Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሶሐቦች የማያውቁት ዒባዳ ዒባዳ አይደለም!


ሶሐቦች የማያውቁት ዒባዳ ዒባዳ አይደለም!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
በየትኛውም የቢድዐ መስመር ላይ የሚገኝ አካል በሶሐቦች ግንዛቤ ሲሞገት ሁሌም ምቾት አይሰጠውም። ምክንያቱም ቁርኣንና ሐዲሥን እንዳሰኘው እየጠመዘዘና እየለጠጠ ነገር ሊያስረዝም ሲጣጣር በሶሐቦቹና በሰለፎቹ ግንዛቤ ተወጥሮ ሲያዝ መፈናፈኛ አያገኝም። በዚህም ሳቢያ በዚህ መልኩ ሲፋጠጡ በቅድሚያ የሚያደርጉት ይህን የቀደምቶች ግንዛቤን እራሱን ከውይይት ጠረንጴዛ ላይ እንዲወርድ መታገል ነው። ለዚህም ነው “ሰለፎች ያልሰሩት ነገር ቢድዐ ነው የምትለዋ ትምህርት ከየትኛው የቁርኣን ወይም የሐዲሥ ዘገባ የመነጨች ናት?” እያሉ ልብ የሚያወልቁት።
አዎ ሰለፎች ያልሰሩትን አምልኮ ኢስላም አያውቀውም። ሶሐቦች የማያውቁት ኢስላም አለ እንዴ? ኢስላም ማለት እኮ ከነብዩ ﷺ ወደ ሶሐቦች፣ ከሶሐቦች ወደ ታቢዒዮች፣ ከታቢዒዮች ወደ መልካም ተከታዮቻቸው የተላለፈ ሃይማኖት እንጂ ማንም እየተነሳ የሚያሻሽለው ሰው ሰራሽ አስተምህሮት አይደለም። ስለዚህ እነዚያ ምርጥ ትውልዶች የማያውቁት ሃይማኖት ኢስላም አይደለም። እነዚያ ኢስላምን በቀጥታ ከመልእክተኛው ﷺ የተማሩ እንቁዎች የማያውቁት አምልኮ ዒባዳ አይደለም። ይልቁንም ቢድዐ ነው፤ ጥመት። ይሄ ሐቅ አእምሮውን ማሰራት ለሚሻ ሁሉ የሚሰወር ባይሆንም ጥቂት ማስረጃዎችን ላጣቅስ፡-

﴿ وَمَنْ يُشَاقِقِ الرَّسُولَ مِنْ بَعْدِ مَا تَبَيَّنَ لَهُ الْهُدَى وَيَتَّبِعْ غَيْرَ سَبِيلِ الْمُؤْمِنِينَ نُوَلِّهِ مَا تَوَلَّى وَنُصْلِهِ جَهَنَّمَ وَسَاءَتْ مَصِيرًا ﴾

{ቅኑ መንገድ ከተገለፀለት በኋላ መልእክተኛውን የሚፃረርና #የአማኞቹ_ያልሆነን_መንገድም_የሚከተል፣ በተሾመበት (ጥመት) ላይ እንሾመዋለን፤ ጀሀነምንም እንከተዋለን። መመለሻይቱም ከፋች!} [አኒ፞ሳእ፡ 115]
የደመቀውን ሀረግ በሚገባ ያጢኑት። ቁርኣኑ በወረደበት ዘመን የነበሩት አማኞች አይነታችን የበዛው እኛ ሳንሆን በተውሒድና በሱና የተሳሰሩት ሶሐቦቹ ብቻ ናቸው። በአንቀጿ ምስክርነት የሶሐቦች ያልሆነን መንገድ የሚከተል አስፈሪ አደጋ አለበት።
﴿ فَإِنْ آَمَنُوا بِمِثْلِ مَا آَمَنْتُمْ بِهِ فَقَدِ اهْتَدَوْا وَإِنْ تَوَلَّوْا فَإِنَّمَا هُمْ فِي شِقَاقٍ فَسَيَكْفِيكَهُمُ اللَّهُ وَهُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ ﴾

