Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የ “ዘመን መለወጫ” ኮተቶች



የ “ዘመን መለወጫ” ኮተቶች

ኢትዮጵያ በምትከተለው ክርስቲያናዊው የዘመን አቆጣጠር መሰረት አዲስ አመት ሊገባ የያዝነው አመት እየተጠናቀቀ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ክስተት ተከትሎ የሚፈፀሙ እምነትን የሚጎዱ በርካታ ጥፋቶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ

1. ቀዳሚው ድግምትና ጥንቆላ ነው፡፡ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ነሀሴ ሊጠናቀቅ ሲል በየጠንቋዩ ቤት የሚልከሰከሱት እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ከዚያም አምስቱ ወይም ስድስቱ የጳጉሜ ቀናት መንገዶች በድግምት ስራዎች ይሞላሉ፡፡ በነዚህ ቀናት ማልዶ የወጣ ሰው እንዲራመዳቸው ታስቦ በጎረቤት መተላለፊያ እና ህዝብ በሚያዘወትራቸው መንገዶች ላይ ፍየሎች፣ ዶሮዎች፣ ድመቶች፣ ጥንቸሎች ወዘተ ታርደው ይጣላሉ፡፡ በደም የተነከሩ ሳንቲሞች፣ ብሮች፣ ጌጣ-ጌጦች፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች እዚህም እዚያም ወድቀው ይታያሉ፡፡ ጥንቆላና ድግምት
  • ከኢስላም የሚያስወጡ ከባባድ ወንጀሎች ናቸው፡፡
)وَاتَّبَعُوا مَا تَتْلُو الشَّيَاطِينُ عَلَى مُلْكِ سُلَيْمَانَ وَمَا كَفَرَ سُلَيْمَانُ وَلَكِنَّ الشَّيَاطِينَ كَفَرُوا يُعَلِّمُونَ النَّاسَ السِّحْرَ( البقرة: ١٠٢
“በሱለይማን ዘመነ-መንግስት ሸይጧኖች የሚያነቡትንም (ድግምት) ተከተሉ፡፡ ሱለይማን ግን አልካደም (ድግምተኛ አልነበረምና፡፡) ግና ሸይጧኖች ሰዎችን ድግምት የሚያስተምሩ ሲሆኑ ካዱ፡፡” [አልበቀራህ፡ 102]
ነብዩም ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-
 "ጠንቋይ ዘንድ ሄዶ በሚናገረው ያመነ፣ በሙሐመድ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ በወረደው ክዷል፡፡" [አስሶሒሐህ፡ 3387]
  • ደጋሚዎችና ከነሱ ዘንድ የሚመላለሱ ሰዎች መቼም ቢሆን ስኬት የላቸውም፡፡ ጌታችን እንዲህ ይላል፡- 
“ድግምተኛም በመጣበት ስፍራ ሁሉ አይቀናውም፡፡” [ጧሃ፡ 69]
  • ደጋሚዎች የሰዎችን ገንዘብ በማታለል የሚበዘብዙ መዥገሮች ናቸው፡፡ ገንዘቡን ለነሱ የሚሰጥ አካልም አላህ ፊት ተጠያቂ ነው፡፡ ነብዩ ዐለይሂስሰላም እንዲህ ብለዋል፡- 
"የኣደም ልጅ በቂያማህ ቀን አምስት ነገሮችን ሳይጠየቅ እግሮቹ አይንቀሳቀሱም፡፡ እድሜውን በምን እንዳጠፋው፤ ወጣትነቱን በምን እንደጨረሰው፤ ገንዘቡን ከየት እንዳመጣው፤ እንዲሁም በምን እንዳወጣው፤ ባወቀው ምን እንደሰራ፡፡" [አስሶሒሐህ፡ 946]
  •  ደጋሚዎች የነገር ቋቶች የማህበራዊ ህይወት ጠንቆች ናቸው፡፡ የተቸገረ ደንበኛቸው መፍተሄ ፈልጎ ሲመጣባቸው በብዛት የችግሩ መንስኤ የሆነው ወይ ጎረቤቱ፣ ወይ ዘመዱ ወይ ደግሞ የቤተሰቡ አባል እንደሆነ በመጠቆም ሰዎች ውስጣቸው እንዲሻክር አለመተማመን እንዲነግስ ያደርጋሉ፡፡ በድግምቶቹ ምክንያት የጤና መጓደል፣ የትዳር መፍረስ፣ የዝምድና መቆራረጥ፣ የጎረቤቶች በጎሪጥ መተያየት አልፎም ደም የሚያቃባ ግጭት እንዲከሰት ሁሉ ሰበብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
  • ጠንቋይና ደጋሚ ዘንድ የሚሄድ ሰው የተነገረውን ባያምን እንኳን ከባድ ቅጣት ይከተለዋል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- 
"ጠንቋይ ዘንድ ሄዶ ስለሆነ ነገር የጠየቀው የአርባ ቀን ሶላቱ ተቀባይነት የለውም፡፡" [ሙስሊም፡ 5957]

