Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የመውሊድ በዓል በሚዛን ላይ







የመውሊድ በዓል በሚዛን ላይ
""""""""""""""""""""""""""

ምስጋና ለአለማት ጌታ ለአላህ የተገባ ነው ፡፡ ሰላት እና ሰላም ለዐለማት እዝነት በተላኩት በነቢያችን ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በሰሃባዎቻቸው እና እነርሱን በመልካም በተከተሉት ሁሉ ላይ እስከ እለተ ቂያማ (ትንሳኤ) ድረስ ይውረድ፡፡
ቁርዓን እና ሐዲስን እንዲሁም ዝርዝር የሸሪዓ ህግጋትን በትክክል መረዳት ለሁሉም ሙስሊም በእጅጉ አስፈላጊ ቢሆንም ቀላል ግን አይደለም።

አላህ ለዚህ ኡማ ታላቅ ውለታ በመዋል ኡለማዎችን ሰጥቶን ያላቸውን ታላቅ ክብር ገልፆልናል፡፡ የሙስሊሞችን እምነት፣ የአምልኮ ‘ዒባዳ’ አተገባበር እና የስነምግባር እሴቶችን ማረም የዑለሞች ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ከሰሀቦችና እነሱን ከተከተሉ ታቢዒዮች መካከል ታላለቅ ዑለማዎች እና የፊቅህ ጠበብቶች ቁርዓንን በተገቢው መልኩ በመረዳት እና ዕድሜያቸውን ሙሉ በማስተማር ሀላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ሰሃባዎች ከማንም በበለጠ በዕውቀት የበለፀጉ ከመሆናቸው ባሻገር የመልእክተኛውን ﷺ ንግግር እና ሱና በመተግበር ፋና ወጊዎች እንደነበሩ አያጠያይቅም።

አብደላህ ኢብን መስዑድ አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና በአንድ ወቅት ስለሰሃባዎች እንዲህ ብለው ነበር፤ "ከዚህ ከነቢዩ ዑመት ከማንም በበለጠ፤ ቅን ልቦና፣ የጠለቀ እውቀት፣ የተቃና ፈለግ እና ያማረ ስብዕና ባለቤት ነበሩ። እነሱ ማለት አላህ ለነብዩ ጓደኝነት የመረጣቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ክብራቸውን እወቁላቸው። ፋናቸውንም ተከተሉ። እነሱ ቀጥተኛው መንገድ ላይ ነበሩ።" ኢብኑ ዐብደል በር / ጃሚዑል በያኒል ዒልም በሚባለው ኪታባቸው ቅጽ 2/946-947

ሰሃባዎች በሐቅ ላይ አንድነታቸውን ለመጠበቅ የተለያዩ ሸሪዓዊ አጀንዳዎች ላይ ይመካከሩና ይተራረሙ ነበር፡፡ ያልደረሳቸውን መረጃ ሲያገኙም ወደ ሐቅ ከመመለስ የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም። ለሐቅ ተገዢ ስለነበሩ እርምት ለሰጣቸው አካል ምስጋና እና ክብራቸው ከመጨመሩ ባሻገር በመካከላቸው የነበረው ወዳጅነት አልጎዳም። ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ብለዋል "ሰሃባዎች፣ ታቢዒዮች እና ከእነርሱ በኋላ የመጡት ዑለማዎች በመካከላቸው አለመግባባት በተፈጠረ ጊዜ የአላህን ትዕዛዝ ይከተሉ ነበር፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል «በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትሆኑ የተከራከራችሁበትን ነገር ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፡፡ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡» ሱረቱ ኒሳዕ : 59

በተለያዩ የዲን አጀንዳዎች ላይ በምክክር መልክ ይወያያሉ፡፡ አልፎ አልፎ የዒልምና እና የተግባር ጉዳዮች ላይ የአቋም ልዩነት ሲኖር መዋደድን፣ መተሳሰርን እና ኢስላማዊ ወንድማማችነትን በጠበቀ ሁኔታ ይተራረማሉ።" መጅሙዑል ፈታዋ 24/172

