Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የወለድ አደጋዎች

የወለድ አደጋዎች
ዘመናችን በርካታ የቂያማ ምልክቶች የሚታዩበት አስፈሪ ዘመን ነው፡፡ ከነዚህ ምልክቶች ውስጥ አንዱ የወለድ መንሰራፋት ነው፡፡ ወለድ በቁርኣን፣ በሐዲሥና በምሁራን ኢጅማዕ የተወገዘ እጅግ አደገኛ ወንጀል ነው፡፡ ወንጀሉ ምንም እንኳን አደገኛ ቢሆንም ነገር ግን እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ነው፡፡ ከጥፋቱ መስፋፋት በላይ ይበልጥ የሚደንቀው ግን በተለያዩ ስልቶች ኢስላማዊ ሽፋን ሊሰጡት አጉል የሚባዝኑ ስራዎች ብቅ ብቅ ማለታቸው ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥም አንዱ “የወረቀት ገንዘብ እና ወለድ” በሚል ርእስ በቅርቡ የወጣው መፅሐፍ ነው፡፡ ፀሐፊው ጥራዝ ነጠቅ ብቻ ሳይሆን ሲበዛ ደፋር ነው፡፡ ስለ መፅሐፉ በሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፣ ኢንሻአላህ፡፡ ላሁን የወለድን አስከፊነት የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡
1. ወለድ ከሰባት ከባባድ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ነብዩ ﷺ “ሰባት አጥፊዎችን ተጠንቀቁ” ይላሉ፡፡ “ምን ምን ናቸው እነሱ?” ሲባሉ፡-
((الشرك بالله، والسحر، وقتل النفس التي حرّم اللَّهُ إلا بالحق، وأكل الربا، وأكل مال اليتيم، والتّولّي يوم الزّحف، وقذف المحصنات الغافلات المؤمنات))
“በአላህ ማጋራት፣ ድግምት፣ አላህ ጥብቅ ያደረጋት ነፍስ መግደል - በሐቅ ካልሆነ በስተቀር፣ ወለድን መብላት፣ የየቲምን ገንዘብ መብላት፣ በጦርነት ጊዜ መሸሽ፣ ጥብቅና (ከጥፋት) የዘነጉ አማኝ ሴቶችን በዝሙት መወንጀል፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
ወለድ ከምን አይነት ወንጀሎች ጋር እንደተቆጠረ ተመልከት፡፡
2. ወለድ እንኳን ለአኺራ ለዱንያም አይጠቅምም፡፡ ይሄውና አላህ ምን እንደሚል፡-
{يَمْحَقُ اللَّهُ الرِّبا وَيُرْبِي الصَّدَقَاتِ }
“አላህ አራጣን ያጠፋል፡፡ ምፅዋቶችንም ያስፋፋል፡፡” [በቀራህ፡ 276]
በየገጠሩ ገበሬውን ባዶውን ያስቀሩት የቁጠባ ተቋማት ናቸው፡፡ ወለድ የገባው ሁሉ እንስሶቹ እያለቁ፣ ሰብሉ እየጠፋ፣ ንግዱ እየከሰረ መቀመቅ የገባው እጅግ በርካታ ህዝብ ነው፡፡ ወላሂ በአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች የወጣ ከዚህ ጋር የተያያዘ ብዙ ለቅሶ ይሰማል፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነት በኢቲቪ እንደሚደሰኮረው አይደለም፡፡ ነብዩ ﷺ “አንድ ሰው ከወለድ አያበዛም ፍፃሜው መመናመን ቢሆን እንጂ” ይላሉ፡፡ [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 5/120]
3. ያለ አስገዳጅ ሁኔታ ከወለድ ጋር የሚነካካ በሁሉም አቅጣጫ የተረገመ ነው፡፡ ሶሐባው ጃቢር ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡-
((لعن رسول الله - صلى الله عليه وسلم -: آكل الربا، وموكله، وكاتبه، وشاهديه))، وقال: ((هم سواء))
“የአላህ መልእክተኛ ﷺ ወለድ የሚበላንም፣ የሚያበላውንም፣ ፀሐፊውንም፣ ምስክሮቹንም ተራግመዋል፡፡ ‘ሁሉም በወንጀሉ እኩል ናቸው!!’ ብለዋል፡፡” [ሙስሊም፡ 1598]
“እኔ ቢቸግረኝ ወሰድኩ እንጂ አራጣ አበዳሪ አይደለሁም” ብለህ እንዳትሸወድ፡፡ ያለፈውን ሐዲሥ ተመልከት፡፡ በተጨማሪም ነብዩ ﷺ “ወሳጅም ሰጪም እኩል ናቸው” ማለታቸውን ያዝ፡፡ [ሙስሊም፡ 1584] ስለዚህ ሙስሊም የሆነ ሰው ሌላው ቀርቶ በወለድ ተቋማት ውስጥ ጥበቃና ፅዳት እንኳን ሊሰራ አይገባውም፡፡
4. ወለድ ውስጥ የገባ ሰው ከአላህ ጋር ጦርነት ውስጥ ነው የገባው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
{يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اتَّقُوا اللَّهَ وَذَرُوا مَا بَقِيَ مِنَ الرِّبا إِنْ كُنْتُمْ مُؤْمِنِينَ * فَإِنْ لَمْ تَفْعَلُوا فَأْذَنُوا بِحَرْبٍ مِنَ اللَّهِ وَرَسُولِهِ}
