Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የመስጂዶች ቃጠሎ ትዝብትና ጥቆማ





*** የመስጂዶች ቃጠሎ ***
*** ትዝብትና ጥቆማ ***
=====================
የዓለማችንን የኑሮ መዘውር ፈር ለማስያዝና ስርዓት-አልበኝነተን ለመታደግ በዋነኝነት ተፅእኖ የሚያሳድሩት ገደቦች ሶስት ናቸው:-
1- የእምነትና የስነምግባር እነፃ
2- የህግ ቁጥጥርና የቅጣት ፍራቻ
3- ገንዘብና የጥቅም ተስፋ
አንዳንዶች በእምነት፣ በእውቀትና በስነምግባር የተገሩ ይሆናሉ፤ ሌሎች በህግ ቁጥጥርና በቅጣት ካልሆነ አይበገሩ ይሆናል፤ ሌሎች ደግሞ ጥቅምና የጥቅም ተስፋ እንጂ አይገዛቸውም፤ የተቀሩት እንደየሁኔታው በሶስቱ መደቦች መሃል ይመላለሳሉ።
አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ብሏል፦
((لَقَدۡ أَرۡسَلۡنَا رُسُلَنَا بِٱلۡبَيِّنَٰتِ وَأَنزَلۡنَا مَعَهُمُ ٱلۡكِتَٰبَ وَٱلۡمِيزَانَ لِيَقُومَ ٱلنَّاسُ بِٱلۡقِسۡطِۖ وَأَنزَلۡنَا ٱلۡحَدِيدَ فِيهِ بَأۡسٞ شَدِيدٞ وَمَنَٰفِعُ لِلنَّاسِ))
«ሰዎች በፍትህ ላይ ይቆሙ ዘንድ መልክተኞቻችንን በርግጥ በግልፅ ማስረጃዎች ልከናል፤ ከነርሱም ጋር መፅሀፍንና ሚዛንን አውርደናል፤ ብርቱ ሃይልና ለሰዎችም ጥቅሞች ያሉበትን ብረትም አውርደናል..» [ሱረቱ'ል-ሐዲድ 25]
🗝 ጥያቄው፦
#መስጂዶችን_እያቃጠሉ_ከሚጨፍሩ_መንጋዎች_ጋር ስለ አገር፣ ስለ ብልፅግና፣ ስለ መቻቻል #በየትኛው_ቋንቋ_መወያየት_ይቻላል?!
ለማንኛውም፦
❶ አዋቂዎችና የአገር ሽማግሌዎች በመጀመሪያው ነጥብ ዙሪያ (የእምነትና የስነምግባር እነፃ) ጥረታቸውን ያነባብሩ፤ ምንም እንኳ ይህን ቋንቋ ዋልጌዎች ባይገነዘቡትም ተሰሚነት ያላቸው ክርስቲያን ወገኖች በመስጂዶች ላይ የተሰነዘሩትን ጥቃቶች በግልፅ ቃና ሊያወግዙ ይገባል፤ አልፎም ውሸቶችን እያቀናበሩና እያሰራጩ ሙስሊም-ጠልነትን የሚዘሩና የተዘራውን ብቅል ተንከባክበው የሚያሳድጉ ሰባኪዎቻቸውን ያለምንም ጭፍን ወገንተኝነት አንድ ይበሉልን። ካልሆነ ግን ለሰላም መደፍረስ፣ ለአገር መፍረስ፣ ለደም መፍሰስ.. በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ ማበርከት ይሆናል።
ከዚህ በፊት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ቃጠሎ ከደረሰ ትክክለኛው አመክንዮ ጥፋተኞችን ለይቶ በሰለጠነ ሂደት ለቅጣት ማብቃት ሲሆን መስጂዶችን በአፀፋ ማቃጠል የኋላ ቀርነት የመጨረሻው ፉርጎ ላይ መንጠላጠል ነው፤ ተሰሚነት ያላቸው "አዋቂ" ተብዬዎች ይህንን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሲደግፉ አይተናል፤ ሰምተናል። ይህ የአዋቂዎቻችሁ መገለጫ ከሆነ የአላዋቂዎቻችሁ ተግባር ምን ሊሆን ነው?!
