Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሳይቃጠል በቅጠል!


ሳይቃጠል በቅጠል!
~~~~~~~~~~~
በሃገራችን በርካታ ሙስሊም ከኢስላማዊ ግንዛቤ በመራቁ የተነሳ እንደ እንቁጣጣሽ፣ መስቀል፣ ኢሬቻ፣ ገና፣ ጥምቀት፣ የግንቦት ልደታ፣ ቡሄ፣ … ያሉ የኩፍር በአላትን ሲያከብር እንደነበር ይታወሳል። ዛሬ ንቃተ ህሊናው በጨመረ ቁጥር አብዛኛው ሙስሊም ከዚህ ብልሹ ባህል እጁን ሰብስቧል― ምስጋና ለአላህ ይግባውና።
ነገር ግን በሚያሳፍር ሁኔታ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በአዲስ ቅብ ዳግም ወደዚህ ጥፋት ሊመልሱ ደፋ ቀና የሚሉ ሰባኪዎች መጥተውብናል። እስኪ ለኩፍር በአላት የፅዳት ዘመቻ ማድረግ ምን ማለት ነው? ዛሬ ላይ ሰዎችን ከመሰል ጥፋቶች ያነቃሉ ተብለው የሚጠበቁ መሻይኾችና ኡስታዞች ከመሀይሙ ብሰው ወደ ጥፋት ሲጣሩ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ይሄ ሲበዛ የሚያሸማቅቅ ነው። አዎ ጌታችን በእምነታችን ሰበብ ካላስቸገሩን ካፊሮች ጋር በመልካም እንዳንዋዋል አልከለከለንም። ይህ ማለት ግን በጥፋት ያውም በኩፍር ላይ ትብብር እናደርጋለን ማለት አይደለም። አላህ እንዲህ ይላል:–
وَتَعَاوَنُوا عَلَى الْبِرِّ وَالتَّقْوَىٰ ۖ وَلَا تَعَاوَنُوا عَلَى الْإِثْمِ وَالْعُدْوَانِ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ

"በበጎ ነገርና አላህን በመፍራትም ተረዳዱ፡፡ ግን #በኃጢአትና_ወሰንን_በማለፍ_አትረዳዱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡" [አልማኢዳህ: 2]

መረዳዳቱ በኩፍር ላይ ሲሆንስ?! ይሄ ጥፋት የነ ዑመር ኮምቦልቻ አይነት አሕባሾች ቢሆን ዝም ይባል ነበር?! ዛሬ ላይ ጥፋትን ለማውገዝ አሰላለፍ ይታያል። የኛ ሲሆን ይወደሳል። የነሱ ሲሆን ይወገዛል። በመልካም የማዘዝና ከመጥፎ የመከልከል ህግ ከማታገያ ስልትነት ባለፈ እውነተኛ ዋጋ ያጣበት ጊዜ!!
እንዲህ አይነቱ በኩፍር ላይ የሚደረግ ትብብር በአስካሪ መጠጥና በወለድ ላይ ከመተባበር የከፋ ነው። እነዚህ ሰዎች ክፉ የሆነ ሱና፞ ነው እየነደፉ ያሉት። ቢያስተውሉ ከዚህ በሁዋላ ለሚቀጥለው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ ናቸው። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–
وَمَنْ سَنَّ فِي الْإِسْلَامِ سُنَّةً سَيِّئَةً كَانَ عَلَيْهِ وِزْرُهَا وَوِزْرُ مَنْ عَمِلَ بِهَا مِنْ بَعْدِهِ مِنْ غَيْرِ أَنْ يَنْقُصَ مِنْ أَوْزَارِهِمْ شَيْءٌ
"በኢስላም ውስጥ መጥፎ ፈለግን የነደፈ ሰው ወንጀሉ በሱ ላይ አለበት። ከሱ በሁዋላ የሰሩበት ሰዎችም ወንጀል አለበት፣ ከነሱ ወንጀሎች ምንም ነገር ሳይቀንስ።" [ሙስሊም: 1017]

እንዲህም ብለዋል:–
وَمَنْ دَعَا إِلَى ضَلَالَةٍ كَانَ عَلَيْهِ مِنَ الْإِثْمِ مِثْلُ آثَامِ مَنْ تَبِعَهُ، لَا يَنْقُصُ ذَلِكَ مِنْ آثَامِهِمْ شَيْئًا