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፡፡ ከአራጣም የቀረውን ተዉ፡፡ አማኞች እንደሆናችሁ (ተጠንቀቁ፡፡) (የታዘዛችሁትን) ባትሰሩም ከአላህና ከመልእክተኛው በሆነች ጦር (መወጋታችሁን) እወቁ፡፡” [አልበቀራ፡ 278-279]
ይቺ በነብዩ ﷺ ላይ መጨረሻ ላይ የወረደች አንቀፅ ነች ይላሉ ኢብኑ ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁ፡፡ [ቡኻሪ፡ 2086]
5. ወለድ የሚበላ ሰው ከቀብር የሚነሳው ልክ በጂን እንደተለከፈ ሰው እየተሳከረ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
{الَّذِينَ يَأْكُلُونَ الرِّبَا لا يَقُومُونَ إِلَّا كَمَا يَقُومُ الَّذِي يَتَخَبَّطُهُ الشَّيْطَانُ مِنَ الْمَسِّ}
“እነዚያ አራጣን የሚበሉ ያ ሰይጣን ከመንካቱ የተነሳ የሚጥለው ሰው (ከአውድቁ) እንደሚነሳ ብጤ እንጂ (ከመቃብራቸው) አይነሱም፡፡” [አልበቀራ፡ 275]
6. ወለድ ምህረት የለሸ ወንጀል ነው፡፡ ነብዩ ﷺ “ምህረት ከማያገኙ ወንጀሎች ተጠንቀቅ፡፡ … ወለድን መብላት፡፡ ወለድን የበላ ሰው በቂያማ ቀን ሸይጧን የሚጥለው እብድ ሆኖ ነው የሚነሳው” ካሉ በኋላ የላይኛውን አንቀፅ አነበቡ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ ተውበት ካልኖነ ጥፋቱ አደገኛ ነው፡፡
7. ወለድ የከሃዲዎቹ አይሁዳውያን ተግባር ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
{وَأَخْذِهِمُ الرِّبا وَقَدْ نُهُوا عَنْهُ وَأَكْلِهِمْ أَمْوَالَ النَّاسِ بِالْبَاطِلِ وَأَعْتَدْنَا لِلْكَافِرِينَ مِنْهُمْ عَذَاباً أَلِيماً}
“ከርሱ በቁርጥ የተከለከሉ ሲሆኑ አራጣንም በመያዛቸውና የሰዎችን ገንዘቦች ያለ አግባብ በመብላታቸውም ሳቢያ (የተፈቀደላቸውን እርም አደረግንባቸው፡፡) ከነሱም ለከሃዲዎቹ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጀን፡፡” [አንኒሳእ፡ 161]
8. የወለድ መብዛት የቂያማ ምልክት ነው፡፡ ነብዩ ﷺ “ቂያማ ሲቃረብ ወለድ፣ ዝሙት እና አስካሪ መጠጥ ይበዛል” ይላሉ፡፡ [ሶሒሑ አትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 1861]
9. ወለድ የሚበላ ሰው አሰቃቂ ስቃይ አለበት፡፡ ነብዩ ﷺ እንዲህ ይላሉ፡-
“ዛሬ ሌሊት ሁለት ሰዎችን አየሁኝ፡፡ ወደተቀደሰች ምድርም ይዘውኝ ወጡ፡፡ ደም የሚጎርፍበት ወንዝ እስከምንደርስም ተጓዝን፡፡ በውስጡ አንድ የቆመ ሰው አለ፡፡ ከወንዙ ዳርቻ አንድ ሰው አለ፡፡ ከፊት ለፊቱ ድንጋዮች አሉ፡፡ ወንዙ ውስጥ ያለው ሰውየ ሊወጣ ሲያመራ ዳር ላይ ያለው ሰውየ አፍ አፉን በድንጋይ እየመታ ወደነበረበት ይመልሰዋል፡፡ ሊወጣ በሞከረ ቁጥር ድንጋይ እየወረወረ አፍ አፉን ይመታዋል፡፡ ከዚያም ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ ‘ማነው ይሄ ወንዙ ውስጥ ያየሁት?’ ስል ‘ወለድ የሚበላ ነው’ ይለኛል፡፡” [ቡኻሪ፡ 2085]
10. ወለድ ከምናስበው በላይ እጅግ የገዘፈ ወንጀል ነው፡፡ ነብዩ ﷺ “ወለድ ሰባ ሶስት አይነት ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ቀላሉ አንድ ሰው እናቱ ላይ ዝሙት እንደመስራት ነው” ይላሉ፡፡ [ሶሒሑ አትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 1851]
11. የወለድ መብዛት በምድር ላይ የአላህን ቅጣት ያስከትላል፡፡ ነብዩ ﷺ “ዝሙትና ወለድ በአንድ ሃገር ላይ ከበዛ በራሳቸው ላይ የአላህን ቅጣት አስወስነዋል” ይላሉ፡፡ [ሶሒሑ አትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 1859]
ወንድሜ! አላህን ፍራ! እህቴ ሆይ! አላህን ፍሪ!! ህይወት ማለት የዱንያ ህይወት ማለት አይደለም፡፡ ይቺማ ጤዛ እኮ ናት፡፡ ይልቅ ነብዩ ﷺ ምን እንደሚሉ ተመልከት፡- “አንድ ሰው የሚያገኘው ገንዘብ ከሐላል ይሁን ከሐራም ደንታ የማይኖርበት ዘመን በሰዎች ላይ ይመጣል፡፡” [ቡኻሪ፡ 2059] ልብህ ካልሞተ ይሄ አስፈሪ መልእክት አለው፡፡ ሰው እንዴት እራሱን የቂያማ ምልክት ያደርጋል? ፍጥጥ ባለ መልኩ ሐራም ላይ መግባት ሲኖርስ? ያውም በአራጣ? አላህ ለሸሪዐዊ ትእዛዝ እጅ የምንሰጥ፣ ከዱንያ ይልቅ ኣኺራን የምናስቀድም ያድርገን፡፡ ኣሚን፡፡
፣ መጋቢት 23/2010)

Post a Comment

1 Comments