Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሸይኽ ሙሐመድ አብዱል ወሓብ እና “ዑዝር ቢል ጀህል” የሚለው አጀንዳ ከራሳቸው ድርሳናት


 
 
ሸይኽ ሙሐመድ አብዱል ወሓብ እና “ዑዝር ቢል ጀህል” የሚለው አጀንዳ ከራሳቸው ድርሳናት፦


C ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ (ረሂመሁላህ) የተክፊር መስፈርቶችንና

አንድን ግለሰብ እነዳይከፍር የሚከለክሉ ምክንያቶችን ጠንቅቀው በመረዳት

ተግባራዊ ያደረጉ ታላቅ ኢማም ናቸው።

አንድን ግለሰብ እንዳይከፍር ከሚከለክሉ ሰበቦች መካከል፦

አለማወቅ፣በግዳጅ ኩፍርን መስራት፣ተእዊል እና ሳያውቁ ስህተትን መፈፀም

ይገኙበታል።

ለነዚህም ነገሮች ከቁርኣንና ከሐዲስ በርካታ መረጃዎች አሏቸው።

ሸይኹ ምንም አዲስ እና እንግዳ ነገር ይዘው አልመጡም፣የእሳቸው ደዕዋ የደጋግ

አበዎች (ሰልፉን ሷሊሂን) ጥሪ አንዱ አካል እንጂ ሌላ አይደለም።

ነገር ግን እዚህ ቦታ ላይ ከብዙ ሰዎች የሚሰወር እውነታ አለ፣

አንዳንዴ ለሐቅ መወገን በሚል የጋለ ወኔ፤ አንዳንዴ ደግሞ

በባጢል እዚህ ርዕስ ላይ ሲዘባርቁ ይስተዋላል።

ይህም ጉዳይ ፦"ዑዝር ቢልጀሕል" አለማወቅ ኡዝር ነው? ወይስ

አይደለም? የሚለው ከባድ አጀንዳ…

አንዳንድ ሰዎች በዚህ ዙሪያ ድርሰት አዘጋጅተው ፦

ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱል ወሃብ ኡዝር ቢል ጀህል የለም

ይላሉ በማለት ከንግግራቸው መካከል ቆርጠው ይህን የሚደግፍ

እና የሚመስል ነገር ሲያቀርቡ ሌሎች “ኡዝር ቢልጀህል” መኖሩን የሚጠቁሙ

ንግግራቸውን ሆን ብለው ይተዋሉ።

የሸይኹን ድርሳናት በደንብ የተከታተሉ እና ያነበቡ ሰዎች

የሚከተለው ፍንትው ያለ ውጤት ላይ መድረሳቸው አይቀሬ ነው።

በመጀመሪያ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር "ኡዝር ቢልጀህል"

የሚባለው ርዕስ ሁለት ክንፎች አሉት።እነሱም፦

1ኛ/ ኡዝር የሚሰጥበት ጉዳይ ይወስነዋል ይህም ማለት፦

ያልተወቀውና ችላ የተባለው ጉዳይ ወሳኝና አንገብጋቢ ርዕሶች እንዲሁም መሰረታዊ አጀንዳ ላይ የሚካተት ነው? ወይስ አይለም?

