Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

FB እና አጅነቢ


FB እና አጅነቢ
.
(ረጅም ፅሁፍ ነው ግን ጠቃሚ ስለሆነ አያምልጣችሁ)
.
እንደ መግቢያ ...

ይህ ፅሁፍ በፌስቡክ አጠቃቀማችን ላይ አላስፈላጊ የተቃራኒ ፆታ ግንኙነትን (ቃሉ ሰፊ ነው) ለማስቀረት መውሰድ ያለብንን እርምጃ ለመጠቆም ያለመ ነው።
.
አላስፈላጊ የተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ለድንበር ያለፈ ወሬና ጨዋታ ብሎም ከዚህ ለከፋ ሐራም ተግባራት አጋልጦ መጨረሻውን ለከባዱ ወንጀል ይዳርጋል። ግለሰቡንም ለስነ-ልቦና ስብራትና የሞራል ድቀት ያበቃል።
.
በምሳሌ ለማስረዳት ... አንድ ለሸሪዓዊ ትእዛዛት እጁን የሰጠ ሰው ፌስቡክን ተጠቅሞ ዲኑን በመማር ላይ ሳለ ከሚያገኘው የተቃራኒ ፆታ ጋር አላስፈላጊ ግንኙነት ውስጥ ከገባ ቀስ በቀስ በሚከተለው ረብ የለሽ ወሬ ከዛም ተግባቦቱን ተከትሎ በሚፈጠረው መላመድ ተገፋፍቶ የማይደፈሩ የሚመስሉ ሐራም ተግባራትን ከመዳፈር አልፎ እስከ አስከፊው ነውር ድረስ ሊዘልቅ ይችላል።
.
ይህ ሁሉ ሲሆን ነፍስያ የሚሰጠው ሽፋን 'የትዳር አጋር ሊሆን ይችላል' የሚል ነው። ይሁንና ይህ ምክንያት ሐራም ሰርቶ አላህ ፊት ከመጠየቅ አያድንም።
.
ይህንን ፈተና ሰውየው በየትኛውም ደረጃ ላይ ያቋርጠው ኋላ ላይ የፈፀመው ስህተት ስለሚቆረቁረው ሞራሉ የተሰበረ እና ስነ-ልቦናውም የተጎዳ እንዲሆን ያደርገዋል። እናም ሰውየው በንፁህ ተውበት ተመልሶ ጠንካራ መንፈስ ካላጎለበተ በስተቀር በቀጣይ የትዳር ህይወቱም ሆነ በኢስላማዊ ስራዎች ላይ ባለው ተሳትፎ ውስጥ ተፅእኖ ሊያሳድርበት ይችላል።
.
ከዚህ ሁሉ ጣጣ ግን አንድ ሰው ራሱን እንዴት ከዚህ ፈተና መታደግ እንደሚችል ጠቃሚ ጥቆማዎች ልስጥ ... (እንኝህ ጥቆማዎች ምክረ ሐሳብ እንጂ የአድርግ አታድርግ መመሪያ አይደሉም)
.
1. ዓላማችንን እንቅረፅ!
.
ወደ ፌስቡክም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ሚድያዎች ስንቀላቀል ዓላማ ይኑረን። ዓላማችንም ሐራም ያልሆነ እና ከጨዋታና ዛዛታ ፍላጎት የጠራ ይሁን።
.
ዓላማን ማስተካከል እና ፍላጎትን ቁም-ነገር ላይ ማድረግ፤ ከዛ ባሻገርም ዲናዊ ዕውቀትን በመሻት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ዓላማን መቅረፅ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ራስን ከፌስቡክ ማግለል ከፈተና ለመጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው።
.
ሌላው መጠንቀቅ ያለብን ከሸሪዓዊ ዕውቀትን የመሻት ዓላማ ጋር አዳብሎ ትዳርን ከፌስቡክ መፈለግ አንድም ለዕውቀት ፍለጋ ስንነሳ ያነገብነውን ኒያ ሊያበላሽብን ሲችል በሌላ መልኩ የማይዘገን ጉምን እንድንመኝ የሚያደርግ ግልብነት ነው።
.
[እንደዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ እምነት በሶሻል ሚድያ የሚደረግ የትዳር ፍለጋ ስኬታማነት የመነመነ፣ ለፈተና እና ሐራም የሚያጋልጥ እንዲሁም ለማታለልና ሽወዳ የሚዳርግ ስህተት ነው - ሌላ ግዜ በሰፊው እመጣበታለሁ ኢንሻ አላህ]
.
