Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ከተውበት ቡሀላ ወደ ወንጀል ከሚመልሡን ምክንያቶች መካከል


ከተውበት ቡሀላ ወደ ወንጀል ከሚመልሡን ምክንያቶች መካከል
የአላህ ሠላት እና ሠላም በመልዕክተኛው እና በባልደረባዎቻቸው ላይ ይሁን
✔ በርካቶቻችን የወንጀላችን መጠን እና አይነቱ ይለያይ እንጂ በወንጀሎች የተጠመድን መሆናችን ምንም ጥርጥር የሌለው ነው ። ሆኖም አላህ ያዘነላቸው ደግሞ ከገቡበት ወንጀል ለመውጣት ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ በተሳካ መልኩ ከወንጀላቸው ተውበት በማድረግ ይቆጠባሉ ሌላው ደግሞ ተውበት ለማድረግ ይፈልጋል ለተውበቱ ቦታ ካለመስጠቱ የተነሣ በድጋሚ ወደ አመፁ እና ወደ ወንጀሉ ለመመለስ ይዳረጋል ወደ ወንጀሉ ለመመለስ ከሚዳርጉት ማዘናጊያዎች መካከል
✔ ባሣለፈው ወንጀል አለመቆጨት እንዲሁም ቀድሞ የሠራውን ወንጀል እያስታወሰ መደሠት ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጎ ማሠብ ወይም ወንጀሉን ማቅለል ፦ ይህን አይነት ስሜት ልብ ውስጥ አስቀምጦ ተውበት ማድረግ ማለት በጭቃ ከመታጠብ የማይተናነስ ነገር ነው
✔ ጊዜአዊ ተውበት ማድረግ ለሣምንት ለወር ― ወይም ወንጀሉን ለመስራት ግዜ እስኪመቻችለት ድረስ የቶበተ መስሎ እራስን መሸወድ ይህም በወንጀል ላይ እንድንዘወትር ከሚያደርገን የሚቆጠር ነው
✔ ተውበትን ማዘግየት ፦ ይህ የሠይጣን ዋና ማዘናጊያ ነው ወንጀል በልብ ላይ ከባድ የሆነ ጭረትን ያሣርፋል ይህ ጭረት በፍጥነት ካልታከመ ወደ ጠባሳነት ተለውጦ ለማከም አዳጋች ይሆናል ይህ ከሆነ ደግም ልብ ይታወራል ልቡ የታወረ ደግሞ መሪ እንደ ሌለው መኪና ይሆናል
✔ በከፊል መቶበት ፦ ሁለት እና ከዛ በላይ ወንጀሎች እያሉበት ከአንድ ወንጀሉ ብቻ ቶበት ማድረግ ፋይዳ ቢስ ተውበት ነው የሚሆነው ምክንያቱም ወንጀል የመሣሣብ ባህሪ አለው አንድ ወንጀል ሌላኛውን ወንጀል የመቀስቀስ አቅም አለው
✔ የኢኽላስ ጉድለት ፦ ወንጀሉን የሚከለክለው ከአላህ ፍራቻ ውጪ ሌላ ነገር መሆን የለበት የሠዎች እይታ ፣ የኢኮኖሚ ችግር ፣ ያለመመቻቸት…እነዚህ እና መሠል ነገሮች ከወንጀል ለመቶበት መነሻ ሊሆኑት አይገባም ምክንያቱም እነዚህ ነገሮችን መፍራት ሢወገድለት ወደ ወንጀሉ ይመለሳልና ።
★ እነዚህ እና ሌሎችም ተጨማሪ ምክንያቶች የአንድን ሠውተውበት ዋጋ ቢስ ያደርጋሉ ከቶበተውም ወንጀል እንዳይቆጠብ ያደርጋሉ ።
★ በተውበት ላይ እንድንፀና ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል
✔ የተውበትን ሸርጥ አሞልቶ ማድረግ ተውበት ከማድረጋችን በፊት ሦስት ነገሮችን አሞልተን ማድረግ ይጠበቅብናል እነሡም
1 ወንጀሉን ሙሉ ለሙሉ ማቆም
2 ባለፈው ወንጀል መፀፀት
3 ወደ ወንጀሉ ላለመመለስ መወሠን
✔ ወደ ወንጀሉ ሊያዳርሱን የሚችሉ ነገሮችን መቁረጥ ምሣሌ ወንጀሉ ሡብሒ ሠላትን በሠአቱ አለመስገድ ከሆነ የዚህ ወንጀል መዳረሻ ሊሆን የሚችለው አርፍዶ መተኛት ነው ስለዚህ ይህን ወንጀል መቶበት የፈለገ ሠው አርፍዶ መተኛት አይኖርበትም
✔ አላህን በተውበት ላይ ፅናትን መለመን "ልቦችን ገለባባጭ የሆንከው ሆይ ልቤን በአንተ ዲን ላይ አፅናው "በማለት አላህን መማፀን
✔ ትዕግስት ማድረግ ያቺ ወንጀሉን እንድንሠራ የምታጣድፈን ወቅት ሊያልፍ እንደሚችል አውቀን መታገስ
✔ አላህ እየተቆጣጠረን መሆኑን ማወቅ እና መገንዘብ ።
እነዚህ እና መሠል ነገሮች ወደ ቶበትነው ወንጀል እንዳንመለስ በአላህ ፍቃድ ይረዳል
አላህን መሀርታውን እንጠይቀዋለት

Post a Comment

0 Comments