ያላለቀ ማስታወሻ!!
እያንዳንዱ የምንሰራው ስራ ነገ አላህ ፊት ስንቆም የማያሳፍረን መሆኑን እናስረግጥ፡፡ “ከመመርመራችሁ በፊት
እራሳችሁን መርምሩ” ይላሉ ዑመር ኢብኑልኸጣብ ረዲየላሁ ዐንሁ፡፡ ጥሩ ሴቶችን የሚመርጡት ጥሩ ወንዶች ናቸው፡፡
መጥፎ ሴቶችን የሚመርጡት ደግሞ መጥፎ ወንዶች ናቸው፡፡ እህቶች ሆይ! የምን አይነት ሰዎች ትኩረት እና ምርጫ
እንደሆንን በመመልከት ምን አይነት ስብእና እንዳለን መረዳት እንችላለን፡፡
እንደ ጤዛ ለሚረግፍ አላፊ ደስታ
ሲሉ አኺራቸውን የሚያጨልሙ ሰዎች ተወዳዳሪ የሌላቸው ቂሎች ናቸው፡፡ ብልጦች የነገ ዘላለማዊ ድሎትን በማለም ዛሬ
ለጥፋት የምትገፋፋ ነፍስያቸውን ይጫናሉ፡፡ ቂሎቹ አላህን በማመፅ የሚያገኟትን እርባና ቢስ ጊዜያዊ ደስታ ብልጦቹ
ለጌታቸው በማደር በተሟላ መልኩ ይጎናፀፉታል፡፡ ቂሎቹ አላህ ካዘዘባቸው ወሰን ላይ ስለቆሙ፣ ነፍሳቸውንም ስለገቱ
ደስታን የሚያጡ ይመስላቸዋል፡፡ ብልጦች ግን የአላህን ትእዛዝ በመፈፀም ማንም ያላየውን እርካታ ያጣጥማሉ፡፡ ወደው
አይደለም ቀደምቶቻችን “ንጉሶችና የንጉሳን ልጆች ያለንበትን ፀጋና ተድላ ቢያውቁ ኖሮ ሊነጥቁን ጦር ይሰብቁብን
ነበር” ማለታቸው፡፡ [አልዋቢሉስሶይዪብ፡ 110] ሱብሓነላህ! እንዴት አይነት ደስታ ውስጥ፣ እንዴት አይነት እርካታ
ውስጥ ቢሆኑ ነው? ለካስ እንዲህም በዒባዳህ ይረካል?! ለካስ እንዲህም የአላህን ትእዛዝ ለመፈፀም ደፋ ቀና
በማለት ነፍስን በሀሴት መሙላት ይቻላል?!! እዚህ ለመድረስ የሚፈለገው አንድ ነገር ነው!!! ኢማን!! ነብዩ
ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “መልካም ስራው ያስደሰተው፣ መጥፎ ስራው ያስከፋው ሰው እሱ ነው አማኝ!” ይላሉ፡፡
[ሶሒሑልጃሚዕ፡ 6294] ጌታችንም እንዲህ ይላል፡- “እነዚያ ያመኑት፡ ልቦቻቸው አላህን በማውሳት የሚረኩ
ናቸው፡፡” እመን አላህ በዋለልህ ፀጋ ትረካለህ፡፡ እመን ጌታህን በማመስገን ትረካለህ፡፡ እመን ፈተናዎችን በመታገስ
ትረካለህ፡፡ እመን የጌታህን ትእዛዝ በመፈፀም ትረካለህ፡፡ እመን ጌታህ ከከለከለህ ነገሮች በመራቅ እርካታን
ትጎናፀፋለህ፡፡ እመን እየረካህ ጌታህን ትገዛለህ፣ እየተገዛህም እርካታን ትጎናፀፋለህ!! ውስጥ አዋቂው ጌታህ ምን