በየዓመቱ የረቢዐል አወል ወር በገባ ቁጥር የነቢያችንን የልደት በዓል መውሊድን የማክበር ጉዳይ ሰዎችን ሲያወዛግብና መነጋገሪያ ሲሆን ይታያል። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሙእሚኖችን በመሰረታዊም ይሁን በቅርንጫፋዊ የዲን ጉዳዮች ላይ አለመግባባት ቢፈጠሩ ጉዳያቸውን ወደ ቁርዓንና ሐዲስ በመመለስ መፍትሄ እንዲፈልጉ በሚከተለው የቁርዓን አንቀጽ አዟል፡፡

فَإِن تَنَازَعْتُمْ فِي شَيْءٍ فَرُدُّوهُ إِلَى اللَّهِ وَالرَّسُولِ إِن كُنتُمْ تُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ ذَٰلِكَ خَيْرٌ وَأَحْسَنُ تَأْوِيلًا ٤:٥٩

«በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ የተከራከራችሁበትን ነገር ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፡፡ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው» ሱረቱ ኒሳዕ : 59

ከዚህ ቁርአናዊ መመሪያ በመነሳት ለአንባቢዎቻችን ነሲሓ ይሆን ዘንድ ትክክለኛውን አቋም እናመላክታለን። አላህ ሀቁን አይተው ከሚከተሉት ሰዎች ያድርገን።
ይህ በዓል በሸሪዓ መሰረት የሌለውና ሰዎች በዲን ውስጥ የጨመሩት አዲስ ነገር ከመሆኑ ባሻገር አላህና መልእክተኛው ያልደነገጉትን ተግባር በቀን የተገደበ ወደ አላህ መቃረቢያ አምልኮ ማድረግ መሆኑ ዋነኞቹ የመውሊድ ችግሮች ሲሆኑ፤ በተጨማሪም ክርስቲያኖችን በመፎካከር የመጣ መሆኑ ከእነሱ ጋር መመሳሰል ነው። በተጨማሪ በዚህ በዓል ውስጥ በሸሪዓ የተወገዙ በርካታ ተግባራት ይፈፀማሉ። መውሊድ አንድን ስራ ቢድዓ የሚያሰኙ ምክንያቶች ሁሉ እንዳሉበት አያጠራጥርም። ይህም በሚከተሉት ሶስት ነጥቦች ይብራራል፤

1) አዲስ ነገር መፍጠር (ኢሕዳስ)፦
ካለ ሸሪዓዊ ማስረጃ፤ ማንኛውንም ቀን ወይም ወር ልዩ ሀይማኖታዊ ክንውን የሚፈፀምበት እንደሆነ በማሰብ በዋጂብነት ወይም ሱናነት ሰዎችን የምናበረታታበት ከሆነ በዲን ውስጥ አዲስ ነገር መፍጠር ነውና ሀራም ነው።

አላህ እንዲህ ብሏል:-

أَمْ لَهُمْ شُرَكَاءُ شَرَعُوا لَهُمْ مِنَ الدِّينِ مَا لَمْ يَأْذَنْ بِهِ اللَّهُ
«ከሀይማኖት አላህ በእርሱ ያልፈቀደውን ለእነሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለእነርሱ አሏቸውን?» ሱረቱ ሹራ ቁጥር 21

