Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የመስጂዶች መዘጋት ጉዳይ!

የመስጂዶች መዘጋት ጉዳይ!
~~~~~~~~~~~~~~~~~
የኮሮና ቫይረስን ሰፊ ስርጭት ተከትሎ የሳዑዲ ታላላቅ ዑለማእ ምክር ቤት በመስጂዶች
የሚፈፀመው የጀማዐና የጁሙዐ ሶላት በጊዜያዊነት እንዲቆም ፈትዋ መስጠቱ የሚታወቅ
ነው። የዑለማእ ስብስቡ ፈትዋውን የሰጠው ከሸሪዐ ማስረጃዎች ባለፈ ስለ ወረርሺኙ ፈጣን
የስርጭት ሁኔታና በቫይረሱ ሰበብ ስለተከሰተው ከፍተኛ የሞት መጠን ታማኝ የህክምና
ሪፖርቶችን ከመረመረ በኋላ ነው። በቦታውም ላይ የጤና ሚኒስትሩ ተገኝቶ ዝርዝር መረጃ
ሰጥቷል። የሰዎች መሰባሰብ ለበሽታው ስርጭት ቀዳሚ መንገድ እንደሆነም አስረድቷል።
ፈትዋው ምን ያክል መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ( ﺍﻟﻮﺍﻗﻊ ) ከግንዛቤ ያስገባ እንደሆነ
ተመልከቱ።
ይህንን ነባራዊ ሐቅ ከተመለከተ በኋላ የኢስላማዊ ሸሪዐን ማስረጃዎች በመንተራስ፣
የሸሪዐውን ግቦች (መቃሲደ ሸሪዐ) ከግንዛቤ በማስገባት፣ ኢስላማዊ መርሆዎችን እና
በጉዳዩ ላይ ያሉ የምሁራንን ንግግሮች በጥልቀት በመመርመር ነው መስጂዶች
በጊዜያዊነት እንዲዘጉ ፈትዋ የሰጠው።
ነገር ግን ይህንን ፈትዋ ተቀብሎ ወገንን ለማትረፍ ሰበብ በማድረስ ፋንታ እነዚህን ታላላቅ
ዑለማዎች በነገር ለመውጋት የሞከሩ አካላት አጋጥመዋል። ለምሳሌ ያክል አንዱ
በአለማቀፍ ደረጃ የሚታወቅ የሆነ ሰው ተከታዩዋን አንቀፅ ያለ አግባብ በመመንዘር
ዑለማዎቹን በሌሉበት ከሷቸዋል:–
( ﻭَﻣَﻦۡ ﺃَﻇۡﻠَﻢُ ﻣِﻤَّﻦ ﻣَّﻨَﻊَ ﻣَﺴَـٰﺠِﺪَ ﭐﻟﻠَّﻪِ ﺃَﻥ ﯾُﺬۡﻛَﺮَ ﻓِﯿﻬَﺎ ﭐﺳۡﻤُﻪُۥ ﻭَﺳَﻌَﻰٰ ﻓِﯽ ﺧَﺮَﺍﺑِﻬَﺎۤۚ ﺃُﻭ۟ﻟَـٰۤﻯِٕﻚَ ﻣَﺎ ﻛَﺎﻥَ ﻟَﻬُﻢۡ
ﺃَﻥ ﯾَﺪۡﺧُﻠُﻮﻫَﺎۤ ﺇِﻟَّﺎ ﺧَﺎۤﻯِٕﻔِﯿﻦَۚ ﻟَﻬُﻢۡ ﻓِﯽ ﭐﻟﺪُّﻧۡﯿَﺎ ﺧِﺰۡﯼࣱ ﻭَﻟَﻬُﻢۡ ﻓِﯽ ﭐﻟۡـَٔﺎﺧِﺮَﺓِ ﻋَﺬَﺍﺏٌ ﻋَﻈِﯿﻢࣱ )
“የአላህንም መስጂዶች በውስጣቸው ስሙ እንዳይወሳ ከከለከለና እነርሱንም
ለማበላሸትም ከሚታገል ሰው ይበልጥ በዳይ ማነው? እነዚያ ፈሪዎች ሆነው እንጂ ወደነሱ
ሊገቡ አይፈቀድላቸውም። ለእነርሱ በቅርቢቱ ዓለም ውርደት አላቸው፡፡ ለነርሱም
በመጨረሻይቱ አገር ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡” [አልበቀራህ: 114]
እስኪ አላህ ያሳያችሁ። የሸሪዐ ማስረጃዎችን አጢነው፣ መሬት ያለውን ሐቅ አገናዝበው፣
