Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የሒጃብ እንቅፋቶች

🍂 የሒጃብ እንቅፋቶች 🍂
እህቴ ሆይ ሂጃብሽን እንዳትጠብቂ ያደረጉሽ ቀጫጭን ምክንያቶችና ስህተቶችሽን ታውቂያቸዋለሽን
①ኛ. የአጉል ተስፈኝነት ምክንያት
“ ኢማን በልብ ነው ሂጃብ በለበሱ አይደለም ፣ ዋናው ከልብ መስተካከል ነው..” የሚል ነው
እህቴ ሆይ ይህንን አባባል ወይም አመለካከት ከወደየት አመጣሽው ?
ኢማን ማለት በልብ ውስጥ ብቻ በመቀመጥ ወጣ ብሎ የማይታይ ምናባዊ መፎከርያ አይደለም።
ይልቅስ ኢማን በልብ የሚያድር በአንደበት የሚነገርና በተግባር የሚገለፅ ነገር ነው።
እነዚህ ሶስቱ ተጣምረው ሲገኙም ነው ኢማን ምሉእ የሚሆነው።
በእርግጥ ከመልእክተኞች በስቀተቀር ከሰው ልጅ በሙሉ ምሉእነት አይጠበቅም ። መሳሳት መርሳት፣ መዘናጋት፣ ኣለማወቅና ማመፅም ባህሪያችን ነው።
ሆኖም አንድን ሸሪኣዊ ትእዛዝ ስንታዘዝ ቀጫጭን ምክንያቶችን በመደርደር ከህጉ ለማምለጥ መሞከር ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም።
ስለሆነም በልቧ እውነተኛ ኢማን የሰረፀባት እንስት ሌሎች እንቅፋቶች ካልገጠሟት በስተቀር ሂጃቧን ስርዓቱን ጠብቃ ከመልበስ የሚያግዳት ነገር የለባትም።
☞ ኢማን በልብ ነው የሚለውም መከራከርያ ስህተትሽን ለመሸፈን ያመጣሽው ተራ ምክንያት ነውና ልትርቂው ይገባሻል።
ልቧ በእውነተኛ ኢማን የተስተካከለላት እንስት ተግባሯም ይስተካከላልና።
②ኛ. ቀጣዩ ኮሳሳ ምክንያቷ ደግሞ
“ አላህና መልክተኛውን እወዳቸዋለሁ፤ ለመውደዴ ደግሞ የግድ ሂጃቤን ጠብቄ መልበስ አይጠበቀኝም....” የሚል ነው።
እህቴ ሆይ ይህ አነጋገር የግል ሃሳብሽ ነው ? ወይስ ከዲንሽ በመማር የቀሰምሽው ነው 
በመሰረቱ የዚህ አይነት ለአላህና ለመልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የሚገለፅ ፍቅር ወይም ውዴታ በቁርኣንም በሀዲስም አልሰፈረም። ይልቁንም በተቃራኒው ነው የተደነገገው።
አላህን በእውነት የሚወድ ያለ ምንም ጥርጥር መልእክተኛውንም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ይወዳል። መልእክተኛውን የወደደ ደግሞ ይዘውት የመጡትን መልእክት ያከብራል ይከተላል።
ይህንን ባዶ ተስፈኝነት ሲያጋፍጥም አላህ እንዲህ ይለናል።
” قُلْ إِن كُنتُمْ تُحِبُّونَ اللَّـهَ فَاتَّبِعُونِي يُحْبِبْكُمُ اللَّـهُ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ذُنُوبَكُمْ ۗ وَاللَّـهُ غَفُورٌ رَّحِيمٌ “
آل إمران﴿٣١﴾
በላቸው : « አላህን የምትወዱ ከሆነ ተከተሉኝ አላህ ይወዳችኋልና
ኃጢያቶቻችሁንም ለእናንተ ይምራልና
አላህ መሀሪ እና አዛኝ ነው:። » በላቸው ።
(ኣሊ-ኢምራን 31)
ስለዚህም አላህና መልክተኛውን መውደድሽን በአንደበትሽ እንደመሰከርሽው ሁሉ በተግባርም ያዘዙሽን ሂጃብ በመልበስ አረጋግጪው።
