Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጥያቄ ፦ #ኢስቲዋእ_ማለት_ምን_ማለት ነው? ብታብራሩልኝ? ግሩፕ ላይ ሲከራከሩበት ግራ ገብቶኝ ነው።



➠ጥያቄ ፦ #ኢስቲዋእ_ማለት_ምን_ማለት ነው? ብታብራሩልኝ? ግሩፕ ላይ ሲከራከሩበት ግራ ገብቶኝ ነው።
➠መልስ ፦ "ኢስቲዋእ" ብሎ ማለት ፦ ከፍ ማለት እላይ መሆን ማለት ነው። ቁርአን ላይ አላህ - ተባረከ ወተዓላ - ግልፅ በሆነ መልኩ በ7 የቁርአን አንቀፆች "አር-ረሕማኑ ዓለል ዐርሺ ስተዋ" { الرَّحْمَٰنُ عَلَى الْعَرْشِ اسْتَوَىٰ } ብሏል።
°
ሱረቱ- ሰጅዳ ፣ ሱረቱል ሐዲድ ፣ አዕራፍ እና ጣሃ ሌሎችም ላይ ፤ እነዚህ የቁርአን አንቀፆች ደጋግ ቀደምቶች "ዓላ , ወርተፈዓ , ወሷዐደ , ወስተቀርረ" ብለው "ፈስረዋቸዋል"/(ተርጉመዋቸዋል)(①)። ደጋግ ቀደምቶች ዘንድ በእነዚህ በ4 ቃላቶች ነው የተተረጎመው። ሁሉም የሚያመላክቱት #እላይ_መሆንን ነው። አላህ - ተባረከ ወተዓላ - ከፍጡራን ሁሉ #ከፍ_ብሎ_ከአርሹ_በላይ_ነው_ያለው። ይሄም የነብያት ፣ የሶሐቦች ፣ የታቢዒዮችና የመላው የደጋግ ቀደምቶች አቋም ነው።
°
"ኢስተዋ" የሚለውን "ኢስተውላ" ብሎ "መፈሰር"/(መተርጎም) አላህ እራሱ እላይ አይደለም ፣ በየሌሊቱም ወደ ቅርቧ ሰማይ የሚወርደው አላህ አይደለም "ረሕመቱ" /(እዝነቱ) ነው ያለ ሠው ወይም ደግሞ ዐርሽ ማለት ንግስና ማለት ነው ብሎ አጣሞ የ"ፈሰረ"/(የተረጎመ) ሰው "ሙብተዲዕ" እንደሆነ ደጋግ ቀደምቶች ጠቅሰዋል፡፡
°
ረሡሉ - ዓለይሂሶላቱወሰላም- እነዚህ የቁርአን አንቀፆችን ሲያነቡ ሶሓቦች "ኢስተዋ" የሚለውን በቋንቋ የሚታወቀውን "ኢስቲዋእ" ነው የተረዱት። ታብዒዮችም ከሰሖቦች ይሄን የቁርአን አንቀፅ ሲማሩ "ኢስተዋ" ማለት እነሱ ዘንድ ከፍ አለ , እላይ ሆነ የሚል ትርጉም ነውና ያለው በዚሁ ተረድተውት ነው ያለፉት። ምርጥ የተባለዉ ትውልድ ካለቀ በኋላ ፣ ሰሓቦች ታብዒዮች ከጌታቸው ከተገናኙ በኋላ ነው "ኢስተዋ" ለሚለው "ኢስተውላ" የሚል ትርጉም የሰጡት።
°
"ኢስተዋ"ም ከፍ አለ , እላይ ሆነ የሚለዉ "ኢስተውላ"/(ተሾመ) ነው ብሎ "ለመፈሰር"/(ለመተርጎም) የሚረዳ የቁርአንም ይሁን የሐዲስ ፣ የሶሐባ ፣ የታብዒይ ንግግር የለም። ዐረብኛ ላይም አይታወቅም መጤ እና ከጊዜ በኋላ የተፈጠረ ቃል ነው ብለዋል ትልልቅ የቋንቋ ሊቃዉንት(②)። ስለዚህ ቁርአን እና ሐዲስ ላይ የማይታወቅ ፣ ሶሐቦች ታዕብዮች ዘንድ የማይታወቅ ፣ የቋንቋ ዑለሞች ዘንድ የማይታወቅ ነገር በመያዝ ግልፅ የሆኑ የቁርአን የሐዲስ ጥቅሶችን በመተዉ ደጋግ ቀደምቶች የተስማሙበትን "ኢስተዋ" "ዓላ" "ወርተፋዕ"#ከፍ አለ ፣ #ከአርሽ_በላይ_ሆነ የሚለውን ትርጉም በመተው ስልጣኑ ከፍ አለ ብሎ "መፈሰር"/(መተርጎም) ትልቅ የሆነ ስህተትና ጥመት ነው፡፡
°