እናም እንዲህ ያለውን ህልመኝነት ትተን የምንፈልገውን ሸሪዓዊ ዕውቀት ጥርት ባለ ኒያ ዓላማችን ማድረግ ይገባናል። (ይህን ስል FBን ከወዳጅ ዘመድ መገናኛነት ወይም የስራ ጉዳይ አናውለው ለማለት እንዳልሆነ ልብ እንበል)
.
2. የከፈትነውን አካውንት እናስተውል!
.
በቅድሚያ ፌስቡክን ለመቀላቀል ስናስብ ስለአጠቃቀሙ እና መጠንቀቅ ስላለብን ነገር እንወቅ። ሌላው ደግሞ የምንጠቀምበትን አካውንት ከአንድ በላይ አናድረግ ወይም በአንድ እንብቃቃ። ከዛ በመቀጠል ...
.
ሀ. የምንጠቀምበትን አካውንት ስንከፍት በስልክ ቁጥራችን የምንከፍት ከሆነ ቁጥሩን እንዳይታይ ማድረግ አንርሳ፤ ይህ ካልሆነ ስልካችን ማንም እጅ ስለሚገባ ፈተናን በራችን ድረስ መጥራት ነው የሚሆነው።
.
ለ. ለአካውንቱ የምንሰጠው ስም ትክክለኛ ወይም ሰዎች ዘንድ የምንታወቅበት ይሁን። ይህ ሲሆን የአካውንቱ ባለቤት ቁም-ነገረኛ መሆኑን ያመለክታል። (ኩንያ የምንጨምርበት ከሆነ 'አቡ' ወይም 'ኡሙ' በሚል መልኩ መጠቀም ከፈተና አይነተኛ መጠበቂያ ነው)
.
ሐ. የምንጠቀመው ስም ትኩረት ሳቢ ከሆኑ መጠሪያዎች እንጠብቀው። ለምሳሌ ... ቆንጆ ... Love ... ሳቂታው ... ቀብራራው ... ከመሳሰሉ ራስን ከሚያጎሉ እና እይታ ውስጥ ከሚከቱ ስሞች መጠንቀቅ።
.
መ. የምንጠቀመውን ፕሮፋይል ፒክቸርም ይሁን ከቨር ፎቶ ልክ እንደስማችን ከትኩረት ሳቢነት እናፅዳው። የራስን ምስል ማስቀመጥ ከምንፈራው ፈተና ጋር እሳትና ጭድ በመሆኑ በፍፁም ማድረግ አይገባም።
.
ሠ. ስለራሳችን የሚገልፁ የፕሮፋይላችን ክፍሎችንም ከላይ ባሳለፍነው መልኩ ትኩረት ሳቢ እንዳይሆኑ ማድረግ። በምንወዳቸው መፅሐፍት፣ ቲቪ ሾው፣ ጥቅሶች የመሳሰሉ ፍላጎትን ማሳወቂያ ቦታዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ።
.
ረ. 'Intersted In' የሚመለውን ምርጫ መተው! ይህ ቦታ ፌስቡክን ለፆታዊ ፍላጎታቸው ማርኪያነት የሚቀላቀሉ ሰዎች ፍላጎታቸውን እንዲለዩበት የተቀመጠ ነው። (ባለማወቅ አንዳንዶች ተመሳሳይ ፆታቸውን ወይም ሁለቱንም ይጠቅሳሉ - ይህ ተቃራኒን ከመጥቀስ የባሰ ትርጉም አለው)
.
ሰ. 'Relationship Status' ላይ ትዳር እንደመሰረትን ለመግለፅ ካልሆነ በስተቀር ሌሎች አማራጮችን አለመጠቀም። ይህ በራሱ ሌላ ጥሪ ነውና!
.
ሸ. ፕሮፋይላችን ላይ የቤተሰብ አባላትን ስንጠቅስ እነርሱ በፎቶ እና መሰል ጉዳዮች ላይ የላላ አቋም ካላቸው የኛን ምስል ሊለቁ ስለሚችሉ ወይም የነርሱን በማየት ልቡ ላይ በሽታ ያለበት መጥፎ ግምት ውስጥ ሊገባ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ።
.
ቀ. በመጨረሻም በዚህ ክፍል ከምናደርገው ጥንቃቄ አንዱ የትውልድ ዘመንን ግልፅ አለማድረግ ነው። ይህ ከሆነ መጥፎ ኒያ ያለው ሰው አይን ውስጥ አያስገባንም።
.
3. ጓደኝነትና መስተጋብር ...
.
ሀ. ፌስቡክ ላይ ጓደኛ እንዲሆኑን የምንፈቅድላቸውን ሰዎች ልንመርጥ ይገባል። መልካም ስብእና የሌላቸውን፣ ካፊሮችን እና ከሱና ጋር የማይገጥሙ አቋሞችን የሚያሰራጩ ሰዎች ለፈተና ቅርብ ናቸውና እነርሱን ከመጎዳኘት መቆጠብ ይኖርብናል። እንዲሁም ሀሰተኛ እንደሆኑ የምንጠረጥራቸውን አካውንቶች ከጓደኝነት ማቀብ።
.
