Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ለቢድዐ ከለላ የሚሰጥ ትግል ከስኬት አያደርስም

ለቢድዐ ከለላ የሚሰጥ ትግል ከስኬት አያደርስም
ዛሬ በርካቶች ረብ የለሽ ወሬ ላይ በተጠመዱበት፣ ከቁርኣን እና ከሀዲስ ይልቅ የቡድን መሪዎቻውን ቃል ባስቀደሙበት እንዲሁም ከወርቃማው የሶሐባና የተከታዮቻቸው እውቀት ባይተዋር በሆኑበት ጊዜ የአላህን፣ የመልእክተኛውን፣ የሶሀቦችን ቃል እያጣቀሰ የሚያወራ ሰው ምንኛ የታደለ ነው? የበርካቶችን ፌስቡክ ፕሮፋይል እዩማ፡፡ ስለ ዲን በማውራታቸው በስሱ ትደሰቱ ይሆናል፡፡ ወደላይ ወደታች ስትቃኙ ግን ደስታችሁ ይተናል፡፡ አንድም የሚጨበጥ ነገር አይታይም፡፡ እንዲሁ ቢከፍቱት ተልባ፡፡ “ዲን ተነካ” ብለን ላንቃችን እስከሚበጠስ እንጮሃለን፡፡ ሲፈተሸ ግን የዲን ስሙ እንጂ ሽታውም የለም፡፡ “አለማወቃችን ነው” እንዳትሉኝ፡፡ እሱ መች ጠፋኝና፡፡ እኔን ግራ የሚገባኝ የጩኸታችንን ያክል ስለዲን ያለንን ግንዛቤ ለማስፋት አለመሞከራችን ነው፡፡ ትላንትም ወሬ፡፡ ዛሬም ወሬ፡፡ አድሮ ጥጃ? እስከ መቼ ትኩረታችን ገለባው ላይ ይሆናል? ለምንስ share, comment, like ስናደርግ እየመረጥን በማይረባው ላይ ሆነ? ብዙዎችን አስተውሉ፡፡ “አናውቅም” ብለው አርፈው አይቀመጡም፡፡ በመሰረታዊ የዲን ጉዳይ ላይ ሳይቀር ያለ ማስረጃ በባዶ ይሟገታሉ እንጂ፡፡ ፕሮፋይላቸው ውስጥ ስትገቡ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ብልግና ሳይቀር ያጋጥማችኋል፡፡ ሁሉንም ማለቴ እንዳልሆነ እስከምናገር አትጠብቁኝ፡፡ ብቻ የአላህን፣ የመልእክተኛውን፣ የሶሀቦችን ቃል እያጣቀሱ ማውራት ለብዙዎች አለመጣሙ፣ ለብዙዎች አለመሳቡ ክስረት ነው፣ አሳዛኝ መክሸፍ፡፡ ስለለፋን ብቻ ድል አይመጣም፡፡ የምንታገልለት ዲን ትእዛዛትና ክልከላዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ለዚያ ዋጋ ካልሰጠን ስለምንድን ነው ልፋታችን? መቼስ ተግባር አልባ “እመን ትድናለህ” እርባና እንደሌለው ለማናችንም አይሰወረንም፡፡
ጌታችን “በሆነም ጉዳይ ብተጨቃጨቁ ወደአላህና ወደ መልእክተኛው መልሱት” እያለ እኛ በመካከላችን ለሚነሱ ልዩነቶች ምንም መመለሻ፣ ማጣቀሻ የሌለን እስኪመስል በየፊናችን ከጮህን ነስሩ እንዴት ይመጣል? ጌታችን “አላህን የምትወዱ ከሆናችሁ ተከተሉኝ አላህ ይወዳችኋልና በላቸው” እያለ እኛ መልክተኛውን ከመከተል በላይ፣ ከኢስላማዊ ህግጋት በላይ ለግለሰቦች