Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዘካተል ፊጥር እና አፈጻጸሙ (በኡስታዝ ጣሀ አህመድ)


ዘካተል ፊጥር እና አፈጻጸሙ (በኡስታዝ ጣሀ አህመድ)

ዘካተል ፊጥር ከረመዳን ወር ፆም መጠናቀቅ ጋር በተያያዘ ግዴታ የሚሆን የዘካ አይነት ነው፡፡ ዘካተል ፊጥርን መስጠት እያንዳንዱ ሙስሊም ላይ በነፍስ ወከፍ ግዴታ ሲሆን፤ እያንዳንዱም አባወራ የራሱን ጨምሮ በእርሱ ስር ስላሉ ቤተሰቦቹ ሁሉ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ኢብኑል ሙንዚር ‘አል-ኢጅማዕ’ በተሰኘው ኪታባቸው ‹‹ዒልምን የተማርንባቸው ዑለማዎች ሁሉ ዘካተል ፊጥር ግዴታ መሆኑን ተስማምተውበታል›› በማለት የጉዳዩን ግዴታነት ከሚያመለክቱት ነብያዊ ሀዲሶች በተጨማሪም የኡለማዎችን አጠቃላይ ስምምነት (ኢጅማዕ) የተገኘበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

√ የተደነገገበት ጥበብ

ድሆች በባዕሉ (ዒድ) እለት ሰዎችን ከመለመን እንዲድኑና የእለቱ ደስታ ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግ እንዲሁም በፆም ወቅት ተከስተው ላለፉ አንዳንድ ጉድለቶች (ግድፈቶች) ማሟያ እንዲሆን ነው፡፡
ይህን አስመልክቶ ዐብደላህ ኢብን አባስ እንዲህ ይላሉ፤
عن ابن عباس ـ رضي الله عنهما ـ قال: "فرض رسول الله صلى الله عليه وسلم زكاة الفطر طهرة للصائم من اللغو والرفث وطعمة للمساكين، فمن أداها قبل الصلاة فهي زكاة مقبولة، ومن أداها بعد الصلاة فهي صدقة من الصدقات" رواه أبو داود
وابن ماجه
‹‹የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ዘካተል ፊጥርን ለፆመኛ ለ ‘ለግዉ’ (ጥቅም ለሌላቸው ውድቅ የቀልድ ንግግሮችና ተግባሮች) እና ለ ‘ረፈስ’ (ፆታዊ ስሜትን ቀስቃሽ ለሆኑ ንግግሮች) ማፅጃ፤ ለምስኪኖች (ድሆች) መብል ሲሆን በግዴታ መልኩ ደንግገውታል፡፡ ስለዚህም ከኢድ ሰላት በፊት (ዘካውን በመስጠት ግዴታውን የተወጣ) ተቀባይነት ያለው ዘካን ሰጥቷል፤ ከኢድ ሰላት በኋላ ዘካውን የሰጠ ከሌላ ግዴታ ያልሆነ ሰደቃ አንዱ እንደሆነ ይታሰብለታል፡፡››
(አቡዳውድ እና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል)

√ የዘካተል ፊጥር መጠን

ኢብኑ ኡመር ሀዲስ ላይ እንዲህ የሚል መልዕክት ስለተላለፈ ነው፤
‹‹የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይሁን) ከተምር ወይም ከገብስ አንድ ‹‹ሷዕ›› በእያንዳንዱ ሙስሊም፤ ባሪያ፣ ጨዋ (ባሪያ ያልሆነ)፣ሴት፣ ህፃን፣ አዋቂ ላይ ግዴታ አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ሰዎች ወደ (ዒድ) ሰላት ከመውጣታቸው በፊት ለሚገባቸው ሰዎች እንዲደርስ አዘዋል፡፡›› (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
ሷዕ የመስፈሪያ አይነት ሲሆን በድሮ ጊዜ የነበረ የእህል መስፈሪያ ነው። በዘመናዊ መለኪያ አንድ ‹‹ሷዕ›› 2.04-2.5 ኪ.ግ ይመዝናል፡፡ 1 ሷዕ = 4 የሁለት ዕጅ እፍኞች ነው።

√ ዘካተል ፊጥር በማን ላይ ግዴታ ይሆናል?

ዘካተል ፊጥር ግዴታ የሚሆነው ሁለት መስፈርቶችን ባሟላ ሰው ላይ ብቻ ነው፤ እነርሱም
  1. ሙስሊም በሆነ 
  2. ዘካተል ፊጥር ማውጣት ግዴታ በሚሆንበት ቀን እና ሌሊት፤ ለራሱ እና ለቤተሰቦቹ የሚበቃ መብል ኖሮት የተረፈው እና ተጨማሪ ነገር ያለው፡፡

√ ዘካተል ፊጥር የሚሰጠው መቼ ነው?