የሚለው የሚታይ ሲሆን፦

2ኛው/ ደግሞ “አላዋቂ” ነው የምንለው ግለሰብ ማንነት መታየት

ይኖርበታል።ይህም ስንል ፦ አዲስ ሰለምቴ ነው ወይስ ከከተማ

እጅግ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ላይ በማደጉ የተነሳ ከእውቀት የራቀ

ነው?ወይስ አይደለም? የሚሉት ነገሮች መታየት ይኖርባቸዋል።

በዚህ ላይ የሽይኹ አካሄድ እና አቋም ግልፅና የማያሻማ ሁኔታ፦

"ኡዝር ቢል ጀሕል" እንዳለ የሚጠቁሙ እጅግ በርካታ ንግግሮች

እንዳሉ ሁሉ አንዳንድ ንግግራቸው ደግሞ ከፊል ሰዎችን ሸይኹ

" ኡዝር ቢል ጀህል" የለም ይላሉ የሚል ግምት ላይ እንዲወድቁ

የሚያደርጉ ንግሮችን እናገኛለን።

ከዚህ በመቀጠል "ኡዝር ቢል ጀህል" መኖርን የሚጠቁሙ የሸይኹ ንግግሮችን

ካቀርብኩ በኋላ የዚህ ተቃራኒውን የሆነውን ንግግር

በመጥቀስ በአላህ ፍቃድ ምላሽ የምሰጥ ይሆናል ።

በመጀመሪያ "ዑዝር ቢል ጀህል" መኖርን የሚጠቁሙ የሸይኹ

ንግግሮችን ላስቀድም፦

የመጀመሪያው ንግግር፦

አላህ ይዘንላቸውና ሸይኹ እንዲህ ይላሉ፦

"አብዱል ቃዲር እና አሕመድ በደዊ የመሳሰሉት ፃድቃን መቃብር ዘንድ የሚገኘውን ጣኦት የሚያመልኩ ሰዎች ይህን ተግባር የሚፈፅሙት ባለማወቃቸውና ይህ ተግባር

ትክክል አለመሆኑን እና ከጅህልናቸው የሚያነቃቸው ሰው ባለመኖሩ የማናከፍር ከሆነ፣በአላህ ያላጋራን ሰው ወደ እኛ ስላልተሰደደ ብቻ ይከፍራል፣ መገደል አለበት እንዴት እንላለን?!

“ሱብሓነከ ሀዛ ቡህታኑን ዐዚም!”ለአላህ ጥራት ይገዋና ይህ እልም ያለ ትልቅ ቅጥፈት ነው።"

【"አዱረሩ ሱኒያ "(1/66)】

===== ===== ===== =====

ይህ ተግባር ትክክል አለመሆኑን እና ከጅህልናቸው የሚያነቃቸው ሰው ባለመኖሩ

የሚለውን አባባላቸውን አፅንኦት በመስጠት ያንብቡልኝ።





ሁለተኛው የሸይኹ ንግግር፦

"ጠላቶቼ ስለኔ የጠቀሱት ፦

እኔ በግምት ተነድቼ እንዲሁም የኔ ወዳጅ ስላልሆነ ብቻ ያለ ምንም ማስረጃ

እንደማከፍር የሚናገሩት በሙሉ

ትልቅ በኔ ላይ የተቀጠፈ ቅጥፈት ነው፣ከዚህም በስተጀርባ የሚፈልጉበት ነገር

ቢኖር ፦ ሰዎችን ከአላህና ከመልክተኛው ዲን ማስበርገግ ነው።"

【"መጅሙዕ ሙአለፋት አሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ዐብዱል ወሓብ"(3/34)】





ሦስተኛው የሸይኹ ንግግር፦

"… ሽርክ ባጢል መሆኑ መረጃ ቀረቦለት በአላህ ብቸኛ ተመላኪነቱ ላይ ያጋራን

ሰው ነው እኛ የምናከፍረው።"

【ሙአለፋት ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ አብዱልወሀብ (ገፅ፡60)



አራተኛው የሽይኹ ንግግር፦

"… ማክፈርን አስመልክቶ እኔ የማከፍረው ሰው ቢኖር፦

የመልክተኛውን ዲን ጠንቅቆ ካወቀ በኋላ ዲኑን የተሳደበ ፣ሰዎችን ከዲኑ የከለከለ እና ዲኑን የተገበርን ሰው ጠላት አድርጎ የሚዘውን ግለሰብ ነው ፣ “ወልሐምዱሊላህ

(ለአላህ ምስጋና ይግባውና) አብዛኛው ህዝበ ሙስሊም እንዲህ አይደለም።"

【ሙአለፋት ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ አብዱልወሀብ (ገፅ፡38)





"አልሐምዱሊላሕ! አብዛኛው ህዝበ ሙስሊም ካፊር አይደሉም።" የሚለውን

አባባላቸው በደንብ ያስተውሉ!

