السلام عليكم ورحمة الله وبركاته
بسم الله الرحمن الرحيم
↪ ተ ው በ ት ↩
ልዕለ ሀያሉ ፈጣሪያችን አላህ ለአማኞች በሙሉ “እናንተ አማኞች ሆይ እመ ኑ !” በማለት እምነታችንን እንድናስተካክል እንድናድስና እንድናጠናክር ያዘናል። ይህ መልእክቱ አምኜአለሁ ብለን ራሳችንን ከሙእሚኖች መቁጠራችን ወይም ሙስሊም ነኝ ብለን መኩራራታችን ብቻውን ሚዛን እንደማይደፋና ለሚፈለገው የስኬት ውጤት እንደማያደርሰን አውቀን የግዴታ የሆኑብንን የእምነታችንን እርከኖች መጠበቅ እንደሚገባን ያስገነዝበናል።
ስለዚህም
#ዐቂዳችንን_ከተለያዩ_ሽርካሽርኮች_የኩፍር_በሽታዎችና_የኒፋቅ_መገለጫዎች መጠበቅና መከላከል እንዳለብን ሁሉ በተግባር ማንፀባረቅ የሚገባንን ቀሪዎቹን የኢስላም መሰረቶችም ከእንቅፋት መከላከል ይኖርብናል። በመሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች ያልፆሙት የረመዳን ፆም ዕዳ ካለብዎት ከቀረበው የረመዳን ወር በፊት ፆመው ማካካስ እንዳለብዎት ሁሉ የዘካ ዕዳ ካለብዎትም ካሁኑ ከፍለው ማካካስ ይጠበቅብዎታል!!
እንደሚታወቀው #ኢስላም_በአምስት_መሰረታዊ_የአምልኮ_ዘርፎች_ላይ_የተገነባ_ሀይማኖት_ነው። እነሱም አምስቱ የኢስላም መሰረቶች በመባል የሚታወቁ ሲሆን፤ አንደኛውና ከሁሉም ቀዳሚው
☞ በሀቅ ሊመለክ የሚገባው ፈጣሪ ጌታችን አላህ ብቻ በመሆኑ#ከሱ_ውጪም_አምልኮ_የሚገባው_ማንም_ሆነ_ምንም_እንደሌለ_መመስከር_እንዲሁም_ሙሐመድ_የአላህ_መልእክተኛ_በመሆን_መልእክቱ_ተሰጥቷቸው_ወደኛ_የተላኩ_መሆናቸውን መመስከር ናቸው።
ከሁለተኛው እስከ አምስተኛው ያሉት መሰረቶች ደግሞ
☞ ሰላትን ስርዓቱንና ግዜውን ጠብቆ ለአላህ መስገድ፣
☞ መጠኑ ለዘካ የደረሰ ሀብት ያለው በየአመቱ የገንዘቡን 2.5% ዘካ ሊሰጣቸው ለሚገቡ የህብረተሰቡ ክፍሎች በአግባቡ መስጠት፣
☞ በየአመቱ ረመዳን የተሰኘውን የአመቱን ዘጠነኛ ወር ስርዓተ ፆሙን ጠብቆ ሙሉውን መፆም፣
☞ የጉዞውን ጣጣዎች ለቻለ ሰው በእድሜው አንዴ ወደ መካ በመጓዝ የሐጅ ስነስርዓትን መፈፀም ናቸው። እነዚህ አምስት መሰረታዊ ነገሮችን ከህይወቱ ጋር በተግባር ያስተሳሰረ ሰው ለፈጣሪው ትእዛዝ አድሯልና ታዛዥ ባርያ ማለትም ሙስሊም ይባላል። ከአካላዊና አንደበታዊ ተግባር ጋር የኢስላም እምነታዊ መርሆችን በልቦናው አስረግጦ ሲያምንበት ደግሞ አማኝ ወይም ሙእሚን ይባላል።
ሌላኛው ልዩ ትኩረት የምንሰጠው የእለቱ የምክክር ምርጫዬ ያለፈውን ጥፋት በማረም ላይ ያጠነጥናል። አላህ ቅኑን ጎዳና እንድንከተል ስላደረገንና ያለፉትን ጥፋቶቻችንን እንድናርም ስላነሳሳን በእጅጉ ልናመሰግነው ይገባል። በዚህም ፅናት ላይ እንድንቀጥልና ከሁሉም አይነት ሃጢኣቶች እንድንመለስ ልቦናችንን ይከፍትልን ዘንድም እማፀነዋለሁ።
