Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ባልሽ ጀነትሽም እሳትሽም ነው!

ባልሽ ጀነትሽም እሳትሽም ነው!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
አንቺ የአላህ ባሪያ! አንዳንዴ ባርነትሽን ትዘነጊያለሽ ልበል? ባሪያ ለጌታው አጎብዳጅ መሆን እንዳለበት ለአፍታ አይሰወርሽ። ደግሞም ባርነትሽ ለሃያሉ ጌታ ነውና የሚያስፈነድቅ እንጂ የሚያሸማቅቅ አይደለም። ባይሆን ለጌታሽ እደሪ። ጌታሽ ከጣለብሽ ሐቅ አንዱ ለባልሽ ታዛዥ መሆን ነው። እወቂ! ባልሽን መታዘዝ ጌታሽን መታዘዝ ነው። ባልሽ ላይ ማመፅሽ ደግሞ ጌታሽ ላይ ማመፅ ነው። ይሄ ሐቅ ይህን ያክል ክብደት እንዳለው አስተውለሽዋል? ስለዚህ ባልሽ ጀነትሽም እሳትሽም ነው። ያሰኘሽን ማንሳት ላንቺ የተተወ ምርጫ ነው። ይህንን ሐዲሥ ተመልከቺና እራስሽን ታዘቢ:–
አንዲት ሴት ከነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም ዘንድ መጣች። ጉዳዩዋን ስታጠናቅቅ
"ባል አለሽ ወይ?" ብለው ጠየቋት።
"አዎ" አለች።
"እንዴት ነሽ ለሱ?"
"የሚያቅተኝን ካልሆነ በስተቀር ምንም አላጓድልበትም" አለች።
በዚህም ጊዜ እንዲህ አሏት:–
"فانظري أين أنت منه فإنما هو جنتك ونارك"
"ከሱ አንፃር የት እንደሆንሽ ተመልከቺ። ምክንያቱም እርሱ ጀነትሽም እሳትሽም ነውና!!"
አልባኒ "ሶሒሕ" ብለውታል። [ሶሒሑ ተ፞ርጊብ ወተ፞ርሂብ፡ 1933]
ምን እያሉ እንደሆነ ገብቶሻል። ጀነትን ከፈለግሽ ሐቁን ጠብቂ። ካልሆነ ግን እሳትን መርጠሻል እያሉ ነው። በይ አሁን ከባልሽ ዘንድ ያለሽን ቦታ ፈትሺ። እሱን ሳይሆን፣ እራስሽን ጠይቂ። ለራስሽ ታማኝ ሁኚና አነጋገርሽን፣ አያያዝሽን፣ አቀራረብሽን፣ አኗኗርሽን መዝኚ። የሚበጅሽን ለራስሽ ምረጪ።
ለአስተውሎት ይረዳሽ ዘንድ ይህንንም ሐዲሥ ደጋግመሽ አስተንትኚው:–
"لا يحل للمرأة أن تصوم وزوجها شاهد إلا بإذنه"
"ለአንዲት ሴት ባሏ እያለ ያለ ፈቃዱ ልትፆም አይፈቀድላትም።" [ቡኻሪ: 4899]

የዚህ ሐዲሥ መልእክት ምን ያክል ተገልጦልሻል? ምን ያክልስ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኝነት አሳይተሻል? የባልሽን ሐቅ በአግባቡ ሳትጠብቂ ትርፍ የሆኑ ዒባዳዎችን በመፈፀም ወደ ጌታሽ እቃረባለሁ ብለሽ አትድከሚ። ከዚህ ይልቅ የባልሽን ፍላጎት ማሟላት ይቀድማል እያሉሽ ነው። የሱን ፍላጎት ማስቀደሙ በላጭ ዒባዳ ነው እያሉሽ ነው። የባሏን ሐቅ ገፍታ በዒባዳ የምትባዝን ሴት አክሳሪ ንግድ ውስጥ የምትዳክር የዋህ ናት። የባሏን ሐቅ የምትጋፋው በዒባዳ ሳይሆን በስንፍና ሲሆንስ? በአልባሌ ነገር ሲሆንስ? በሐራም ነገር ሲሆንስ? አላ፞ሁል ሙስተዓን!!
ባልሽን መታዘዝ ያለውን ዋጋ ታስተውይ ዘንድ ይህንን ሐዲሥ በሚገባ አጢኝውማ። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ይላሉ:–
"إذا صلت المرأة خمسها و صامت شهرها و حصنت فرجها و أطاعت زوجها قيل لها : ادخلي الجنة من أي أبواب الجنة شئت"
"አንዲት ሴት:–
* አምስቷን (የአምስት ወቅት ሶላቷን) ከሰገደች፣
* ወሯን (ረመዳንን) ከፆመች፣
* ብልቷን (ከሐራም) ከጠበቀች፣
* ባሏን ከታዘዘች
ከጀነት በሮች በፈለግሺው በኩል ግቢ ትባላለች!"
[ሶሒሑል ጃሚዕ: 660]
ባልን መታዘዝ ከምን አይነት ትእዛዛት ጋር እንደተቆጠረ አየሺው? የተዘጋጀውን ሽልማት? ከዚያ አንቺ ከነዚህ ትእዛዛት አንፃር የት እንዳለሽ እራስሽን ጠይቂ።
እህቴ ሆይ! ከባልሽ ጋር ሂሳብ አታወራርጂ። "እሱን እንዲህ እያረገ እኔስ…?" አትበይ! ሂሳብሽ ከጌታሽ ጋር ነው። እሱን የምትታዘዢው ጌታሽን ለመታዘዝ ነው። አንዳንድ እህቶች ግን የምእራባውያን ጩኸት ሽውታ መቷቸዋል። ከአንደበታቸው ባይወጣ እንኳን ከባላቸው ጋር ያላቸው አቀራረብ በሂሳብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ይታያል። ይሄ ግልፅ ስህተት ነው። እህቴ ሆይ! በቅድሚያ በሚገባ ልታሰምሪበት የሚገባ ነገር ቢኖር ባልሽን መታዘዝ ጌታችን መታዘዝ መሆኑ ነው። አትጠራጠሪ! የባልሽን ሐቅ ሳትጠብቂ የጌታሽን ሐቅ አትጠብቂም። ይህን የምለው ከራሴ አይደለም። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–
فإني لو كنت آمرا أحدا أن يسجد لغير الله لأمرت المرأة أن تسجد لزوجها والذي نفس محمد بيده لا تؤدي المرأة حق ربها حتى تؤدي حق زوجها ولو سألها نفسها وهي على قتب لم تمنعه"
"እኔ አንድ ሰው ከአላህ ሌላ ላለ አካል እንዲሰግድ የማዝ ብሆን ኖሮ ሴትን ለባሏ እንድትሰግድ አዝ ነበር። የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ይሁንብኝ! አብዲት ሴት የባሏን ሐቅ ሳትወጣ የጌታዋን ሐቅ አትወጣም። በ‘ቀተብ’ ላይ ሆና እንኳን (ለግንኙነት) ቢጠይቃት አትከለክለውም።"
‘ቀተብ’ ማለት እንደ ኮርቻ ወይም አናቦ ያለ አነስተኛ ለመጫኛነት የሚያገለግል ግመል ላይ የሚቀመጥ ነገር ነው። መልእክቱ ሊኖር የሚገባውን የታዛዥነት መጠን ማመላከት ነው።
ሐዲሡን ሸይኹል አልባኒ ረሒመሁላህ ሶሒሕ ብለውታል።
https://t.me/IbnuMunewor

Post a Comment

1 Comments