ከዚህ አባባላቸው የምንረዳው ፦

ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ አብዱልወሓብ ከራሳቸው ውጭ ያለን ሙስሊም በሙሉ

ያከፍራሉ ለሚሉ አወናባጆች ግልፅ ምላሽ ነው።

ይህንና የመሳሰሉ የሸይኹ ንግግሮች እጅግ በርካታ ናቸው ለግዜው እዚሁ ላይ እናብቃ።

" ኡዝር ቢልጀህል " የለም የሚል ምልክትን ሊያስይዙ የሚችሉ የሸይኹ ንግሮች፦

አንደኛው የሸይኹ ንግግር፦

"… ይህን ካወቅክ፤ ያም ፦አንድ ሰው ከአንደበቱ በሚወጣ ቃል የተነሳ ይከፍራል፣

ይህንም ቃል ሲናገር ባለማወቅ ሊሆን ይችላል፣በዚህም ጉዳይ ኡዝር አይሰጠውም።"





ሁለተኛው የሸይኹ ንግግር፦

ዒምራን ኢብኑ ሑሰይን ያስተላለፉት ሐዲስን ሲያብራሩ፦

"የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አንድ ሰው ጡንቻው ላይ ከመዳብ የሆነ

ሂርዝ አስሮ ተመለከቱና፦

"ወዬልህ! ምንድነው? ይህ ነገር? " አሉት

እርሱም፦"ጡንቻ ላይ ያለ በሽታ ለመከላከል ፈውስ ነው።" አላቸው

እሳቸውም፦" በሽታህን እንጂ ሌላ አትጨምርህም ፣መንጭቀህ ጣለው፣(ወርውረው)፣እርሷ ባንተ ላይ እያለች ሞተህ ቢሆን ኖሮ ዘላለም ከእሳት ነፃ አትወጣም ነበር።"

አሉት ።

ሸይኹ እዚህጋ እንዲህ ብለዋል፦

"ከዚህ የምንረዳው፦ አለማወቅ ኡዝር አይደለም።"

እነዚህንና መሰል ሌሎች የሸይኹ ንግግሮች በመሰብሰብ በምናስተውልና ትኩረት

ሰጥተን ስናነብ ሸይኹ "ኡዝር ቢልጀህል" አለ እንደሚሉ መረዳት ለማንም

አይሰወርም።

"ምናልባትም ሳያውቅ የኩፍር ንግግር ከአንደበቱ ሊወጣ ይችላል ነገር ግን ባለማወቁ ኡዝር አይሰጠውም።"የሚለውን ንግግራቸውን እንዴት ነው? መረዳት ያለብን ታዲያ?የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። አግባብ ያለው ጥያቄ ነው።

እዚህ ላይ መልሱ ሊሆን የሚችለው እንደሚከተለው ይሆናል፦

ይህ ከላይ ያነሳነው የሸይኹ ንግግር ኡዝር ቢልጀህል አለ ከሚለው አባባላቸው ፈፅሞ

አይቃረንም፣ምክንያቱም ጅህልና(አለማወቅ) ሁሉም ቦታ በልቅ ኡዝር ሆኖ

አይቀርብም።

Cይህንንም ጉዳይ ሸይኹ እንዲህ ሲል ያጠናክሩታል፦

"መማር፣መጠየቅ እየቻሉ ይህን ባለማድረጋቸው በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሰው ልጆች ባለማወቃቸው በጅህልናቸው ኡዝር አይሰጣቸውም ፣ ይህ ችላ በማለቱ የመነጨ

ነውና።"

ከዚህ ንግግር የምንረዳው፦ ኢማም ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ አብዱልወሃብ ዘንድ

ይህ አይነት ግለሰብ ነው ኡዝር የማይሰጠው።

ለዚህም መረጃቸው፦ የአላህ አዘወጀለ ንግግር ነው፦

"የማታውቁ ከሆነ የዕውቀት ባለቤቶችን ጠይቁ።" 【አነህል፡43】

ሸይኹ ሌላ ቦታ ላይ እንዲህ ይላሉ፦

"…ማስታወሻ!ጃሂል ኡዝር አይሰጠውም ምክንያቱም መጠየቅ መረዳት እድሉ

አለውና።"



ሐዲሱ ዒምራን ላይ ኡዝር አልሰጡትም።"የሚለው አባባል ላይ የሚሰጠው ምላሽ፦

ሁላችሁም እንደምታውቁት ይህ የሰሓባው ተግባር ትንሹ ሽርክ ውስጥ የሚመደብ ነው እንጂ ትልቁ ከኢስላም የሚያስወጣው ሽርክ አይደለም።