③ኛ. ሶስተኛው ቀዝቃዛ ምክንያት ደግሞ
“ ወላጆቼ ሂጃብ እንድለብስ አይፈቅዱልኝም ” የሚል ነው።
በመጀመርያ ደረጃ ሙስሊም ወላጆች አላህን ሊፈሩትና ነቢያቸውንም ሊያከብሩ በሃይማኖታቸውም ሊኮሩ ይገባል።
ምንም የማይጎዳቸውን ይልቁንም የሚያኮራቸውን የሴት ልጃቸውን መከበር ኣለመፍቀዳቸው ተገቢ ባለመሆኑ ከዚህ አይነቱ ስህተት ሊመለሱ ግድ ይላቸዋል።
ቀጥሎም በልጆቻቸው ላይ መብታቸው እስከየት እንደሆነም መረዳት አለባቸው። መውለድ፣ መቀለብ፣ ማኖርና ማልበሳቸው እንዲሁም ጣጣቸውን ችለው ተንከባክበው ማሳደጋቸው የልጃቸውን መብት ለመግፈፍና የአላህን ዲን ለመፃረር ሊያበቃቸው አይገባም።
እህቴ ሆይ ካንቺ የሚጠበቀው ቤተሰቦችሽን በመልካም ፀባይ ይዘሽ ሃይማኖትሽ ያዘዘሽን የመተግበር ግዴታ እንዳለብሽ፣ የከለከለሽንም የመራቅ ሃላፊነት እንደሚጠበቅብሽ ልታሰረጂያቸው ግድ ይልሻል።
አሻፈረን ቢሉ እንኳ እስከዚህ ድረስ ሃያልነት የላቸውምና አለባበስሽን ማስተካከል አያቅትሽም።
ያውም ባሁኑ ዘመን የትኞቹ ወላጆች ናቸው ልጆቻቸውን ሙሉ በሙሉ አየመሩ ያሉት የአላህን ትእዛዝ ለመጣስ ሲሆን ብቻ ነው ወላጅ የሚፈራው 
ነብዩም ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም
(لا طاعة لمخلوق في معصية الخالق)،
“ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለመጣስ ለፍጡር መታዘዝ የለም ” ብለዋልና ሰበብሽ ውድቅ ነው፡፡
ምክንያትሽ ልባዊና ተጨባጭ ከሆነ በዚህ ይስተካከላል። ቀዝቃዛው ሰበብ ከሆነ ግን አላህን ፈርተሽ ወደ ዲንሽ ልትመለሺና ክብርሽን ልትጠብቂ ይገባሻል።
④ኛ. አራተኛው የተቀዣበረ ምክንያት
“ሂጃብ ስለብስ ይጨንቀኛል ራሴንም ያመኛል..” የሚል ነው
ይኸ ምክንያት ብዙ አይነት ገፅታ ይኖረዋል።
በእውነት ይህ ጉዳይ ከተከሰተብሽ ሸይጣን በአንቺ ላይ የሚጫወትብሽ ጨዋታ ነውና ራስሽን ከጉትጎታው ጠብቂ፡፡
እሱ ያመሳስልብሻል፣ ጥብብ እንዲልሽና መከበርያ ሂጃብሽን እንድትጠዪው ይገፋፋሻል።
ምክንያቱም የራስ ህመም ገላን ከመሸፈን ፀጉርን ከመደበቅ ጋር ምንም አይገናኝምና።
ፀጉርሽን ለቅቀሽ፣ ደረትሽን ገልብጠሽ፣ ሰውነትሽን ከፋፍተሽ ወጥረሽ ያንንም ይኸንንም እየሳብሽ እንድትኖሪ የሚፈልገው ሸይጣን ብቻ ነው።
ራስሽን አሳምነሽ ከእርሱ ልትርቂ ይገባሻል ። እርሱንም እወቂው የኔም፤ ያንቺም፤ የነሱም የጌታሽም ግልፅ ጠላት ነውና፡፡
እያቀረብሽ ያለሽው ምክንያት ከሂጃብ ማምለጫ ከሆነ ግን ልቦናሽ ያውቀዋልና አላህን ልትፈሪው ግድ ይልሻል። እሱ የረቅርቡንም የሩቁንም ድብቁንም ግልፁንም የሚያውቅ አምላክ ነውና።
⑤ኛ. ግልጥ ያለ የአመፀኝነት ምክንያት
“ መደነቅን ስለምወድ ቁንጅናዬና ደም ግባቴ እንዲሁም አቋሜ እንዲታይልኝ ፈልጋለሁና ሂጃብ ደግሞ ይህንን ይጋርድብኛል ”
ይኸ ምክንያት ሰብሰብ ሲደረግ እንጂ በውስጡ በርካታ አባባሎች ኣሉት።
ቆንጆ ልብስ ለምን አስፈለገኝ ?