❷ መንግስት ደግሞ የጥፋቱ ተሳታፊዎችንና አነሳሾችን መቀጣጫ በማድረግ ሁለተኛውን ነጥብ ቢያስፈፅም ብዙ የመፍትሄ እርምጃዎችን መሄድ ይቻል ነበር፤ ይህ እንደተለመደው ሲያልፍ የሚረጋጋ ጊዜያዊ "ሁከት"፣ "ግጭት" ወይም "አደጋ" እንደሆነ በሚዲያ እየተገለፀ በዋዛ መታለፉ ወደ ፊት ብዙ ዋጋን ያስከፍላል። ጉዳዩ የበዳይና የተበዳይ ነው፤ ጉዳዩ በዘር ፖለቲካ እየታገዘ፣ በህቡእ ስብሰባ እየተዶለተ የሚፈፀም የታቀደ ጥቃት እንጂ ሌላ አይደለም። ስለሆነም ችግሩን ከመሰረቱ ነቅሎ መጣል የሚቻለው መዋቅር ነድፎ በትጋት መስራት ሲቻል ነው።
ይህም የሚጀምረው ከቤተ መንግስቱ እስከ ቀበሌና ፖሊስ ጣቢያ በመንግስት የአፈፃፀም እርከኖች ውስጥ ተስግስገው ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ህዝብን ከህዝብ የሚያባሉ አሜኬላዎች ተመንጥረው የሚወጡበትን ብልሃት በመቀየስ ነው።
የጎበጠውን ሲያቃኑ አንዳንዴ መሰበር ሊኖር ይችላል።
የማይበርድ ግንፍልተኝነት ካልተመከተ፣ የማይከስም እብሪት በልኩ ካልቆመ፣ የሰው አረም ካልተመነጠረ፣ የማያርፍ እጅ ካልተቆርጠ …ወጤቱ አሁን ካለንበት ተጨባጭ የባሰ ይሆናል።
((وَلَوۡلَا دَفۡعُ ٱللَّهِ ٱلنَّاسَ بَعۡضَهُم بِبَعۡضٖ لَّهُدِّمَتۡ صَوَٰمِعُ وَبِيَعٞ وَصَلَوَٰتٞ وَمَسَٰجِدُ يُذۡكَرُ فِيهَا ٱسۡمُ ٱللَّهِ كَثِيرٗاۗ وَلَيَنصُرَنَّ ٱللَّهُ مَن يَنصُرُهُۥٓۚ إِنَّ ٱللَّهَ لَقَوِيٌّ عَزِيزٌ))
{አላህ ሰዎችን ከፊላቸውን በከፊሉ መግፋቱ ባይኖር ገዳማት፣ ቤተ ክህነቶች፣ ምኩራቦችና የአላህ ስም በብዛት የሚወሳባቸው መስጂዶችም በተፈርሱ ነበር፤ አላህ (ሀይማኖቱን) የሚረዳውን ይረዳዋል፤ አላህ በርግጥ ብርቱ እና ሃያል ነው።} [ሱረቱ'ል-ሐጅ 40]
ይህ አንቀፅ ከሚያስገነዝባቸው በርካታ ፍሬ ነገሮች ሁለቱን መጥቀስ እሻለሁ፦
1ኛ፦ አላህ በጥበቡ አንዱን ለሌላው መድሀኒት ያደርገዋልና የከፊሉን እብሪት በከፊሉ ያበርደዋል፤ የአንዱን ተንኮል በሌላው ያከስመዋል!
ይህንን ሚና ከማንም በፊት መንግስት ቢወጣው ሌሎች ችግሩን የሚያባብሱ አፀፋዊ እርምጃዎች እንዳይከሰቱ ያደርጋል!
