Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሰባቱ የሰይጣን ማጥመሚያ መንገዶች

ሰባቱ የሰይጣን ማጥመሚያ መንገዶች

ኢባዳችን ከንቱ ሆኖ ፍጹም ከአላህ ውዴታ እንድንርቅ  የተለያዩ ስልቶችንና ጥበቦችን ነድፎ የሚንቀሳቀስ ስውር የሆነ ጠላትን አላህ - سبحانه وتعالى -  በሰው ልጆች ላይ አድርጓል፡፡ እርሱም ዘወትር በቀኝም በግራም በፊትም በኋላም የሚከታተለን እርጉም የሆነው ሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን የአላህ ባሮች ተኝተውም ይሁን ነቅተው ብቻ እነርሱን የጀሀነም ጓዶቹ ለማድረግ ሌሊት እና ቀን በትጋት ይንቀሳቀሳል፡፡ አላማውን የማይዘነጋ እስከትንሳኤ ቀን ድረስ እንዲያቆየው ጌታውን የተማጸነ እርኩስ ፍጡር ነው፡፡
አላህ ከእርሱ ተንኮል ይጠብቀን!!
ሙዕሚኖች በሰይጣን የሚፈተኑበት ሰባት እርከኖች እንዳሉ ኢብን አል’ቀይም رحمه الله እንደሚከተለው ገልጸዋል፡-

1- የሰይጣን ከፍተኛ ፍላጎት ሙዕሚኖች በአላህ፣ በባህሪያቶቹ እና በመሳሰሉ የኢማን መሰረቶች እንዲክዱ በማድረግ ዘላለም የጀሀነም ጓዶች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሳካለት የሚችለው በቅድሚያ በኢልምና በኢማናቸው ጣልቃ በመግባት ነው፡፡ ይህ ከተሳካለት ከፍተኛ የሆነ እርካታን ያገኛል፡፡ ካልተሳካለት ግን ቀጣይ ወዳጠመደው መለስተኛ ወጥመድ እንዲገባ ከፍተኛ ጉትጎታ ያደርጋል፡፡

2- እርሱም  ከኩፍር ቀጥሎ ወደሚገኘው የቢድዓ ወንጀል ማሸጋገር ነው፡፡ ወጥመዶቹ  በሁለት መልኩ ተፈጻሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንደኛው መንገድ  አላህ ሩሱሎችን በላከበት ወይም መጽሀፉን ባወረደበት እውነታ ተቃራኒ እንዲያምኑ በማድረግ ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ አላህ ባልፈቀደው ሁኔታ ኢባዳን እንዲፈጽሙ በማድረግ ነው፡፡ ወንጀለኞች የወንጀልን ክልክልነት አውቀው ስለሚፈጽሙ የመጸጸት እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ቢድዓ የሚፈጽሙ ሰዎች ግን ከመሰረቱ ወደአላህ ያቃርበናል ብለው ስለሚፈጽሙት አላህ የሻላቸው ሰዎች ካልሆኑ በቀር የመጸጸት እድላቸው የመነመነ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቢድዓ ከወንጀል የበለጠ ከሰይጣን ዘንድ ተወዳጅ የሆነው፡፡ 
ሰይጣን የሚከተለውን እንደሚናገር ከአንዳንድ ሰለፎች ተወስቷል፡-
“ሙዕሚኖችን በወንጀል ለማጥፋት ብሞክርም በስቲግፋር እና በላኢላሃ ኢለላህ እኔን ያጠፋኛል፡፡ ስሜትን በነፍሳቸው ላይ እፈጥራለሁ፡፡ ከዚያም በዲን ላይ አዳዲስ ፈጠራዎችን ይፈበርካሉ፡፡ በመጨረሻም መጥፎ የሆነውን ስራ በመሸላለም ከጥፋት ላይ እንዲወድቁ አደርጋቸዋለሁ፡፡”
 
ከዚህ ሙከራ በኋላ የሰይጣን እቅድ ቢኮላሽ ቀጣይ ወዳጠመደው ወጥመድ እንዲገባ ከፍተኛ ጉትጎታ ያደርጋል፡፡

3- የተስፋን በር በመክፈት ታላላቅ  ወንጀሎችን እንዲፈጽም ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ፡- ዝሙትን፣ ቁማርን እና የመሳሰሉ ታላላቅ ወንጀሎችን መፈጸም ቀላል አድርጎ ያሳየዋል፡፡  ከዚያም ሰይጣን “ኢማን በልብ ነው” “አላህ ሽርክን እንጅ ወንጀልን መሀሪ ነው” “ከሸርክ ጋር መልካም ስራ እንደማይጠቅም ሁሉ ከተውሂድ ጋር ወንጀል ሊጎዳ አይችልም” እና የመሳሰሉ የማዘናጊያ ቃላቶችን እንዲናገር ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ እነዚህን ፈተናዎች ካለፈ ሰይጣን ተስፋ ቆርጦ ወደ አራተኛው የማጥመጃ እርከን ያሸጋግረዋል፡፡

