Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሙስሊም ያልሆነን ሁሉ እንድንዋጋ አልታዘዝንም


ሙስሊም ያልሆነን ሁሉ እንድንዋጋ አልታዘዝንም!

አልሀምዱሊላህ፤ ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላምና እዝነት በመልእክተኛው ላይ ይስፈን።
በመቀጠል፤

ዲናዊ መረጃዎችን ስንገነዘብ ጥቅል እና ቁንፅል መልእክቶችን ማጣጣም አለመቻል ከባድ የአመለካከት ስህተትን ይፈጥራል። ከጥንት ጀምሮ የጂሀድን ፅንሰሀሳብ በማፋለስና ኢስላምን ሰዎችን ሁሉ ለማጥፋት በሚያልም ደመኛ ሀይማኖት ቀርፀው በማሳየት የሚታወቁት ኸዋሪጆች ናቸው። የአመለካከታቸው ጠርዘኝነት በነብያዊ እውቀት ከበሰለ ትውልድ የሚሰወር ስላልነበር እንዲሁም የነብዩ ባልደረቦችና ተከታዮቻቸው ስለተጋፈጧቸው ሙስሊሙ ዘንድ ቦታ አጥተው ኖረዋል። ይሁንና፤ ከነዚህ ብርቅ ትውልዶች ዘመን በራቀ ቁጥር የዋሆች ላይ ብዥታን በመፍጠር ብዙዎችን ከጎናቸው ያሰልፋሉ። ይህንን በማስመልከት ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ እንዲህ ብለዋል፤ «ኸዋሪጆችም እንደዚሁ፤ የሰይፍና የግድያ ሰዎች በመሆናቸው ጀማአን መፃረራቸው ግልፅ ሆኖ ነበር። ዛሬ ግን ብዙሀኑ ማህበረሰብ አያውቃቸውም» አኑቡዋት መፅሀፍ ገፅ 193

በሀይማኖት ማስገደድ የለም የሚለው ቁርአናዊ መልእክትና እና በጂሀድ አንቀፆች መካከል ምንም አይነት መጣረስ የለም። ምክኒያቱም፤ አጋሪዎችን መዋጋትን የሚያዙ አንቀፆች መልእክት አስገድዶ ኢስላምን እንዲቀበሉ ለማድረግ አይደለም። ይህ ቢሆን ኖሮ ኢስላም ድልን ባገኘበት ጊዜ አይሁድ እና ክርስቲያኖችን ሁሉ እንዲሰልሙ ባስገደደ ነበር። የኢስላምን ታሪክ ከምንጩ ላጠና ግን በሁሉም ዘመናት አይሁድና ክርስቲያኖች በኢስላማዊ መስተዳድር ጥላ ስር ማንነታቸውን ሳይቀይሩ የአምልኮ መብታቸው ተከብሮላቸው ኖረዋል።

ሸይኹ’ል ኢስላም ኢብኑ ተይሚይያህ ይህንን አስመልክቶ ያሰፈሩት ትምህርት እጅግ ጠቃሚ መርሆ ነው።
«“ሰዎች ከአላህ በቀር (እውነተኛ) አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን እስኪመሰክሩ፣ እንዲሁም ሰላትንም እስኪያዘወትሩና ዘካትንም እስኪሰጡ ደረስ እንድጋደላቸው ታዝዣለሁ” የሚለው ነብያዊ ንግግር የተፈለገበት እነዚያ ሊጋደሏቸው አላህ የፈቀደ የሆኑት ተዋጊ ጠላቶችን ነው፤ አላህ ቃላችንን እንድናከብርላቸው ያዘዘን የሆኑትን ቃል ኪዳነኞች ለማለት ፈልገው አይደለም..» [መጅሙዑ’ል-ፈታዋ (19/20)] ¹

በሌላ ንግግራቸውም፤
« መጋደል የተባለው ሀይማኖታችንን ግልፅ ስናደርግ የሚዋጋንን አካል ብቻ ነው። ስለዚህም አላህ እንዲህ ብሏል፤
{ﻭَﻗَﺎﺗِﻠُﻮا ﻓِﻲ ﺳَﺒِﻴﻞِ اﻟﻠَّﻪِ اﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳُﻘَﺎﺗِﻠُﻮﻧَﻜُﻢْ ﻭَﻻَ ﺗَﻌْﺘَﺪُﻭا ۚ ﺇِﻥَّ اﻟﻠَّﻪَ ﻻَ ﻳُﺤِﺐُّ اﻟْﻤُﻌْﺘَﺪِﻳﻦَ} البقرة 190

«እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን በአላህ መንገድ ተጋደሉ፡፡ ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎን አይወድምና፡፡»
አል በቀራህ 190
[መጅሙዑል ፈታዋ 28/354] ²