"በርሱ እናንተ ባመናችሁበት ብጤ ቢያምኑ በእርግጥ ተመሩ፞፡፡ ቢዞሩም እነርሱ በጭቅጭቅ ውስጥ ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱንም አላህ ይበቃሃል፤ እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው፡፡" [አልበቀራህ: 137]
"እናንተ" የተባሉት ቁርኣኑ ሲወርድ ሐዲሡ ሲነገር በአካል የነበሩት ሶሐብዮች ናቸው። ስለዚህ መዳን የፈለገ እነሱ ባመኑበት መልኩ ይመን።
③ “ከናንተ የሚኖር ብዙ ውዝግቦችን ያያል። ያኔ ባወቃችሁት ሱና፞ዬ እና ከኔ በኋላ ያሉ ቀጥተኛና የተቀኑ የሆኑ ምትኮቼንም ሱና፞ አደራችሁን” ይላሉ ነብዩ ﷺ። [አሶ፞ሒሐ፡ 937]
④ ሑዘይፋ ኢብኑል የማን ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡- “የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሶሐቦች አላህን ያላመለኩበትን እያንዳንዱን አምልኮት አላህን አታምልኩበት። የመጀመሪያዎቹ ለኋለኞቹ የተውት ዘርፍ የለምና። [አዙ፞ህድ፡ 47]
⑤ ዑመር ኢብኑ ዐብዲል ዐዚዝ እንዲህ ይላሉ፡- “ሰዎቹ (ሶሐቦች) ከቆሙበት ቁም። እነሱ ከእውቀት ነው የቆሙት። ከጥልቅ ግንዛቤም ነው የታቀቡት። በርግጥም እነሱ ከናንተ በበለጠ እሷን (መጤዋን) በመግለጥ ብርቱ ነበሩ። በሷም ላይ ትሩፋት ቢኖር ይበልጥ የተገቡ ነበሩ። ‘ከነሱ በኋላ ነው የተፈጠረው’ ካላችሁ መመሪያቸውን የጣሰ፣ ከሱናቸው የዞረ እንጂ አልፈጠረውም። ከእውቀት፡ የሚያረካን ግልፅ አድርገዋል። በቂ የሆነንም ተናግረዋል። ከነሱ በላይ የሚጥር ከንቱ ደካሚ ነው። ከነሱ ያሳጠረ ወደኋላ የቀረ ነው። የሆኑ ሰዎች ከነሱ ቀሩና ራቁ። ሌሎች ከነሱ አለፉና ፀነፉ። እነሱ ግን እዚህ መሀል ላይ ቀጥ ካለ ቅናቻ ላይ ናቸው።” [ሉምዐቱል ኢዕቲቃድ፡ 8-9]
⑥ አልኢማም አልአውዛዒ እንዲህ ይላሉ፡ “እራስህን በሱና ላይ አፅና። ሰዎቹ (ሶሐቦች) ከቆሙበትም ቁም። እነሱ ያሉትን በል። እነሱ ከታቀቡት ታቀብ። የመልካም ቀደምቶችህን መንገድ ተከተል። ለነሱ የበቃቸው ይበቃሀልና!!!” [ሸርሑ ኡሱሊ ኢዕቲቃዲ አህሊ ሱና፞ ወልጀማዐህ፣ ላለካኢይ: ቁ• 315]]
⑦ በድጋሚ አውዛዒ እንዲህ ብለዋል:– "የቀደምቶችን ቅሪት ያዝ አደራህን። የሰዎችን ግላዊ እይታዎች ተጠንቀቅ፣ በቃላት ቢያሸበርቁልህም እንኳን። አንተ በቀጥተኛው መስመር ላይ ከሆንክ ነገሩ ሲገለጥ ይገለጣል።" [አሸ፞ሪዐ: 63]
⑧ ኢማሙ ማሊክ፡- “የዚች ህዝብ ቀደምቶቿ ያልነበሩበትን የሆነን ነገር የፈጠረ በርግጥም የአላህ መልእክተኛ ﷺ ተልእኳቸው ላይ ሸፍጥ ሰርተዋል ብሎ ሞግቷል። ምክንያቱም አላህ {ዛሬ ለናንተ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ} ብሏልና። ያኔ ዲን ያልነበረ ነገር ዛሬ ዲን አይሆንም።” [አልኢዕቲሷም፡ 2/53]
ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ! ይሄ የኢማሙ ማሊክ ንግግር ለቢድዐህ አራጋቢዎች ከባድ መብረቅ ነው!
⑨ አሁንም ኢማሙ ማሊክ፡- “የዚች ህዝብ መጨረሻዋ አይስተካከልም፣ የመጀመሪያዋ በተስተካከለችበት ቢሆን እንጂ። ያኔ ዲን ያልነበረ ነገር ዛሬ ዲን አይሆንም።” ላሉ [ሐጀ፞ቱ ነ፞ቢይ፡ 103]
(10) ኢማሙ አሕመድ፡- “እኛ ዘንድ የሱና መሰረቶች የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሶሐቦች በነበሩበት አጥብቆ መያዝ፣ እነሱን መከተል፣ ቢድዐዎችን መተው ነው። እያንዳንዷ ቢድዐ ጥመት ነች” ይላሉ። [ኡሱሉ ሱ፞ና፞: 1]
①① ኢብኑ ከሢር፡- “አህሉ ሱና፞ ወልጀማዐ ግን እያንዳንዱን ከሶሐቦች ያልተገኘን ተግባርም ይሁን ንግግር ‘ቢድዐ ነው’ ይላሉ። ምክንያቱም በጎ ቢሆን ኖሮ ወደሱ ይቀድሙን ነበርና። ለምን ቢባል የመልካም ነገር ቀንዘል ሆኖ ሳይሽቀዳደሙበት የተውት የለምና።” [ተፍሲር ኢብኒ ከሢር፡ 7/256]


Ibnu Munewor 


አድራሻዎቻችን ይቀላቀሉ

ፌስቡክ           ቴሌግራም         ዩቲዩብ

Post a Comment

0 Comments