"ወደ ጥመት የተጣራ የተከተሉት ሰዎች አምሳያ ወንጀሎች አሉበት። ይህም (በሱ ላይ መታሰቡ) ከወንጀሎቻቸው ምንም አይቀንስም።" [ሙስሊም: 2674]
ስለዚህ ሞተን እንኳን የማይቋረጥ ወንጀል ጥለን እንዳናልፍ ልንጠነቀቅ ይገባል።

ሙስሊም የሆነ ሰው በተለይም አስተማሪዎች ክፉ ተመሳሌቶች እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ ይገባል። ነብያችን ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም "በህዝቦቼ ላይ ከምፈራው ሁሉ እጅግ አስፈሪው አጥማሚ መሪዎች ናቸው!" ብለዋል። ሐዲሡን አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል። [ሶሒሑል ጃሚዕ: 1551] [አሶ፞ሒሐህ: 1582]

አጉል ማማሀኛ:–
ይሄ ፈፅሞ ከመቻቻልና በመልካም መኗኗር ጋር የሚገናኝ ነጥብ አይደለም። ደግሞም ዛሬ በጊዜ ካልተገታ ነገ የሚከተለው ነገር የበለጠ አስፈሪ ነው።
"ጠ/ሚውን ወይም ሌላን አካል እንዳናስከፋ" አይነት ምክንያት አይሰራም። ይበልጥ ልንፈራም ልናከብርም የሚገባው አላህን ነው። ነብዩ ሶለ፞ላ፞ሁ ዐለይሂ ወሰለ፞ም እንዲህ ብለዋል:–
( مَنِ الْتَمَسَ رِضَى اللَّهِ بِسَخَطِ النَّاسِ ، رَضِيَ الله عَنْهُ ، وَأَرْضَى النَّاسَ عَنْهُ ، وَمَنِ الْتَمَسَ رِضَا النَّاسِ بِسَخَطِ اللَّهِ ، سَخَطَ اللَّهُ عَلَيْهِ ، وَأَسْخَطَ عليه الناس )
"ሰዎች እየተከፉም ቢሆን የአላህ ውዴታ የፈለገ ሰው አላህ ይወደዋል። በሰዎችም ያስወድደዋል። አላህን በማስቆጣት የሰዎችን ውዴታ የፈለገ ሰው አላህ ይቆጣበታል። ሰዎችንም ያስቆጣበታል።" [ኢብኑ ሒባን ዘግበውታል።]

ሃይማኖትህ የማይፈቅደው ቦታ ላይ "አይሆንም" ማለት ካልቻልክ መቋጫ ለሌለው ፈተና ትጋለጣለህ። ትላንት ሉሲን ተከትለህ ስትዞር ነበር። ዛሬ ለመስቀል በአል ሽር ጉድ ልትል ነው። ነገስ? ጉዳዩ ምን ሲደርስ ነው "አይሆንም" የምትለው? ቢገባህ ይሄ ልፍስፍስነትህ አካሄድህ "ተራማጅ" "ዘመኑን የዋጀ" ያስብለኛል ብለህ ስታልም ያስንቅሀል። ደግሞም ልትናቅም ይገባሀል። በጊዜ አላህን ፍራ!!

ሌሎቻችን ይህንን አስቀያሚ ጥፋት በሚገባ ልንቃወመው ይገባል። ዝምታ ለሁሉም የሚተርፍ ጦስ አለው። አላህ እንዲህ ይላል:–
(لُعِنَ الَّذِينَ كَفَرُوا مِنْ بَنِي إِسْرَائِيلَ عَلَىٰ لِسَانِ دَاوُودَ وَعِيسَى ابْنِ مَرْيَمَ ۚ ذَٰلِكَ بِمَا عَصَوْا وَكَانُوا يَعْتَدُونَ * كَانُوا لَا يَتَنَاهَوْنَ عَنْ مُنْكَرٍ فَعَلُوهُ ۚ لَبِئْسَ مَا كَانُوا يَفْعَلُونَ)
[سورة المائدة 78 - 79]
"ከእስራኤል ልጆች እነዚያ የካዱት በዳውድና በመርየም ልጅ በዒሳ ምላስ ተረገሙ፡፡ ይህ ትእዛዝን በመጣሳቸውና ወሰንን የሚያልፉ በመሆናቸው ነው፡፡ #ከሰሩት_መጥፎ_ነገር_አይከላከሉም_ነበር፡፡ ይሰሩት የነበሩት ነገር በእርግጥ ከፋ!" [አልማኢዳህ: 78–79]
አላህ በዲን ጉዳይ የወቃሾችን ወቀሳ የማንፈራ ያድርገን።
°
(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 8/2012)

Post a Comment

0 Comments