2ኛ፦ አንቀፁ መስጂዶች ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች ነብያት "ተከታዮች" ቤተ እምነቶችም መፍረሳቸው የሚወገዝ መሆኑን እንደሚያመላክት ብዙ ሊቃውንት ያወሳሉ።
የእኛ ኢስላም በጦርነት ጊዜም ቤተ አምልኮን ማፍረስን ይከለክላል። በኢስላም ህግ ስር ለምእተ አመታት ሲተዳደሩ በቆዩ ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናት ሳይነኩ ተትተዋል፤ ይህም የታላቁን መልእክተኛ ፈለግ የተከተለ ስነ ምግባር ነው።
- መልእተኛችን በኑ'ል-ሓሪሥ ኢብን ከዕብ ለሚሰኙት ጎሳዎችና ለነጅራን ተጠሪ ጳጳሳት፣ ካህናትና መነኩሴዎች እንዲሁም በስሮቻቸው ላሉት ተከታዮች ያፃፉት ቃል ኪዳን ከፊል ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል፦
(( أَنَّ لَهُمْ مَا تَحْتَ أَيْدِيهِمْ مِنْ قَلِيلٍ وَكَثِيرٍ مِنْ بِيَعِهِمْ وَصَلَوَاتِهِمْ وَرَهْبَانِيَّتِهِمْ، وَجوَارُ اللَّهِ وَرَسُولِهِ: أَلَّا يُغَيَّرَ أَسْقُفٌ عَنْ أَسْقُفِيَّتِهِ، وَلَا رَاهِبٌ عَنْ رَهْبَانِيَّتِهِ، وَلَا كَاهِنٌ عَنْ كَهَانَتِهِ، وَلَا يُغَيَّرَ حَقٌّ مِنْ حُقُوقِهِمْ، وَلَا سُلْطَانِهِمْ وَلَا شَيْء مِمَّا كَانُوا عَلَيْهِ مَا نَصَحُوا وَأَصْلَحُوا فِيمَا عَلَيْهِمْ غَيْرَ مُثْقَلينَ بِظُلْمٍ وَلَا ظَالِمِينَ))
«ለነርሱ በእጃቸው ያሉት ቤተ ክህነቶች፣ ምኩራቦችና ገዳማት ጥቂትም ይሁኑ ብዙ አላልቸው፤ እንዲሁም ጳጳስ ከጵጵስናው፣ መነኩሴም ከምንኩስናው፣ ካህንም ከካህንነቱ እንዳይነሳ፤ ከመብታቸውም ይሁን ከስልጣናቸው እንዲሁም ከነበሩበትም ሁኔታ ምንም ነገር እንዳይቀየር ቅን ሆነው ያለባቸውን (ግዴታ) አሳምረው እስከተወጡ ድረስ በደል ሳይጫንባቸውና ሳይበድሉ እንዲኖሩ የአላህና የመልእክተኛው ከለላ አልላቸው…»
["አጥ-ጦበቃት አል-ኩብራ" - ኢብን ሰዕድ - (1/266)፣ "አል-አምዋል" - አቡ ዑበይድ - (244) እና ሌሎችም የዘገቡት ነው።]
- እንደዚሁም ታላቁ ኸሊፋ ዑመር ኢብኑ'ል-ኸጥ-ጧብ በ 15ኛው አመተ-ሂጅራ ለእየሩሳሌም ነዋሪዎች የፃፉት ቃል ኪዳንም የሚከተለውን ይመስላል፦
"بسم اللَّه الرحمن الرحيم، هذا ما أعطى عبدُ اللَّهِ عمرُ أميرُ المؤمنين أهلَ إيلياء من الأمان: أعطاهم أمانا لأنفسهم وأموالهم، ولكنائسهم وصلبانهم، وسقيمها وبريئها وسائر ملتها: أنه لا تُسكن كنائسهم ولا تهدم، ولا ينتقص منها ولا من حيزها، ولا من صليبهم، ولا من شيء من أموالهم، ولا يكرهون على دينهم، ولا يضار أحد منهم.."
