Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በርግጥ እንደ ሙስሊም የአንድ ሰው ሂዳያ መጎናፀፍ በእጅጉ ያስደስተናል፡፡ ሆኖም ግን ነገሮች ልክ ሲኖራቸው ጥሩ ነው፡፡

እጅግ በጣም ርህሩህና አዛኝ በሆነው አላህ ስም እጀምራለሁ፡፡
ማንም ቢሰልም ለራሱ ነው!
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የዮናስ ሙሉነህ በቅፅል ስሙ “ዮናስ ማኛን” መስለም በሰፊው ሲራገብ እያየን ነው፡፡ በርግጥ እንደ ሙስሊም የአንድ ሰው ሂዳያ መጎናፀፍ በእጅጉ ያስደስተናል፡፡ ሆኖም ግን ነገሮች ልክ ሲኖራቸው ጥሩ ነው፡፡
ማንም ቢሆን ወደ ኢስላም ሲመጣ “እንኳን ወደ ተፈጥሯዊው እምነትህ መጣህ” ብለን የሚጠቅመውን በግሉ ልንመክረው ይገባል፡፡ ሙስሊም ማለት ምን ማለት ነው? እንደ ሙስሊም የሚጠበቁበት ቀዳሚ ነገሮች ምን ምን ናቸው? ቀድሞ ከነበረበት እምነት አንፃር ሊኖሩበት ይችላሉ ተብለው የሚሰጉ ብዥታዎችን መግለጥ፣ የኢስላም ጠላቶች በኢስላም ላይ ያለመታከት የሚያነሷቸውን ብዥታዎች መግለጥ፣ ወዘተ ይገባል፡፡ በተረፈም ኢስላምን በሚገባ ይረዳ ዘንድ ወሳኝ የሆኑ ምንጮችን መጠቆም ነው የሚገባው፡፡ በተለይ ደግሞ በሚናገረውም ይሁን በሚፅፈው ላይ ኢስላማዊ ስነ-ምግባር እንዲላበስ ማገዝ ከኛ የሚጠበቅ ነው፡፡
ከዚያ በፊት ግን እኛ እራሳችን ከእንዲህ አይነት ክስተት አንፃር የምንይዘውን አቋም ጤነኛነት ብንገመግም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ለማንም መስለም የተጋነነ ግምት ልንሰጥ፣ የህዝብ መነጋገሪያ ልናደርግ አይገባም፡፡ እንዲህ አይነት አካሄድ ለኢስላምም፣ ለሙስሊሞችም፣ ለሰለምቴዎቹም ብዙ ጣጣ እያመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-
1. አንዳንዶች በምንሰጣቸው የተጋነነ ግምት ተሸውደው ያለ በቂ ግንዛቤ ወደ ዳዕዋው መድረክ እንዲወጡ እያደረግን ነው፡፡ በዚህም ብዙ ጥፋቶች እየተፈፀሙ ነው፡፡ አንዳንዶች ቀደምቶቻችን ስንት መስዋእትነት የከፈሉለትን አጀንዳ እንደ ዋዛ እየጠመዘዙ ሲያቀርቡ እየተመለከትን ነው፡፡
2. ከዚሁ ተነጥሎ የማይታየው አንዳንዶቹ በሚሰጣቸው የተጋነነ ሙገሳ ተሸውደው ኢስላምን በቅጡ ለመረዳት ከመጣር እየተዘናጉ ነው፡፡
3. አንዳንዶቹ አጨብጭበንላቸው፣ አሞግሰናቸው ሳንጨርስ ከኢስላም ሊወጡ ይችላሉ፡፡ “ታዲያ ይሄ ምን ችግር አለው? ሂዳያ ያለው በአላህ እጅ ነው፡፡ ሲሰልሙ ተደስትን እንጂ….” ሊባል ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር ጉዳዩ ከዚህ ያለፈ አንድምታ አለው፡፡ ጉዳዩን በራሳችን አረዳድ አንመልከተው፡፡ የሰዎች የግንዛቤ ደረጃ እንደሚለያይ አንዘንጋ፡፡ አንድ ሰው ሲከፍር ቀድሞ “በታዋቂነቱ” የፈፀምነው የተጋነነ ማራገብ ቀላል የማይባሉ ሰዎች ላይ ነውጥ ይፈጥራል፡፡
