Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የዘካ ፋይዳዎች እና ዘካን ያለመስጠት አደጋዎች!




የዘካ ፋይዳዎች እና ዘካን ያለመስጠት አደጋዎች!

~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~

ለሰጪው

① ዘካ ከአምስቱ የኢስላም ምሰሶዎች አንዱ እንደመሆኑ በትክክል የሚሰጥ ሰው ይህን የኢስላሙን ምሰሶ ነው ያፀናው። ባይሰጥ ደግሞ ይህን ምሰሶውን ነው ያናጋው።
② ዘካ በኢኽላስ እስከተወጣ ድረስ ኢማንን ይጨምራል፤ የአላህን ውዴታ ያጎናፅፋል።
③ ዘካ ወንጀልን ያብሳል። ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም "ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋው ሶደቃ ሃጢአትን ያጠፋል" ብለዋል።
④ ዘካ ፈተናን መከራን ይመክታል ።
⑤ ዘካ ማውጣት የአዛኝነት፣ የርህሩህነት፣ የተቆርቋሪነት ባህሪን ያላብሳል። ዛሬ ራስ ወዳድነት በነገሰበት ዘመን ለሙስሊም ወገን ከምላስ ባለፈ ከልብ መቆርቆርና ማዘን ትልቅ መታደል ነው።
⑥ ዘካ የቀልብ መለዘብ፣ በሞራል መገራት፣ ከክፋት፣ ከስስት፣ ከድንበር ዘለል የዱንያ ፍቅር እንዲወጡ ሰዎችን ያግዛል።
⑦ ዘካ የህሊና እርካታን ፣ መንፈሳዊ ሰላምን፣ ስነ ልቦናዊ መረጋጋትን ያጎናፅፋል።
⑧ ዘካ ገንዘብን ያፋፋል፣ በረካ ይጨምርበታል።
⑨ ዘካ ለችግር ጊዜ ደራሽ ወገን እንዲኖረንም ይጠቅማል። መቼም ሁሌ ድሎት፣ ሁሌ ምቾት የለም። ዱንያ ተገለባባጭ ናት።

ለተቀባዩ ደግሞ

~~~~~~~~
① በዘካ ድሃዎች ይደጎማሉ ወይም ይቋቋማሉ።
② ሃብታሙን በቅናትና በክፋት ከማየት እንዲታቀቡ ያግዛቸዋል።
③ ይህን የሚደጎሙበትን ህግ ለዘረጋው ጌታ ውዴታ ለሃይማኖታቸውም ቀናኢነትን እንዲያሳድሩ ይጠቅማቸዋል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ከፊሉ ጌታውን ሊያማርር፣ ኢማኑ ሊሸረሸር ይችላል።
④ ለገንዘብ ሲሉ እምነታቸውን ከመሸጥ፣ በጥፋት ላይ ከመሰማራት ያቅባቸዋል።

የዘካ ማህበራዊ ፋይዳዎች

~~~~~~~~~~~
① በሰጭና በተቀባይ መካከል ትስስር እንዲጠነክር ያደርጋል። ዝምዳናን ይቀጥላል። የሰመረ ጉርብትና እንዲኖር ያግዛል። ምክንያቱም ነፍስ በጎ ለዋለላት አካል ተዘንባይ ነችና።
② ዘካ በአግባቡ ከተወጣ በሀብታሙና በደሃው መካከል ያለውን የሃብት ርቀት ስለሚያጠብ ለጤናማ ኢኮኖሚ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
③ ዘካ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ወገኖች ተስፋ በመቁረጥ ወደ ስርቆትና ዝርፊያ በማምራት ማህበራዊ ቀውስ እንዳይፈጥሩ ይታደጋል።
④ ዘካ ሀብታሙን ሃላፊነት እንዲሰማው ስለሚያደርግ ከስግብግብ የካፒታሊዝም አስተሳሰብ በማቀብ የሃገር ሐብት በጥቂቶች እጅ ብቻ እንዳይሆን ያግዛል።

ዘካ አለመስጠት ያለው አደጋ

~~~~~~~~~~~~~~~~~
ባጭሩ እስካሁን የተዘረዘሩትን ፋይዳዎች ያሳጣል። የዱንያም የአኺራም ኪሳራን ያስከትላል። ሰጪንም፣ ተቀባይንም፣ ማህበረሰብንም አገርንም ይጎዳል።

ወገኔ ሆይ! ዘካ ወጅቦብሀል? እንግዲያውስ ውለታ ቢስ አትሁን። ላንተ የሰጠህ ጌታ ነው "ስጥ" ብሎ ያዘዘህ። በሰፊው ከሰጠህ ነው ጢኒጥየ ቆንጥረህ ስጥ ያለህ። ልብህ ፈታ ብሎ፣ ደስ ብሎህ ስጥ። ደስ እያለህ ጀነትን ትወርሳለህ።
ደግሞ አትሸወድ! ዘካ ገንዘብህን ያፋፋዋል እንጂ አይቀንሰውም። ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም "የአንድን ባሪያ ገንዘብ ሶደቃ አይቀንሰውም" ብለዋል።
በነገርህ ላይ የዘካው መጠን ያንተ ድርሻ፣ ያንተ ገንዘብ አይደለም። ዘካውን ባስቀረህ ጊዜ የሰው ሐቅ እየበላህ እንደሆነ ይታወቅህ። አይሰቀጥጥም? "ላቤን ጠፍ አድርጌ ያመጣሁት ነው" እያልክ የምትጎረር ከሆንክ ግን የነ ቃሩን ባቡር ላይ ተሳፍረሀል። ወዴት እንደሚወስድህ አልነግርህም።
ወንድሜ! ያገኘህ ባንተ ብልጠትም ብቃትም አይደለም። ስንት የበቁ የነቁ በድህነት እየማቀቁ መሰለህ?! ስንት መንቻካ ዶክተሮች ፕሮፌሰሮች ስንት ቁልቁል መደመር የማይችሉ ቱጃሮች አሉ።
ይልቅ ልንገርህ! ሌሎችን በድህነት የሚፈትነው ጌታ አንተን በሃብት እየፈተነህ ነው። እራስህ በምታዝበት ገንዘብ ፈተናውን ከወደቅክ አሳዛኝ ክሽፈት ነው። ገንዘብህ ተከትሎህ ቀብር አይገባም። ወራሽ ወገኖችህ የቀብር ጥያቄን፣ የአላህን ምርመራ አይታደጉህም። ዛሬ ነገ አትበል! ሞት አለቅጥ የበዛበት ዘመን ላይ ነን። እንደ ወጣ የሚቀረውን ብዛት እያየን ነው። ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘካ የማያወጣ ሰው ነገ በቂያማ ቀን የገዛ ገንዘቡ እባብ ሆኖ እንደሚያሰቃየው የተናገሩትን አስብ።
ደግሞም ዙሪያ ገባህን አስተውል። እድለኛ ማለት ሌላው ከደረሰው የተመከረ ነው። አላህ ሃብት ከሰጣቸው በኋላ ዘካ ሳያወጡ፣ሳያውቁ ሐጅ ሳይፈፅሙ አልፈው በቁጭት ወላፈን እየተለበለቡ ያሉ ስንት አግኝተው ያጡ ወገኖች አሉ?!
ባጭሩ ገንዘብህ ወይ ጀነትህ ወይ ጀሀነምህ ነው። ምርጫው ደግሞ በእጅህ ነው። ያሻህን ምረጥ።

Post a Comment

0 Comments