ቡኻሪ እና ሙስሊም በዘገቡት የተረጋገጠ ሰሂህ ሐዲስ ነቢያችን ﷺ ብለዋል፤

مَنْ أحْدَثَ في أمْرِنَا هَذَا مَا لَيْسَ مِنْهُ فَهُوَ رَدٌّ

«በዲናችን ውስጥ ከእርሱ ያልሆነን ነገር የፈጠረ ስራው ተመላሽ ይደረግበታል» ብለዋል።

ይህ ማለት በሸሪዓ ያልተደነገገን ነገር ፈጥሮ ቢፈፅም ተቀባይነት አያገኝም ማለት ነው።
እንደሚታወቀው፤ መውሊድን ረሱል ﷺ የተከበሩት ኸሊፋዎች እና ሌሎችም ሰሀባዎች አላከበሩትም። እንደዚሁ በተከበረው ዘመን ውስጥ የኖሩት ሰሀባዎችን በመልካም ሲከተሉ የነበሩ ታቢዒዮች አልሰሩትም። እነሱ ደግሞ ከማንም በላይ የሱና አዋቂዎችና ለነቢያችን የነበራቸው ውዴታም ከማንም በላይ እንደነበር እሙን ነው። የነብዩን ፈለግ በሚገባ በመከተልም የማይታሙ እንደ ነበሩ ለማንም ግልፅ ነው። ለኛ አርአያ መሆናቸውም ተነግሮናል። ምንም ሳንጨምር መንገዳቸውን አጥብቀን እንድንይዝ የአላህ መልዕክተኛ አደራ ብለውናል፤

عَلَيْكُمْ بِسُنَّتِي وَسُنَّةِ الْخُلَفَاءِ الرَّاشِدِينَ الْمَهْدِيِّينَ، وَعَضُّوا عَلَيْهَا بِالنَّوَاجِذِ، وَإِيَّاكُمْ وَمُحْدَثَاتِ الْأُمُورِ، فَإِنَّ كُلَّ مُحْدَثَةٍ بِدْعَةٌ، وَكُلَّ بِدْعَةٍ ضَلَالَةٌ

«የእኔን እና የቅን ምትኮቼን ሱና አደራ! በጥርሶችችሁ አጥብቃችሁ ያዙ! አዳዲስ ፈጠራዎችን ተጠንቀቁ (ተከልከሉ)፣ በዲን ውስጥ የተጨመረ ፈጠራ ሁሉ ጥመት ነው» ኢማሙ አህመድ ዘግበውታል

መውሊድ በቀደምቶቹ ዘመን እንዳልነበረ እና ኃላ የተፈጠረ (ሙህደስ) ለመሆኑ መውሊድ አክባሪዎች ሁሉ የማይክዱት እውነታ ነው። መውሊድ ማክበርን ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመሩት ከአራተኛው ክ/ዘመን በኋላ እራሳቸውን ፋጢሚዮች ብለው ይጠሩ የነበሩት ኡበይዲዩች ግብፅን በ362 ዓመተ ሂጅራ የወራሩ ጊዜ ነበር።

አልሚቅሪዚይ "አልመዋኢዝ ወል-ኢዕቲባር" በተሰኘው ድርሳናቸው ቅፅ 2 ገፅ 436 ላይ እንዲህ ብለዋል፦ የፋጢሚያ (ዑበይዲዮች) ነገሥታት አመቱን ሙሉ የተለያዩ በአላት ነበሯቸው። ለምሳሌ፤ የአመቱ መግቢያ፣ የመጀመሪያው አመት፣ የዓሹራ ቀን፣ የነብዩ ﷺ መውሊድ ይገኙበታል። በተመሳሳይ መልኩ አቡ ሻማህ–አል-ባዒስ አላ ኢንካሪል-ቢደዕ ወልሀዋዲስ ገፅ 23 ላይ እንዲህ ብለዋል፤ በኛ ጊዜ ከሚፈፀሙ ተመሳሳይ መጤ (ሙህደስ) ተግባራት መካከል፤ በኢርበል ከተማ በየዓመቱ የሚፈፀመው የሰደቃ፣ የበጎ አድራጎትንና ደስታን ለመግለፅ ተውቦና ደምቆ በመዋል (የሚከበረው) የነቢዩ ﷺ የልደት ቀን አንዱ ነው።

