Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኢሬቻ እና መስቀል




#ኢሬቻ እና #መስቀል
.
.
ሐይማኖቶች አጥሮቻቸው ሳስተው በተቀላቀሉባት ሀገራችን መስከረም ወርን ጠብቀው ከሚከበሩ ቅይጥ በዓሎች የተወሰኑትን ለዛሬ እንመልከት። 
.
በዓሎቹ በክርስትና እምነት እና በዋቄፈና ዘልማዳዊ እምነት ላይ የሚከበሩ ናቸው። በዓላቱ እርስ በእርሳቸው የተደባለቀ እና ወደ ሌላውም የሰረገ አተገባበር ፈጥረው በጊዜ ሂደት ከሐይማኖታዊ ድባብ ባሻገር ባህላዊ ገፅታን ተላብሰዋል። 
(ስለዋቄፈና እምነት ለማወቅ ይህንን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ http://bit.do/exnAz )
.
በሌላበኩል በሀገራችን ያለው የብሄሮች የርስ በርስ ፉክክር እያንዳንዱ ብሔር በተወላጆቹ የሚከበረውን ሀይማኖታዊ በዓል ባህላዊ መልኩን በማጉላት የብሄሩን ገፅታ ለመገንባት እና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ሲጠቀምበት ይታያል። (የቅርብ ግዜውን 'የአሸንዳ' ፣ 'ሻደይ' ፉክክር ማስተዋል ይቻላል)
.
ከነዚህ በዓላት መካከል ደግሞ የመስከረም ወርን ተከትለው የሚመጡት የመስቀል በዓል እና ኢሬቻ ዋነኞቹ ናቸው።
.
#የመስቀል_በዓል የአላህን አንድነት ክደው ሶስት ነው ባሉት እና ከሰማይ ወርዶ በሰው እጅ ተሰቅሎ ሙቷል ብለው በሚያምኑት የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታዮች የሚከበር ሐይማኖታዊ በዓል ነው።
.
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እና በከተሞች አካባቢ የእምነቱ ተከታዮቹ እንደየስፍራው ባህላዊ ገፅታ ቢያላብሱትም በዋናነት ጭራሮ በማንደድ ሐይማኖታዊ መልኩን አጉልተው ያከብሩታል።
.
በኦሮሚያ አካባቢም ጉባ/መስቀላ እየተባለ ይከበራል። በዋቄፈታዎች ዘንድ ግን እምነትነቱን ትተው እንደ ተራ ባህላዊ በዓል አድርገው ያሳልፉታል። 
.
በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ደግሞ ባንዳንዶቹ ዘንድ 'ያሆዴ መስቀላ' ፣ 'ማሽቃሮ' እየተባለ እንደ ዘመን መለወጫ ሲቆጠር በሌሎች ዘንድ ደግሞ 'ዮ ማስቃላ' ፣ 'መስቀር' እየተባለ እንደ ቤተሰብ መጠየቂያ እና አመታዊ መገናኛ በዓል ይደረጋል።
.
በነኝህ አካባቢዎች በዓሉ ከእምነትነቱ ወደ ባህሉ ያዘነበለ ገፅታ ያለው ቢሆንም መነሻው የክርስትና እምነት ክብረበዓል እንደመሆኑ መሰረቱን አልለቀቀም።
.
.
ወደ #እሬቻ ስንመጣ ደግሞ በዓሉ በዘልማዳዊው የዋቄፈና እምነት ከሚከበሩት ሁለት እሬቻዎች አንደኛው ነው። በቀድሞ ግዜ በጠንቋዮች አማካኝነት ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ባለው ወቅት ቀኑ የሚቆረጥ ነበር። አሁን አሁን ግን የመስቀል በዓልን ተከትሎ እስከ መስከረም 24 ድረስ ባለው እሁድ እንዲከበር ተደርጓል።
.
