Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አስደማሚ ታሪክ ከኢብኑ መስዑድ ጋር


አስደማሚ ታሪክ ከኢብኑ መስዑድ ጋር
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
የቢድዐ ቆንጆ የለም። ነብዩ ﷺ “(በዲን ውስጥ) መጤ የሆኑ ነገሮችን ተጠንቀቁ። መጤ ፈሊጥ ሁሉ ፈጠራ ነው። ፈጠራ ሁሉ ጥመት ነው። ጥመት ሁሉ ወደ እሳት ነው” ማለታቸው የሚታወቅ ነው። [ኢርዋኡል ገሊል፡ 608] በየኹጥባውም ላይ እንዲህ ይሉ ነበር፡- “ከንግግር ሁሉ በላጩ የአላህ ንግግር ነው። ከመመሪያ ሁሉ በላጩ የሙሐመድ መመሪያ ነው። ከነገሮች መጥፎው አዲስ መጤው ነው። መጤ ነገር ቢድዐ ነው። ቢድዐ ሁሉ ጥመት ነው።” [ሙስሊም፡ 2042]
ስለዚህ ቢድዐ በጥሩ ኒያ ስለተፈፀመ ጥሩ አይሆንም። ጥሩ ኒያ መጥፎ ስራን ጥሩ አያደርግምና። “ቢድዐ ሁሉ ጥመት ነው! ሰዎች መልካም ነው ብለው ቢያስቡትም” የሚለው የሶሐባው ኢብኑ ዑመር ንግግር ይታወስ። አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል። [አሕካሙል ጀናኢዝ፡ 200] ስለሆነም ቢድዐ በጥሩ ኒያ ቢሰራም አያሸልምም። ይህንን አስደማሚ ታሪክ ያስተውሉ።
ዐምር ኢብኑ ሰለማህ እንዲህ ይላሉ፡- “ከሱብሕ ሶላት በፊት ከዐብዱላህ ኢብን መስዑድ በር እንቀመጥ ነበር። ሲወጣ አብረነው ወደ መስጂድ እንሄዳለን። አንድ ጊዜ አቡ ሙሳ አልአሽዐሪ ወደኛ መጣና ‘የአብዱርረሕማን አባት ወጥቷል?’ ሲል ጠየቀን። ‘አልወጣም’ አልነው። እስከሚወጣ ከኛ ጋር ተቀመጠ። ሲወጣ ጊዜ ሁላችንም ወደሱ ተነሳን።
አቡ ሙሳም፡- ‘የዐብዱረሕማን አባት ሆይ! እኔ አሁን መስጂድ ውስጥ የጠላሁት ነገር አይቻለሁ። ምስጋና ለአላህ ይሁንና መልካምን እንጂ አላሰብኩም’ አለ።
ኢብኑ መስዑድ፡- ‘ምንድን ነው እሱ?’ አለው።
አቡ ሙሳ፡- ‘ከኖርክ ታየዋለህ’ አለው። ቀጠለና ‘መስጂድ ውስጥ ክብ ክብ ሰርተው በመቀመጥ ሶላትን የሚጠባበቁ ሰዎችን አየሁ። በእያንዳንዱ ክብ ውስጥ አንድ ሰው አለ። በእጆቻቸው ጠጠሮችን ይዘዋል። ‘መቶ ጊዜ አላሁ አክበር በሉ’ ሲላቸው መቶ ጊዜ ‘አላሁ አክበር’ ይላሉ። ‘መቶ ጊዜ ላኢላሀ ኢለላህ በሉ’ ሲላቸው መቶ ጊዜ ‘ላኢላሀ ኢለላህ’ ይላሉ። ‘መቶ ጊዜ ሱብሓነላህ’ በሉ ሲላቸው መቶ ጊዜ ‘ሱብሓነላህ’ ይላሉ’ አለ።
ኢብኑ መስዑድ፡- ‘እናስ ምን አልካቸው?’ አለ።
አቡ ሙሳ፡- ‘ያንተን ሀሳብ እየጠበቅኩ ስለሆነ ምንም አላልኳቸውም’ አለ።
ኢብኑ መስዑድ፡- ‘ከመልካም ስራዎቻቸው ምንም እንደማይጠፋ ዋስትና ሰጥተህ ወንጀላቸውን እንዲቆጥሩ አታዛቸውም ነበር?’ አለ።
ከዚያም ተጓዘ። አብረነውም ተጓዝን። ከዚያም ከነዚህ ስብስቦች ውስጥ አንዱ ስብስብ ዘንድ ሄደና ካጠገባቸው ቆመ።
ኢብኑ መስዑድ፡- ‘ምንድን ነው ይሄ ስትሰሩት የማያችሁ?’ አላቸው።
እነሱ፡- ‘የዐብዱርረሕማን አባት ሆይ! አላሁ አክበር፣ ላኢላሀ ኢለላህ እና ሱብሓነላህ የሚሉትን ዚክሮች የምንቆጥርበት ጠጠር ነው’ አሉት።