2. ሌላው በ “ዘመን መለወጫ” አካባቢ የሚፈፀመው ጥፋት በአንዳንድ አካባቢ ያለው ጳጉሜን ተከትሎ ለዱዓህ መሰባሰብ ነው፡፡ እነዚህ አካላት የጳጉሜ ዱዓህ “መቅቡል ነው” (ተቀባይነት ያለው ነው) በማለት ነው ወቅቱን በዱዓእ የሚያሳልፏት፡፡ በጣም የሚገርመው ለዱዓህ የሚጥጠሩት እስልምናን ያውቃሉ ሰዎችን ያስተምራሉ የሚባሉት ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም 
አላህ እውቀትን ከባሪያዎቹ መንጠቅን አይነጥቅም፡፡ ይልቁንም ዑለማዎችን በመውሰድ (በመግደል) እውቀትን ይወስዳል፡፡ ከዚያም ዓሊም እስከማይቀር ድረስ፡፡ በዚያኔ ሰዎች መሀይማንን መሪዎች አድርገው ይይዛሉ፡፡ ሲጠየቁም ያለ እውቀት ፈትዋ ይሰጣሉ፡፡ በዚህም ይጠማሉ፣ ያጠማሉም” 
ማለታቸው ምንኛ የሚደንቅ ሐቅ ነው?!! ዲን ያስተምራሉ ተብለው የሚታሰቡት አካላት ክርስቲያናዊ አቆጣጠርን መሰረት ያደረገ ዒባዳህ እየፈፀሙ ሰዎችን ወደ ጥፋት ሲወስዱ በገሃድ ይታያሉ፡፡

3. ሌላኛው የ “ዘመን መለወጫን” ተከትሎ የሚፈፀመው ጥፋት መስከረም አንድን ወይም እንቁጣጣሽን ማክበር ነው፡፡ አቆጣጠሩ ሀገራዊ እንጂ እምነታዊ መሰረት እንደሌለው ሊያሳምኑ በከንቱ የሚዳክሩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገሩ እጅጉን የፈጠጠ እውነታ ሆኖ ሳለ በዚህ ላይ የሚሸወድ መኖሩ እጅጉን የሚደንቅ ነው፡፡ ብቻ ለማንም እንደማይሰወር ባስብም ለማስታወስ ያክል አቆጣጠሩ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው በሚሲዮናውያን መሆኑ፣ አመቱ ሲፃፍ መጨረሻ ላይ “ዓመተ ምህረት” መባሉ፣ የነብዩ ዒሳን (ሰላም በሳቸው ላይ ይስፈንና) መወለድ መሰረት ያደረገ እንደሆነ መሞገታቸው እንዲሁም ይበልጥ ለማረጋገጥ የ “ዘመን መለወጫ” ወቅት ላይ “እንኳን ከዘመነ ምንትስ ወደ ዘመነ ምንትስ አደረሳችሁ ማለታቸው ጥሩ ጠቋሚ ናቸው፡፡

ስለዚህ ከየትኛውም ከአይሁድ፣ ከክርስቲያን እና ከሌሎች እምነቶች ጋር ከሚያመሳስሉ ነገሮች እራስን መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “በሰዎች የተመሳሰለ ከነሱው ነው” ይላሉና፡፡

ወሶለላሁ ዐላ ነቢይዪና ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊሂ ወሶሕቢሂ ወሰለም፡፡


(ኢብኑ ሙነወር፣ ነሐሴ 26/2007)


አድራሻዎቻችን ይቀላቀሉ

       
 ፌስቡክ    
      




Post a Comment

2 Comments