① ሐቅን ያላማከለ ዝንጉርጉር "አንድነት " የመሰረቱ ሰዎች ውሽልሽል ህብረታቸው እንዳይናድ በመስጋት ብዙ ጊዜ ስለ ሺርክ ስለ ቢድዐ በሚገባ አያስተምሩም። ቢያስተምሩም ቦታ እያዩ ነው።
② የዐቂዳ ችግር ያለበት ሰው የተውሒድ ደዕዋ ምቾት አይሰጠውም።
③ ቢድዐ ውስጥ የሚንቦጫረቅ ሰው "ቢድዐ ሁሉ ጥመት ነው " የሚለው ሐዲሥ ያስበረግገዋል።
④ ከወላጆቹ ጋር የተፋጠጠ ወጣት ስለ ወላጅ ሐቅ መስማት አይፈልግም።
⑤ ልጆቹን ወልዶ የረሳን አባት ስለ አባታዊ ሃላፊነት በአቅራቢያው እንዲወራ አይፈልግም።
⑥ ጎረቤቱን አዛ የሚያደርግ ነገረኛ ስለ ጎረቤት ሐቅ ሊናገር ቀርቶ መስማት አይፈልግም።
⑦ ሚስቱን መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣ ባል ስለ ሚስት ሐቅ መስማት አይፈልግም።
⑧ የባሏን ሐቅ የማትወጣ ሚስት ስለ ባል ሐቅ መስማት አትፈልግም።
⑨ ቃሚው ስለ ጫት፣ አጫሹ ስለ ሲጋራ መስማት አይፈልግም።
10. ዘረኛው ስለዘረኝነት ሊናገር ቀርቶ ሌሎች ቢናገሩ ቅር ይሰኛል።
.
.
.
ሰለፊውም በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የአህሉል ቢደዕ ጩኸት ተፅእኖ አሳድሮበት ብዙ በቅጡ የማይዳስሰው ርእስ አለው። እስኪ በመካከላችን ስለ ኢስላማዊ ወንድማማችነት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ አኽላቅ፣ ዑለማዎችን ስለ ማክበር፣ ወዘተ ምን ያክል ይወራል?! እነዚህ አጀንዳዎች ትልልቅ የዲናችን ክፍሎች አይደሉምን?! እንዲያውም እኮ በነዚህ ርእሶች ላይ ማተኮራችን መንታ ፋይዳ ነበረው። በአንድ በኩል ፅንሰ ሐሳቡን በማዳበር ኢስላማዊ ግዴታችንን ለመወጣት ሲያስችለን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በነዚህ ርእሶች ላይ ተንጠላጥለው ብዥታ ለሚነዙ ሰዎች መልስ ለመስጠት ይመቸን ነበር። እዚህ ላይ ምሳሌ እየጠቀሰ የሚሞግት ወይ ቅር የሚሰኝ ሊኖር ይችላል። ግና ያለው በቂ እንዳልሆነ እየጠቆምኩ እንጂ ከነ ጭራሹ እያስተባበልኩ እንዳልሆነ ይሰመርልኝ።
ባጭሩ ማለት የፈለግኩት ደረጃውና መልኩ ቢለያይም ስሜትን የተከተለ፣ ነፍስያን ያማከለ ሚዛን በየጓዳችን አለ። ሁለት ሰዎች ቢቃረኑ ከስሜት ነፃ ሆኖ የሁለቱንም ጥፋት መመልከት የሚችለው ከስንት አንዱ ነው። አብዛሀኛው "የኔ" የሚለውን አካል ጥፋት ማረም ቀርቶ መመልከትም አይፈልግም። ይልቁንም ተቃራኒ አድርጎ የሳለውን አካል ማጋለጥ ላይ ያነጣጥራል። የሚወደው ሰው ቢፈፅመው አጭብጭቦ የሚቀበለውን ጉዳይ ያስተላለፈው የሌላ ሰልፍ አካል ስለሆነ ብቻ ያጣጥላል። ሸይኹ ኡስታዙ ቢፈፅመው ጎልቶ የማይታየው ጥፋት የተፈፀመው በሌላ መስመር ሰው ስለሆነ ብቻ ያቀጣጥላል። ኢንሷፍ፣ ተቅዋ፣ ሙራቀባ ከብዙዎቻችን ዘንድ ተዘንግተዋል። ዋ ለራሴ! ወላሂ ነፍሳችንን የዘነጋነው ብዛታችን! ቀብር፣ ቂያማ፣ ሲራጥ፣ ሒሳብ፣ ከአላህ ፊት መቆም፣ ... ተዘንግቶ ነገሩ ሁሉ የሚለካው በቡድናዊ ሚዛን ሆኗል። አንድ ጉዳይ "ጥፋት ነው ወይስ አይደለም" የሚለውን ገለልተኛ ሆነን ከመወሰን ይልቅ ቀድመን ፈፃሚው "የኛ" ነው ወይስ "የነሱ" የሚለውን መለየትን የምንመርጥ ብዙ ነን። በሌላ በኩል ለቡድናዊ ትርፍ ሲባል በሌላው ላይ ተራ የዱርየ ስራ ቆሻሻ ሸፍጥ እስከመፈፀም የምንወርደው ስንቶች ነን?! ወላሂ በቂላቂሎች ቆሻሻ አካሄድ ሳቢያ ይሄ ታላቅ ዲን ክብሩን ሲያጣ ማየት ምንኛ ልብ የሚያደማ ነው?! ብቻ በሱና ስም ፍርደ ገምድል ውሳኔዎችን ለምንወስን ሁሉ፣ በሰለፍያ ስም ወደ ቆሻሻ የመንደር ዱርዬዎች ባህሪ ለምናሽቆለቁል ሁሉ፣ በዲን ስም ለጮኸ ሁሉ ሳናስተውል ለምናራግብ ሁሉ፣... በኛ ብልሹ አካሄድ ሳቢያ ከሱናም ከኢስላምም በሚርቁ ሰዎች ተጠያቂ ከመሆናችን በፊት ጊዜው ሳያልፍ እንመለስ። አደራው ለራሴም ጭምር ነው። አላህ ይርዳን።
