Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ” ክፍል ሶስት ለሶላት መቆም


“ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ”
ክፍል ሶስት
ለሶላት መቆም

[ሀ] ግዴታ ሶላቶችን ለመስገድ መቆም ከሶላት ማእዘኖች (አርካን) አንዱ ነው፡፡ ጌታችን አላህ እንዲህ ይላል፡- “ታዛዦች ሆናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡” [አልበቀራህ፡ 239] ነብዩም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግዴታ የሆነን ሶላት ቆመው እንጂ ሰግደው አያውቁም፡፡ ለምሳሌ መንገድ ሲጓዙ ግዴታ ያልሆኑ ሶላቶችን ከተቀመጡባት እንስሳ ላይ ሆነው ይሰግዱ ነበር፡፡ ነገር ግን ሶላቱ የግዴታ ሶላት ከሆነ ወርደው ቆመው ነበር የሚሰግዱት፡፡ አልኢማም ኢብኑ አብዲልበር ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “በግዴታ ሶላት ላይ መቆም በእያንዳንዱ ጤነኛ እና መቆም የሚችል ሁሉ ላይ ፅኑ ግዴታ ለመሆኑ ዑለማዎች ወጥ አቋም አላቸው፡፡” [አትተምሂድ፡ 6/138] ነገር ግን
[ለ] ህመምተኛ ከሆነ ግዴታም ይሁን ትርፍ ሶላት ተቀምጦ መስገድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ታመው ተቀምጠው ሰግደዋል፡፡ [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 77] ተቀምጦ የሚሰግድ ሰው ለሱጁድ የሚጠቀምበት ትራስ ወይም ሌላ ከፍ የሚያደርገው ነገር መጠቀም አይፈቀድለትም፡፡ በአንድ ወቅት ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አንድ የታመመን ሰው ሲጠይቁ ትራስ ላይ ሱጁድ ሲያደርግ ተመለከቱት፡፡ ይዘው ወረወሯት!! እንጨት ያዘ ሊሰግድበት (ሱጁድ ሊያደርግበት)፡፡ እሱንም ይዘው ወረወሩትና እንዲህ አሉ፡- “ከቻልክ መሬት ላይ ስገድ፡፡ ካልሆነ መጠቆምን ጠቁም፡፡ (ያቅሙን ያክል ዝቅ እያለ ማለት ነው፡፡) ሱጁድህን ከሩኩዕህ ዝቅ ያለ አድርገው፡፡” [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 78]
[ሐ] መቆም ቀርቶ ተቀምጦ መስገድም ያልቻለ ሰው ወይ ተንጋሎ ወይ ደግሞ በጎኑ ተጋድሞ መስገድ ይችላል፡፡ ሶሐባው ዒምራን ኢብኑ ሑሶይን ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላል፡- “ኪንታሮት ነበረብኝና የአላህ መልእክተኛን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም (እንዴት እንደምሰግድ) ስጠይቃቸው እንዲህ አሉኝ፡- “ቆመህ ስገድ፡፡ ካልቻልክ ተቀምጠህ፡፡ ካልቻልክ ደግሞ በጎንህ (ተጋድመህ ስገድ፡፡) [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 78]
[መ] መኪና፣ አውሮፕላን፣ ጀልባ እና መሰል መጓጓዣ ላይ እየተጓዘ ለመቆም ከተቸገረ ግዴታም ይሁን ትርፍ ሶላትን ተቀምጦ መስገድ ይቻላል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በጀልባ ላይ ስለመስገድ ሲጠየቁ “መስመጥን ካልፈራህ ቆመህ ስገድ” ብለዋል፡፡ [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 79] የጠላት ጥቃት ባንዣበበት የስጋት ወቅት ሶላት ወይም በጦርነት ውስጥ የሚሰገድ ሶላትም ባለበት መጓጓዣ ላይ ሆኖ መስገድ ይቻላል፡፡
[ሠ] ከዚህ በተጨማሪ ህመም ወይም እርጅና ወይም ድካም ያለበት ሰው ብትር ነገር ወይም ምሰሶ ተደግፎ መስገድ ይችላል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እድሜያቸው በገፋና ትልቅ ሰው በሆኑ ጊዜ ምሰሶን ይይዙ (ይደገፉ) ነበር፡፡ [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 79]
[ረ] ግዴታ ያልሆነን (ነፍል) ሶላት መቆም የሚችል ሰው እንኳን ቢሆን ተቀምጦ መስገድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ምንዳው (ሠዋቡ) በግማሽ ይቀንሳል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “የተቀማጭ ሶላት ቆሞ የሚሰገድን ግማሽ ያክል ነው” ይላሉ፡፡ [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 78]
[ሰ] የሌሊት ሶላትን (ተሀጁድን) በተመለከተ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አንዳንዴ ረጅም ሶላትን ቆመው ይሰግዱ ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ ረጅም ሶላትን ተቀምጠው ይሰግዱ ነበር፡፡ ታዲያ ቆመው ቁርኣንን ከቀሩ ቆመው ሩኩዕ ያደርጉ ነበር፡፡ እንዲሁም ተቀምጠው ከቀሩ ተቀምጠው ሩኩዕ ያደርጉ ነበር፡፡ [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 79] አንዳንዴ ግን ተቀምጠው ይሰግዱ ነበር፡፡ እንደተቀመጡ ሲቀሩ ቆይተው ሰላሳ ወይም አርባ አንቀፆች ያክል ሲቀሯቸው ይነሱና ቆመው ይቀራሉ፡፡ ከዚያም ሩኩዕና ሱጁድ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም በሁለተኛዋም ረከዐህ ልክ እንዲሁ ያደርጋሉ፡፡” [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 79-80] ነገር ግን የትርፍ ሶላቶችን ተቀምጠው ይሰግዱ የነበረው በህይወታቸው መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ [ሲፈቱ ሶላቲንነቢይ፡ 80] ስለዚህ ትርፍ ሶላትም ቢሆን በተቻለን ቆመን ለመስገድ ብንጠናከር ይበልጥ የተመረጠ ነው፡፡
ኢን ሻአላህ ይቀጥላል፡፡
(ጥቅምት 04/2008)

Post a Comment

0 Comments