Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዘካተል ፊጥር


#ዘካተልፊጥር
ዘካተልፊጥር ማለት ምን ማለት ነው?
ዘካተል ፊጥር ማለት ማንኛውም ሙስሊም የረመዷንን ወር ደርሶ የዒድሌሊትን ያገኘ የሆነ ሰው ለድሆች ሊሰጠው የሚገባ የተመጠነ የምግብ አይነት ነው።
°
#የተደነገገበት_ጥበብ
ጥበቡ ፆመኛ ሰው በፆሙ ወቅት ካጋጠመው ጉድፈቶች ማሟያ እና ጉድለቶችን ደግሞ ማረሚያ ነው። ሌላው ደግሞ ሚስኪኖች በዒድ ቀን እንዲደሰቱ ለማድረግ ነው። ይህንን የሚያመላክት ዐብደሏህ ኢብኑ ዐባስ የተናገረው ሐዲስ አለ ፦ [ ረሱል - ﷺ - ዘካተልፊጥርን ለፆመኛው ከጨዋታ እና ካዛዛታ ማፅጃ እንደዚሁም ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተያያዥ ለሆኑ ንግግሮች ማፅጃ እና ለሚስኪኖች መመገቢያ እንዲሆን በማለቱ ግዴታ አደረጉ። ከሶላትበፊት የሰጣት እንደሆነ እሷ ተቀባይነት ያላት ዘካህ ነች ፤ ከሶላት በኋላ የሰጣት ከሆነ ግን ከሶደቃዎች ውስጥ አንድ ሶደቃ ነች። ] (ኡቡዳውድ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል።)
°
ዘካተልፊጥር ፍርዱ ምንድን ነው?
ዘካተልፊጥር ፍርዱ ግዴታ ነው። ምክንያቱም በሐዲሱ ላይ ረሱል - ﷺ - "ፈረደ" ወይም ግዴታ አደረጉ የሚለው ቃል ስለተጠቀሰ ማለት ነው።
°
ማን ላይ ነው ግዴታ የሚሆነው?
ግዴታ የሚሆነው በትልቁም በትንሹም በባሪያውም በጨዋውም በወንዱም በሴቱም በሁሉም ሙስሊሞች ላይ ነው። ሙስሊሞችን ነው የሚመለከተው ሲባል የሚያወጣው ሰውም የሚሰጠውም ሰው ላይ ነው። የሚያወጣውም ሰውዬ ግዴታ እንዲሆንበት ዘንድ ለሱ እና ለቤተሰቡ የዒድ ሌሊቱን እና ቀኑን በተጨማሪም ከዛ የተረፈ ቀለብ ካለው ነው።
°
የፆመውን ሰው ብቻ ነው የሚመለከተው ወይስ?
የረመዷንን ወር ፆምን የፆመም ይሁን ያልፆመም ሰው ዘካተልፊጥር ይመለከተዋል። ለዚህም ሲባል ለህፃን ልጅ ማውጣቱ ተገቢ ነው።
°
እያንዳንዱ ሰው ለየራሱ ነው ማውጣት ያለበት ወይስ ለሌላ ሰው ማውጣት ግዴታ ይኖርበታል?
ዘካተልፊጥር ግዴታው የሚመለከተው እያንዳንዱን ሰው ነው።
ብዙሀኑ ኡለማዎች አንድ ግለሰብ የማስተዳደር ግዴታ ላለበት ሰዎች ለምሳሌ ለባለቤቱ ማውጣት ግዴታ ይሆንበታል ይላሉ። ሌሎቹ ግን ግዴታ አይሆንበትም ይላሉ። በዚህም መሰረት ባለቤቱ እሱን ሳትጠብቅ ለራሷ ብታወጣ ትችላለች። እሱም በቂ ገንዘብ ከሌለው ሚስት ለራሷ ማውጣት ግዴታ ይሆንባታል። ለቤት ሰራተኞች ማውጣት ግዳታ አይሆንበትም። ምክንያቱም የቤት ሰራተኞችን ቀለብ በሱ ላይ ግዴታ አይሆንበትም። ቢያወጣ ችግር የለበትም።
°
#ምንድን_ነው_የሚወጣው?
የሚወጣው ሰዎች በተመልዶ ከሚመገቡት የምግብ አይነት ነው። ዐብደሏህ ኢብኑ ዑመር - ረዲየሏሁዐንሁ - እንዲህ ይላል ፦ [ ረሱል - ﷺ - ዘካተልፊጥርን ከረመዷን ከቴምር አንድ "ሷዕ" ወይም ከገብስ አንድ "ሷዕ" ደነገጉ። ] (ሙተፈቁን ዓለይሂ) በሌላም ሐዲስ ላይ አቢሰዒዲኒል ኹድሪይ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን ዘርዝሯል።
የምግቡም አይነት የሰውልጆች አብዛኛው የሰውነት ክፍላቸው የሚገነባበት የምግብ አይነት መሆን አለበት። ማለትም ስንዴ ገብስ እና ሌሎች ሰዎች በተለምዶ የሚመገቧቸው ምግቦች ማለት ነው። እንጂ ቡና ምናምን ማውጣቱ ተገቢ አይደለም።
ዱቄት ማውጣት ይቻላል።
°
#በገንዘብ_ተምኖ_ማውጣት
