የእርጋታ ትሩፋቶች فوائد التَّأنِّي
~~~~~~~~~~~~~~~~~
ዛሬ
ዛሬ ከየትኛውም ግዜ በባሰ ሁኔታ ሰዎች ችኩል ሆነው ይታያሉ። አላህ በእዝነቱ የጠበቃቸው ሲቀር እድሜ ፆታና
የትምህርት ደረጃም ሳይለይ ባገኙት ነገር ላይ ሁሉ ጥልቅ የሚሉ ሰዎችን ማየት የተለመደና በሰፊው የሚነበብ ጉዳይ
ሆኗል።
ይባስ ብሎም መረጋጋት፣ ነገሮችን ማጣራት፣
በእውቀትና በአቅም ልክ መጓዝ ተወቃሽ ተደርጎ፤ ያለ አቅም፣ ያለ በቂ እውቀት፣ ያለ ደረጃና ያለ ቦታው ባገኙት
ርዕስ ሁሉ ላይ መዘፍዘፍ፣ ነገሮችን ማንቦጫረቅ፣ ነካክቶና በጥብጦ ፈተናን ማባባስ ችሎታና ተቆርቋሪነት፣ ብቃትና
ክፉን ተከላካይነት ተደርጎ እየተጨበጨበለት ይታያል ይሰማልም።
ነገር ግን ችኩልነት ተወቃሽ እንጂ
ምስጉን ባህሪ አይደለም። ያገኙትን ሁሉ መበተን ወረኛነት እንጂ መረጃ ማስተላለፍ አይሆንም። ኢስላም የመረጃ
ሃይማኖት ነው። መረጃው ግን ሁሉም ትክክለኛ በሆነ ሰንሰለታማ ማስረጃ የተደገፈ ነው። ስለዚህም ብዙ እንጠቀማለንና
እንረጋጋ ! !!
① እርጋታ☞ የአእምሮ ስክነትንና የአስተሳሰብ ቅንነትን እንዲሁም የልብ እርካታን ያስገኛል።
② እርጋታ☞ ከጥመትና ከስህተት ያድናል።
ኢብኑ ዑሰይሚን ረሂመሁላህ ስለ እርጋታ አስፈላጊነትና ስለ ችኩልነት አስከፊነት ቀጣዩን ብለዋል።
« እርጋታ ማለት በነገሮች ላይ ኣለመቻኮል ማለት ነው። አብዛኛው ሰው እየጠፋና እየተዋረደበት ያለውም በነገሮች
ላይ ችኩል ከመሆኑ የተነሳ ነው። ይህም ዜናዎችን ወሬዎችን በማቀባበሉ እንዲሁም አንድን ነገር እንደሰማ ፍርድ
በመስጠቱና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በመጣደፉ ነው። አንዳንዱ ሰው አንድን ዜና እንደሰማ (እርግጠኛ ሆኖ) ወዲያው
ያወራል። ያስተላልፋል። አንዳንዱ ደግሞ ፍርድ ለመስጠት ይቻኮላል። የሆነ ነገር ስለ አንድ ግለሰብ ይሰማና በቃ
ይህንን ነገር ያ ግለሰብ ተናግሯል ወይም አድርጎታል ብሎ በእርግጠኝነት ፍርድ ለመስጠት ይጣደፋል። ከዚያም ያ ሰው
ተሳስቷል… ያሰው ጠምሟል… እና የመሳሰሉትን በመለጣጠፍ ፍርድ ይሰጣል። ይህ ግን ስህተት ነው። ስለዚህም እርጋታ
በሁሉም ነገር ላይ መልካም ነው።»
(ሸርሁ ሪያዱ-ስሳሊሂን: 3/577-578)
③ እርጋታ☞ በዱንያም ሆነ በኣኺራ መጨረሻው ያማረና ምስጉን የሆነ ባህሪ ነው።
④ እርጋታ☞ ውጉዝ ከሆኑ ባህርያት ይከላከላል።
ኢብኑል ቀይዪም ረሂመሁላህ እንዲህ ይመክሩናል። «እርጋታና ልስላሴ ከባህሪ ላይ ስትወገድ ያቺ ፀባይ ወይ
ወደ ችኩልነት፣ ውርደትና ግትርነት ትቀየራለች። ወይ ደግሞ ወደ ድንበር አላፊነት እንዲሁም ልስላሴና እርጋታን ያጣች
ብኩን ትሆናለች።»
[መዳሪጅ አስሳሊኪን: 2/296]
⑤ እርጋታ☞ የአላህን ፍቅርና ውዴታ ለማግኘት ሰበብ ይሆናል።
የአላህ መልእክተኛ صلى الله عليه وسلم ለአሸጅ ዐብደል ቀይስ ረዲየላሁ አንሁ እንዳሉት
«አላህ የሚወዳቸው ሁለት ባህርያት ኣሉብህ። እነሱም ትዕግስትና እርጋታ ናቸው።» [ሙስሊም ዘግበውታል:25]
⑥ እርጋታ☞ የሰውን ልጅ ከሸይጣን ተንኮልና በሱ ላይ ሰፍሮ የበላይ እንዳይሆንበት ይከላከላል።
ይህም የሸይጣን የበላይነት መገለጫ መሆኑን ነቢዩ صلى الله عليه وسلم ሲገልፁ «እርጋታ ከአላህ ሲሆን ችኮላ ግን ከሸይጣን ነው።» ብለዋል።
[ሐዲሱን አቡ ያእላና በይሀቂይ ዘግበውታል። አል አልባኒ በሰሂህ አልጃሚዕ ሀሰን ብለውታል። (3011)]
የእርጋታን ጥቅምና የጥድፊያን ክፋት አልገዛሊ ሲያብራሩ «አንድን ነገር መተግበር ካወቁትና ከተገነዘቡት በኋላ
መሆን ይገባዋል። ማወቅ ደግሞ ማስተዋልና መረጋጋትን ይጠይቃል። ችኮላ ግን ይህንን ያሳጣል። በችኮላ ወቅት ሰውየው
በማያውቀው አቅጣጫ ሸይጣን ሸሩን ይረጭበታል።»
[ኢህያእ ዑሉሙዲን: 3/33]
⑦ እርጋታ☞ ከፀፀት ታድናለች። የሰሙትን ወይም ያዩትን ዜናና ወሬ ሁሉ ከማስተላለፍ ቆም ማለት ከቁጭት ለመጠበቅ ሰበብ ይሆናል።
«እናንተ አማኞች ሆይ! ነገረኛ ወሬን ይዞ ከመጣችሁ (ከማመናችሁና ከማስተላለፋችሁ በፊት ተረጋግታችሁ) አጣሩት።
በስህተት ላይ ኾናችሁ ሕዝቦችን እንዳትጎዱና በሠራችሁት ነገር ላይ ተፀፃቾች እንዳትኾኑ (አረጋግጡ)፡፡» [አል
ሁጁራት: 6]
አላህ የሰከነ አዕምሮና የተረጋጋ ልቦና ይለግሰን። ከአላስፈላጊ ችኮላና ጥድፊያ እንዲሁም ያገኙትን ወሬ ሁሉ በታኝ ከመሆን ይጠብቀን።
•••••••••••••••√
✍🏽Abufewzan
ሰፈር 13/1438
Nov 13/2016