የህክምና ባለሙያዎችን ጥናቶች አስተውለው በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ሊደርስ የሚችልን
አደጋ ቢቻል ለመከላከል፣ ካልሆነ ቢያንስ ለመቀነስ የሰጡትን ፈትዋ ጭራሽ መስጂዶችን
እንደማፈረስ፣ የአላህ ስም እንዳይወሳባቸው እንደመከልከል ተደርጎ ሲቀርብ ምን
ትላላችሁ? ስሜት ያውራል፣ ያደነቁራል። ለማንኛውም መስጂዶች እንዲዘጉ ፈትዋ
በመስጠት የሳዑዲ ዑለማዎች ብቸኛ አይደሉም። ይልቁንም በበርካታ ሃገራት ተመሳሳይ
ፈትዋዎች ወጥተዋል። ለምሳሌ ያክልም በኩወይት፣ ኢማራት፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ኳታር፣
ዮርዳኖስ፣ ኦማን፣ ሊቢያ፣ ቱርክና ሌሎችም።
ብዥታዎች
በዑለማዎቹ የተሰጠውን ፈትዋ ለማጣጣል የተለያዩ ማመሃኛዎች ያቀረቡ አካላት አሉ።
# ብዥታ_አንድ :– “የበሽታው ጉዳት ከልክ በላይ ተጋኗል እንጂ መስጂድ ለመዝጋት
የሚደርስ አይደለም” የሚሉ አሉ።
ተከታዮቹን ነጥቦች አስተውሉና ይሄ ሙግት ውሃ የማያነሳ መሆን አለመሆኑን እራሳችሁ
ፍረዱ።
ሀ/ የበሽታው ተስፋፊነት ፍጥነት:–
ጣልያንን እንደምሳሌ ብንወስድ የመጀመሪያው ኬዝ የተመዘገበው በ31/1/2020 ነው።
እስከ 06/02/2020 ድረስ ውጤቱ ባለበት ነበር። ሁለት ኬዝ ብቻ። ከዚያስ? ልክ በወሩ
በ06/03/2020 አራት ሺህ አካባቢ ደረሰ። ከ20 ቀን በኋላ 80 ሺ አለፈ። የአለምን ካየን
የተያዘው 615 ሺ ተሻግሯል። ከቻናዋ ውሃን ግዛት የተነሳው ወረርሽኝ በአሁኑ ጊዜ ከ190
በላይ ሃገራት ውስጥ ገብቷል። ከአራት ቀን በፊት የአለም ጤና ድርጅት ሃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ
አድሀኖም በሰጠው መረጃ መሰረት “በኮሮና ቫይረስ የተያዘው የመጀመሪያ ሰው ሪፖርት
ከተደረገ በኋላ የመጀመሪያዎቹ 100ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ለመያዝ 67 ቀናት ወስደዋል።
ቀጣዮቹ 100ሺህ ሰዎች የተያዙት በ11 ቀናት ውስጥ ሲሆን ፤ ሦስተኛ 100ሺህ ሰዎች
የተያዙት ደግሞ በ4 ቀናት ውስጥ ነው።” ይህን በተናገሩ ቀን አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ
ሰዎች ቁጥር 350 ሺ አካባቢ ነበር። አሁን ደግሞ ከ615ሺ በላይ።
ለ/ የበሽታው ገዳይነት:–
በጣልያን ብቻ ከ9 ሺህ ሰው በላይ ሞቷል። በአለም ላይ ባጠቃላይ የሞተው ደግሞ እንደ
ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ሪፖርት ይህንን በምፅፍበት ሰዓት 28,717 ደርሷል።
