Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

 


“የቆንጆ” ቢድዐ ቁርኣናዊ “ማስረጃ”
~ ~ ~ ~ ~ ~ ~~ ~ ~ ~ ~ ~~
በኢስላም የዒባዳ ፈጠራ የተወገዘ እንጂ የተወደሰ ምግባር አይደለም። ነብዩ ﷺ ቢድዐን በተደጋጋሚ ሲያወግዙም “ይሄ ሲቀር” ብለው ነጥለው ያስቀሩት የለም። “የእኛ ትእዛዝ የሌለበትን ስራ የሰራ ስራው ውድቅ ነው” አሉ እንጂ “በራሳችሁ መደንገግ ትችላላችሁ” አላሉም። “በዚህ (የዲን) ጉዳያችን ላይ ከሱ ያልሆነን አዲስ ነገር ያመጣ እሱ ተመላሽ ነው” አሉ እንጂ “የሚያስመነዳ ቢድዐ አለ” አላሉም። “ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ”፣ “የሐጅ አፈፃፀሞቻችሁን ከኔ ውሰዱ”፣ “በኔ ላይ ለእናንተ መልካም ተምሳሌት አለ” አሉ እንጂ “አትጨናነቁ በራሳችሁም መጨመር የምትችሉት ዒባዳ አለ” አላሉም። የሶሐቦችም አካሄድ ይህንን ነው የሚያጠናክረው። ለቢድዐ ቀዳዳና መፈናፈኛ የማይሰጡ በርካታ ከባባድ ንግግሮችን ጥለው አልፈዋል። ይህም ሆኖ ግን ለሚፈፅሙት ቢድዐ “ጥሩ” የሚል ጭምብል የሚያለብሱ አካላት በየዘመኑ ያጋጥማሉ። ለዚህም ምንም እንኳን አዋጭ ባይሆኑም የሚጠቀሟቸው ብዥታዎች አሏቸው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ተከታዩዋ አንቀፅ ነች፦
(تُدَمِّرُ كُلَّ شَيۡءِۭ بِأَمۡرِ رَبِّهَا فَأَصۡبَحُواْ لَا يُرَىٰٓ إِلَّا مَسَٰكِنُهُمۡۚ) [الأحقاف: 25]
{በጌታዋ ትእዛዝ ሁሉን ነገር ታጠፋለች። ከመኖሪያዎቻቸውም በስተቀር ምንም የማይታዩ ሆኑ።} [አልአሕቃፍ፡ 25]

አንቀጿ የነብዩ ሁድ ዐለይሂ ሰላም ህዝቦች ባስተባበሉ ጊዜ ስለተላከችባቸው የቅጣት ነፋስ ነው የምታወራው። የቢድዐ ደጋፊዎች ግን “ቢድዐ ሁሉ ጥመት ነው” የሚለውን ሐዲሥ ለመገደብ ይህቺን አንቀፅ እንዴት እንደሚተነትኗት ተመልከቱ፡-
“ሁሉም ነገር ከሚለው ገለፃ ውስጥ ሰማይና ምድር፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ፀሀይ፣ ጀነትና እሳት፣ መላኢካ፣ ጂን፣ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች፣ እፅዋት፣ እንስሳት፣ ግኡዛን… ሁሉ ይጠቃለላሉ። በተግባር ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች አልወደሙም። አህቃፍ የተባለችው የከሃዲዎች መንደር ብቻ ናት የጠፋችው። የአንቀጿ ገለፃ ዐሙን መኽሱስ ይሰኛል። ገለፃው አጠቃላይ ቢሆንም በተጨባጭ እውነታ የተገደበ ነው። ቢድዐህ ሁሉ ጥመት ነው የምትለዋ ሀዲስም እንደዚሁ ገለፃዋ አጠቃላይና ሁሉንም አዲስ ነገሮች (ቢድዐዎች) የሚያካትት ቢመስልም በሌሎች ሀዲሶችና በሸሪዐው መርሆዎች የተገደበች ናት።”

ምላሽ:-
====

1. በአንቀጿ ውስጥ “ሁሉ” የሚለው ቃል የቢድዐ አጋፋሪዎች የሚዘረዝሩትን ሁሉ የሚያካትት አይደለም። ነፋሷ የተላከችው ወደ አሕቃፍ ነው፣ ወደ ነብዩ ሁድ ሰዎች። በሌላ ቦታ አላህ እንዲህ ይላል፡-

