Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጌታችን አላህ የሌሊቱ ሲሶ(1/3)ኛ ሲቀር ወደ ቅርቢቱ ሰማይ ይወርዳል. ጌታችን አላህ ከዐርሽ በላይ መሆኑን እናምናለን



ጌታችን አላህ የሌሊቱ ሲሶ(1/3)ኛ ሲቀር ወደ ቅርቢቱ ሰማይ ይወርዳል.
ጌታችን አላህ ከዐርሽ በላይ መሆኑን እናምናለን
አሏሁ - ተዓላ - መልካም ስሞች እና ባህሪያቶች አሉት። የአላህን - ሱብሀነሁወተአላ -መልካም ስሞች እና ባህሪያቶች ስናረጋግጥ የሚከተለውን የቁርአን አንቀጽ መሰረት በማድረግ ነው። አሏሁ - ተዓላ - እንዲህ ይላል ፦
{ۚ ﻟَﻴْﺲَ ﻛَﻤِﺜْﻠِﻪِ ﺷَﻲْءٌ ۖ ﻭَﻫُﻮَ اﻟﺴَّﻤِﻴﻊُ اﻟْﺒَﺼِﻴﺮُ}
[| እሱን የሚመስለው ምንም ነገር የለም።እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው። |]
(ሱረቱ - አሽ-ሹራ ፥ 11)
°
ይሀውም ስናረጋገጥ ከፍጡራን ጋር ካለማመሳሰል ጋር (إثباتا بلا تمثيل) እና ከጎደሎ ባህሪያት ደግሞ ስናጠራ ትርጉሙን ካለ ማራቆት ጋር ማለት ነው። (تنزها بلا تعطيل).
_____
ይህንን እንደመግቢያ ከተመለከትን ከጌታችን ባህሪያቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ማለትም አሏሁ - ተዓላ - የሌሊቱ ሲሶ(1/3)ኛ ሲቀር ወደ ቅርቢቱ ሰማይ እንደሚወርድ እንደምናምን እና ይህን በተመለከተ አሕባሾች እና ሌሎች የጥመት አንጃዎች የሚያመጡትን ማምታቻዎች እንመለከታለን።
°
አሏሁ - ተዓላ - የሌሊቱ ሲሶ(1/3)ኛ ሲቀር ወደ ቅርቢቱ ሰማይ እንደሚወርድ የአላህ መልእክተኛ - ﷺ - እንዲህ ሲሉ ይነግሩናል ፦ [ አላህ - ሱብሓነሁወተዓላ - የሌሊቱ ሲሶ(1/3)ኛ ሲቀር ወደ ቅርቢቱ ሰማይ ይወርዳል ከዛም ይላል ፦ ማንነው የሚለምነኝ እሺ የምለው ፤ ማንነው የሚጠይቀኝ የጠየቀውን የምሰጠው ፤ ማንነው መሀርታን የሚጠይቀኝ የምምረው። ] (ቡኻሪ ፥ 1145)
°
በዚህ ሐዲስ መሰረት አሏሁ - ተዓላ - የሌሊቱ ሲሶ ሲቀር ወደ ቅርቢቱ ሰማይ እንደሚወርድ እናምናለን። ይወርዳል ተብለናል እንደሚወርድ እናምናለን። ስናምንም ከፍጡራን ጋር ሳናመሳስል ነው። ነገር ግን የአወራረዱን ሁኔታ እንዴት እንደሆነ አናውቅም ምክንያቱም አልተነገረንም። አናውቅም የምንለው የአወራረዱን ሁኔታ እንጂ ይወርዳል የሚለውን ትርጉሙን አይደለም። ትርጉሙ ግን ይታወቃል። ሰለፎችም የአላህን ስሞች እና ባህሪያቶች ትርጉማቸውን ያውቁ ነበር ፤ አናውቅም የሚሉት ትርጉማቸውን ሳይሆን እንዴታነታቸውን ነው። በመሆኑም የአላህ ስሞች እና ባህሪያቶች ከሙተሻቢህ(ትርጉማቸው አሻሚ) ሳይሆኑ ከሙሕከም (ትርጉማቸው ግልፅ ከሆኑት የቁርአን አንቀጾች) ውስጥ ነው የሚመደቡት።
°
ይህም ለመሆኑ ኢማሙ ማሊክ - አላህ ይዘንላቸውና - አንድ ግለሰብ አላህ እንዴት ነው ከዐርሽ በላይ ከፍ ያለው ብሎ እንዴታነቱን ሲጠይቃቸው እንዲህ ብለው መልሰዋል ፦ [ ኢስቲዋእ(የአላህ ከዐርሽ በላይ መሆን) የታወቀ ነው ፤ እንዴታነቱ አይታወቅም ፤ በሱም ማመን ግዴታ ነው ፤ ስለሱ(ስለሁኔታው) መጠየቅ ቢድዓ ነው። ] (ላለካኢይ በሸርሕ ኡሰሊ ኢዕቲቃዲ አህሊስ-ሱንነቲ ወልጀማዐህ ገጽ ፥ 664 ላይ ዘግበውታል።).
