩት የኢስላም ጠላት የሆኑት ፋጢሚዮች ነን ባዮች ናቸው፡፡ እነርሱ እንደሚሉት መውሊድን የጀመረው ንጉስ ቢሆን እንኳ የንጉሶች ተግባር ከመቼ ወዲህ ነው የዲን መረጃ ሆኖ የሚቀርበው? መልካም አላማ መጥፎ ስራን ተቀባይ እንዲሆን አያደርግም፡፡ ዓሊም ፍትሃዊ መሆኑ ከስህተት ጥብቅ መሆኑን አያስረዳም፡፡ 

ብዥታ 24

 “መውሊድን የምናከብረው መልካምን አስበን ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 24

 ኢብን መስዑድ 4 የተናገሩትን ንግግር እኛም እንናገረዋለን፡፡ (كم من مريد للخير لم يصبه) (ስንት ሐቁን ያላገኘ መልካም አሳቢ አለ፡፡) (አድ ዳሪሚይ፡210) 

ብዥታ 25

 የመውሊድ ባለቤቶች የመውሊድን ቢድዓነት እያረጋገጡ መልካም ቢድዓ በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህን ይበሉ እንጅ በእነርሱ እይታ መልካም ተግባር ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነርሱ ከያዙት እምነት የመነጨ ሲሆን መልካም ቢድዓና መጥፎ ቢድዓ በማለት ቢድዓን በሁለት ይከፍሉታል፡፡ 

 መልስ 25

 ቢድዓን መልካምና መጥፎ በማለት መከፋፈሉ ሙስሊሞችን ለልዩነት የሚዳርግ እንጅ አንድም ጥሩ ውጤት የሚያመጣ አይደለም፡፡ ቢድዓን መተው ከዲኑ የሚያጎድለው አንድም ነገር የለም ፤ የሱና ተከታይ ያደርጋል እንጅ ከነብዩ ﷺሱና አፈንጋጭ አያደርግም፡፡ 

ብዥታ 26

 “እኛ መውሊድን የምናከብረው ነብዩ ሙሐመድን ﷺ ለማስታወስ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 26

 በመውሊዳችሁ ትውስታውን ህያው ለማድረግ የምትሞክሩት የረሡል ﷺ ትውስታ ፍጹም የተረሳና የሞተ መሰላችሁ? የረሡል ﷺ ትውስታ ሁሌም በአዛን በየኹጥባው ከፍ የተደረገ መሆኑን አልሰማችሁም? የረሡልን ﷺ ትውስታ መሰረተ ቢስ በሆነው መውሊድ ከፍ ለማድረግ ሙከራ ማድረግ ከንቱና ውድቅ የሆነ አመለካከት ነው፡፡ ሶለዋት እንኳ አብዙ ተብለን የታዘዝነው በጁሙዓ ቀን እንጅ ረቢዑል አወል 12ኛው ቀን ላይ አይደለም፡፡ 

ብዥታ 27

 አንዳንዶች “መውሊድን የምናከብረው የአላህን ዚክር ለማብዛት ነው፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 27

 አላህን መዝከር ከመውሊድ በዓል ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ከሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀን መርጦ በአንድ ቀን ወይም በአንድ ሌሊት ዚክር መዝከር አላህን በብዛት አስታውሱ ከሚለው የአላህ ትዕዛዝ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ አንዳንድ ወደእውቀት ተጠጋን የሚሉ ሰዎች ለመውሊድ ስርዓት እና ደንብ በማስቀመጥ በዓሉ እንዲከበር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ፤ ፈትዋ ሲጠየቁ “የመውሊድ አላማው ሰዎች የነብዩን ﷺ ታሪክ የሚያውቁበት በመሆኑ ችግር የለውም፡፡” የሚል ምላሽ በመስጠት ህዝብን ያታልላሉ፡፡ ሱበሓን አላህ! መውሊድ ተብሎ የሚጠራ ኢባዳ አለን? ወይም የነብዩን ﷺ ታሪክ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ አስታውሱ የሚል ዒባዳ አለን? እንኳን በቁርኣን እና በሐዲስ ሊኖር ይቅርና በአራቱ የፊቅህ መዝሐብ እንኳ በፍጹም የለም፡፡ 

ብዥታ 28

 አንዳንዶች “መውሊድን በማክበር በርካታ ጥቅሞችን እናገኛለን፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 28