በዓሉን በአሁኑ ግዜ ከሶስት ፐርሰንት የማይልቁት የዋቄፈና እምነት ተከታዮች እንደ ሀይማኖታዊ በዓል ያከብሩታል። በዓሉ በዋቄፈታዎች ዘንድ ከድሮ ጀምሮ "ከክረምት ጨለማ ስለወጣን ለ'ዋቃ' ምስጋና እናቅርብ" ብለው የሚያከብሩት እንደነበረ ይነገራል። በአሁኑ ግዜ ግን እምነታቸው ክርስትና የሆኑ አንዳንዴም ሙስሊም ነን የሚሉም ሰዎች በዓሉን ለመታደም ሲገኙ ይስተዋላል።
.
#እሬቻ በሀይቅ ወይም ወንዝ ዳር ቄጠማ ይዞ በመሄድ እና በውሀው ላይ በመበተን ይከበራል። ቢሾፍቱ ሆራ-አርሰዴ እንደሚታየው ማለት ነው። የበዓሉ ታዳሚዋች 'አያንቱ' ለሚባሉ 'የሙት መንፈስ ያረፈባቸው ናቸው' ብለው ለሚያምኑባቸው ሰዎች ገንዘብ እየሰጡ ይለማመናሉ። ለሀይቁ (በውስጡ አለ ብለው ለሚያምኑበት ጂን) የተለያዩ ስጦታዎችን (ሽቶ፣ ዶሮ ...) ሲጥሉ እና ሲለማመኑም ይስተዋላል።
.
የኢሬቻ በዓል ግልፅ የዋቄፈና ዘልማዳዊ እምነት ተግባር መሆኑ አያሻማም። እንዳውም በበዓሉ የተለያዩ ባዕድ አምልኮዎች የሚፈፀሙበት የሽርክ መነኻሪያ የሆነ በዓልም ነው። 
.
ይሁንና አንዳንዶች ይህን በመሸፋፈን በዓሉን ከኦሮሞ ባህል እሴቶች አንዱ በማስመሰል ለማቅረብ ሲታትሩ ይታያል። ይህ በተለይ ለዋቄፈታዎች እምነታቸውን በኦሮሞ እሴት ስም እንዲያስፋፉ በር ከፍቶላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከመቃወም አፋቸውን እንዲይዙ ምክንያት ሁኗል።
.
አሁን ያለው የመንግስት አወቃቀር ክልሎች እና ልዩ ዞኖች በዘውግ ፓለቲካ እንዲተዳደሩ ያደረገ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ብሔር በእኔ እበልጥ መንፈስ ባህሌ ብሎ የሚያስበውን ሁሉ መገለጫው ለማድረግ ይደክማል። 
.
በተጨማሪም ብሄርተኛው ባህሌ ባለው እሴት ላይ የሚቀርብ ሐይማኖታዊም ሆነ ሌላ ትችት እንደ ብሔር ጥቃት ወይም ጥላቻ ንግግር (hate speech) ለመቁጠር ወይም ለማስቆጠር ይሞክራል። በዚህም ከትችት ለመዳን ሲጥር ይታይል።
.
በሌላ በኩል የየክልሉ ወይም ዞኑ አመራር የቱሪስት ወይም የኢንቨስትመንት ገቢ ለማግኘት ሲል ሐይማኖታዊ በዓሎችን የተለየ ባህላዊ ገፅታ በማላበስ በፌስቲቫል መልክ ራስን ማስተዋወቂያ ለማድረግ ይጥርባቸዋል።
.
በዚህ ሂደት የብሄሩ ተወላጆች አንድም ከብሄርተኝነት በመነሳት በሌላ በኩል ደግሞ በቀና መንፈስ አካባቢያቸውን ለማልማት በማሰብ እንኝህን በዓላት የኔ ብለው እንዲቀበሉ እየተደረገ ይገኛል። 
.
