Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የ ጀነት ፀጋ ሴቶች በጀነት ባል ይኖራቸዋልን ?



 የ ጀነት ፀጋ

ሴቶች በጀነት ባል ይኖራቸዋልን ?

ጀነት አላሁ ሱብሃነሁ ወተዓላ ለደጋግ ባሮቹ ሊሸልመው ያዘጋጀው ወሰንና ልክ የሌለው የፀጋ፣ የምቾት፣ የደስታ፣ የመንደላቀቅ ስፍራ ነው።

በዚህም ጀነት ውስጥ ለመግባት የታደሉ ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች የተለያዩ መደሰቻ ሽልማቶችን ይጎናፀፉበታል።

ከነዚያም መካከል አንዱና ዋነኛው አብረው የሚንፈላሰሱትን ፍቅረኛ አጋር ማግኘት ነው።

በዚህም መሰረት ለወንዶች "ሁ… ሩን ዒ…ን" የተሰኙ፣ ሁሌም ደናግልት የሆኑ፣ ውበታቸው እንደ ሉል የሚያጓጉ፣ ገላቸው ድንቅ የሆኑ፣ ሁሌም ወጣት፣ ሁሌም ተናፋቂና የማይሰለቹ እንስቶችን መሸለም ነው።

ይህ ልገሳ ለወንዶች ሲሆን ሴቶችስ በጀነት ምን አይነት ባል ይኖራቸዋል? ስለዚህም ጉዳይ ሴቶቹም ይጠይቃሉና ባሎቻቸው እነማን ይሆኑ ?

አል-አል'ላማህ ሸይኽ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን [ረሂመሁላህ] … በጀነት ለወንዶች "ሑ…ሩን ዒ…ን" የተሰኙ ሚስቶች እንዳላቸው ተጠቅሷል፤ ለሴቶችስ ? ተብለው ተጠየቁና በሚቀጥለው መልኩ ምላሽ ሠጡ ☞

{[ የታላቅ ግርማና ኃያልነት ባለቤት የሆነው አላህ ለጀነት ሰዎች ያደረገውን ዘልዓለማዊ ፀጋ አስመልክቶ

” وَلَكُمْ فِيهَا مَا تَشْتَهِي أَنْفُسُكُمْ وَلَكُمْ فِيهَا مَا تَدَّعُونَ
نُزُلًا مِنْ غَفُورٍ رَحِيمٍ. “

«ለእናንተም በእርሷ ወስጥ ነፍሶቻችሁ የሚሹት ሁሉ አለላችሁ ፡፡ ለእናንተም በእርሷ ውስጥ የምትፈልጉት ሁሉ አለላችሁ ። መሐሪ አዛኝ ከሆነው አላህ የተደረገላችሁም መስተንግዶ ነው።» ይባላሉ ይለናል ።
【 አስ-ሰጅዳህ: 31-32】

በተጨማሪም ኃያሉ አምላካችን

” وَفِيهَا مَا تَشْتَهِيهِ الْأَنْفُسُ
وَتَلَذُّ الْأَعْيُنُ
وَأَنْتُمْ فِيهَا خَالِدُونَ. “

«በእርሷም (በጀነት ) ውስጥ ነፍሶች የሚከጅሉት፣ አይኖችም የሚደሰቱበት ሁሉ አልለ። እናንተም በውስጧ ዘውታሪዎች ናችሁ።» ይለናል።
【አዝ-ዙኽሩፍ : 71】

እንደሚታወቀው ትዳር ነፍሶች ከሚሹት ዋነኛው ነው። ይህም ለጀነት ሰዎች ለወንዱም ይሁን ለሴቷ በጀነት ውስጥ ይገኝላቸዋል።،

ክብሩ የላቀው አምላካችንም በጀነት ውስጥ ሴቷ እንድታገባ ያደርጋታል። ለእንስቷ በዱንያ ላይ ባሏ ለነበረውም ሰው ይድራታል።

ሃያሉ አላህ እንዳለውም

” رَبَّنَا وَأَدْخِلْهُمْ جَنَّاتِ عَدْنٍ الَّتِي وَعَدْتَهُمْ
وَمَنْ صَلَحَ مِنْ آبَائِهِمْ وَأَزْوَاجِهِمْ وَذُرِّيَّاتِهِمْ
إِنَّكَ أَنْتَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ “.

«ጌታችን ሆይ ! እነርሱንም ከአባቶቻቸውና ከሚስቶቻቸውም፣ ከዝርዮቻቸውም የበጀውን ሁሉ
እነዚያን ቃል የገባህላቸውን የመኖሪያ ጀነቶች አግባቸው [አስገባቸው]።
አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህና። ]}
[አል-ሙእሚን: 8]

【መጅሙዑ-ፈታዋ ወረሳኢሉ ኢብኑ-ዑሰይሚን 2/51】

በዚህ መሰረት ለሴቶቹም የሚፈልጉትን አይነት ምርጥ ባል እንደሚሰጣቸው ተረድተናል።

በሌላ በኩል በዱንያ ላይ ባሏ ለነበረውም እንደምትዳር በተገለፀው መሰረት በዱንያ ላይ ከአንድ በላይ ባል አግብታ የነበረችና ባሎቿ የነበሩት ሁሉም የጀነት ከሆኑ የትኛውን ታገባዋለች በሚለው ዙርያ ምሁራን የተለያየ ራእይ አስቀምጠዋል።