እንደሚታወቀው አላህ ባርያው ጥፋቱን አውቆ ወደ ሀቅ ሲመለስ ይደሰትለታል። ታላቁ ጌታችን ከሁሉም ነገሮች የተብቃቃ እንደመሆኑ ከኛ ሰደቃም ሆነ ከሰላታችን ምንም ጉዳይ የለውም። መልካም የምንሰራው ለራሳችን ስንል ነውና ስናጠፋም በራሳችኑ ላይ ነው በደልን የፈፀምነው። እሱ እንደሆን ከኛ የሚሻው ታዛዥነታችንን ብቻ ነው። በዚህም ነው በትክክል እሱን ማምለካችን የሚረጋገጠው።
ከዚህም ጋር እጅግ መሃሪና አዛኝ በመሆኑ ይቅርታ የጠየቀን ይምራል። ተውበቱን ይቀበላል። ያለፈውን ስህተታችንን ለማረምና ለማካካስ ዝግጁ በመሆናችንም ሌላ የበረከት መንገዱን ይከፍትልናልና ለዚሁ እንዲያገራን እንለምነው።
ወደ ገደለው እንግባና ዘካን በወቅቱና በአግባቡ በማውጣት ላይ ዝንጉና ቸልተኛ የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ የኢስላም ሊቃውንት የሰጡትን አስተያየት፣ ምክርና የእርምት ምላሽ ላካፍላችሁ ስለወሰንኩ ቀጣዩን የታላቁ ፈቂህ የሸይኽ ሙሀመድ ቢን ሷሊህ አልዑሰይሚንን (ረሂመሁላህ) ፈትዋ በጥሞና አንብባችሁ ትተገብሩት ዘንድ እጋብዛችኋለሁ።
አላህ ራህመቱን ያስፍንባቸውና ለሸይኽ ሷሊህ አልዑሰይሚን ቀጣዩ ጥያቄ ቀረበላቸው።
“አንድ ግለሰብ ለአምስት አመታት ያህል ዘካ ከማውጣት ተዘናግቶ ነበር። አሁን ግን ከጥፋቱ ተውበት አድርጎ ተመልሷል። ለመሆኑ ከነበረበት ዝንጉነት ተውበት አድርጎ ዲኑን ወደ መተግበር መመለሱ ብቻ ባለፉት አመታት ያልወጡትን ዘካዎች ያስምርለታልን? ካልሆነስ መፍትሄው ምንድነው? የገንዘቡ መጠንም ከ10,000 በላይ እንደነበረ እንጂ በትክክል ስንት እንደሆነ አያውቀውም።”
ምላሽ:-
«ከሀብት ላይ ዘካውን ማውጣት ማለት በአንድ ጎኑ አላህን በአግባቡ በመታዘዝ ማምለክ ሲሆን በሌላኛው ገፅታው ደግሞ የድሆችን ሀቅ አክብሮ ማድረስ ነው። በመሆኑም አንድ ግለሰብ ዘካ ከመስጠት ታቀበ ማለት የሁለቱንም መብት ባለመወጣት ተዳፈረ ማለት ነው። ይህም ማለት በሱ ላይ ያለውን የአላህን ሀቅና የድሆችን እንዲሁም የሌሎች ዘካ ተከፋይ ግለሰቦችን መብት በመጣሱ ነው። ይሁንና
{وهو الذي يقبل التوبة عن عباده ويعفو عن السيئات} الشورى 25
“እሱ ባሪያዎቹ ከጥፋታቸው ሲመለሱ በይቅርታ ይቀበላል። ኃጢኣቶችንም ያልፋቸዋል።” በማለት አላህ ስለራሱ በገለፀው መሰረት በጥያቄው ላይ እንደተገለፀው ከአምስት አመታት በኋላም ቢሆን ተውበት አድርጎ ወደ ሀቅ እስከተመለሰ ድረስ የሀያሉ አምላካችን የአላህ ሀቅ ይሰረይለታል። (ያለፈው ጥፋቱ ይቅርታ ይደረግለታል።)
ነገር ግን ሁለተኛው ሀቅ ይኖርበታል። እሱም የዘካ ባለመብቶች የሆኑት የድሆችና የሌሎቹ ዘካ ተቀባዮች ሀቅ ነው። የነዚህን ሀቅ በማክበር መለገሱ ግዴታ ነው። በልቦናው ላይ በሚያድረው የተውበቱ ትክክለኛነት ደረጃ ግምት ውስጥ ገብቶ በተግባር ደግሞ ዘካን ሲያወጣ የአላህ ፀጋ ሰፊ ነውና ይህ ግለሰብ ዘካዎቹን በመክፈሉ ሰበብ የሚገኘውን ምንዳ የሚጎናፀፍ ይሆናል።
የዘካውን መጠን ሂሳባዊ ስሌት በተመለከተ ደግሞ በሚችለው መጠን የሀብቱን ልክ በመገመት የዘካውን መጠን ለማወቅ መጣር አለበት። እንደሚታወቀው "አላህ ማንኛዋንም ነፍስ ከአቅሟ በላይ አያስገድዳትም።"