በተመሳሳይ ማብራሪያ ታላቁ አሊም
ኢብኑልዓረቢ አልማሊኪይ ረሂመሁላህ እንዲህ ብለዋል፤ «አጋሪዎችን ግደሏቸው» የሚለው ጥቅል ገለፃ ቢሆንም ከላይ እንደተብራራው የነብዩ አስተምህሮ ህፃናት፣ ሴቶች፣ ባህታውያንን እንዲሁም ምንም ውስጥ የማይገቡ ሲቪሎችን ከዚህ ጥቅል ገለፃ ለይቷል። ይህ አንቀፅ የሚመለከተው ሙስሊሞችን የሚወጉትን ወይም ለመውጋትና ለማወክ የሚዘጋጁትን ነው። ስለዚህ የአንቀፁ መልእክት "የሚጋደሏችሁን አጋሪዎች ተጋደሉ!" ለማለት መሆኑ ግልፅ ነው። [አህካሙል ቁርአን 4/177 ] ³

ኢስላም በመጋደል ያዘዘው ሁለት አይነት ክፍሎችን ብቻ ነው።
1) ሙስሊሞች ላይ ጥቃት የሚሰነዝርና በህልውናቸው ላይ የሚያሴር፤ ኢስላምን በሀይል ለማክሰም የሚንቀሳቀስ። ይህ አይነቱን ጠለት መከላከል እና መመከት በሁሉም ህዝቦችና በሁሉም ሀይማኖቶች እንዲሁም ማህበራዊ ህጎች የተደነገገ ህገዊ እርምጃ ነው።

2) በኢስላም ላይ ማእቀብ የሚጥልን አካል መታገል ሲሆን፤ ይህም የሀቅ ድምፅ እንዳይሰማ በማድረግ ኢስላማዊ ጥሪን የሚከለክል፣ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ለኢስላም እንዳይጋበዙ መሰናክል የሚሆንን አካል በማሸነፍ ኢስላምን የመስበክ ነፃነትን መጎናፀፍ ነው።

ልብ ልንለው የሚገባው ግን በሁለቱም አይነት ዉጊያዎች ላይ ነብያዊ የጦርነት ስርአቶችንና የምርኮኛ አያያዝን የተመለከቱ የእዝነት መመሪያዎችን መጠበቅ ግድ እንደሚል ነው።

አላህ ሀቅን ለመረዳትና ለማስረዳት እውቀትን፣ ትእግስትንና ጥበብን ይለግሰን፤ ከወገንተኝነትና አላዋቂነት ይጠብቀን፤ ሀቅና ባጢለወ ከተመሳሰለባቸው ኸዋሪጆች ብዥታዎች ይሰውረን።


አልወሰጢያ ወልኢዕቲዳል
ዙልቂዕዳ 17, 1436 ዓ.ሒ

www.fb.com/wesetiya
--------------------
¹ قال شيخ الإسلام ابن تيمية – رحمه الله - : " وقول النبي صلى الله عليه وسلم ( أُمِرْتُ أَنْ أُقَاتِلَ النَّاسَ حَتَّى يَشْهَدُوا أَنْ لاَ إِلهَ إِلاَّ الله وَأَنَّ مُحَمَّداً رَسُولُ الله وَيُقِيمُوا الصَّلاَةَ وُيُؤتُوا الزَّكَاة ) مراده : قتال المحاربين الذين أذن الله في قتالهم لم يُرد قتال المعاهَدين الذين أمر الله بوفاء عهدهم " . انتهى من " مجموع الفتاوى " ( 19 / 20 ) .

² قال شيخ الإسلام ابن تيمية – رحمه الله – : " القتال هو لمن يقاتلنا إذا أردنا إظهار دين الله ، كما قال الله تعالى ( وَقَاتِلُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ الَّذِينَ يُقَاتِلُونَكُمْ وَلَا تَعْتَدُوا إنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْمُعْتَدِينَ ) البقرة/ 190 " . انتهى من " مجموع الفتاوى " (28 / 354 ) .

³ قال ابن العربي المالكي – رحمه الله - : " قوله تعالى ( فَاقْتُلُوا الْمُشْرِكِينَ) عامٌّ في كل مشرك ، لكنَّ السنَّة خصَّت منه من تقدم ذكره قبل هذا من امرأة ، وصبي ، وراهب ، وحُشوة [ وهم رذال الناس ، وتبعهم ، ومن لا شأن له فيهم ] ، حسبما تقدم بيانه وبقي تحت اللفظ : مَن كان محارباً أو مستعدّاً للحرابة والإذاية ، وتبيَّن أن المراد بالآية : اقتلوا المشركين الذين يحاربونكم " انتهى من " أحكام القرآن " ( 4 / 177 )

Post a Comment

0 Comments