ኢብኑ ነሓስ – ተንቢሁል ጋፊሊን ገፅ 331 ላይ እንዲሁም ኢብኑል ሀጅ – አልመድኸል ቅፅ 2 ገፅ 2 ተመሳሳይ መልዕክቶችን አስፍረዋል።
በዚሁ አጋጣሚ መውሊድን ስለጀመሩት ሰዎች ማንነት አንዳንድ ነገሮችን ማንሳት ግድ ይለናል፤ "ዑበይዲዮች" ምንም እንኳ ራሳቸውን ወደ ፋጢማ ቢያስጠጉም፤ ሸሪዓዊ ትዕዛዛት እና ክልከላዎች የራቁ ትርጉሞችን በመስጠት ስርአት አልበኝነትን የሚከተለውን የባጢኒያ አመለካከት በማራመድ፣ የዲነልኢስላም ፋና እንዲጠፋ የቻሉትን ሁሉ በማድረግና ኡለማዎችን በመጨፍጨፍ የታወቁ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የኩፍር ንግግሮችን በመናገራቸዉ፣ አላህንና ነብያቶችን በግልፅ በመሳደባቸዉ፣ ክልክሎችን ሀላል በማድረጋቸዉ ወዘተ... ታላላቅ የኢስላም ሊቃዉንት ከኢስላም ምንም ድርሻ እንደሌላቸዉ ተናግረዋል። ሰላሀዲን አል-አዩቢይ አላህ ይዘንለትና ቁድስን ካስለቀቀ በኋላ ሙስሊሙን ከነዚህ ሰዎች ወረራ ለማላቀቅ ዘምቶባቸው ሙስሊሙን ህብረተሰብ እፎይ አሰኝቷል። ከፊሎቹ ደግሞ መውሊድን የጀመረው በ630 ዓ.ሒ የሞተው ንጉስ መሊክ ሙዞፈር ሲሆን እሱ ደግሞ ፍትሃዊ ንጉስ ነበር ይላሉ። በዘመኑ የነበረው የታሪክ እና የጂዖግራፊ ሊቅ ያቁተል ሀመዊ ሙዘፈርን ሲገልፀው “የሰው ንብረት ይዘርፋል ግን ለድሃዎች ያበላል፣ ስራዎቹ ሁሉ ግራ የሚያጋቡ ናቸው” ይላል። መውሊድን ማንም ቢጀመረው ከብዙ ክፍለ ዘመናት በኋላ በዲን ላይ የተጨመረ ለመሆኑ ምስክር ነው።

ከላይ በተዘረዘሩት መረጃዎች መሰረት መውሊድ የዲን አካል ያልነበረ የዑበይዲዮች ወይም የኢብኑ ሙዞፈር ፈጠራ እንደሆነ ግልፅ ነው።

مَنْ أحْدَثَ في أمْرِنَا هَذَا مَا لَيْسَ مِنْهُ فَهُوَ رَدٌّ» متفق عليه

ረሱል ﷺ እንዲህ ብለዋል:- “በዲናችን ውስጥ ከእሱ ያልሆነን ነገር የፈጠረ ስራው ተመላሽ ነው” ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውታል

2) ዒባዳን በጊዜ መለየት (ተኽሲስ)፦
ጊዜያትን ለተለያዩ ዒባዳዎች መፈፀሚያ አድርጎ የወሰነልን አላህ ነው። በሸሪዓችን ረመዳን ለፆም ዙልሒጃ ለሐጅ እንደተለዩት በጊዜ የተገደቡ ዒባዳዎችን በመወሰን በዚህ ቀን ወይም ወር ይህ ይፈፀማል የሚል ድንጋጌ ማውጣት ለማንም አይፈቀድም።

መውሊድ የሚያከብሩ ወገኖች ግን በሸሪዓችን ያልተደነገገውን የረቢዕን ወር አስራ ሁለተኛ ቀን በተለያዩ የዒባዳ ተግባራት ለማሳለፍ በአል አድርገው መርጠውታል። አቡሁረይራህ ባስተላለፉት ሐዲሥ ረሱልﷺ እንዲህ ብለዋል፤

