Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኢስቲጋሳ (የድረሱልኝ ጥሪ)





ኢስቲጋሳ ማለት ከችጋር እና ጥፋት ለመውጣት ከሌላ እርዳታን መሻት ነው፡፡ ኢስቲጋሳ ምርጥ ከሚባሉት ስራዎች አንዱ ነው፡፡ በበድር ዘመቻ ወቅት የመካ አጋርያን ቁጥር ከአንድ ሺህ የሚልቅ ሲሆን በነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዙሪያ የተሰለፉት ሶሀባዎች ገን 313 ብቻ ነበሩ፤ ያውም በበቂ ሁኔታ ያልታጠቁ፡፡ ነቢያችን(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በዚህ የጭንቅ ወቅት ያደረጉት ቢኖር ኢስቲጋሳ ነበር፡፡ እጃቸውን ወደ ጌታቸው አንስተው የድረስልኝ ጥሪ ማሰማቱን ተያያዙት፤ ችክ ብለው ለመኑት፡፡ አላህም ቃል የገባውን ሞላ፤ መላእክቶቹን አወረደ፡፡ ኢስላምን ለማጥፋት የመጡት የመካ ሙሽሪኮች ተሸንፈው በውርደት እንዲመለሱ አደረገ፡፡ ምስጋና ለአላህ ይገባው!
إِذْ تَسْتَغِيثُونَ رَبَّكُمْ فَاسْتَجَابَ لَكُمْ أَنِّي مُمِدُّكُم بِأَلْفٍ مِّنَ الْمَلَائِكَةِ مُرْدِفِينَ [٨:٩]
“ከጌታችሁ እርዳታን በፈለጋችሁ ጊዜ «እኔ በሺህ መላእክት ተከታታዮች ሲኾኑ እረዳችኋለሁ» ሲል ለናንተ የተቀበላችሁን (አስታውሱ)” አል-አንፋል 9
ታዲያ ኢስቲጋሳ በጭንቅ ጊዜ ወደ አላህ የምንተኩሰው የድረስልኝ ጥሪ ሲሆን በአምልኮት ተግባራት (በመተናነስ፣ መስገድ፣ ስለት በመግባት፣ በፍራቻ፣ ሙሉ ተስፋ በማድረግ …) በመፈጸም የሚጠየቅ ኢስቲጋሳ ፈጽሞ ከአላህ ውጪ ለሆነ አካል መስጠት አይቻልም፤ እንዳውም ከኢስላም የሚያስወጣው ከባዱ ሽርክ ነው፡፡
ነገርግን አንዳንዴ ህያው እና በጉዳዩ ላይ ቻይ የሆኑ ፍጡራን ለችግራችን እንዲረዱን ብንጠይቃቸው አያስወቅስም፡፡ ፍጡራንን እርዳ ለመጠየቅ የሚከተሉት መስፈርቶች መሟላት አለባቸው
1. ተጠያቂዎቹ በህይወት መኖር አለባቸው
2. እርዳታ ስንጠይቃቸው ህዋሳዊ በሆነ መንገድ ሊሰሙን የሚችሉ መሆን አለባቸው
3. እርዳታ በምንጠይቃቸው ጉዳይ ላይ ቻይ(ብቃት ያላቸው) መሆን አለባቸው፡፡
ተጠያቂዎቹ አካላት ሙታን ከሆኑ ሰውየው እየፈጸመው የሚገኘው ከባዱ ሽርክ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አደጋ ሲደርስ እንደ ቃጥባሬ፣ አብሬት፣ አባድር፣ አብዶዬ፣ ውቃቢ፣ አድባር፣ ቆሪጥ … የመሳሰሉትን የሞቱ ደጋግ የአላህ ባሮችንና ምንም አቅም የሌላቸው ደካማ ጂኖችን ድረሱልኝ ብሎ መጠየቅ ስራን ሁሉ የሚያበላሽ ሽርክ ነው፡፡
እንደዚሁም በህይወት ያሉ ነገር ግን የሰውየውን ጥሪ ሊያደምጡ የማይችሉ ወይም በሚጠየቁበት ጉዳይ ላይ እርዳታ መለገስ የማይችሉ ፍጡራንን መማፀን በጀሀነም ዘውታሪ የሚያደርገው አላህ የዛተበት የሽርክ ተግባር ነው፡፡
ለምሳሌ አንዳንድ ክፍለ ሀገራት ሰርግ አሊያም ለቅሶ ሲኖር እና በድግሱ ቀን ዝናብ ሊዘንብ ከደማመነ ነዋሪዎቹ ያዘጋጁት ፕሮግራም በዝናቡ እንዳይበላሽባቸው በመስጋት ገንዘብ አዋጥተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ በዚህ ስራ የሚታወቅ ሸህ/ወሊይ/ቃልቻ(ጠንቋይ) ዘንድ በመሄድ ዝናቡን “እንዲይዝላቸው” ይማጸናሉ፡፡ የሚገርመው አላህ በራሱ ፈቃድ ዝናቡን ቢያቆመው ያ ሸህ ተብዬ ዝናቡን እንደያዘው የሚወራለት ሲሆን የአላህ ቀድር ሆኖ ቢዘንብ ግን ሸህየው ወይ የተሰጠው ገንዘብ አንሶት አሊያም ሰዎቹ በአግባቡ የሚሰጠውን ነገር ሳያደርሱ ቀርተው ነው ተብሎ ይወራለታል፡፡ ሱብሀን አላህ!
ይህ ግልጽ የሆነ የሽርክ ተግባር ሲሆን ፈጻሚዎቹ ምናልባት ባለማወቅ ሊፈጽሙት ስለሚችሉ ሙሽሪክ ናችሁ ብለን አንደመድምም፤ ለተክፊር አንፈጥንም! ነገር ግን የተውሂድ ትምህርት እንዲደርሳቸውና እየፈጸሙት ካሉት እጅግ አደገኛ ተግባር እንዲታቀቡ በጥበብ ማስተማር የሁላችን ሐላፊነት ነው፡፡
አላህ ሀላፊነታችንን የምንወጣ ያድርገን!


Abu Ibrahim Mohammed Ibrahim