ብዙሀኑ ዑለማዎች እንደሚመርጡት ዘካተልፊጥርን በገንዘብ ማውጣት አይፈቀድም። ምክንያቱም በነብዩ - ﷺ - ገንዘብ የመገበያያ መሳሪያ ከመሆኑ ጋር በገንዘብ እንዲወጣ አልመፍቀዳቸው ወይም በዘመናቸው በገንዘብ ይወጣ እንደነበረ መፍቀዳቸው ምንም አይነት መረጃ አለመዘገቡ ከምግብ ጋር የተገናኘ የተገደበ የአምልኮ ዘርፍ መሆኑን ይጠቁማል። ሌላው በገንዘብ ማውጣት እንደማይቻል የሚያመላክተው በየትኛው የምግብ አይነት ተተምኖ ነው የሚወጣው? በገብስ ነው ወይስ በስንዴ? በአንዱ ነው ካልክ መረጃ ልትጠየቅ ነው ማለት ነው። ስለዚህ የተሻለው ረሱል -ﷺ- እና ከዛበኋላ ሶሐባዎች ሲያወጡት እንደነበረው በእህል ማውጣት ነው።
°
#ምን_ያህል_ነው_የሚወጣው?
የአላህ መልእክተኛ -ﷺ- የጠቀሙት የመስፈሪያ ቃል እንጂ የክብድት ቃል አይደለም። ስለዚህ የሚወጣው አንድ ሷዕ ነው። አንድ ሷዕ ደግሞ አራት እፍኝ ነው። አራት እፍኝ በሚዛን እንደየእህሉ ሊለያይ ቢችልም አነስተኛው ሚዛን 2.04kg ነው። ነገር ግን ሌሎች ዑለማዎች ጨምረው የተናገሩ ስላሉ ከኺላፉ ለመውጣት ጨመር አድርጎ 2.5kg መስጠቱ የተሻሉ ነው።
°
#ግዴታነቱ_መቼ_ነው_የሚጀምረው?
ግዴታነቱ የሚጀምረው የዒድ ቀን ሌሊቱ ላይ ነው። ይህም የሆነው ፀሀዩ ሲጠልቅ ረመዷን ስለሚወጣ ነው። በዚህም መሰረት ፀሀይ ከመጥለቁ ከደቂቃዎች በፊት አንድ ሰው ቢሞት ማውጣት ግዴታ አይሆበትም። ነገር ግን ፀሀይ ከጠለቀች በኋላ ቢሞት ለሱ ይወጣለታል። በሌላ በኩል አንድ ህፃን ልጅ ፀሀይ ከመጥለቋ ከደቂቃዎች በፊት ቢወለድ ለሱ ማውጣቱ ግዴታ ይሆናል። ነገር ግን ፀሀይ ከጠለቀች ከደቂቃዎች በኋላ ቢወለድ ለሱ ማውጣቱ ግዴታ አይሆንም። ቢወጣለት ግን ችግር የለውም።
°
#ለማን_ነው_ሚሰጠው?
የተሻለውች አቋም የሚሰጠው ለ"ፉቀራኦች"/ድሆች እና ለሚስኪኖች ነው።
°
#መቼ_ነው_የሚሰጠው?
ጊዜውን በተመለከተ የሚሻለው ከዒድ ሶላት በፊት ባለው ጊዜ ነው። ነገር ግን ከዛ በፊት አንድ ቀን ሁለት ቀን አዘግይቶ ቢሰጥ ችግር የለውም። ዐብደሏህ ኢብኑ ዑመር ይህንን ያደርግ ነበር።
ከዒድ በኋላ ቢሰጥ አያብቃቃውም ምክንያቱም ዐብደሏህ ኢብኑ ዐባስ - ረዲየሏሁዐንሁ - እንዲህ ይላል ፦ [ ከሶላትበፊት የሰጣት እንደሆነ እሷ ተቀባይነት ያላት ዘካህ ነች ፤ ከሶላት በኋላ የሰጣት ከሆነ ግን ከሶደቃዎች ውስጥ አንድ ሶደቃ ነች። ] (ኡቡዳውድ እና ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል።)
°
__
ከርእሱ ጋር ባይገናኝም ከመድረኩ ዒድ እና ጁሙዐ አንድ ላይ ቢገጥሙ ምን ማድረግ አለበን? የሚል ጥያቄ ተነስቶ በጥቅሉ ኡስታዝ ኢልያስ ዒድ የሰገደ ሰው ጁሙዓን መተው እንደሚችል በምትኩ ግን የዙህርን ሶላት መስገድ ግዳታ እንደሆነ እና ዒድንም ጁሙዓንም መስገድ ደግሞ በላጭ መሆኑን ጠቅሷል።
_
ምንጭ ፦ በ2002 ዓ.ል ላይ "ዘካተልፊጥር" በሚል ርእስ ከተደረገው የኡስታዝ ኢልያስ አሕመድ የድምፅ ፋይል ላይ የተወሰደ
✍️አቡልዓባስ አሕመድ ኢብን ያሕያ @ Ibn yahya Ahmed
ሰኔ 6/2010 # June 13/2018 ላይ የተፃፈ.


ለሌሎች ሙሀደራዎች፣ደርሶች፤ አጠር አጠር ያሉ የነቢዩ ሀዲሶችን እና የሰለፎችን ንግግር ለማግኘት ይህን የቴሌግራም ቻናል ጆይን ያድርጉ፦
https://telegram.me/ibnyahya7
የኡስታዝ ኢልያስ አሕመድ ትምህርቶችን ለመከታተል ይህን ቻናል ይቀላቀሉ ፦
https://t.me/ustazilyas
የፌስቡክ ፔጃችንን ላይክ ያድርጉ ፦ https://m.facebook.com/ibnyahya777

Post a Comment

0 Comments