لَا تَخْتَصُّوا لَيْلَةَ الْجُمُعَةِ بِقِيَامٍ مِنْ بَيْنِ اللَّيَالِي، وَلَا تَخُصُّوا يَوْمَ الْجُمُعَةِ بِصِيَامٍ مِنْ بَيْنِ الْأَيَّامِ، إِلَّا أَنْ يَكُونَ فِي صَوْمٍ يَصُومُهُ أَحَدُكُمْ

“የጁምዓ ሌሊትን ከሌሎች ለሊቶች በመለየት በቂያም አትለዩ። ምን አልባት ከምትፆሙት ፆም ጋር ከገጠመ እንጂ የጁምዓ ቀንን ከሌሎች ቀናት በመለየት አትፁሙ» ሙስሊም ዘግበውታል

በዚህ ሐዲሥ የነቢዩ ንግግር ተኽሲስን ያመለከታል። ከጁምዓ ጋር አያይዘው ስለ ተከለከለ ወይም ስለ ታዘዘ ነገር ሲነግሩን ችግሩ በሸሪዓ ልዩ ያልተደረገን ጊዜ በተወሰኑ ኢባዳዎች መለየት ላይ መሆኑን እንረዳለን። አንድን ጊዜ ከሌሎች ጊዜያት በፆም በሶላት አትለዩት ተብሎ መከልከሉ ለሚሰራው ስራ መበላሸት መንስኤው በሸሪዓ ያልተገደበለትን ጊዜ መገደብ (ተኽሲስ) መሆኑን ያስረግጥልናል።

3) ሙስሊም ካልሆኑ ጋር መመሳሰል (ተሸቡሕ)፦

መውሊድን ማክበር ክርስቲያኖች የእየሱስ ልደት (ገና) ብለው ከሚያከብሩት በአል ጋር በእጅጉ ተመሳሳይነት አለው።
አንዳንድ የቢድዓ ሰዎች ነቢዩን ለማላቅ በማሰብ መውሊድን ሲጀምሩት ክርስቲያኖች እንዴት "የነብያቸውን የውልደት ቀን በማውሳት ይቀድሙናል" ከሚል የፉክክር ስሜት ነው። ይህንኑ እውነታ በማረጋገጥ አሕባሽ በመባል የሚታወቀው ቡድን መስራች የሆነው ዐብዱላህ አልሐበሺ የ ‘ኢዝሀሩል አቂደቲሱኒያህ’ የድምፅ ማብራሪያ ካሴት ቁ.9 የመጀመሪያው ክፍል ላይ መውሊድን ለመጀመሪያ ጊዜ ያከበረው የኢርቢሉ ንጉስ ሙዘፈር እንደሆነ እና አጀማመሩም ክርስቲያኖች የመሲህን ልደት ሲያከብሩ አይቶ "ሙሀመድﷺ ወደዚህ አለም ብቅ በማለታቸው አላህን ላመስግን" በማለት እንደጀመረው ተናግሯል።

ቡኻሪ ከአቢ ሰዒድ አልኹድሪይ ረዲየላሁ ዐንሁ እንደዘገቡት የአላህ መልዕክተኛﷺ እንዲህ አሉ፤

لَتَتَّبِعُنَّ سَنَنَ مَنْ قَبْلَكُمْ شِبْرًا بِشِبْرٍ، وَذِرَاعًا بِذِرَاعٍ، حَتَّى لَوْ سَلَكُوا جُحْرَ ضَبٍّ لَسَلَكْتُمُوهُ»، قُلْنَا يَا رَسُولَ اللَّهِ: اليَهُودَ، وَالنَّصَارَى قَالَ:«فَمَنْ»

"ከናንተ በስተፊት የነበሩትን (ህዝቦች) ፈለግ ስንዝር በስንዝር እርምጃ በእርምጃ ትከተላላችሁ። የተሳቢ እንስሳ ጉድጓድ እንኳ ቢገቡ ትከተሏቸዋላችሁ" የአላህ መልዕክተኛﷺ ሆይ አይሁዶችንና ነሳራዎችን ነው? ተብለው ሲጠየቁ፤ «ሌላ ማንን ነው!» (እነሱን ነው እንጂ) በማለት መለሱ።