የበሽታው የተስፋፊነትና የገዳይነት አቅም ይህን ያክል ነው። ኧረ እንዲያውም ከዚህም
በላይ ነው። ምክንያቱም
– እንደ ቻይና፣ ኢራን፣ ቱርክና አሁን ደግሞ የአፍሪካ ሃገራት የሰለባዎችን ቁጥር እየደበቁ
እንደሆነ ብዙዎች ዘንድ ይታመናል።
– በብዙ ሃገራት ታሞ እርዳታ ከሚጠይቀውና ከሱ ጋር ከተነካኩ አካላት ውጭ ሰፊ
ምርመራ አልተካሄደም። በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ቻይናንና
ጣልያንን አልፋ ከ100 ሺ በላይ አስቆጥራለች። ይህ የሆነው ግን ሰፊ የምርመራ ዘመቻ
በመክፈቷ ነው። እንዲህ አይነቱ መጠነ ሰፊ የምርመራ ዘመቻ በሌሎች ሃገራት
አልተሰራበትም። እውነታው ይህ ከመሆኑ ጋር አንዳንዶች በሽታው ተጋኖ እንጂ ያን ያክል
ጉዳት የሚያደርስ አይደለም እያሉ ነው።
ሐ/ ሁሉንም ክፍል ያጠቃል።
አንዳንዶች ስለ በሽታው ከያዟቸው የተዛነፉ እይታዎች ውስጥ ቫይረሱ የሚያጠቃው
አረጋውያንንና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውን ብቻ ነው የሚለው ነው። ይሄ እሳቤ በተለያየ
ምክንያት ጤነኛ አይደለም።
→ አባባሉ ከፊል እውነት ከመያዙም ጋር ብዛት ያላቸው ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸውም፣
ወጣቶች ጭምር እንደተጎዱና እንደሞቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።
→ ወጣቶችን አይጎዳም ተብሎ ቢታመን እንኳን በመስጂዶች ውስጥ የጀማዐ ሶላት
መቀጠል የተነሳ በሽታውን ከያንዳንዱ ቤት እንዲገባ ያደርገዋል። መቼም ሰጋጆቹ
ከማህበረሰብ ተገልለው የሚኖሩ አይደሉም።
# ብዥታ_ሁለት :– “ዑለማዎቹ መንግስትን ለመታዘዝ ብለው ነው ፈትዋ የሰጡት” የሚልም
አለ።
ይሄም ከእውነት የራቀ አነጋገር ነው። ማስረጃዎችን ዘርዝረው፣ የዑለማዎችን ንግግሮች
አስተውለው፣ የጤና ሚኒስትሩን ጠርተው ማብራሪያ ካገኙ በኋላ የሰጡትን ፈትዋ መሪን
ለመታዘዝ ብቻ ብለው ነው የሰጡት ማለት ምናልባት ክፉ እሳቤ ከሌለበት ከባድ የግንዛቤ
ችግር ነው።
# ብዥታ_ሶስት :– “ከዚህ ቀደም ብዙ ወረርሽኝ ከመከሰቱም ጋር መስጂዶች ተዘግተው
አያውቁም”
– በመጀመሪያ ከዚህ በፊት መስጂዶች የተዘጉበት ሁኔታ ላለመኖሩ መረጃ አታቀርቡም።
እንዲያውም በወረርሺኝ ሳቢያ መስጂዶች የተዘጉባቸው የተለያዩ ዘመናት ገጥመዋል።
ለማሳጠር ያክል አንድ ሁለት ብቻ ልጥቀስ። አልኢማሙ ዘሀቢ ረሒመሁላ፞ህ የ448 ሂጅሪያ
ታሪክ ባሰፈሩበት ቁርጡባ ላይ በደረሰው ከባድ ድርቅና ወረርሽኝ የተነሳ መስጂዶች