ለ. ፌስቡክ ላይ ፍሬንድ ካደረግናቸው አካላት ጋር ሁሉ ትውውቅ ለመፍጠር አለመጣር። ራስን ለማሳወቅ አለመድከም።
.
ሐ. ፍሬንድ ካደረግናቸውም ይሁን ሌሎች የሚደረጉ ፓስቶችን ሁሉ ላይክ፣ ሼር ወይም ኮመንት ከማድረግ መቆጠብ። ይልቁን ጠቃሚ የሆኑትንና ከታማኝ ምንጭ የተገኙትን በአግባቡ መያዝ።
.
መ. ሌላው ምንም ፋይዳ ሊያገኝበት የማይችልበትን ፓስት ከማድረግ መታቀብ። ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር ግላዊ ውይይቶችን በኮመንት ከማድረግ ይልቅ በውስጥ መስመር ማድረግ። ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ሌላውን ሊፈይዱ የማይችሉ ምልልሶችንም እዛው መጨረስ።
.
ሠ. ግለሰቦች ከሚለቁት ፎቶ፣ ግላዊ ፓስቶች የመሳሰሉ ቦታዎች ላይ ያለፋይዳ ኮመንት ከማድረግ መቆጠብ።
.
ረ. ዲናዊ ፓስቶችን በምናጋራበት ወቅት ወይም ኮመንት በምናደርግበት ወቅት ትኩረታችንን መልእክቱ ላይ ማድረግ። ግለሰቦችን ከእይታ ማውጣት። እኛም ይህን ስናደርግ ሰዎች በዚህ እይታ እንዲያዩት ማድረግ።
.
ሰ. ተሳትፎአችንን ተከትለው የሚመጡ አድናቆቶችን በተከፈተ ልብ አለመቀበል። አንድም ኒያችንን ሊያበላሽ ይችላል በሌላ ጎን ደግሞ በአድናቂዎች ላይ እንድናተኩር በር ይከፍታል።
.
ሸ. ጥያቄዎች ወይም ማብራሪያዎችን በተቻለ መጠን በኮመንት ለመጨረስ መሞከር። የኮመንት ምልልስ ላይ የተቃራኒ ፆታን ስም ከማቆላመጥ መቆጠብ፤ ጭፍን ከሆነ ድጋፍም ሆነ ግብዝ አለሁ ባይነት ራስን ማቀብ።
.
4. ሚሴጅ/ቻት!
.
ሀ. ከአላፊ አግዳሚ ወሬ ለመጠበቅ ቻትን 'Off' ማድረግ። አስፈላጊ ካልሆነ ሚሴንጀርም አለመጠቀም።
.
ለ. ማንም ይሁን ማን ከተቃራኒ ፆታ ጋር ግድ ካልሆነ በስተቀር መልእክት አለመለዋወጥ።
.
ሐ. መልእክቱን ስንለዋወጥ ከዋና ሰላምታ በስተቀር ወደ ዝርዝር ደህንነት ጥየቃ አለመግባት፤ ስምን አለማቆላመጥ እንዲሁም ቁም ነገሩ ላይ ብቻ ማተኮር። በሚሴጅ ለሚያወራን ሰው ውጭ ከሚታየው ባህሪያችን የተለየ አለማሳየት።
.
መ. ሰበብ እየፈጠሩ መልእክት ከመለዋወጥ መቆጠብ። እንዲሁም ያለ በቂ ምክንያት መልእክት እየተላከልን እንደሆነ ከጠረጠርን ቶሎ መልስ አልመስጠት፣ ችላ ማለት፣ ጥርጣሬው ካየለብን ደግሞ ከናካቴው መተው።
.
ማጠቃለያ
.
በFB መልካም ነገርን በመሻት እስከቆየን ድረስ የመልካምነትን ካባ የደረቡ የቀበሮ ባህታዊዎች በዙሪያችን እንዳሰፈሰፉ ልብ ልንል ይገባል። ከሁለቱም ፆታ አላማቸው ፈሳድ ሆኖ ሳለ ከላይ መልካም ነገር በማሳየት የሰዎችን ትኩረት በመሳብና ታዋቂነት በማትረፍ ለእኩይ ተግባራቸው የሚያመቻቹ አሉ።
.
እናም ራሳችንን ከነኝህና መሰሎቻቸው ተንኮል ለመታደግ ይቻለን ዘንድ ከላይ የተቀመጡትን ቅድመ ጥንቃቄዎች ብናደርግ እመክራለሁ።
.
ይህንንም አድርገን ግን ገፍቶ የሚመጣ አካል ካለ አንድም ቅድም እንዳልነው የቀበሮ ባህታዊ ነው ወይም ደግሞ በመጀመሪያ እንዳወሳነው ደመና ለመዝገን የሚጥር ሞኝ ነው። ከሁለቱም ጋር የምናሳልፈው ግዜ መጨረሻው ውድቀት መሆኑን አምነን ሁለቱንም በግዜ መሸኘት መልካም ነው እላለሁ።
.
Notice፦ በዚህ ፅሁፍ ላይ ተቃራኒ ፆታ ሲባል የተፈለገበት አጅነቢ የሆነውን ነው።
.
አላህ ከፈተና ይጠብቀን!




Post a Comment

0 Comments