(وَفِي عَادٍ إِذۡ أَرۡسَلۡنَا عَلَيۡهِمُ ٱلرِّيحَ ٱلۡعَقِيمَ ٤١ مَا تَذَرُ مِن شَيۡءٍ أَتَتۡ عَلَيۡهِ إِلَّا جَعَلَتۡهُ كَٱلرَّمِيمِ) [الذاريات: 41-42]

{በዓድም ህዝብ ላይ አጥፊ የሆነችን ነፋስ በላክን ጊዜ (የሆነውን አስታውስ።) በላዩ ላይ የመጣችበትን ማንኛውንም ነገር እንደ በሰበሰ አጥንት ያደረገችው ብትሆን እንጂ አትተወውም።} [አዛሪያት፡ 41-42]

ስለዚህ ነፋሷ ወደ አሕቃፍ መንደር ነው የተላከችው። ሰማይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ፀሀይ፣ ጀነትና እሳት፣ … በአሕቃፍ መንደር አይደለም ያሉት።
2. በዚያ ላይ {በጌታዋ ፈቃድ} የሚል ቃል አለ። ስለዚህ እንድታጠፋ የተፈቀደላትን ብቻ ነው “ሁሉ” ሲል የገለፀው።
3. {ከመኖሪያዎቻቸውም በስተቀር ምንም የማይታዩ ሆኑ} ማለቱን አስተውሉ።
4. ከ21ኛዋ አንቀፅ ጀምራችሁ እያነበባችሁ ብትወርዱ እየተረከ ያለው ስለ ዓድ ህዝቦች እንደሆነ ግልፅ ነው። በዚህ አገባብ ውስጥ “ሁሉ” የሚለው ቃል ፍንትው ያለ ሆኖ ሳለ ሰማይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ፀሀይ፣ ጀነት፣ እሳት፣ መላኢካ፣ ጂን፣ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች፣ እፅዋት፣ እንስሳት፣… እያሉ ማተራመስ እጅግ የሚደንቅ ነው። “አስራ ሰባት ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ደብረ-ብርሃን ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ተገልብጦ በውስጡ የነበሩት ሁሉም ተሳፋሪዎች አለቁ” በሚለው ዜና ውስጥ “ሁሉ” የሚለው ቃል እንደሱፍዮች አረዳድ ከአለም ህዝብም ተሻግሮ ጂንና መላእክትን ሁሉ ይገልፃል ማለት ነው። ከንዲህ አይነት የዛገ አመለካከት አላህ ይጠብቀን።

ለማንኛውም የቁርኣን ተንታኞች ስለ አንቀጿ ምን እንደሚሉ እንመልከት፡-

1. ኢብኑ ጀሪር አጦበሪ (310 ዓ.ሂ.) ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡-
وإنما عنى بقوله (تُدَمِّرُ كُلَّ شَيْءٍ بِأَمْرِ رَبِّهَا) مما أرسلت بهلاكه
“{በጌታዋ ትእዛዝ ሁሉንም ነገር ታጠፋለች} ሲል ማለት የፈለገው እንድታጠፋው የተፈለገውን ማለት ነው።” [ተፍሲር ኢብኒ ጀሪር፡ 22/129]

2. ቁርጡቢም (671 ዓ. ሂ.) እንዲህ ይላሉ፡-
كُلُّ شَيْءٍ مَرَّتْ عَلَيْهِ مِنْ رِجالِ عَادٍ وَأَمْوَالِهَا. قَالَ ابْنُ عَبَّاسٍ: أَيْ كُلُّ شَيْءٍ بُعِثَتْ إِلَيْهِ
“ያለፈችባቸውን የዓድ ሰዎችና ንብረቶቻቸውን ለማለት ነው። ኢብኑ ዐባስ፡ ‘የተላከችበትን ሁሉ ማለት ነው’ ብሏል።” [ተፍሲሩል ቁርጡቢ፡ 16/206]

ሲጠቃለል በየትኛውም ሁኔታ “ሁሉ” የሚለው ቃል አገባቡን የሚከተል እንጂ የቢድዐ ልክፍተኞች እንደሚሉት ጀነትና እሳት ሳይቀር ከፈጣሪ ውጭ ያለን ነገር በሙሉ የሚያጠቃልል አይደለም። “ቢድዐ ሁሉ ጥመት ነው” ሲባልም እንዲህ አይነት ልጓም አልባ የሆነ አረዳድ የሚረዳ አንድም የለም። የቢድዐ ፍቅር የማገናዘብ አቅማቸውን ያሽመደመደባቸውን ወገኖቻችንን አላህ ዐቅላቸውን ይመልስላቸው።

ኢብኑ ሙነወር

Post a Comment

0 Comments