አንዳንዶቹ ምርጫ ታደርግና በስነምግባሩ የተሻለውን መርጣ ታገባዋለች ብለዋል።

ከፊሎቹ ደግሞ በዱንያ ላይ ሳለች የመጨረሻውን ባሏን ታገባዋለች ብለዋል። ለዚህም አባባላቸው መደገፊያ ያደረጉት አስረጅ ከነቢዩ [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] በተዘገበው
” المَرْأَةُ لِآخِرِ أَزْوَاجِهَا “ صححه الشيخ الألباني رحمه الله
«እንስቷ ለመጨረሻው ባሏ ነው የምትሆነው።» የሚለውን ሀዲስ ነው።

ይህንንም ሀዲስ ሸይኽ አል አልባኒ [ረሂመሁላህ] በሲልሲለቱል-ሀዲስ አስ'ሰሂሃ ድርሳናቸው [3/275 ቁጥር 1281] ላይ ሰሂህ ብለውታል።

በዱንያ ህይወቷ አግብታ የማታውቅ እንስት ወይም አግብታው የነበረው ባል መጨረሻው የጀነት ሰው ካልሆነስ ምላሹ ምን ይሆን ?

ይህንን በተመለከተ ከላይ ሸይኽ ሷሊህ አልዑሰይሚን ባስቀመጡት አጠቃላዊ ቁርኣናዊ ጥቆማ መሰረት ለየትኛዋም ለጀነት የበቃች ሴት የፈለገችውን ሁሉ እንደምታገኝ ተገልፇል።

ከዚህ በተረፈ ለየት ያለ ቀጥታዊ ዝርዝር ጠቋሚ ነገር ግን አልተጠቀሰም።

ይሁንና ይህንን መጠይቅ በተመለከተ እንደ ተጨማሪ ማብራርያ ልንፅናናበት የሚያስችለን የሊቃውንት ንግግር ኣለ።

ለምሳሌ አል-አሉሲ [ረሂመሁላህ] እንዳሉት
« በዱንያ ላይ ሳለ ሚስት ያልነበረው ወንድ በዱንያ ላይ ሳያገቡ ከሞቱ ሴቶች መሃል አላህ የፈለገውን በጀነት ይሰጠዋል። ከአንድ በላይ ባሎችን አግብታ የነበረቿ ደግሞ ለመጨረሻው ባሏ ትሆናለች። ወይም የመጀመርያው ባሏ ሳይፈታት ተለይቷት [ሞቶባት… ] ከሆነ እሱን ታገባዋለች።

ኣሊያም ከዱንያ ባሎቿ መሃል ከሷ ጋር በመልካም ስነምግባር የተኗኗረውን ትመርጣለች።
የካፊር ሚስት የነበረች ከሆነች ደግሞ እሷ ጀነት ከገባች አላህ ለፈለገው ይድራታል።» ብለዋል

【[ሩሁል-መዓኒ: 25/136] ይህም በመጅሙዑ-ፈታዋ ወመሳኢሉ-ኢብኑ ዑሰይሚን : 2/52 ላይ ሰፍሯል።】

ስለዚህ ዋናው አሳሳቢ ጉዳይ ጀነት ውስጥ ያለውን ፀጋ በዝርዝር ማወቁ ሳይሆን ከአሳማሚው የእሳት ስቃይ ተርፎ ለዘለኣለማዊው ጀነት መብቃቱ ነው።

እዚያ ይደረስ እንጂ
وَلَكُمْ فِيهَا مَا تَشْتَهِي أَنْفُسُكُمْ وَلَكُمْ فِيهَا مَا تَدَّعُونَ
እንዳለው
በጀነት ወስጥ ነፍሶቻችን የሚሹት፣ የሚፈልጉት፣ የሚናፍቁት፣ የሚከጅሉትና የሚጓጉለት ሁሉ እንዳለልን ነግሮናል፡፡ በዚህም የጌታችን ችሮታ ለወንዶች ሆነ ለሴቶች ልዩነት የለምና አምላካችን አላህ ለጀነቱ ያብቃን።

እምነታችንን እንደ ሽርክ፣ ኩፍርና ኒፋቅ ካሉት በካይ ነገሮች በመከላከል፣ ከቢድዓና ከሀራም ነገሮችም በመራቅ፣ ግዴታ በተደረጉብንና በሌሎቹ መልካም ስራዎች ላይም በመትጋት አላህን እንለምነው።

አንተ ቸርና ለጋስ የሆንከው አላህ ሆይ ! የጀነት መግቢያ ብቸኛ ሰበብ የሆነውን እስልምናን እንዳጎናፀፍከን ሁሉ ወንጀላችንን ማረን። መጨረሻችንን አሳምርልን። በጀነትህም ምርጥ የሆነውን የትዳር አጋርና ልክ የሌለው ፀጋህን ለግሰን። ኣሚን

ወሰለላሁ ዓላ ነቢዪና ሙሀመድ ወዓላ ኣሊሂ ወሳህቢሂ ወሰለም።
-------------
01/12/1437
21/10/2015

Post a Comment

0 Comments