እናም የኛው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሁሉም ወደየጎጡ እየገባ በጎሳው ጥላ ስር ሲሰበሰብ በሚፈጠርበት የከማን አንሼ ግፊት እርሱም 'የአካባቢዬን ሰው ልጥቀም' ፣ 'የኔን አካባቢ ላልማ' በሚል ወይም በእልህ በሚነሳ የብሄርኝነት መንፈስ የማያምንበትንና ከዲኑ የሚያጋጨውን የሌላ እምነት በዓል እንዲያከብር ምክንያት እየፈጠረ ይገኛል።
.
ይህ ደግሞ በግለሰቡ እምነት/ተውሒድ ላይ ከሚያደርሰው ብልሽት በተጨማሪ ለሙስሊሙ ባጠቃላይ የዓቂዳ/እምነት መበከልን የሚያመጣ እንዲሁም ሙስሊሙን የሚከፋፍል መቅሰፍት ይሆናል።
.
ይህን እያየን እንዳላየን የምናልፍ ከሆነ ሙስሊሙ ወገናችን በባህል ተታኮ በየሽርክ ማጥ ውስጥ ሲዘፈቅ እንዲሁም እስልምናን ክዶ ሲከፍር የምናፀድቅ ሁነናል ማለት ነው። በዚህ አካሄድ ኩፍር በእያንድንዳችን ደጃፍ ከመድረሷ ቀድሞ ዳዕዋ ባለማድረጋችን የሚመዘገብብን ወንጀል የገዘፈ ይሆናል።
.
ስለሆነም በቅድሚያ ሙስሊሙን ማሕበረሰብ ወደ ብሄርተኝነት ከሚወስደው የዘረኝነት ደዌ ማስጠንቀቅ እና ዘረኝነት ነብያችን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ያወገዙት የጃሂሊያ/ድንቁርና መገለጫ ከባድ ወንጀል መሆኑን ማስተማር አለብን። [ስለ ዘረኝነት አጥፊነት የሚያትቱ የነብያችንን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሐዲሶች በዚህ ሊንክ ያገኛሉ http://bit.do/exny8 ]
.
በመቀጠል እስልምናችን ከየትኛውም ባህል እና ወግ ተቀዳሚ እንደሆነ እና ዲናችን የህይወት መመሪያችን በመሆኑ እርሱን ከሚቃረን ማንኛውም ነገር ልንታቀብ እንደሚገባ ማሳወቅ አለብን።
.
በተለይ በከሀድያን በዓላት መገኘት እጅግ ከባድ የሆነ ወንጀል መሆኑን እና በበዓሉ አምነንበት ከሆነ ደግሞ ከእስልምናም የሚያስወጣን የኩፍር ወንጀል መሆኑን ማስተማር አለብን። 
.
እንኳንስ የኩፍር በዓልን መታደም ይቅርና 'እንኳን አደረሳችሁ' ማለት እንደማይፈቀድ፣ በበዓላቸውም ሆነ እምነታቸው እነርሱን መተባበር ክልክል መሆኑን ማሳወቅ አለብን። (የከሀድያንን በዓል ማክበርን በተመለከተ ስለ አሸንዳና ቡሄ የተፃፈውን ፅሁፍ ከዚህ ሊንክ ይመልከቱ http://bit.do/exoEv )
.
እምነታንን የምንጠብቅበት ድንበር ምን መምሰል እንዳለበት በይበልጥ ለመረዳት 'አጥር አለ' የሚለውን ተከታታይ ፅሁፍ እንዲያነቡት እጠቁማለሁ። ፅሁፉን በዚህ ሊንክ http://bit.do/ewmkz ያገኙታል። በዚሁ ርእስ ስር ከከሀድያን ጋር የምንኗኗርባቸውን መሰረታዊ ምሳሌዎች የሚያትተውን ክፍል ደግሞ በዚህ ሊንክ ያገኙታል http://bit.do/ewAyq 
.
.
አላህ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ያፅናን!
.
.
#Share ማድረግ አይዘንጉ!


Mohammed Ibrahim Ali

Post a Comment

0 Comments