ለምሳሌ (ካፒታሉ ከ10,000 በላይ ነው በተባለው መሰረት) የአስር ሺህ ዘካት በአመት ስንት ይሆናል ካልን 250 ነው የሚሆነው። በዚህ ስሌት መሰረት ያለፉትን አምስት አመታት በያንዳንዱ አመት 250 በመመደብ ማውጣት ይችላል። በሌሎቹ አመታት የገንዘቡ መጠን ጨምሮ የነበረ ከሆነ ግን በጭማሪው ልክ ሂሳቡን ይሰራል።
በአንፃሩ ቀንሶ የነበረ ከሆነ ደግሞ አሁን በመጨረሻው አመት ላይ ባለው ከፍ ባለው ካፒታሉ ልክ አስቦ ሲያወጣው ይሸፈንለታል ማለት ነው።» በማለት አብራርተዋል።
" أسئلة الباب المفتوح " (س 494 ، لقاء 12)
[ከ አስኢለቱል-ባቢል መፍቱህ 12/494]
እንግዲህ ከላይ ታላቁ ምሁር እንዳብራሩት እርስዎም በእጅዎ የሚገኘውን የሀብት መጠን በንብረት ወይም በእቃ ሆነ በካሽ ገምተውና ቆጥረው ልኩን ካወቁ በኋላ ከጠቅላላው ገንዘብ 2.5 በመቶ ያህሉን ለያንዳንዱ አመት በማድረግ የተዘናጉባቸውን አመታት ድምር ማውጣት ይገባዎታል። ነገር ግን ባለፉት አመታት በያንዳንዱ አመት የነበረዎት ካፒታል መጠኑ የሚለያይ ከነበረና ይህንኑ ልኩን የሚያውቁት ከሆነ በዚያ እርግጠኛ በሆኑበት መጠን ልክ ያወጣሉ። የማያውቁት ከሆነና እየጨመረ ወይም እየቀነሰ ሲዋዥቅ ለዘንድሮ ከደረሰ ያሁኑን ካፒታልዎን ታሳቢ በማድረግ ላለፉት አመታት ከዚህ እስከዚህ ይሆናል በሚል ወደ እውነት ያደላ ግምታዊ ቁጥር ሰጥተውት ዘካውን ያውጡ። ያለፉት አመታት ካፒታልዎ ከዘንድሮው የሚያንስ መሆኑን ካወቁ ግን ሁሉንም በዘንድሮው መጠን ልክ አስበው ቢያወጡለት በአላህ ፈቃድ መልካም ይሆንልዎታል።
ለምሳሌ:-
የዘንድሮው ካፒታልዎ 100,000 ብር ከሆነ ዘካው 2,500 ብር ይሆናል።
የአምስት አመታት እዳ ያለብዎት ከሆነ አሁን የሚከፍሉት የዘካ መጠን
2,500×5 = 12,500 ብር መሆኑ ነው።
በተረፈ እያንዳንዱ ሙስሊም ግለሰብ ነጋዴም ሆነ ተቀጣሪ ሰራተኛ፣ ጡረተኛም ሆነ ሌላ በተለያዩ የገቢ መንገዶች 85ግራም ወርቅ ወይም 595 ግራም ብር መግዛት የሚችል ተቀማጭ ወይም በንግድ ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ወይም ሊሸጠው ያዘጋጀው እቃና ንብረት ያለው ይህ የገንዘብ መጠን በሱ ዘንድ ኖሮ አመት ከሞላው ዘካውን የመክፈል ግዴታ አለበት።
በዚህም መሰረት የዘንድሮው አነስተኛው የአንድ ግራም የወርቅ ዋጋ 1,000 ከሆነ ማንኛውም 85,000 እና ከዚያ በላይ የሆነ ብር ያለው ወይም ለሽያጭ ያሰናዳው ከዚህ የሚስተካከል ንብረት ያለው ሁሉ የዘካ ግዴታ ውስጥ ገብቷል። ዘካ የሀብታም ነጋዴዎች ግዴታ ብቻ ኣለኘሆኑን አስተውሎ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል።
والله أعلم
።።።።።።።።።።።።።።
by
Abufewzan Ahmed siira
03may2018 ሻዕባን 17/1439
0 Comments