Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሶስት ዓይነት ኡለሞች እንዳሉ ያውቁ ኖሯል?



ሶስት ዓይነት ኡለሞች እንዳሉ ያውቁ ኖሯል?

1ኛ፡- ኡለማኡ አድ’ደውላህ
2ኛ፡- ኡለማኡ አል’ኡመህ
3ኛ፡- ኡለማኡ አል’ሚለህ

1ኛ፡- ኡለማኡ አድ’ደውላህ
ኡለማኡ አድ’ደውላህ ፡ የሚባሉት የአገሪቱን እና የመንግስትን የልብ ትርታ እያዳመጡ ተስማሚ የሆነ ፈትዋ የሚሰጡ ኡለሞች ናቸው፡፡ አላማቸው ይሳካ እንጅ ሐዲስ ያልሆነውን ሐዲስ ብሎ ማውራት ከእነርሱ ዘንድ ችግር የለውም፡፡  ይህ ብቻ አይደለም የቁርዓን አንቀጽም ካገኙ አንገቱን ቆልምመው ለሚፈልጉት አላማ ማዋል ልክ ውሃ የመጠጣት ያክል ቀላላቸው ነው፡፡ ምክንያቱም አላህን መፍራት ከልባቸው ውስጥ ተጠራርጎ ወጧል፡፡ ብቻ እነርሱ መንግስት ምን አዋጅ አወጣ? ምን ፖሊሲ ቀረጸ? የሚለው ጉዳይ ብቻ ነው በአእምሯቸው ውስጥ የሚያቃጭለው፡፡ ለመረጃ ጥራት ብዙም አይጨነቁም፡፡ አሁንም ይሁን ቀድሞ  አዳዲስ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ ለፖሊሲው ድጋፍ የሚሆኑ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመንግስት ማቀበል የተለመደ ባሕሪያቸው ነው፡፡ በእነርሱ ዓላማ ተቃራኒ የሆኑ ኡለሞችን ከማሳደድ፣ ከማሳሰር፣ ከማስገረፍ እና ከማስገደል ወደኋላ አይሉም፡፡
ለምሳሌ፡- የሶሻሊስት ስርዓት በተለያዩ የአለም ክፍሎች ይፋ በሆነ ጊዜ ሀብት ንብረት የጋራ ነው የሚል አዋጅ ታወጀ፡፡ ሐብት ማከማቸት እንደወንጀል እና እንደበደል መታየት ጀመረ፡፡ መንግስት የግለሰብን ሐብት ለድሆች አቀራመተ የፈለገውን ሐብት ወረሰ፡፡ በወቅቱ የነበሩ ኡለሞች መንግስት  ካወጣው ፖሊሲ ጋር የሚስማማ ፈትዋ ለመስጠት አንገታቸውን ቀና አደረጉ፡፡ የቁርኣን እና የሀዲስ መረጃዎችን ማፈላለግ  ጀመሩ፡፡ በዚህም ከመንግስት በኩል ከፍተኛ የሆነን ተቀባይነትና ድጋፍ አገኙ፡፡
የሶሻሊስትን ስርዓት ለመደገፍ ካቀረቧቸው የቁርዓንና የሐዲስ መረጃዎች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፡-
إن الرسول صلى الله عليه وسلم قال: "الناس شركاء في ثلاث : الماء والكلأ والنار" . أخرجه أحمد وأبو داود
“ሰዎች በሶስት ነገሮች ላይ ተጋሪ ናቸው፡ በውሃ፣ በእሳር እና በእሳት”
إن الرسول صلى الله عليه وسلم قال: "من كان له أرض فليزرعها أو ليزرعها أخاه"  أخرجه البخاري
“መሬት ያለው ሰው መሬቱን በመዝራት ይጠቀም፡፡ ካለበለዚያ ለወንድሙ ያስረክበውና ወንድሙ ይዝራው፡፡”
በነዚህ ኡለሞች ፈትዋ መሰረት  ሰፊ መሬት ቢኖርህና መጠቀም ካልቻልህ መስራት ለሚችሉ ሌሎች አካላት ንብረትህ ይዛወራል ማለት ነው፡፡
ለሶሻሊስት ስርዓት የሚከተለውን የቁርዓን ማስረጃም አቅርበዋል፡-
"ضرب لكم مثلا من أنفسكم هل لكم من ما ملكت أيمنكم من شركاء في ما رزقنكم فأنتم فيه سواء"
 الروم : 28
“ለእናንተ ከነፍሶቻችሁ የሆነን ምሳሌ አደረገላችሁ፡፡ (እርሱም) እጆቻችሁ ከያዟቸው (ባሮች) ውስጥ በሰጠናችሁ ጸጋ ለእናንተ ተጋሪዎች አሏችሁን? ታዲያ እናንተና እነርሱ በእርሱ ትክክል ናችሁን?”
(አር’ሩም፡ 28)
የዚህ የቁርኣን አንቀጽ ትክክለኛ ትርጉም  አላህ በሰጣችሁ ንብረት ባሮችን እና እናንተን  እኩል አታደርጉም፡፡ ታዲያ ይህ ከሆነ ለአላህ ተጋሪዎችን የምታደርጉ ለምንድን ነው? የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ይህን የቁርዓን አንቀጽ ያለትርጉሙ በማጣመም ንብረት በሙሉ የጋራ እንደሆነ አድርገው ቅጥፈትን ይነዛሉ፡፡ ለአገር ልማት የዘካ ገንዘብ ማዋል ይቻላል የሚል ፈትዋ በአንድ ወቅት እነዚሁ ኡለሞች በሬዲዮ አሰራጭተዋል፡፡  ይህ ፈትዋ በሬዲዮ ሲተላለፍ መረጃ ያደረጉት ለዘካ የወረደውን የቁርኣንን አንቀጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡  ዘካ ከሚሰጣቸው ስምንት ክፍሎች አንዱ ፊሰቢሊላህ የሚወጡ ሰዎች ናቸው፡፡ አገርን ማልማት ከፊሰቢሊላህ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ባለሀብቶችን በማሳመን ከዘካ ገንዘባቸው የተወሰነውን ፐርሰንት በየአመቱ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርጉ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል ብለዋል፡፡   
አላህ እንዲህ ብሏል፡-