4- የአላህን እዝነተ-ሰፊነትና መሀሪነት የሚጠቁሙ የቁርዓን አንቀጾችን እና ነብያዊ ሐዲሶችን በማስታወስ ትናንሽ ወንጀሎችን እንዲፈጽም ያደርገዋል፡፡
ትናንሽ ወንጀሎች ተጠራቅመው የሰውን ልጅ እንዴት ኪሳራ ውስጥ እንደሚከቱት የአላህ መልክተኛ صلى الله عليه وسلم    በሚከተለው ሐዲሳቸው በምሳሌ ገልጸውታል፡-

وقال النبي صلى الله عليه وسلم : "إياكم ومحقرات الذنوب ثم ضرب لذلك مثلا بقوم نزلوا بفلاة من الأرض فجعل هذا يجيء بعود وهذا بعود حتى جمعوا حطبا كثيرا فأوقدوا نارا وأنضجوا خبزتهم فكذلك فإن محقرات الذنوب تجتمع على العبد حتى تهلكه" أخرجه أحمد

የአላህ መልክተኛ صلى الله عليه وسلم
“ጥቃቅን ወንጀሎችን አደራ ተጠንቀቁ! በማለት ከተናገሩ በኋላ የሚከተለውን ምሳሌ ሰጡ፡-  ሰዎች ከበረሃማው ምድር ላይ ሲያርፉ (ለማገዶ የሚሆን እንጨት ቢያጡ) ከፊሉ አንድ እንጨት ከፊሉ ሌላ እንጨት በማጠራቀምና በማቀጣጠል የሚፈልጉትን ምግብ አብስለው ይበላሉ፡፡ ልክ እንደዚሁ ጥቃቅን ወንጀሎች  ቀስ በቀስ ተጠራቅመው ሰውየውን ያጠፉታል፡፡”
(ሐዲሱን አህመድ ዘግበውታል፡፡)
ወንጀለኛ የሆነ ሰው ተውበት፣ ኢስቲግፋር እና መልካም ስራዎችን ካበዛ ሰይጣን ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ከዚያም ወደ አምስተኛው ወጥመድ ያሸጋግረዋል፡፡

5- ክልክል ባልሆኑና በተፈቀዱ ነገሮች እንዲጠመድ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ድርጅቶችን በማስፋፋት ሀብትን ከመጠን በላይ በመለጠጥ ከሶላተል ጀመዓ እንዲዘናጋ ያደርገዋል፡፡ ሀብት ሳይሸነግለው ለአኼራው ከሰራ ግን ሰይጣን ወዲያውኑ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ከዚያም ወደ ስድስተኛው ወጥመድ ያሸጋግረዋል፡፡

6- በምንዳ በላጭ የሆኑ ስራዎችን እያስተወ ምንዳቸው ዝቅተኛ በሆኑ ኢባዳዎች እንዲጠመዱ ያደርጋል፡፡ ግዴታ የሆኑ ስራዎችን እያስተወ ለሱና  ትኩረት እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡ ይህን ካልቻለ ወደ መጨረሻውና ለማንም የማይቀር ወደሆነው ፈተና ያሸጋግረዋል፡፡

7- የአላህ ባሮች ተስፋ ቆርጠው ከኢልም፣ ከዳዕዋ እና ከሌሎች መልካም ተግባራት እንዲሰናከሉ ሰይጣን ሙዕሚኖችን እንዲሳደቡ እንዲያነውሩ ሰራዊቶቹን ያሰማራል፡፡
ኢልም ከሌለ ከሰይጣን ፈተናዎች የሚተርፍ አንድም አካል የለም፡፡  በምን ምሽግ ተደብቆ ማምለጥ ይችላል? የጠላቱን መግቢያና መውጫ እንዴት ማወቅ ይችላል? ጠላቱን በምን አይነት መሳሪያ እንደሚዋጋ ያላወቀ እንዴት ማጥቃት ይችላል? የቁስሉን መድሃኒት ያላወቀ እንዴት መዳን ይችላል? በመሆኑም የሰይጣንን  ማንነት፣ ተንኮሉን፣ የምንዋጋበትን መሳሪያ ጨምሮ አላህ በበርካታ የቁርዓን አንቀጾችና ረሱልም صلى الله عليه وسلم በሀዲሳቸው ስላብራሩት እያንዳንዱ ሙስሊም ወደቁርዓን እና ወደሐዲስ በመመለስ ዲኑን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ 
الله أعلم
وصلى الله على نبينا محمد وعلى آله وأصحابه وسلم
(مفتاح دار السعادة : 1/191)

https://t.me/alateriqilhaq

Post a Comment

0 Comments