ይህ ከታወቀ ዘንድ ሸይኹ ከላይ እንዳሳለፍነው መረጃ ካልቀረበለት ትልቁን ሽርክ

እንኳ ቢፈፅም ኡዝር እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

የሳቸው የልጅ ልጅ የሆኑት ሸይኽ ዐብዱለጢፍ ኢብኑ አብዱራሕማን ኢብኑ ሐሰን

ኢብኑ ሙሐመድ ኢብኑ አብዱልወሃብ፦

C"ትንሹ ሽርክ ከትልቁ ሽርክ በላይ ኡዝር ሊሰጠው ይገባል።"

Cታላቁ የዘመናችን ፈቂህ ሸይኽ ዑሰይሚን(ረሂመሁላህ)

የሸይኹን ንግግር ሲያብራሩ ፦

"ባለ ማወቁ ኡዝር አልሰጡትም።" ማለት፦

"ካሳወቁት እና አውጥተህ ጣል ካሉት በኋላ ።"ማለት ነው።

ይህ የሸይኽ ዑሰይሚን ንግግር ወሳኝ ነጥብ ነው፡ ምክንያቱም የኡለማ ንግግርን

መረዳት የሚችለው ዓሊሞች ናቸውና።

ከዚህ በመነሳት የምንረዳው ነገር ቢኖር አንዳንድ ሰዎች የሸይኹን ድርሳናት

ቆራርጠው የኢንተርኔት ዌብሳይቶች ላይ በመልቀቅ፦ ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ አብዱልወሃብ "ኡዝር ቢል ጀህል " የለም፣ ተገዶ ኩፍርን ቢፈፅምም ይከፍራል፣ሌላም ሌላም ይላሉ እያሉ ይለጣጥፋሉ።

ንግግራቸውን በመቆራረጥ አገባቡን በማሳት ሌላ መልዕክት እንዲኖረው ያደርጋሉ፣ይህ ሸይኹ ላይ ታላቅ በደል ከማድረስ ይቆጠራል።

Cሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ ኩፍርን በልቁ ከመጠቀም በጣም ጥንቁቅ

ሲሆኑ ያለ አግባብ ከማክፈር እጅግ የራቁ ታላቅ ኢማም ነበሩ።

የኢስላም ማዕዘናት መሰረቶች ጠቅሰው እያብራሩ እንዲህ ይላሉ፦

C"ሁለቱን የምስክር ቃሎችን የተወ ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንንም አናከፍርም።

" ሰላት የተወ ሰው በኢስላም ያለውን ቦታ ጠቅሰው እንዲህ አሉ፦

"…ኡለማዎች ሰላትን ግዴታ ነው ብሎ ነገር ግን በስንፍና ሰላት የተወ ሰው ላይ

አስመልክቶ የተለያየ አቋም አላቸው።"

"የእኔ አቋም ሙስሊም ሊቃውንት ተስማምተው ይከፍራል ባሉት የኩፍር አይነት

እንጂ ማንንም አላከፍርም።"

በአጭሩ የሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ አካሄድ የሰለፎች አካሄድ ነው፣ይህም ድንበር በማለፍ እና በመቸኮል ማክፈርም ሆነ ሙብተዲዕ ነው ከማለት የተቆጠቡ ሲሆኑ፣ከዚሁ ትይዩ መስፈርቶች ከተሟላ እና እንዳይክፍር የሚያግዱ ከለላዎች ከተወገዱ

ከማክፈር ወደ ኋላ የማይሉ አቻ የሌላቸው ትውልዶች ነበሩ ።ሚዛናዊ እና ማዕከላዊ አካሄድ ላይ ነበር መንሃጃቸው የተመሰረተው።

አላሁ ሁላቸውንም ስራቸውን ይውደድ እና ይቀበላቸው፣ይዘንላቸውም

እኛንም ለውዴታውና ወዶ ለሚቀበለው ስራ ይግጠመን እያልኩ ፅሑፌን

በዚህ አበቃሁ።

ወሰላሙ አልይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካትሁ።

== == == == == == == == == ==

አቡ ሑዘይፋ

ጥር 13/2008