ብዙ ሰዎች ሻፍዒይ ነን ከማለታቸው ጋር ኢማሙ-ሻፍዒይ ግልፅ በሆነ መልኩ ኪታቦቻቸው ላይ አላህ ሠማይ (ላይ) እንደሆነ ፣ ከዐርሹ በላይ እንደሆነ እናምናለን ብለው የተናገሩትን ንግግራቸውን (③) አይቀበሉም። አሽዐሪይ ነን ከማለታቸው አቡልሐሰን አሽዐሪይ እንዲዚሁ በርካታ የመዝሀባቸው ተከታዬች አላህ - ተባረከወተዓላ - ከዐርሽ በላይ መሆኑን በግልፅ በማያሻማ መልኩ ተናግረው ሳለ ግልፁን ትተው በፊቅህ እነሱን እንከተላለን በዐቂዳ አቡልሐሰን አልአሽዐሪይን እንከተላለን ይላሉ። አቡልሐሰን አልአሽዐሪይ ቶብተዋል መጨረሻ ላይ .. (ብዙ ሰዎች እንዳወሩት ማለት ነው) ፤ ወደ ሶሖቦች , ታብዒዮች መንገድ ተመልሰዋል።
°
አላህ ከዐርሽ በላይ ነው ካልን አላህ በቦታ መገደብ ይሆንብናል ነው ሚሉት። ይህ ለቁርአንና ሐዲስ ጥቅሶች እጅ እግር ያለመስጠት ምልክት ነዉ። ቁርአን እና ሐዲስ ላይ ከተረጋገጠ ሙእሚን መሻሻ ሊኖረዉ አይገባም ፤ አምኛለሁ ተቀብያለሁ ሊል ነው የሚገባው። ለኛ የሚከብዱን ነገሮች ካሉም ሶሐቦች እና ታብዒዮች ምን ብለው "ፈሰሩት"/(ተረጎሙት) , እንዴት ተረዱት ልንል ነው የሚገባው። ሰሐቦች የበቃቸዉ ሊበቃን ይገባል።#እነሱ_ያላንኳኩትን_በር_ከማንኳኳት_ልንጠነቀቅ_ይገባናል
°
"አር-ረሕማኑ ዓለል ዐርሺስተዋ"/ { الرَّحْمَٰنُ عَلَى الْعَرْشِ اسْتَوَىٰ } የሚለዉን ግልፅ በሆነ መልኩ ሰባት የቁርአን አንቀፆች ላይ ነብዩ (- ﷺ -) ሲያነቡ, ሶሐቦች ሲሰሙት "ከይፈ-ስተዋዕ?" ምን ማለት ነዉ ኢስተዋ ማለት? እንዴት አላህ ከዐርሽ በላይ ይሆናል? ይህ ለአላህ ቦታ ማፅደቅ, አላህን በአቅጣጫ መገደብ አይሆንም ወይ? ብሎ የትኛውም ሶሐባ አለነሳም ፤ የትኛውም ታብዒይ አላነሳም። እነሱ ያላነሱትን ማንሳታችን ወይም ከእነሱ በኢማን በዒልም በልጠናል ማለት ነው ፤ (ካልሆነ) ጠመናል ማለት ነው። ከእነሱ በኢማን በዒልም እንደማንበልጥ አላህ, ቁርአን ነግሮናል , ነብይ (- ﷺ -) ነግረውናል ፤ እንግዲያዉስ ሊሆን የሚችለዉ ሁለተኛው ነው። (አላህን ከዚህ ሰላም እና ዐፊያ እንዲያደርገን እንጠይቀዋለን።)
°
{ فَإِنْ آمَنُوا بِمِثْلِ مَا آمَنتُم بِهِ فَقَدِ اهْتَدَوا ۖ .. } (④)
ሶሓቦች ባመኑት መልኩ ካመንን ቀናዉን መንገድ እንደጨበጥን አላህ መስክሮልናል ፤ ግራ ቀኙን ካልን ከአላህ እና ከመልክተኛዉ እንደተጋጨን ቁርአን በይፋ ነግሮናል።
°
በርካታ የ"አሳር"/(የፋና) የሱና ዘጋቢዎች እንደጠቀሱት ከኢማሙ ማሊክ ጋ አንዱ መጥቶ "አር-ረሕማኑ ዓለል ዐርሺስተዋ" "ከይፍ ኢስተዋ"? አላቸዉ ፤ ቁርአን ላይ "አር-ረህማኑ ዓለል ዐርሺስተዋ" ብሏል ፤ እንዴት ነዉ ኢስተዋእ ያደረገው? ሲላቸው |" ኢማሙ ማሊክ አንገታቸዉን ደፉ , ላብም ጠመቃቸው , ሰዎች በጣም ተደናገጡ ፤ ከዛ ቀና ብለዉ "ኢስቲዋእ" ምን ማለት እንደሆነ ሰዎች