ሃሜት አስቀያሚ ወንጀል እንደሆነ ለብዙዎቻችን አይሰወርም፡፡ ግና ከዚህ አደገኛ ወንጀል ለመራቅ የምናደርገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የሚገርመው ይበልጥ የምናማው ይበልጥ ሐቅ ያለብን አካል መሆኑ ነው፡፡
1. ከሩቅ ሰው ይልቅ ጎረቤታችንን እናማለን፡፡ ግና “በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ሰው ጎረቤቱን ያክብር” ነበር የተባልነው፡፡
2. ከባዳ ይልቅ ዘመዳችንን እናማለን፡፡ የዝምድና ሐቅ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ አይሰወረንም፡፡ እኛ ግን ዝምድናን ከመቀጠል ይልቅ ዝምድና የሚቆረጥበት ምላጭ እንሆናለን፡፡
3. ከጠላት ይልቅ ወዳጃችንን እናማለን፡፡ ይሄ አደገኛ ሸፍጥ ነው፡፡ እስኪ አሁን ማን ነበር ይበልጥ ባለሐቁ?! ከፊት አብሮ ገልፍጦ ዞር ሲሉ በነገር ጩቤ መውጋት ምን አይነት ክህደት ነው?!
4. ውለታ ከሌለብን ይልቅ ውለታ ያለብንን እናማለን፡፡ ሱብሓነላህ!! የኛ ነገር ሲበዛ ግራ ነው፡፡
5. ከካፊር ይልቅ ሙስሊምን እናማለን፡፡ ግና “ሙስሊም ህይወቱም፣ ገንዘቡም፣ ክብሩም ሐራም ነው” ተብለን ነበር፡፡
6. ቅርበት ከሌለን ይልቅ ጓደኛችንን እናማለን፡፡ አላሁል ሙስተዓን፡፡ ሰው እንዴት ጓደኛውን ያማል?! ሰዎች ስንባል ምን ያክል መሰሪዎች ነን?!
7. ኧረ ከዚህም በላይ ወላጆቻችንንና ባለቤቶቻችንን ሁሉ እናማለን፡፡ ኢንና ሊላሂ ወኢንና ኢለይሂ ራጂዑን!! “ኡፍ እንዳትል” እየተባልን እኛ ግን የት እንደምንደርስ አስቡት፡፡ “ከናንተ በላጫችሁ ለቤተሰቡ መልካም የሆነው ነው” እየተባልንም እኛ ግን የት እንደምንደርስ አስቡት፡፡ አቤት የኛ ነገር፡፡ ጌታችን “የሰው ልጅ በዳይና ደንቆሮ ነው!” ሲል ምንኛ እውነት ተናገረ?!!
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጳጉሜ 2/2008)