ተዘግተው ነበር ይላሉ። [አስሲየር: 18/311] የታሪክ ፀሐፊው አልመቅሪዚ ረሒመሁላህ
በ749 ሂጅሪያ ግብፅ ውስጥ ስለተከሰተው ወረርሺኝ ሲያትቱም፡- “በበርካታ ቦታዎች አዛን
ተራቆተ (ቆመ)። በሚታወቅ ቦታ አንድ አዛን ብቻ ቀረ። አብዛኞቹ መስጂዶችና ዛዊያዎች
ተዘጉ” ብለዋል። [አስሱሉክ ሊ መዕሪፈቲ ዱወሊል ሙሉክ፡ 4/88]
– ሁለተኛ ይሄ በሽታ ከሌሎች ወረርሽኞች የሚለይበት ልዩ ነጥብ አለው። እሱም በትንፋሽ የሚተላለፍ መሆኑ ነው። ይሄ ከኮሌራና መሰል በሽታዎች ይለያል። በሽታው የቫይረሱ
ተሸካሚ ሆኖ ነገር ግን መታመሙን የማያውቅ ከሆነ አካል ጋር በመገናኘታቸው ብቻ ሰዎች
በቀላሉ የሚለከፉበት በሽታ ነው። "በዚህ ዘመን ወረርሽኝ ከመከሰቱ ጋር ግን መስጂድ
አልተዘጋም" ለሚሉ አካላት የምንጠይቃቸው በታሪክ ያለፉት ወረርሽኞች የዚህ አይነት
ለመሆናቸውስ መረጃ መጥቀስ ትችላላችሁን? ካልቻላችሁ ዝም በሉ።
– ሶስተኛ በሽታው በቀላሉ የሚቀጣጠልና ህዝብ የሚፈጅ እንደሆነ በተጨባጭ እየታየ
ነው። ሸሪዐችን ደግሞ ነፍስን እንድንጠብቅ፣ ጉዳት ወደሚያደርስ ነገር እራሳችንን
እንዳናስገባ፣ በተቻለ መጠን የሙስሊሞችን ነፍስ እንድናተርፍ የሚያሳስብ ነው። ማስረጃ
የማልጠቅሰው ሐቁ ለማንም እንደማይሰወር በማሰብ ነው። ስለዚህ የበሽታው ቀዳሚ
መተላለፊያ የሰዎች መሰባሰብ ከሆነ የሙስሊሞችን ህይወት ለመጠበቅ ሲባል ይህንን
ሰበብ ለማድረስ በጊዜያዊነት መስጂድ መዝጋቱ የሚወደስ እንጂ የሚነቀፍ አልነበረም።
ሸሪዐችንኮ ህይወትን ለሚያሰጋ አደጋ ቀርቶ ለዝናብ እንኳን ዑዝር የሚሰጥ ነው።
# ብዥታ_አራት :– “አላህ በላውን እንዲያነሳው ወደ መስጂዶች መሄድ እንጂ መዝጋት
መፍትሔ አይደለም” ያሉም አሉ።
ይሄ በየዋህነት ስናየው ጤነኛ የሚመስል ግን የሚገርም የሆነ እይታ ነው። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ
ዐለይሂ ወሰለ፞ም ልክ ከአንበሳ እንደምንሸሸው ተላላፊ በሽታ ካለበት ሰው እንድንሸሽ
አልነገሩንም?! በሽተኛ እንስሶች ያሉት ከጤነኞች ጋር እንዳያቀላቅል አላተናገሩም?
“በአንድ ሃገር ወረርሺኝ መግባቱን ከሰማችሁ ወደሷ አትግቡ። ባላችሁበት ሃገር ከተከሰተ
ከሷ አትውጡ” አላሉም? ስጋ ደዌ ያለበትን ሰው "እኛ ቃል ስለተጋባንህ ተመለስ!"
አላሉትም? እነዚህ ማስረጃዎች ምንድነው የሚያመላክቱት? አላህ ለሁሉም ነገር ሰበብ
አድርጓል። ከበሽታዎችም ንክኪን መተላለፊያ መንገድ ያደረገባቸው አሉ። በዚህ የተነሳ
ከንክኪ እያስጠነቀቁን ነው ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም። ተላላፊ በሽታ ያለበትን ሰው