እንደሚል ስማ “ንቁ! አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ!!” [አርረዕድ፡ 28] አዎ አማኝ የሆነ ሰው እርካታውን
የሚፈልገው ጌታውን በሚያስደስቱ ምግባሮች ነው፡፡ በሶላት በፆሙ ይረካል፡፡ በዚክሩ፣ ቁርኣንን በመቅራቱ ይረካል፡፡
ወላጆቹን በማገልገሉ ዝምድናን በመቀጠሉ ይረካል፡፡ ህግና ደንቡን በተከተለ ግብይቱ፣ ከሐራም በመጠበቁ ይረካል፡፡
ምላሱን በመሰብሰቡ፣ ስነ ምግባሩን በማለስለሱ ይረካል፡፡ በጥቅሉ ለመልካም በመነሳሳቱ ከክፉ እራሱን በማቀቡ
ይረካል፡፡ ወንዱ ለቤተሰቡ ቅን በመሆኑ እርካታ እንጂ የበታችነት አይሰማውም፡፡ ሴቷ ለባሏ ታዛዥ በመሆኗ እርካታ
እንጂ ባርነት አይሰማትም፡፡
አዎ ከእርካታ ጣራ ላይ መድረስ የሚሻ ጌታውን ይታዘዝ፡፡ ከዛሬ እርካታው በላይ
እጅግ የሚያስቋምጥ የሆነ ሌላ ደስታን፣ ሌላ እርካታን፣ ሌላ ሀሴትን ነገ ይጎናፀፋል፡፡ አይን ያላየው፣ ጆሮ
ያልሰማው፣ ልቦና ውስጥ ውል ብሎ የማያውቅ ልዩ መስተንግዶ ከአርረሕማን ዘንድ ይጠብቀዋል፡፡ እስኪ የትኛው የዱንያ
ፀጋ ነው ከዚህ ጋር የሚወዳደረው? እስኪ የትኛው የዚች ጠፊ አለም ደስታ ነው ከዚህ ጋር የሚነፃፀረው?!
እኔ እምልሽ እህቴ! ምን ፍለጋ ነው ቅጥ ያጣ አለባበስ የምትለብሺው? “ደስታ” እንዳትይኝ ሸሪዐዊ አለባበሳቸውን
ጠብቀው ካንቺ በተሻለ ደስታን የሚጎናፀፉት ስንትና ስንት ናቸው!! “ውበት” እንዳትይኝ ወወላሂ ወቢላሂ ወተላሂ
ውበት ያለው ስርኣት ካለው አለባበስ ውስጥ ነው፡፡ እመኚኝ ይሄ ቅጥ ያጣ አለባበስሽ አያምርብሽም!! “አይኔን
ግንባር ያርገው” ካልሽ አትጠራጠሪ የውስጥሽን መታወር ነው ገሀድ እያወጣሽ ያለሺው፡፡ ምናልባት “ውበት
እንደተመልካቹ ነው” እያልሽ እራስሽን ትሸውጂ ይሆናል፡፡ አልተሳሳትሽም ውበት እንደተመልካቹ ስለሆነ ብልግናም
ለባለጌዎች ያምራል!! አዎ ውበት እንደተመልካቹ ስለሆነ ጋጠ ወጥነትም ለጋጠ ወጦች ያምራል፡፡ ልክ ነሽ ውበት
እንደተመልካቹ ስለሆነ ርካሽነትም ለርካሾች ያምራል!! ልክ ነሽ ህሊናችን ሲገለበጥ አስተሳሰባችንም ምርጫችንም
ይገለበጣል፡፡
ምናልባት እንዲህ የምትለብሺው “የህይወት አጋር ፍለጋ” እንዳትይኝ በዚህ አለባበስሽ
አይናቸውን የሚጥሉብሽ ያለጥርጥር ርካሽ ወንዶች ናቸው፡፡ የህይወትሽ አጋር፣ ውሃ አጣጪሽ እንዲሆን የምትፈልጊው
ርካሽ ወንድ ነው? አላሁልሙስተዓን!!