ቡኻሪ እና ሙስሊም በዘገቡት ሌላ ሐዲሥ “ሙሽሪኮችን ተፃረሯቸው” ብለዋል። ይህ ማለት በማንነታችሁ ላይ አትደራደሩ፣ በሀይማኖታዊ ጉዳዮች ሌሎችን ከመምሰል ተጠንቀቁ ነው።

በሌላ በኩል በመውሊድ በዓል ላይ በነቢያችን ﷺ ላይ ድንበር በማለፍ እና የአላህን ስልጣን በመስጠት የሚያወድሱ ግጥሞች ይነበባሉ። እርሳቸው ግን የዚህ አይነቱን ድንበር ማለፍ ከልክለዋል፤

لاَ تُطْرُونِي، كَمَا أَطْرَتْ النَّصَارَى ابْنَ مَرْيَمَ، فَإِنَّمَا أَنَا عَبْدُهُ، فَقُولُوا عَبْدُ اللَّهِ، وَرَسُولُهُ
«ክርስቲያኖች የመርየምን ልጅ እንዳጋነኑት እኔንም አታጋንኑኝ፤ እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፤ የአላህ ባሪያ እና መልዕክተኛ ብቻ በሉኝ» ሀዲሱን ቡኸሪ ዘግበውታል።

በመሆኑም መውሊድን የሚያከብሩ ሰዎች ሁለት የመመሳሰል (ተሸቡሕ) ጥፋቶችን ፈፅመዋል።
1ኛ:- ከኩፋሮች ጋር በበዓል መመሳሰል
2ኛ:- ድንበር ባለፈ የውዳሴ አካሄድ መመሳሰል
ሲጠቃለል፤

የመውሊድ በዓል የሸሪዓ አካል ስላልሆነ፣ ተቀባይነት የሌለው፣ መሰረታዊ የአምልኮ መርሆዎችን የሚጥስ የቢድዓ ተግባር ነው።
እርግጥ ነው የነብዩ ውዴታ ‘መሐባ’ እና እሳቸውን ማላቅ በእጅጉ የሚያስፈልገን ነገር ነው። ሆኖም ውዴታቸውን የምንገልፀው መንገዳቸውን በመከተል፣ ሱናቸውን አጥብቀን በመያዝ እና ከአዳዲስ ፈጠራዎች በመራቅ መሆን አለበት። ‘የነብዩ ውዴታ’ በሸሪዓ መሰረት ያለው፤ ብሎም የኢማን መገለጫ መሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም፤ ከተለያዩ የቢድዓ ተግባራት ጋር ተጣምሮና በቀን ተገድቦ ከተፈፀመ ግን በቢድዓነት ይፈረጃል።

መውሊድ ቢድዓ ከመሆኑ ባሻገር በየጊዜው እንግዳ ጥፋቶች እየታከሉበት እምነትን ከሚጎዱ ብዙ ተግባራት ጋር ከሁለቱ ኢዶች እኩል ወይም ከነሱ በደመቀ ሁኔታ በይፋ በመከበር ላይ ነው። በተለይም በአንዳንድ ቦታዎች ከተራ ወንጀሎች እስከ ቀብር አምልኮ የሚደርሱ ጥፋቶች ይሰራሉ። በተለይ ደግሞ ዓዋቂ የሚባሉ ሰዎች ሲሳተፉበት የቢድዓ አራማጆችም ተራ ሙግቶችን በጥሩ ገለፃዎች ከሽነው በስፋት ሲያሰራጩ ብዙሀኑን ህዝብ መደናገር ውስጥ ይከታሉና ሐቁን መግለፅ የሁሉም አዋቂዎች ግዴታ መሆኑን እናስታውሳለን።

አላህ እውነተኛ የነብዩ ወዳጆችና ተከታዮች ያድርገን። ሀሰትን ተከትሎ መንገድ ከመሳት ይጠብቀን።

ወል ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን!


 
ነሲሓ መፅሔት ቅፅ 2 ቁጥር 1

Post a Comment

0 Comments