Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

السعي لنفع المسلمين. 🌐 " ሙስሊሞችን በመጥቀሙ ጉዳይ ላይ መሯሯጥ "

السعي لنفع المسلمين. 
🌐
" ሙስሊሞችን በመጥቀሙ
ጉዳይ ላይ መሯሯጥ "

ኢስላም ከመሰረቱ ያለው አስተምህሮት ራስን፣ ቤተሰብን፣ ጎረቤትንና ዘመዶችን አልፎም ጓደኛንና ማህበረሰቡን እያለ የሰው ልጅን ሆነ ሌሎች ፍጡራንን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መሰማራትን በማስተማር ነው የመጣው።
በዚህም አስተምህሮት ራስን ከጎጂ ነገር ከመከላከል ጀምሮ የሰዎችን ችግር በማቅለሉ ረገድ የቅርብ የቅርብ እያለ እየሰፋ ይሄድና በተለይ ፍላጎታችን የአላህን ውዴታ ለማግኘትና የምንችለውን ያህል መልካም አስተዋፅኦ ለሙስሊም ወገናችን ካበረከትን ለከፍተኛ ክብር ያደርሰናል።
ያለዚህ ለብቻችንም ሆነ ከሌሎች ጋር ተሰባስበን የምናሰላው፣ የምንወያየው፣ የምንጨዋወተውና የምንመካከረው ጉዳይ ሁሉ ጥቅሙ አይታይም። ምክንያቱም ለራሱም ለሌሎችም በማይፈይድ ነገር ግዜና አቅልን እንዲሁም ገንዘብና ጉልበትን ማባከን ምንም ኸይር የለውምና።
ይህንንና ሌሎች ነጥቦችን በሚገልፅ መልኩ አላሁ ሱብሀነሁ ወተዓላ በተከበረው ቃሉ
(لَا خَيْرَ فِي كَثِيرٍ مِنْ نَجْوَاهُمْ إِلَّا مَنْ أَمَرَ بِصَدَقَةٍ أَوْ مَعْرُوفٍ أَوْ إِصْلَاحٍ بَيْنَ النَّاسِ ۚ وَمَنْ يَفْعَلْ ذَٰلِكَ ابْتِغَاءَ مَرْضَاتِ اللَّهِ فَسَوْفَ نُؤْتِيهِ أَجْرًا عَظِيمًا). 
[سورة النساء : ١١٤ ].

"ከውይይታቸው በምጽዋት ወይም በበጎ ሥራ ወይም በሰዎች መካከል በማስታረቅ ከሚያዝዙ ሰዎች ውይይት በስተቀር በበርካታው (ውይይታቸው) ውስጥ ደግ ነገር የለበትም፡፡ ይኸንንም (ጠቃሚ ውይይት) የአላህን ውዴታ በመፈለግ ለሚሠራ ሰው ታላቅ ምንዳን እንሰጠዋለን፡፡" ይላል
[አን-ኒሳእ: 114]

ለዚህም ተጨማሪ ማብራርያ የሚሆነንን አላህ ስራውን ይውደድለትና በጃቢር ቢን አብደላህ ሀዲስ እንደተገለፀው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ስለ ምርጥ ሰዎች ሲያወሱ
عَنْ جَابِرِ بنْ عَبْدُ اللهِ عنِ النَّبيّ صلّى اللهُ عَليْهِ وَسَلّمَ أنّهُ قالَ: 
( خيرُ الناسَ أنفعُهُمْ لِلناس ). 
【رواه الطبراني وحسنه الالباني.】
«ከሰዎች መሃል በላጩ ሰውን የሚጠቅም ነው።" ብለዋል።
【ጦበራኒ ዘግበውታል… አልባኒም ደህና ዘገባ ነው ብለውታል።】