በቋንቋ ያውቁታል ፤ ከላይ መሆን ማለት ነዉ። (ይህ ከኢማሙ ማሊክ - አላህ ይዘንላቸውና - አባባል ትክክለኛው ትርጉም ነው)። "ኢስቲዋእ" ማለት ቃሉ ይታወቃል ትርጉሙ አይታወቅም እንደሚሉት አይደለም ፤#ትርጉሙም_ቃሉም_ግልፅ_ነው። በዐረቦች ዘንድ ከፍ አለ, ከላይ ሆነ ማለት ነው ፤ በዚህ ማመን "ዋጂብ" እና ግዴታ ነው። "ከይፊያው" እንዴት እንደሆነ አላህ በምን መልኩ ግን ከአርሽ በላይ እንደሆነ አይታወቅም። እንዴት ነው አላህ ከዐርሽ በላይ የሆነው ብሎ መጠየቅ ቢድዓ ነው። አንተ ደሞ ተንኮለኛ ሸረኛ ሰው ትመስለኛለህ ፤ አስወጡት ከዚ መድረክ ብለው እንዲወጣ አድርገዋል። "| (⑤)
°
(ስለዚህ) አላህ ከዐርሽ በላይ ነዉ ብሎ ማመን የኢማሙ አቡ ሐኒፋ ፣ የኢማሙ ማሊክ ፣ የኢማሙ አሽ-ሻፍዒይ ፣ የኢማሙ አሕመድ እና የነሱ ቅርብ ደረሳ እና ተማሪዎች እና ተከታዮቻቸው በሙሉ የጋራ አቋማቸዉ ነው (⑥)። ለራሱ "ነጃትን"/(ስኬትን) ፣ ሰላምን የሚፈልግ ሰው እነሱ በሄዱበት መንገድ ሊሄድ ይገባዋል። ኢብኑ ዐብዱልበር የሚባሉት የፊቅህና የሐዲስ አዋቂ 463ኛው አመተ ሒጅራ ላይ የሞቱት |" አህሉስ-ሱንና ወል ጀማዐህ ቁርአንና ሐዲስ ላይ የተነገሩ የአላህን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ አምኖ መቀበል ላይ ተስማምተዋል። ስለአላህ ባህሪያት የሚናገሩ የቁርአን ጥቅሶችም "መጃዝ" ሳይሆኑ ሐቂቃም እንደሆኑ ተስማምተዋል ፤ ነገር ግን የአላህን ባህሪ እንዲህ ብለው ከፍጡራን ጋር አያመሳስሉም።
°
አህሉል ቢድዓዎች ግን ጀህምዮች እና መሰሎቻቸውም እንደዚሁ ሙዕተዚላዎች የአላህ ባህሪያት ውድቅ ያደርጋሉ አይቀበሉም ፤ መጃዝም ነው ይላሉ ፤ ቁርአንና ሐዲስ ላይ ስለ አላህ ባህሪያት የሚናገሩ ጥቅሶችን ለምሳሌ ፦ አላህ ከዐርሽ በላይ ነው የሚሉ ፣ አላህ ይናገራል የሚሉ ፣ አላህ በየሌሊቱ ወደ ቅርቧ ሰማይ ይወርዳል የሚሉ ፣ የቂያም ቀን ለፍርድ ይመጣል የሚሉ ፣ መሰል ቁርአን ወይም ሐዲስ ላይ የተጠቀሱ ወይም ሁለቱም ላይ የተጠቀሱ ባህሪያትን አምኖ የተቀበለ ሰው አላህን ከፍጡራን (ጋር) ያመሳስላል ይላሉ ፤ ሐቂቃው ግን ቁርአንና ሐዲስ ላይ የተነገረውን በሙሉ አምኖ መቀበል ነው ፤ በዚህ ጉዳይ ላይም ደጋግ ቀደምቶችም መከተል ነው ብለዋል። "| (⑦)
°
አላህ እራሱ አልለ ብለን እንደ ምናምነው ሁሉ ቁርአንና ሐዲስ ላይ የተነገሩን የአላህ ባህሪያትንም አምነን ልንቀበል ይገባናል። አላህ አልለ ብለን አናምንም ምክንያቱም መኖር የሰው ልጅ ባህሪ ነው ፤ አላህም ይኖራል ካልን ከጡራን ጋር ማመሳሰል ነው ይሆናል እንደማንለው ሁሉ አላህ ከዐርሽ በላይ ነው። በምን መልኩ? አናውቅም ፤ አላህ ይስቃል። በምን መልኩ አናውቅም ፤ ለአላህ - ተባረከ ወተዓላ - እጅ አለው እግር አለው በቁርአን ተነግሮናል ፤ ምን አይነት ነው? አናውቅም ፤ እኛ የተነገረን እንዳለው ብቻ ነው ፤ እንዴት እንደሆነ ምን አይነት እንደሆነ አልተነገረንም። የተነገረንን ነገር ማመን አላህ ከፍጡራን ጋር ማመሳሰል አይደለም። {ۚ ﻟَﻴْﺲَ ﻛَﻤِﺜْﻠِﻪِ ﺷَﻲْءٌ } [| እሱን የሚመስል የለም። |]. ይሄ እጅግ በጣም ብዙዎች ፣ የጠመሙበት ፣ የሳቱበት ፣ ከረሱል ሱና የወጡበት ነጥብ ነውና መፍትሄው ቁርአን እና ሐዲስን ደጋግ ቀደምቶች በተረዱበት መልኩ መረዳት ነው።
°
አዳዲስን ነገር ይዘው የመጡ ሰዎች ማንም ይሁኑ ማን በእድሜ በዒልም የደረሱበት ቢደርሱ ፤ ደጋግ ቀደምቶች ያላመጡትን ነገር ካመጡ ፤ ደጋግ ቀደምቶች የተናገሩትን ካልተቀበሉ ፤ ልንከተላቸው አይገባም።#ሐቅን_በሰዎች_ልንለካ_አይገባም። ዲንን በዐቅልም ልንከተል አይገባም። በብዛትም ልንመዝነው አይገባም። ሐቅ ማለት ቁርአንና ሐዲስ ላይ በሶሐቦች ግንዛቤ መሰረት መረጃ ያለው ነገር ሲሆን ብቻ ነው። አላህ - ተባረከ ወተዓላ - ከፊትና ፣ ተሳስቶ ከማሳሳት ይጠብቀን ፣ "ኻቲማችንን"/(መጨረሻችንን) ያስተካክልልን። እሱ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ ነውና።
_______________
(①).(እንደምሳሌ ፦ "ኢትሀፉል ኸይረህ አልመሀረህ" ሊልቡሰይሪ ፥ 1/186 ፤ "አልመጧሊቡል ዓሊያ" ሊብኑ ሐጀር ፥ 12/570 ፤ ተፍሲሩ-ጦበሪ ፥ 27/216 ፤ ኢብኑልቀይም ፊ "ካፊያ ወሽ-ሻፊያ" ፥ 1/440)
(②).(እንደምሳሌ ፦ "ኢስባቱ ሲፋቱልዑሉው" ሊብኒ ቁዳማ ፥ 92-93)
(③).(ኢጅቲማዕ ጁዩሽ አልኢስላሚ ፥ 165 / "ኢስባተል ዑሉው" ፥ 124)
(④).(አልበቀራህ ፥ 137)
(⑤).(አስሷቡኒ ፊ "ዓቂደቲ አስ-ስለፍ አስሓቡል ሐዲስ" ፥ 17-18 ፤ ላለካኢይ ፊ" ሸርሕ ዓቂደቲ አህሊስ-ሱንነቲ ወልጀማዐህ ፥ 1/249)
(⑥).(እንደምሳሌ ፦ የኢማሙ አቡሐኒፋን "ፊቅሁል አብሰጥ" ፥ 46 ፤ የኢማሙ ሻፍዒይን "ኢጅቲማዕ ጁዩሽ አልኢስላሚ" ፥ 165 ; "ኢስባተል ዑሉው" ፥ 124 ፤ የኢማሙ ማሊክን "ኢብኑዐብዱልበር ፊ ተምሂድ" 7/13 ፤ የኢማሙ አሕመድን "ደርእ ተዓሩድ አልዐቅል ወንነቅል" 2/30)
(⑦).(ኢብኑ ዐብዱልበር ፊ "ተምሂድ" ፥ 7/129)
_______________________________________
ምንጭ ፦ ከኡስታዝ አህመድ አደም የዛዱል መዓድ ፈትዋ ቁ.55 ኦዲዮ ፋይል ላይ የተወሰደ።
✍️ከድምፅ ወደ ፅሑፍ የተለወጠው በሒክማ ቢንት ዐብዱልበር @ አፈር ነኝ
✍️ፅሑፉ ኤዲት የተደረገው በአቡልዓባስ አሕመድ ኢብን ያሕያ @ Ibn yahya Ahmed
ዙልሒጃህ 28/1439ሂ. # Sep. 8/2018

የቴሌግራም ቻናላችን ጆይን ያድርጉ፦ https://telegram.me/ibnyahya7
የፌስቡክ ፔጃችንን ላይክ ያድርጉ፦ https://m.facebook.com/ibnyahya777

Post a Comment

0 Comments