ቀድሞ ነገር የአንድ ሙዚቀኛ ወይም ፖለቲከኛ ወይም እስፖርተኛ መስለም በየእለቱ በየሰፈራችን ከሚሰልሙ ሰዎች ሁኔታ ያን ያክል የተለየ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በክፉም ይሁን በበጎ ታዋቂ የነበሩ ሰዎች ሲሰልሙ ህዝብ ዘንድ የሚፈጥረው ግለት የተለየ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን የምናስተናግድበት መንገድ ባለ ጉዳዩንም ይሁን ሌሎችን ዋጋ የሚያስከፍል እንዳይሆን በውል መፈተሽ ይበጃል፡፡ በተለይ ጥንቃቄ እንዲኖረን የሚያመላክቱ ጠቋሚ ምልክቶች (ቀራኢን) ሲኖሩ ደግሞ ረጋ ማለት ይኖርብናል፡፡ “እኛ ስለ ልቡ ምን አገባን” “ውስጡን ለአላህ መተው ነው” … ወዘተ የምንለው አገላለፅ በእውነተኛ ቃላት የተጠቀለለ ግልብ ትንታኔ ነው፡፡ እርግጥ ነው በማንም ልብ ውስጥ ገብተን የመፍረድ ስልጣኑም፣ ብቃቱም ፍላጎቱም የለንም፡፡ ከምንም ተነስተን ክፉ ጥርጣሬ እንድናሳድርም አይፈቀድልንም፡፡ አላማየም ወደ መጠራጠር መጣራት አይደለም፡፡ ይልቁንም ማንም ሲሰልም ጉዳዩን የምንይዝበት መንገድ ጤናማ መሆኑን እናረጋግጥ ለማለት ነው፡፡ ያለበለዚያ ሰውየውን አጉል ቦታ ሰጥተን እንሸውደዋለን፡፡ ያለምንም ግንዛቤ በሰለመ በማግስቱ ወደ ደዕዋ እንዲገባ አድርገን ለሌሎችም መሳሳት ሰበብ እንሆናለን፡፡ ምናልባት ካፈነገጠም ዛሬ የምናደርገው የተጋነነ አቀራረብ ከወትሮው በተለየ መልኩ የጠላት መሳለቂያ ያደርገናል፡፡ ይሄ ደግሞ በተራው አንዳንድ ደካሞች ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ውጤት አለው፡፡
በመጨረሻም ለዮናስም ይሁን ለሌሎች ወደ ኢስላም ለሚመጡ ሁሉ አላህ ፅናትን እንዲሰጣቸው እየተመኘሁ ኢስላም ባዶ “እመን ትድናለህ” አይደለምና ግንዛቤን መሰረት ያደረገ ተግባራዊ ኢስላም ይኖራቸው ዘንድ መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ በሚፅፏቸውና በሚናገራቸው ነገሮችም ኢስላም የእልህ እና የብሽሽቅ ሃይማኖት አይደለምና ከፀያፍ ቃላትና ትርርብ በመቆጠብ እራሳቸውን በመልካም ስነ-ምግባር ሊያንፁ ይገባል፡፡ ክርስትና ውስጥ ለሚኖሩ ቤተሰቦችና ወገኖች ተቆርቋሪነትና ርህራሄ የሚስተዋልበት አቀራረብ በመቅረብ ወደ ኢስላም ሊጠሯቸው ይገባል፡፡ ወደ ኢስላም ለሚመጡ ሰለምቴዎች ከተዘጋጁ በርካታ ድረ-ገፆች ውስጥ ለናሙና ያክል እነዚህን ቢመለከቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