እስኪ ውስጥሽን አዳምጪው፡፡ የወረደ አለባበስ የምትለብሺው የነቁ
በሚመስሉሽ፣ “ስም” ባላቸው ዘፋኞች፣ ነጮች፣ …. ከሃዲዎች፣ ጋጠ ወጦች ለመመሳሰል ነው ወይስ አይደለም? ከሆነ
ነገ አላህ ፊት ያለምንም አስተርጓሚ እርቃንሽን ለምርመራ ትቆሚያለሽ!! ያኔ ምን ይውጥሻል? በተለይ ደግሞ ጋጠ
ወጦችን ተከትለሽ ከፈፀምሺው ጉዳዩ ምን ያክል አሳፋሪ ምን ያክል አሸማቃቂ እንደሚሆን ለአፍታም ቢሆን ከዚያ አስፈሪ
ቦታ ላይ እራስሽን አቁሚና ታዘቢው፡፡ ነው ወይስ አንቺ ጀነትን አትፈልጊም? ታማኙና እውነተኛው፣ ከስሜታቸው
የማይናገሩት ነብይ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ አይነት ቅጥ ያጣ አለባበስ ላይ የወደቁ ሴቶችን ጀነትን ቀርቶ
ሽታዋንም አያገኙም እያሉ ነው፡፡ እኔ እምልሽ የኔ እህት! እጣ ፈንታሽ ይሄ እንዲሆን ትፈልጊያለሽን?!
አንተስ ወንድሜ! ፀጉርህን እንደ ቻይና ፅሁፍ አንጨባረህ መሄድህ ነው ውበቱ? የተውለቀለቀ ሱሪህን መቀመጫህ ላይ
ሸብ አድርገህ በቅጡ በማትሸፍን እራፊ መስገድህ ነው ንቃቱ? ነጩን ሰው ተከትለህ በእስኪኒ ሱሪ ተወጣጥረህ መውጣትህ
ነው ብቃቱ? ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂዑን!! ስማኝ እንጂ የኔ ወንድም ጧት ማታ የሚራገጡ ነጮችን ለማየት ቲቪ
እስክሪን ላይ እያፈጠጥክ መሰረታዊ የዲንህ መገለጫዎችን አለመለየትህ አያሳፍርምን? እኔ እምልህ የኔ ወንድም ዋጋ
ያልሰጠኸው ዲን ላይ ውዝግቦችን ሰምተክ “ማንን እንደምንከተል ግራ ገባን” ብትል ውሃ ይቋጥራል፡፡ ቀድሞ ነገር መቼ
ትኩረት ሰጥተኸው ነው ግራ የሚገባህ? ለመሆኑ ለኳስ የምትሰጠውን ትኩረትና ጊዜ ያክል ለዲንህ ሰጥተሃልን? ለ
“ዘመናዊ” ትምህርት የምትሰጠውን ዋጋ ያክል ለዲንህ ዋጋ ሰጥተሃልን? ለፖለቲካ የምትሰጠውን ቦታ ያክል ለዲንህ
ሰጥተሃልን? ለቢዝነስህ የምትሰጠውን ሽርፍራፊ ጊዜ ታክል ለእምነትህ ሰጥተሃልን? ታዲያ ዋጋ ባልሰጠኸው፣ ትኩረትህን
በነፈግከው ዲን ላይ ውዝግቦችን ሰምተህ “ማንን እንደምንከተል ግራ ገባን” ብትል ውሸት አይሆንብህምን? ራስን
ማታለልስ አይሆንምን?
ስማኝ እስኪ የኔ ወንድም! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ንቁ የአላህ ሸቀጥ
(ጀንናህ) ውድ ነች!!” እያሉ ነው፡፡ ይህን ስትሰማ ምን ያቃጭልብሃል? ለዲንህ ዋጋ ልትሰጥ፣ ለጀነትህ ልትለፋ
እንደሚገባ አትረዳምን?...
ፅሁፉ ሲጀመር ለአንዲት ወጣ ያለ አለባበስ ላስተዋልኩባት እህት ማስታወሻ
ነበር፡፡ ባልጠበቅኩት እዚህ ደረሰ፡፡ የተንገረበበ ነገር ቢኖረውም ምናልባት ፖስት ቢደረግ የሚጠቀምበት ይኖር
ይሆናል ብየ ስለገመትኩኝ አወጣሁት፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት 1/2008)
0 Comments