 በዚህ አዲስ ፈጠራ ማንኛውም ጠቀሜታ እንኳ ቢኖር ወደርሱ ፊታችንን ልናዞር አይገባም፡፡ ዋናው ቁምነገሩ አላህና ረሡል ﷺ በደነገጉት ህግ ላይ መዘውተር ነው፡፡ አንድን ነገር አላህ ወይም ረሡል ﷺ ሀራም ካደረጉት ከዚያ በኋላ ሙብተዲዖች ጠማሞች በሚሸላልሙት ፈጠራ ፊታችንን ወደርሱ ልናዞር አይገባም፡፡ ዋናው ቁምነገሩ አላህና ረሡል ﷺ በደነገጉት ህግ ላይ መዘውተር ነው፡፡ አንድን ነገር አላህ ወይም ረሡል ﷺ ሀራም ካደረጉት ከዚያ በኋላ ሙብተዲዖች ጠማሞች በሚሸላልሙት ፈጠራ ፊታችንን ወደርሱ ልናዞር አይገባም፡፡ ጥቅም በሚባለው ቁማር እና አስካሪ መጠጦች እንኳ የተወሰነ ጥቅም እንዳላቸው አላህ - ሱብሃነሁ ወተዓላ - ነግሮናል፡፡ ነገር ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ በማመዘኑ ሙሉ በሙሉ ሊከለከል ችሏል፡፡ አንድ ነገር ሀራም ሆኖ በውስጡ ጥቅም እንኳ ቢኖረው ሀራም ከመሆን አይዘልም፡፡
 

ብዥታ 29

“መውሊድ በውስጡ በረከት፣ መልካም ነገር እና እዝነት አለበት፡፡” ይላሉ፡፡ የመውሊድ ባለቤቶች መውሊድ የተገኘ ሰው ከፍተኛ ትርፍ ያተርፋል ፤ አካሉ ይፈወሳል ፤ ችግሩ ከእርሱ ላይ ይወገዳል፡፡ ከመውሊዱ ያልተገኘ ደግሞ በበሽታ ይለከፋል ፤ ቤተሰቦቹ ይሞታሉ ፤ ንብረቱ ይወድማል እና የመሳሰሉ ሽብሮችን ይነዛሉ፡፡ 

መልስ 29

 አንድ ነገር ቢድዓ የሚል ስያሜ ከተሰጠው በተንኮል የተሞላ፣ መከፋፈልን የሚያመጣ እና የሱና ተቃራኒ ከመሆን አይወገድም፡፡ 

ብዥታ 30

 “በመውሊድ በዓል የነብዩ ﷺ የዘር ሐረግና በአጠቃላይ ታሪካቸው ይደመጣል ፤ በዚህ ቀን ምስኪኖች ምግብ ይበላሉ ፤ ረሡል ﷺ በመወለዳቸው ሰዎች ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡” ይላሉ፡፡ 
መልስ 30፡- የነብዩን ﷺ ታሪክ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ መስማት በቂ አይደለም ፡፡ እንዴውም የነብዩን ﷺ ታሪክ እና ባህሪ እያንዳንዱ ሙስሊም ዘወትር ሊከታተለው ፣ ሊያደምጠውና ሊማረው ይገባል፡፡ በመውሊድ በዓል ምስኪኖች ምግብ ይበላሉ ለተባለው በአመት አንድ ጊዜ ምስኪኖችን አብልቶ መበተን ሳይሆን ኢስላም ዘወትር ያዘዘበትና የቀሰቀሰበት አንዱ የዒባዳ ዘርፍ (የተራበን መመገብ) ነው፡፡ ረሡል ﷺ የሚከተለውን ሐዲስ ተናግረዋል፡-
 (أيها الناس أفشوا السالم وأطعموا الطعام).....
 (እናንተ ሰዎች ሆይ! ሰላምታን ግልጽ አድርጉ ምግብ አብሉ….) (አህመድ፡6450 ቲርሚዚይ፡1854 ኢብኑ ማጀህ፡1334)

ብዥታ 31 

አንዳንድ ጃሂሎችን ከዚህ ቢድዓ ወይም መሰረተ ቢስ ተግባር ስትከለክላቸው “ይህ ቢድዓ ነው እንዴ?” ወይም “ቢድዓ ብትሆንም ትንሽ ቢድዓ ናት” በማለት ይሳለቃሉ፡፡ 