በሌላኛው ከአቡሁረይራ ረዲየላሁ አንሁ በተወራው ሀዲሳቸው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ሰዎች እርስ ለርሳቸው እንዲተዛዘኑና እንዲረዳዱ፣ ሙስሊሙ የወንድሙ ጭንቀት እንዲሰማውና የራሴ ጉዳይ ነው ብሎ ያን ችግሩን ለመቅረፍ እንዲሯሯጥ ለማነሳሳት በዚህም የሚያገኘውን ሽልማት በማውሳት
وعن أبي هريرة رضي الله عنه قال : قال رسول الله صلى الله عليه وسلم : ( من نفس عن مؤمن كربة من كرب الدنيا ، نفس الله عنه كربة من كرب يوم القيامة ، ومن يسّر على معسر ، يسّر الله عليه في الدنيا والآخرة ، ومن ستر مؤمنا ستره الله في الدنيا والآخرة ، والله في عون العبد ما كان العبد في عون أخيه...... الحديث ) . 
【 رواه مسلم 】
"ከዱንያ ላይ ጭንቀቶች መካከል የሆነ ጭንቅን ከሙእሚን ላይ ለገላገለ ሰው አላህም ከትንሳኤው ቀን ጭንቀቶች መካከል እንዲሁ ከጭንቁ ይገላግለዋል። ከተቸገረ ሰውም ችግሩን ላቀለለት አላህም ዱንያውንና አኺራውን ያቀልለታል። የሙእሚኑን ነውር ለሸፈነለትም አላህ በዱንያም በአኺራም ከክፉ ነገር ይሸፍነዋል። አንድ ባሪያ ወንድሙን በመርዳት ላይ እስካለ ድረስ አላህም ባሪያውን በመርዳት ላይ ይገኛል…" ብለዋል።
【ሙስሊም ዘግበውታል።】

ይህንን ሀዲስ ኢማም አን-ነወዊ አላህ ይዘንላቸውና ሲያብራሩት 
قال النووي رحمه الله:
"في هذا فضل إعانة المسلم وتفريج الكرب عنه وستر زَلاَّته، ويدخل في كشف الكربة وتفريجها مَنْ أزالها بماله أو جاهه أو مساعدته، والظاهر أنه يدخل فيه مَنْ أزالها بإشارته ورأيه ودلالته". 
【شرح صحيح مسلم [١٦ / ١٣٥ ].】

« ይህ ሐዲስ ሙስሊሞችን በስልጣኑ፣ በገንዘቡና በእገዛው የመርዳት፣ ከችግራቸው እንዲላቀቁ የማገዝ፣ ስህተቶቻቸውን የማለፍ ትሩፋትን ያመላክታል። እንዲሁም ሀዲሱ ላይላዩን እንደሚያሳየው [የቸገረው መፍትሄ እንዲያገኝ] በሚሰጠው ጥቆማው፣ በሚያቀርብለት አስተያየትና በሚያመላክተው አቅጣጫ ችግርን ያስወገደ ሰው ትሩፋቱን ከሚያገኙት ይካተታል። »
【ሸርሕ ሰሂህ ሙስሊም: 16/135】

አላህ በእዝነቱ የጠበቀው ሰው ሲቀር አብዛኛው የዘመናችን ሰው እንኳንስ የሙስሊሞችን ችግር ለመቅረፍ ሊንቀሰቀስ ቀርቶ ራሱን ውጥረት ውስጥ ከመዝፈቅ ጀምሮ የትዳር አጋሩንና ልጆቹን በማማረር፣ ቤተሰቦቹን በማወክ፣ ጎረቤቶቹን ሰላም በመንሳት፣ ጓደኞቹን በመመቅኘትና የሌላውንም ሰው መብት በመተላለፍ የተፈተነ ነው።
የኢስላም ዕንቁዎቹ ትውልዶችና እነሱን በዓርዓነት የተከተሉት ግን ከአላህ ምንዳን በመፈለግ የሙስሊሞችን ችግር መቅረፍ ከተጨማሪ የግል ዒባዳቸው ይልቅ እነሱ ዘንድ ተወዳጅ ተግባር እንደሆነ ከሰሃቦች የተገኙት መረጃዎች ያመላክታሉ። እንደምሳሌነትም በርካታ የሚጠቀሱ ተምሳሌቶች ይኖራሉ አላህ ተግባሮቻቸውን ይውደድላቸው።
በአጠቃላይ ሙስሊም ለሙስሊም እንደ አንድ አካል እንደመሆኑ አንዳችን ያንዳችን ህመም ሊሰማን ይገባል። በተለይ በቤተሰቦቻችን፣ በዘመዶቻችን፣ በጎረቤቶቻችንና በጓደኞቻችን ላይ የሚደርሱ አስጨናቂና አሳሳቢ ጉዳዮች ከእይታችንም ሆነ ከመስሚያችን የተሰወረ ባለመሆኑ እንዳላወቀ፣ እንደማይመለከተውና እንደማይችል ሰው ሆነን ችላ ልንለው አይገባም።
በዚህ ድጋፋችን ከምናገኘው መልካም ትሩፋት ባሻገር ተጠያቂነትም ስላለብን በጉልበታችን፣ በእውቀታችን፣ በገንዘባችንና በግዜያችን ብሎም ባለን ተሰጥኦና ተሰሚነታችን ልክ ወገንን ለመርዳት እንንቀሳቀስ 

አላህ ከችግር ያውጣን። ለሌሎችም ደራሽ ያድርገን።