«በአላህ ስም፤ እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፤ ይህ የአላህ ባርያ ዑመር የሙእሚኖች መሪ ለእየሩሳሌም ነዋሪዎች የሰጠው የሰላም ዋስትና ነው፤ ለራሳቸው፣ ለንብረታቸው፣ ለአብያተ ክርስቲያናቸውና ለመስቀሎቻቸው፤ እንዲሁም ለበሽተኞቻቸውም ለጤነኞቻቸውም፣ ለሁሉም እምነት ተከታዮቻቸውም ዋስትና ሰጥቷቸዋል፦ ቤተ ክርስቲያኖቻቸው መኖሪያ እንዳይደረጉ፣ እንዳይፈርሱ፣ ከነርሱም ሆነ ከ(ግቢ) ይዞታቸው፣ እንዲሁም ከመስቀሎቻቸውና ከንብረታቸው ምንም ያህል እንዳይቀነስባቸው፣ በሃይማኖታቸው እንዳይገደዱ፣ አንዳቸውም ለጉዳት እንዳይዳረጉ…»
- ለሌሎችም ተመሳሳይ ዋስትና ፅፈዋል።
["ታሪኹ አጥ-ጦበሪይ" (3/609)]
- ኻሊድ ኢብኑ'ል-ወሊድም ለደማስቆ ነዋሪዎች ተመሳሳይ ቃልኪዳን ፅፎላቸዋል። ["ፉቱሑ'ል-ቡልዳን" - አል-በላዙሪ - (120)]
- እንዲሁም አቡ ዑበይዳህ ለበዕለበክ ነዋሪዎች ["ፉቱሑ'ል-ቡልዳን" (129)]፣
- ሹረሕቢል ኢብኑ ሐሰናህ ለጦበሪያ ሰዎች ["ፉቱሑ'ል-ቡልዳን" (115)]፣
- ዒያድ ኢብኑ ጉንም ለረቅ-ቀህ (ሰሜን ሶሪያ) ነዋሪዎች ["ፉቱሑ'ል-ቡልዳን" (172)]፣
- ሐቢብ ኢብን መስለማህ ለደቢል ነዋሪዎች ["ፉቱሑ'ል-ቡልዳን" (199)] ተመሳሳይ ዋስትናዎችን ፅፈዋል።
እነዚህ በሙሉ የመልእተኛው ሰሓቦች ናቸው።
- በተመሳሳይ መልኩ ታላቁ የሙስሊሞች መሪ ዑመር ኢብኑ ዐብዲ'ል-ዐዚዝ የሚከተለውን ትእዛዝ አስተላልፈዋል፦
«لاَ تُهْدَمُ بِيعَةٌ ، وَلاَ كَنِيسَةٌ ، وَلاَ بَيْتُ نَارٍ صُولِحُوا عَلَيْهِ»
«ገዳም፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ስምምነት የተደረገበት የእሳት ቤትም አይፈርስም» ["አል-ሙሶን-ነፍ" - ኢብኑ አቢ ሸይባህ - (17/513) ቁ. 33654፣ እንዲሁም "አል-አምዋል" - አቡ ዑበይድ - (123)]
- ብሎም በርሳቸው ዘመን ያለ አግባብ የተወሰደ አንድ ቤተ ክርቲያን አስመልሰዋል። ["አል-አምዋል" - አቡ ዑበይድ - (201)]
🗝 የኛ እምነት በጦርነት ጊዜ እንኳ ቤተ እምነቶችን ቀርቶ ተራ ግንባታዎችን ያለ አግባብ ማፍረስን ይከለክላል! ከመልዕክተኛው ህልፈት በኋላ የመጀመሪያው የሙስሊሞች መሪ የሆኑት ታላቁ ኸሊፋ አቡ በክር አስ-ሲድ-ዲቅ በአንድ አጋጣሚ የዚድ ኢብኑ አቢ ሱፍያንን ለዘመቻ ሲልኩት እንደሚከተው እንደመከሩት ተዘግቧል፦
".. وَإِنِّي مُوصِيكَ بِعَشْرٍ: لَا تَقْتُلَنَّ امْرَأَةً، وَلَا صَبِيًّا، وَلَا كَبِيرًا هَرِمًا، وَلَا تَقْطَعَنَّ شَجَرًا مُثْمِرًا، وَلَا تُخَرِّبَنَّ عَامِرًا، وَلَا تَعْقِرَنَّ شَاةً، وَلَا بَعِيرًا إِلَّا لِمَأْكَلَةٍ، وَلَا تَحْرِقَنَّ نخلا، وَلَا تُغَرِّقَنَّهُ، وَلَا تَغْلُلْ، وَلَا تَجْبُنْ "
«..አስር ነገሮችን አደራ እልሃለሁ፦ ሴትን፣ ህፃንንም፣ ያረጀ ሽማግሌንም እንዳትገድል፤ የሚያፈራ ዛፍን እንዳትቆርጥ፤ ግንባታዎችን እንዳታፈራርስ፤ በግን፣ ፍየልንና ግመልን በአግባቡ ለመብላት ካልሆነ በቀር እንዳታቆስል፤ የተምር ዘንባባን (አንዳንድ መዛግብት ላይ፦ የንብ ቀፎን..) እንዳታቃጥል፤ በውሃም እንዳታሰምጠው፤ የምርኮ ንብረትንም ሳይከፋፈል እንዳትወስድ፤ እንዳትፈራም!»