ኢብኑ መስዑድ፡ ‘ይልቅ ወንጀላችሁን ቁጠሩ። ከመልካም ስራዎቻችሁ ምንም እንደማይጠፋ እኔ ዋስትና እወስዳለሁ። ወዮላችሁ እናንተ የሙሐመድ ህዝቦች ሆይ! ምነው ጥፋታችሁ ፈጠነ?! ይሄውና የነብያችሁ ﷺ ሶሐቦች በብዛት አሉ። ይሄውና የነብዩ ልብሶቻቸው አልበሰበሱም። እቃዎቻቸው አልተሰበሩም። ነፍሴ በእጁ በሆነችው እምላለሁ! ወይ እናንተ ከሙሐመድ ሃይማኖት ይበልጥ የተቀና መንገድ ላይ ናችሁ! ወይ ደግሞ የጥመት በር ከፋቾች ናችሁ!!!’ አለ።
እነሱ፡- ‘የዐብዱረሕማን አባት ሆይ! ኧረ እኛ መልካምን እንጂ ሌላ አላሰብንም’ አሉ።
ኢብኑ መስዑድ፡- ‘ስንት መልካምን እያሰበ ፈፅሞ የማያገኘው አለ?! የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‘የሆኑ ሰዎች ቁርኣንን ይቀሩታል። ግና ጉሮሯቸውን አያልፍም። ልክ ቀስት ከምትታደነዋ እንስሳት ተስፈንጥሮ እንደሚሾልከው ከኢስላም ተስፈንጥረው ይወጣሉ’ ብለው ነግረውናል። በአላህ ይሁንብኝ! ከነዚያ ሰዎች ውስጥ አብዛሀኞቹ ከናንተ እንዳይሆኑ ሰጋሁ!!’ አለ።
ከዚያም ከነሱ ዞረ። እነዚያን ፍጥረቶች እንዳለ የነህረዋን ዘመቻ ቀን ከኸዋሪጆች ሆነው ሲወጉን አየናቸው!!” [አሶ፞ሒሐ፡ 2005]
አስተዋይ ለሆነ ሰው ይሄ ታሪክ አስፈሪ መልእክቶችንና ብዙ ቁምነገሮችን ይዟል። ሱናን ሳይጠብቁ “ኒያዬ ጥሩ ነው” የሚል ማመካኛ እንደማያዋጣ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ቢድዐ የት እንደሚያደርስም ተመልከቱ። ዛሬ እኛ ያለንባቸውንና ኢብኑ መስዑድን ይህን ሁሉ እንዲናገሩ ያደረጋቸውን ጥፋትም እናነፃፅር። ሱብሓነላህ!! ሸይኹል አልባኒ ረሒመሁላህ በዚህ ሐዲሥ ላይ ጥናት ያደረጉበትን ምክንያት ሲገልፁ እንዲህ ብለዋል፡-
“በዚህ ውስጥ ለሱፍያ ጦሪቃ ተከታዮችና ከሱና ተፃራሪ የዚክር መሰባሰብ ለሚያደርጉ አካላት ጥሩ ትምህርት አለበት። እነዚህ ያሉበትን ጥፋት የሆነ ሰው ሲቃወማቸው ከነጭራሹ ‘ዚክር ተቃወመ’ ብለው ይወነጅሉታል። ይሄ ዱንያ ውስጥ ሙስሊም የማይፈፅመው ክህደት ነው። ይልቁንም ጥፋቱ ዚክሩ ላይ የተለጠፈው አፈፃፀሙና ስብስቦቹ ናቸው። እነዚህ በነብዩ ﷺ ዘመን የተደነገጉ አይደሉም። ያለበለዚያ ኢብኑ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ በነዚህ ስብስቦች ላይ የተቃወመው ምኑን ነው? በተገደበ ቀን ተሰብስበው መረጃ ባልመጣበት ግና በየክቦቹ ላይ የተመደበው ሰው በሚገድበው ቁጥር መዘከራቸውን እንጂ ሌላ አይደለም። ከራሱ በሆነ ገደብ ያዛቸዋል። ልክ ከአላህ የሚደነግገው እሱ ይመስል። … ከዚህ ታሪክ ከምንወስዳቸው ቁምነገሮችም አንዱ ትንሽ ቢድዐ ወደ ትልክ ቢድዐ አሻጋሪ እንደሆነ ነው። እነዚህ ሰዎች (ቢድዐቸው) መጨረሻ ላይ በትክክለኛው ኸሊፋ ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ እስከመገደል ያደረሳቸው ኸዋሪጅ እስከመሆን ሲያደርሳቸው አታይምን?!” [አሶ፞ሒሐ፡ 2005]
(ኢብኑ ሙነወር፣ ህዳር፡ 08/2012)


Post a Comment

1 Comments