ዘካተል ፊጥርን ከ(ዒድ) ሰላት በኋላ ማዘግየት የተከለከለ ሲሆን፤ ማውጣቱ ግዴታ የሚሆንበት ወቅት የሚጀምረው ከረመዳን የመጨረሻው እለት ፀሀይ ከጠለቀችበት ወይም ዒድ መሆኑ ከተረጋገጠበት ሰዓት አንስቶ ነው፡፡ ነገር ግን ኢብኑ ዑመርን ጨምሮ ሌሎቹም ሰሀቦች ያደርጉት እንነበረው ከዒድ አንድ ወይም ሁለት ቀን ቀድሞ ዘካተል ፊጥርን ማውጣት ይፈቅዳል፡፡

√ ለዘካተል ፊጥር የሚሰጡ የእህል አይነቶች

ዘካተል ፊጥር ሙስሊሞች ከሚመገቡዋቸው እንደ እሩዝ፤ በቆሎ፤ ጤፍ…. ባሉ የምግብ እህል አይነቶች ነው። መልእተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይሁን) በሀዲስ የጠቀሷቸው የምግብ እህሎች (እንደ ገብስ፤ ተምር፤ ዘቢብ) የመሳሰሉት ሲሆኑ፤ ነገር ግን የምግብ አይነቶቹ በነዚህ ላይ ብቻ እንደማይገደቡ የሻፊዒያ እና የማሊኪያ መዝሀብ ዑለማዎች ሲስማሙበት ሸይኹል ኢስላምም የመረጡት አቋም ነው፡፡
የአላህ መልአክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይሁን) ከተምር ወይም ከገብስ አንድ ‹‹ሷዕ›› እንዲወጣ ማዘዛቸውን በተመለከተም እነዚህ ዑለማዎች የሚሰጡት ምላሽ ‹‹መልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይሁን) እነዚህን የምግብ አይነቶች የጠቀሱት የመዲና ሰዎች በምግብነት ይጠቀሟቸው የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር ነው፡፡ ስለሆነም የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይሁን) አነሱ የሚያገኙትንና የሚመገቡትን የምግብ አይነት ነው እንዲያወጡ ያዘዟቸው›› የሚል ነው፡፡
በዚህም መሰረት በማንኛውም አካባቢ የሚኖር ሙስሊም ማህበረሰቡ አዘውትሮ ከሚመገባቸው የምግብ እህሎች ዘካተል ፊጥሩን መልዕክተኛው ሲጠቀሙበት በነበረው መስፈርያ መጠን ማውጣት ይችላል፡፡

√ ዘካተል ፊጥር መሰጠት የሚገባው ለማን ነው?

በዚህ ጉዳይ ላይ ዑለማዎች ሁለት አይነት አመለካከት ያለቸው ሲሆን ሚዛን የሚደፋው ሀሳብ ለምስኪኖች እና ለድሆች ብቻ ይሰጣል የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም በኢብኑ አባስ ሀዲስ ላይ መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይሁን) ‹‹ለምስኪኖች መብል …›› በማለት ዘካተል ፊጥር የተደነገገበትን አላማ ከመግለፃቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡

√ ዘካተል ፊጥርን በገንዘብ ተምኖ መክፈል

ዘካተል ፊጥርን በዋጋ ተምኖ መክፈል አይፈቀድም።
ምክንያቱም፤ በኢብኑ አባስ ሀዲስ ላይ መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በሳቸው ላይ ይሁን) ዘካተል ፊጥር የተደነገገበትን አላማ ሲገልፁ ‹‹ለምስኪኖች መብል …›› በማለታቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡
አቢ ሰዒድ አልኹድሪይ እንዲህ ብለዋል፤
“የአላህ መልዕክተኛ በነበሩበት ዘመን ዘካተል ፊጥር የምናወጣው ከምግብ አንድ ሷዕ ነበር” ብለዋል።
ዘካተል ፊጥርን ከተገደበለት ጊዜ ማስቀደም ወይም ማቆየት እንደማይቻል ሁሉ የአወጣጡን አይነትም መቀየር አይቻልም። ዒባዳ ሁልጊዜ በአላህ የሚደነገግ እንጂ በአስተያየት ምንፈፅመው አይደለም። ማንኛዉም ሙስሊም ዒባዳው እንዳይበላሽበት ሊጠነቀቅ ይገባዋል። በገንዘብ መተመን በቀደምት ሰለፎች አልተፈፀመም። ከጥቂቶች በቀር አብዛኞቹ የኢስላም ሊቃዉንት በገንዘብ ማዉጣትን ይቃወማሉ። አል-ኢማም ማሊክ፣ አል-ኢማም አሻፊዒይ እና አል-ኢማም አህመድ ይህ መዝሀባቸው ነው። ስለዚህም በተባለው መልኩ በእህል ያወጣ ሰው በሁሉም ስምምነት ትክክለኛ ዒባዳ ሰርቷል።

√ ዘካተል ፊጥርን ወደ ሌላ ቦታ መላክ፤

እያንዳንዱ ሙስሊም በጾመበት ቦታ ዘካተል ፊጥርን ማዉጣቱ ቢሆንም የሚያስፈልገው ነገር ግን ምግብ የሚቀበል ሚስኪን ሰው የሌለበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በቤተሰቦቻቸዉ ወይም ጓደኞቻቸው አማካኝነት ችግረኞች ወዳሉበት ቦታ መላክ ይችላሉ።
በጥቅሉ ማንኛዉም ሰው ኢባዳውን በኢልም ላይ የተመሰረተ በማድረግ ኢስላምን በሚገባ ለመተግበር መሞከር ይገባዋል።
تقبل الله الصّيام والقيام وجميع الطّاعات

ዝክረ ረመዳን مجالس شهر رمضان


አድራሻዎቻችን ይቀላቀሉ

ፌስቡክ           ቴሌግራም         ዩቲዩብ