[አል-ኢማም ማሊክ - በ“አል-ሙወጥ-ጠእ” ቁጥር (1627) ላይ ከየሕያ ኢብን ሰዒድ አስተላልፈውታል፤ የዘገባው ሰነድ የተቋረጠ ቢሆንም በሌሎች ደጋፊ ምክንያቶች ይጠናከራል።]
- በሌላ ዘገባ ላይ፦ «ገዳማታንም አታፍርሱ!» የሚል ጭማሪ አለ። ["አስ-ሱነን አል-ኩብራ" - አል-በይሀቂይ - (18/284)፣ "ታሪኽ ዲመሽቅ" - ኢብኑ ዐሳኪር - (2/75)]
- አል-ኢማም አል-አውዛዒይ ይህን አስመልክቶ የሚከተለውን ብለዋል፦
وَنَهَى أَبُو بَكْرٍ الصِّدِّيقُ [يزيدَ] أَنْ يَقْطَعَ شَجَرًا مُثْمِرًا، أَوْ يُخَرِّبَ عَامِرًا، وَعَمِلَ بِذَلِكَ الْمُسْلِمُونَ بَعْدَهُ
«አቡ በክር አስ-ሲድ-ዲቅ የሚያፈራ ዛፍን እንዳይቆርጥና መኖሪያ ግንባታን እንዳያፈራርስ [የዚድን] ከልክለዋል፤ ሙስሊሞችም ከርሳቸው በኋላ ይህንን (መመሪያ) ተግብረዋል።»
[ሱነኑ’ት-ቲርሚዚይ - አብዋቡ’ስ-ሲየር - ከቁጥር 1552 ቀጥሎ የሰፈረ ነው።]
በሌሎች የእምነት መፅሐፍ እንኳን ለግንባታ፤ ጭራሽ ለማይዋጉ ወንዶች፣ ሴቶች፣ አዛውንት፣ ህፃናት፣ እንስሳት እንዳይታዘን የሚያነሳሱ አናቅፅ እንዳሉ ከዚህ በፊት ምሳሌዎችን ዘርዝሬያለሁ።
ያም ሆነ ይህ…
ሰላም በአንድ ወገን ጥረት አይሰፍንም፤ አንድ እጅ አያጨበጭብም፤ አንዱ የሚገነባውን እሴት ሌላው የሚያፈርስ ሲሆን የአገር ግንባታው ይሰናከናል!
❸ ሁለቱ ( 1/ የእምነትና የመልካም ስነ ምግባር እነፃ፣ 2/ የህግ ቁጥጥርና ቅጣት) ከተሳኩ በኢኮኖሚው ምህዳር ላይ ወዳ ኋላ የሚጎትት አንድ ሳንካ በመቀነሱ ሶስተኛው ነጥብ (ገንዘብና የጥቅም ተስፋ) በከፊል ሊሟላ ስለሚችል የሶስቱ ገደቦች ጥምረት ፍሬ ሊያፈራ ይችላል።
=====
ባጭሩ፦
የጥላቻ ሰባኪዮች ባቀጣጠሉት እሳት ህዝቡ መጠበስ የለበትም፤
በመንግስት ቸልተኝነት ሙስሊሙ ዋጋ ሊከፍል አይገባም፤
በመሃይማን ትዕቢት አገር ሲፈርስ ማየት አንሻም፤
=====
በመጨረሻም በደረሰብን ታላቅ በደል ብንቆጣም፣ ውስጣችን ከመስጂዶቻችን ጋር አብሮ ቢቃጠልም፤ ችግሩን ከማባባስ ባልዘለለ መፍትሄ ሊሆኑ የማይችሉ ግላዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ በመቆጠብ በአብሮነት በመወያየት ዘላቂነት ያላቸውን መፍትሄዎች መቀየስ ይኖርብናል።
- አንዱ የሙእሚን መሳሪያ ዱዓ ነው!
- ሰብር ጋሻ ነው፤
- አላህን መፍራት የድል መንገድ ነው፤
((وَإِن تَصۡبِرُواْ وَتَتَّقُواْ لَا يَضُرُّكُمۡ كَيۡدُهُمۡ شَيۡـًٔاۗ إِنَّ ٱللَّهَ بِمَا يَعۡمَلُونَ مُحِيطٞ))
{ብትታገሱና (አላህን) ብትጠነቀቁ ሴራቸው ምንም አይጎዳችሁም፤ አላህ የሚሰሩትን ሁሉ የሚያካብብ ነው!} [ሱረቱ ኣሊ ዒምራን 120]
والسلام!
====
🖌 አቡ ሑነይፍ፤ ኢልያስ



አድራሻዎቻችን ይቀላቀሉ

ፌስቡክ           ቴሌግራም         ዩቲዩብ

Post a Comment

0 Comments