መልስ 31

 ቢድዓ ከሆነ ትንሽ እንኳ ብትሆን መራቁ ተገቢ ነው የሚል መልስ እንሰጣቸዋለን፡፡
 ኢማም አል'በርበሃሪይ - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡- (ቢድዓ ትልቅ መሆኑ አይቀርምና ጥቃቅን የሆኑትን ከወዲሁ ተጠንቀቅ፡፡ በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ የተከሰቱ ፈጠራዎችን ስንመለከት በርካታው ሰው እንደ ትንሽ ሲቆጥራቸው የነበሩ ነገር ግን ለትክክለኛው መንገድ ተቃራኒ በመሆን የገቡበት እንኳ መውጫ እስከሚያጡ ድረስ የዲን መርሆ ተደርገው የተያዙ ናቸው …) ጠበቃቱ አል ሓናቢላ፡ ኢብን ሐጀር - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ተናግረዋል፡-
 (إن الذي يحدث البدعة قد يتهاون بها لخفة أمرها في أول األمر وال يشعر بما )المفسدة من عليها يترتب 
(ቢድዓን የሚፈጥሩ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያስከትለውን ችግር ባለማወቅ ነገሯን እንደ ቀላል ቸል ይሏታል ፡፡) (ፈትሁ አል ባሪ፡13/302) 

ብዥታ 32

 “ሶሃቦችና ተከታዮቻቸው ለረሡል ﷺ ዘመን ቅርብ ስለነበሩ መውሊድ ለማክበር ምንም ዓይነት ምክንያት አልነበራቸውም፡፡” ይላሉ፡፡ 

መልስ 32

 በእኛና በረሡል ﷺ ዘመን ያለው ክፍተት ሰፊ በመሆኑ አዳዲስ ፈጠራዎችን መፍጠሩ ችግር የለውም ማለቱ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ በሶስት መቶው ክፍለ ዘመን ውስጥ የነበሩ ምርጥ ትውልዶች መውሊድን ካላከበሩ እኛም መከተል የሚገባን ይህን ምርጥ ትውልድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ 

ብዥታ 33

 “ሙስሊሙ ደካማ ፤ ከሐዲዎች ደግሞ ጠንካራ በሆኑበት ዘመን ለምን ቅርንጫፋዊ በሆነው የመውሊድ ጉዳይ እንከፋፈላለን? ለምን ለጠላት ምቹ እንሆናለን? ለምን እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድ አንሆንም?” ይላሉ፡፡ 

መልስ 33 

ለድክመታችን ለመከፋፈላችን ለመለያየታችን ምክንያት የሆነው ቢድዓና ወንጀል አይደለምን? ሽርክ እና ኩፍር ላይ የወደቁ ሙስሊሞችን ስንመለከት ምን ይሰማናል? ተውሂድ ለሙስሊሞች መሰባሰብ ፣ አላህን ለመታዘዝ ፣ የሙስሊሞችን ቃል አንድ ለማድረግ መሰረት ነው፡፡ አላህ በተከበረው ቁርኣን የሚከተለውን ተናግሯል፡-
"وَٱعْتَصِمُوا۟ بِحَبْلِ ٱللَّهِ جَمِيعًا وَلَا تَفَرَّقُوا۟ " آل عمران ٣:١٠٣
 “የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ፡፡ አትለያዩም፡፡” (አል ኢምራን፡103)
"وَأَنَّ هَٰذَا صِرَٰطِى مُسْتَقِيمًا فَٱتَّبِعُوهُ وَلَا تَتَّبِعُوا۟ ٱلسُّبُلَ فَتَفَرَّقَ بِكُمْ عَن سَبِيلِهِۦ ذَٰلِكُمْ وَصَّىٰكُم بِهِۦ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ " الأنعام ٦:١٥٣
 “ይህም ቀጥተኛ ሲሆን መንገዴ ነው፡፡ (የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፡፡ ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና፡፡ እነሆ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ፡፡” አል አንዓም፡ ቢድዓን ርቀን ቅኑን ጎዳና እንዲመራን ፤ ግልጽና ስውር ከሆኑ ፈተናዎች እንዲጠብቀን ፤ እርሱን በመታዘዝ ላይ እንዲያግዘን ፤ በሐቁ ላይ እንዲያጸናን አላህን እማጸናለሁ፡፡

 وصىل هللا عىل نبينا محمد وعىل أ ل وحصبه وسمل

ዝግጅት:‐ ዩሱፍ አህመድ



ፒዲኤፍ ፋይሉን ለማውረድ


Post a Comment

1 Comments