°
አሕባሾች እና መሰል የጥመት አንጃዎች ይህንን ሐዲስ አጣመው ይተረጉሙታል። ምክንያቱም አላህ ይወርዳል ካሉ አላህ ከላይ እንደሆነ ሊያረጋግጡ ነው ስለዚህ ይወርዳል የተባለው አላህ ሳይሆን መላኢካ ነው ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ትእዛዙ ነው የሚወርደው ይላሉ። ይህንንም ሊሉ የቻሉት አላህ ይወርዳል ካልን አቅጣጫ ሰጠነው ከፍጠራንም ጋር አመሳሰልነው ብለው ግልፅ የሆኑ ቁርአናዊ እና ሐዲሳዊ ማስረጃዎችን ከመከተል ይልቅ ደካማ የሆነ አዕምሯቸውን ያስቀድማሉ።
°
ለነሱ የምንሰጣቸው መልስ ቀላል ነው። እሱም የአላህ መልእክተኛ ይወርዳል ብለው ነግረውናል እንደሚወርድ እናምናለን ነው። የሚወርደው ደግሞ ከላይ ስለሆነ ነው። አላህ ደግሞ ከፍጥረታቱ በላይ ከዐርሽ በላይ መሆኑን በሰባት የቁርአን አንቀጾች ላይ ነግሮናል ስለዚህ ከዐርሽ በላይ እንደሆነም እናምናለን። አንቀጾቹን ለማስታወስ ያክል (አዕራፍ ፥ 54 / ረዕድ ፥ 2 /ጦሃ ፥ 5 / ፉርቃን ፥ 59 / ሰጅዳህ ፥ 4 እና ሐዲድ ፥ 4) ናቸው። በጥቅሉ አላህ ከላይ ለመሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ማስረጃዎች አሉ። ለጊዜው ርእሴ ስላልሆነ ማስረጃዎቹን ማምጣት ትቼዋለሁ።
°
ለነሱም ይህን ጥያቄ እንጠይቃቸዋለን በነሱ አባባል መላኢካ ወይም ትእዛዙ ነው የሚወርደው ከተባለ ሐዲሱ ላይ በግልፅ አላህ ይወርዳል እያለ መላኢካ ወይም ትእዛዙ ለመሆኑ ማን ነገራችሁ? እንላቸዋለን። እንደገና መላኢካ ነው የሚወርደው ከተባለ ታዲያ መላኢካ እንዴት ብሎ ነው [ ማንነው የሚለምነኝ እሺ የምለው ፤ ማንነው የሚጠይቀኝ የጠየቀውን የምሰጠው ፤ ማንነው መሀርታን የሚጠይቀኝ የምምረው። ] ብሎ የሚናገረው። ወንጀልን መማር መሀርታ ማድረግ የአላህ ስልጣን ብቻ አይደለምን?. በተጨማሪም ትእዛዙ ነው የሚወርደው ከተባለ የአላህ ትእዛዝ ከሌሊቱ ሲሶ ላይ ብቻ ተገድቦ እንዴት ይወርዳል? የአላህ ትእዛዝ ሁልጊዜ አይደለምን የሚወርደው? ብለን እንጠይቃቸዋለን።
°
በመሆኑም አሏሁ - ተዓላ - የሌሊቱ ሲሴ(1/3)ኛ ሲቀረው ወደቅርቢቱ ሰማይ እንደሚወርድ እና [ ማንነው የሚጠይቀኝ የጠየቀውን የምሰጠው ፤ ማንነው መሀርታን የሚጠይቀኝ የምምረው እንደሚል እናምናለን። ] ስለዚህ በዚህ ሰዓት ላይ በመነሳት ጌታችንን እንዲምረን መጠየቅ እና ዱዓ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
_____________________
✍️አቡልዓባስ አሕመድ ኢብን ያሕያ @ Ibn yahya Ahmed

የቴሌግራም ቻናላችንን ጆይን ያድርጉ፦https://telegram.me/ibnyahya7
የፌስቡክ ፔጃችንን ላይክ ያድርጉ፦ https://m.facebook.com/ibnyahya777

Post a Comment

0 Comments