አላህ እንዲያነሳልህ "ወደ መስጂድ ሽሽ" አላሉትም። ይልቁንም ከመቀላቀል ነው ያገዱት።
የዑለማዎችም አቋም ይሄው ነው።
# ብዥታ_አምስት :– “በሽተኛው ብቻ ይቅር እንጂ ሌሎች ላይ ለምን መስጂድ ይዘጋል?”
የሚሉም አሉ።
ለዚህ የምንለው በመጀመሪያ ስለ በሽታው ባህሪ በቂ ግንዛቤ እንያዝ ነው። ይሄ በሽታኮ
ቫይረሱ ያለበት ሰው የህመም ምልክት ሳይታይበት ለሳምንታት ሁሉ ሊቆይ ይችላል።
መታመማቸውን ያላወቁ ሰዎች ከሌሎች ጋር እየተቀላቀሉ እኮ ነው በሽታው ዛሬ የደረሰበት
የደረሰው። ጣልያንኮ ከ2 ሰው ተነስቶ ነው 80 ሺን የተሻገረው። በኢራን፣ ማሌዥያ፣
ፓኪስታን፣ ሲንጋፖር፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢንዶኔዥያ ፣ ብሩኔይ፣ … በሽታው በምን
ምክንያት እንደተሰራጨ መረጃ አገላብጡ። ከመስጂዶች፣ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከሺዐ የዶሪሕ
(መቃብር) አምልኮ ስብሰባ በኋላ ነው የተስፋፋው። የኢራኑ ወረርሽኝ ዋና ማእከል በቀብር
አምልኮ ህዝብ የሚጨናነቅባት የቁም ከተማ ነች። ማለት የፈለግኩት ሰዎች
መታመማቸውን ሳያውቁ ስለሆነ ወደ ሌሎች የሚያስተላልፉት “በሽተኛው ብቻ ነው
መታገድ ያለበት” የሚለው ሙግት ውሃ አያነሳም። ያለው መፍትሔ ህዝብ ከሚያልቅ አላህ
ፈረጃውን እስከሚያመጣ በጊዜያዊነት መስጂዶችን መዝጋት ነው።
ምናልባት አንዳንዶች “እየሰገድን እንሙት። መስጂዳችንን አትንኩ” ሊሉ ይችላሉ።
መስጂድ የለይቶ ማከሚያ ቦታ (ኳረንታይን) አይደለም። ከመስጂድ ወጥታችሁ ከቤተሰብ፣
ከህዝብ ጋር ስትቀላቀሉ ጣጣችሁ ለህዝብ ይተርፋል። ማሌዥያ ውስጥ ከተካሄደ
የተብሊግ ስብሰባ በኋላ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ለምሳሌ ቫይረሱ ወደ ቡሩኔይ የገባው በዚህ ስብሰባ ላይ በተካፈሉ ሰዎች አማካኝነት
ነው። ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በአንዲት ሴት ሰበብ እንዴት እንደተሰራጨ መረጃ አገላብጡ።
በጣም ጥቂት የነበረው ተጠቂ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት የተሰራጨው ይህቺ
ሴት ቤተ ክርስቲያን ገብታ በማስተላለፏ የተነሳ ነው።
በነገራችን ላይ የኢስላም ሊቃውንት ከህመምተኞችም ባለፈ የመታመም ስጋት ያለባቸውም
ሰዎች ከጀማዐ መቅረት እንደሚችሉ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያክል ዐላኡዲን አቡል ሐሰን
አልመርዳዊይ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ:
" ﻭﻳُﻌﺬﺭ ﻓﻲ ﺗﺮﻙ ﺍﻟﺠﻤﻌﺔِ ﻭﺍﻟﺠﻤﺎﻋﺔِ ﺍﻟﻤﺮﻳﺾُ ﺑﻼ ﻧِﺰﺍﻉٍ، ﻭﻳُﻌﺬَﺭ ﺃَﻳﻀًﺎ ﻓﻲ ﺗﺮﻛﻬﻤﺎ ﻟﺨَﻮﻑِ ﺣُﺪﻭﺙِ
ﺍﻟﻤﺮﺽ "
“ህመምተኛ ሰው ያለ ንትርክ ጁሙዐንና ጀማዐን የመተው ፈቃድ አለው። ልክ እንዲሁ
የህመም መከሰትን የሚሰጋም ሰው ሊተዋቸው ይፈቀድለታል።” [አልኢንሷፍ አዲ መዕሪፈቲ
ራ፞ጂሕ ሚነል ኺላፍ: 4/464]
ይህንን ያዙና አሁን ያለንበትን ሁኔታ በውል አጢኑ። ስጋቱ ለማንም እንደማይሰወረው ድፍን
ህዝብን የሚያሰጋ ነው። የትኛውም መሰባሰብ እንዳለ ለህዝብ ደህንነት አስጊ እየሆነ ነው።
እዚህ ላይ "ላ ዶረረ ወላ ዲራር" የሚለውን ሐዲሥ አስታውሱ። ለሐዲሡ ከተሰጡት
ትንታኔዎች አንዱ “ሆን ብሎ መጉዳትም ሆነ መጉዳትን ሳያስቡ ጉዳት ማድረስም
አይቻልም” የሚል ነው። ለሶላት መሰባሰቡ ደግሞ ታስቦበት ባይሆን እንኳ ሌሎች ላይ አደጋ