ፀጉሬን መሰራት ለምን አስፈለገ ?
መዋብ ማማር መቀባባት ለምን ?
እንዳሮጊት ተጀቡኜ ልኑር ?
እዚህ ውስጥ ተሸሽጌ ማን ሊያየኝ ነው ?
ባልስ እንዴት ነው ማገኘው ?
የመሳሰሉ ምክንያቶችን በማሰብ በሂጃብ ጥላ ስር ላለመጠለል ይሟገታሉ።
በመሰረቱ የተዘረዘሩት ነገሮች በሙሉ ካገባሽ በኋላ ለባልሽ የምታደርጊውና ለቅርብ ቤተሰቦችሽ ብቻ የሚፈቀድልሽ ነውና እህቴ ሆይ ሂጃብሽን አደራ
የዓለም ህዝቦች በአጠቃላይ ቁንጅናሽን ቢያደንቁልሽ አንቺን ከአንቺነትሽ ስንዝር ከፍ የሚያደርጉሽ ይመስልሻልን ? አይምሰልሽ
ይሄ አካሄድሽ ጉራ ፍለጋም ይመስላል። አላህ ደግሞ ጉረኛን አይወድም።
መሸፈንሽ ውበትሽ ነው። በአላህና በመልእክተኛው ዘንድም ቆንጆ የሚያስብልሽ ነው።
መገላለጥሽ ደግሞ በሰይጣንና በጭፍሮቹ ዘንድ አድናቆትን ያተርፍልሽ ይሆናልና የሚሻልሽን የመከበርያሽን መንገድ ብትመርጪ ይበጅሻል።
⑥ኛ. እንጭጭ ምክንያት
“ ሂጃብ በመልበስ አምናሁ፣ ግን እኔ ገና ወጣት ነኝ ”
ኢስላም ለህፃናትም፣ ለታዳጊዎችም፣ ለወጣቶች፣ ለጎልማሶችና ለአዛውንቶችም የራሱ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ኣለው።
አንቺንም ሴት ልጅ እንደመሆንሽ ችላ አላለምና ሂጃብሽን እንድትጠብቂ አዝዞሻል።
በሂጃብ የታዘዝሽውም እድሜሽ ደርሶ ወይም አድገሽ ወንዶችን መማረክ ስትደርሺ የግድ ትሸፈኛለሽ። ያለዚያ ለራስሽም ለሌሎችም አደጋ ነሽና መከራከርያሽን መርምሪው።
የትኛው የዋስትና (የኢንሹራንስ) ድርጅት ነው ልጅ ነሽና ችግር የለውም ለአቅመ ሄዋን አልደረስሽም ሂጃብሽን አትጠብቂ ያለሽ
ይህንን እንጭጭና የልጅ ምክንያት እርግፍ አድርጊውና ሂጃብ የማድረግ ግዴታሽንወ ተወጪው።
ጌታችንም እንዲህ ይላል
” فَاسْتَبِقُوا الْخَيْرَاتِ ۚ “
« ወደ መልካም ሥራዎችም ተሽቀዳደሙ፡፡ »
(አል-በቀራ 148)
ያ ዓመተላህ 
አንቺ መልካም የአላህ ባሪያ ሆይ
ከውስወሳዎች ራቂና እንደ ሙስሊምነትሽ ለመኖር ራስሽን አሳምኚው።
በብዥታዎች እንዳትዳክሪም በኢልም ላይ በርቺ። ግንዛቤሽን አሳድጊ። መልካም ጓደኞችም ምረጪ።
አንድ ቀን ሂጃብ የህይወቴ ብርሃን ብለሽ እንደምትመሰክሪም ተስፋ አደርጋለሁ ።
አላህ ቀጥተኛውን መንገድ እኛንም አንቺንም ይምራን።

🌿ተንቢሃት ዋትሳፕ ግሩፕ🌿
www.facebook.com/tenbihat