"ربنا إنا أطعنا سادتنا وكبراءنا فاضلونا السبيلا ربنا ءاتهم ضعفين من العذاب والعنهم لعنا كبيرا"
 الأحزاب: 67-68
“ይላሉም “ ጌታችን ሆይ! እኛ ጌቶቻችንንና ታላላቆቻችንን ታዘዝን፡፡ መንገዱንም አሳሳቱን፡፡ “ጌታችን ሆይ! ከቅጣቱ እጥፍን ስጣቸው፡፡ ታላቅን እርግማንም እርገማቸው፡፡”
(አህዛብ፡ 67-68)

2ኛ፡- ኡለማኡ አል’ኡመህ

ኡለማኡ አል’ኡመህ ደግሞ በአገሪቱ ፖሊሲ ቀጥታ ጣልቃ ገብነት የሌላቸው ሲሆኑ ትኩረታቸው ለኡማው እና ለህዝቡ ማሰብ ነው፡፡  ህብረተሰቡ ምን ይስማማዋል? ህዝቡ ምን ይፈልጋል? የሚለውን ጥያቄ ዘወትር ያነሳሉ፡፡ ባጠቃላይ ህዝብ ተኮር እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ የህዝቡን ስሜት ካላሳካን በህዝቡ እንዋጣለን ብለው ያስባሉ፡፡ ስለዚህ ለህዝቡ ተስማሚ የሆነውን ፈትዋ መፈለግ ግድና ግድ ሆኖባቸዋል፡፡
ለዚህ ክፍል አንድ ምሳሌ እንጥቀስ፡- ሰዎች ፈታዋ ፈልገው ወደአንድ አሊም ይመጣሉ፡፡ ከዚያም  “ከባንክ በወለድ ብድር መበደር ፈልገን በዚህ ጉዳይ ሸሪዓው ምን ይላል?” የሚል ጥያቄ ለአሊሙ ያነሳሉ፡፡ አሊሙም “ይህ ነገር በሸሪዓ አይፈቀድም፡፡”  የሚል ምላሽ ሰጣቸው፡፡ ሰዎቹም “ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከባንክ በወለድ ብድር ቢበደር በርካታ ምስኪኖች ተጠቃሚ ይሆናሉ ድሀው ሱቅ ከፍቶ ይነግዳል ገበሬው ያርሳል እና በአጠቃላይ ለአገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አላህ ጀዛዎትን ይክፈልዎና እባክዎ ይፍቀዱልን?!”  በማለት አሊሙን ይማጸናሉ፡፡  አሊሙም፡- “የዚህን ያክል አሳሳቢ ከሆነ እስኪ የተወሰነ ቀን ስጡኝና ኪታብ ተመልክቸ ልምጣ፡፡”  በማለት መልስ ይሰጧቸዋል፡፡ ከተወሰነ ቀን በኋላ ሰዎቹ ወደአሊሙ ይመጣሉ፡፡ “ኪታብ አዩልን ሸኾቹ?”  በማለት ይጠይቃሉ፡፡ አሊሙ እንዲህ ይላሉ፡-  “ኪታቡ ምን ይላል መሰላችሁ? ሸሪዓው የመጣበት ዋና አላማ “ጥቅምን ለማስገኘት መጥፎን ነገር ለመከላከል” የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የባንኩ አላማም ህዝብ እንዲለወጥ ኢኮኖሚው እንዲያድግ በአጠቃላይ የህብረተሰብን ጥቅም መሰረት ያደረገ በመሆኑ ባንክ ብትበደሩ ሸሪዓችን አይከለክልም፡፡” የሚል የማግራሪያ ፈትዋ ይሰጣቸውና ሰዎቹ በሐሴት ተውጠው ይመለሳሉ፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ  ኡለማኡ አል’ኡማህ በመባል የሚጠሩት፡፡

3ኛ፡- ኡለማኡ አል’ሚለህ
ኡለማኡ አል’ሚለህ የተባሉት ደግሞ ፍላጎታቸው ከህዝብም ከመንግስትም ጋር አይደለም፡፡ እነርሱ የሚጓዙት የአላህ ዲን ወይም የአላህ ቃል የበላይ እንዲሆን ብቻና ብቻ ነው፡፡ ከቁርዓንና ከሐዲስ ጋር ከተጋጨ ለአገርም ይሁን ለህዝብ ፍላጎት ጣጣ የላቸውም፡፡ እነዚህ አሊሞች ከህዝብ መካከል ቢኖሩ ህብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አላህ እዝነቱን እና በረካውን ያወርዳል፡፡ ለህብረተሰብ ሁጃ  ለህዝብ እርካታ ለማንኛውም ችግር መመለሻ ይሆናሉ፡፡
አላህ የኡለማኡ አል’ሚለህን ቁጥር ያብዛልን!
እኛንም የኡለማኡ አል’ሚለህ ተከታዮች ያድርገን!!

الله أعلم
وصلى الله على نبينا محمد وعلى آله وأصحابه وسلم

https://t.me/alateriqilhaq

Post a Comment

0 Comments