ይደቅናል። ይሄ ስሜት ካልታከለበት በስተቀር በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው ሰው በቀላሉ
የሚገነዘበው ነው።
መሰባሰብ ለቫይረሱ ስርጭት ቀዳሚ መንገድ ስለሆነም ነው በርካታ ሃገራት ኢኮኖሚያቸው
እየተሽመደመደም ሙሉ የሰው እንቅስቃሴ የዘጉት። በረራ በአብዛኛው ሃገራት ቆሟል።
ህንድ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊየን ዜጎቿን ከቤት እንዳይወጡ ከልክላለች። አሜሪካ አርባ
ሚሊየን ዜጎቿን ከቤት እንዳይወጡ ካገደች ሰነባበተች። አሁን ላይ ከዚህም በላይ ያሰፋች
ይመስለኛል። ሃገራት ክልከላውን በሚተላለፉ ዜጎቻቸው ላይ በእስራት፣ በከፍተኛ የገንዘብ
ቅጣት፣ በፖሊስ ድብደባ ጭምር እርምጃ እየወሰዱ ነው። እንዲያውም ሩዋንዳ ውስጥ
ፖሊስ አልታዘዝ ያሉ ወጣቶችን እስከ መግደል ደርሷል።
# ብዥታ_ስድስት :– "ከዚህ በተለየ መስጂዶች እንዳይዘጉ ፈትዋ የሰጡ ዓሊሞች" አሉ
ከተባለ:–
በጣም ጥቂት ዓሊሞች የተለየ ፈትዋ ቢሰጡም ነገር ግን ከፊሎቹ እንደተሳሳቱ አምነው
ተመልሰዋል። ከፊሎቹ የቫይረሱ የስርጭት አድማስ ከመጨመሩና የታላላቅ ዑለማዎች
ምክር ቤት ፈትዋ ከመውጣቱ በፊት ስለሆነ ዑዝር ሊኖራቸው ይችላል። ከፊሎቹ ላይ
በሌሎች ዓሊሞች ብርቱ ሂስ ተሰንዝሮባቸዋል።
በነገራችን ላይ ለብዙዎች እንደማይሰወረው በአለም ዙሪያ ይህ ሀሉ ሟች በአጭር ጊዜ
እንደቅጠል የረገፈው፣ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የታመመው የሞት ሺረት ትግል እየተካሄደ፣
ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ከመሆኑ ጋር ነው። ነገር ግን የሙስሊም ሃገራት የአንዳንዶችን
ፍላጎት ተከትለው መስጂዶችን ቢከፍቱ ችግሩ የት ሊደርስ እንደሚችል አስቡት። እንዲህ
አይነቱን መዘናጋት የተወኩል ካባ እያለበሱ ማቅረብ እራስን ከማታለል ባለፈ ሸሪዐን ለአጉል
ጀብደኝነት መጠቀም ነው።
ማጠቃለያ
~~~~~
ሁላችንም እንደምናስተውለው በሽታው በአንድና ሁለት ሃገር ላይ የተወሰነ ሳይሆን አለምን
እያናጋ ያለ ሙሲባ ነው። ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ከገባም ሰነባበተ። እንዲያውም ከዋና
ከተማ ወጥቶም ወደ ክልል ከተሞች እየተሻገረ ይመስላል። በዚያ ላይ የሃገራችን አቅም
ደካማ በመሆኑ ሰፊ ምርመራ አልተደረገም እንጂ ችግሩ አሁን ላይ ሪፖርት ከሚደረገው
እንደሚብስ ይጠበቃል። ለምርመራና ለለይቶ ማከም ጥሩ እይታ የሌለው ወገን መኖሩም
ይበልጥ ነገሩን ያውሰበስበዋል። ስለዚህ ስጋቱ ከሌላቸው አካባቢዎች በስተቀር ችግሩ
ተመሳሳይ በሆነበት የምናምናቸውን ታላላቅ ዑለማዎች ፈትዋ የማንወስድበት ምንም
ምክንያት አይኖርም። እንዲያውም የኛ ሃገር ነባራዊ ሁኔታ የጀማዐ እግድ ከወጣባቸው 
ሃገራት የሚሻል አይደለም። ምክንያቱም:–
– የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በትክክል ማወቅ አይቻልም።
– በኖሯችን ደካማነት የተነሳ አብዛኛው ህዝብ በአንድና በሁለት ክፍል ውስጥ ሰፊ ቤተሰብ
በጋራ ነው የሚኖረው።
እነዚህ ምክንያቶች ለበሽታው ስርጭት መባባስ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይታመናል።
– ታማሚዎችን የምናክምበት በቂ አቅምና ዝግጅት የለንም።
የበሽታው ባህሪና አደጋ በተጨባጭ የሚታይ ስለሆነ እነዚህ ነገሮች መላምት አይደሉም።

ወላሁ አዕለም (ኢብኑ ሙነወር)

@IbnuMunewor

Post a Comment

0 Comments