ቅድሚያ ከሰጠን ድሉ ከየት ይመጣል? ጌታችን “እነዚያ የመልክተኛውን ትእዛዝ የሚጥሱ ሰዎች ፈተና እንዳታገኛቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ” ማለቱን ዘንግተን ትእዛዝ እየጣስን ከፈተና እንዴት ይወጣል? ዛሬ ነብያዊ ትእዛዝን ባለማክበራችን ምክኒያት ከፈተና ማዕበል ውስጥ እየዋለልን የእጃችንንም እያጨድን ነው፡፡ ታዲያ ላለንበት ውርደት ካበቃን ጥፋት ካልራቅን የሚደርስብን ነገር ምን ይገርመናል? እስኪ ማነው ጤፍ ዘርቶ ባቄላ የሚጠብቅ? ያለነው ውርደት ላይ ነው፡፡ መውጫው ደግሞ ትእዛዝ ማክበር ነው፡፡ “ውርደትና ክብረ-ቢስነት ትእዛዜን በጣሰ ላይ ይሁን” ይላሉ መልእክተኛው ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ ትእዛዛቸውን ጥሰን ክብረ-ቢሶችም ሆነናል፡፡ ስለሆነም ለማስመለስ ትእዛዝ ማክበር አለብን ለሱና መታገል፡፡ ከቢድዐ ባህር ውስጥ እየዋለሉ ስለ ድል ማሰብ ቅዠት ነው- የቢድዐን አስከፊ ጥላ ለሚረዳ፡፡ እዚህ ጋር “ድል ቢድዐን ሳይሆን ሱናን ተከትሎ ነው የሚመጣው” የሚለው የሸይኽ አልባኒ አባባል ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ሶሐቦች ተራራ ሳይሆን ዐለምን ያንቀጠቀጡት በሱና እንጂ በቢድዐ አልነበረም፡፡ ቢድዐ ላይማ ሰይፍ ነበሩ የተሰላ ሰይፍ፡፡ እኛ ግን በዙሪያችን ያሉ ሙብተዲዖችን ላለማስከፋት ስንል ከሶሀቦች በላይ ሒክማ አዋቂ፣ ከሶሐቦች በላይ አርቆ አሳቢ፣ ከሶሐቦች በላይ ለኡማው ተቆርቋሪ፣ ከሶሐቦች በላይ ለአንድነት አሳቢ .. “ሆነን” ከሙብተዲዕ ጋር ህብረት ፈጥረናል፡፡ ሱኒው ላይ ጠንክረን ሙብተዲዑ ላይ ግን ለስልሰናል፡፡ አጥፊውን ላንጠቅመው ካለበት እንዳይነቃ የእንቅልፍ ክኒን ሰጥተናል፡፡ ከባባድ ቢድዐ ስናይ ምንም አይጎረብጠንም፡፡ ይልቁንም የሚጎረብጠን ስለቢድዐ መወራቱ ነው፡፡ ዛሬ ስንቶች ናቸው ቢድዐን የሚያወግዙ ሐዲሶች ሲነሱ የሚያንገሸግሻቸው? ሐዲሳቸውን እየጠሉ “ነብዩን እንወዳለን” የሚል ሙግት ምን የሚሉት ልክፍት ነው? ከእነኚህ አስተዋይ መሳዮች “አቀራረቡን እንጂ ርእሱን አንቃወምም” የሚሉ አሉ፡፡ እውነታቸውን ከሆነ ለምን አቀራረቡን አስተካክለው ስለቢድዐ አያስተምሩም? ቢድዐ አደገኛ ነቀርሳ ነው፡፡ የቢድዐ ፍቅር ያደረበት ሰው በብዛት ቢድዐን የሚያወግዙ የሱና ሰዎችን አይወድም፡፡ በዚህ ረገድ “በዱንያ ላይ የሐዲስ ሰዎችን የማይጠላ ሙብተዲዕ የለም፡፡ አንድ ሰው ቢድዐ ሲፈጥር የሐዲስ ጥፍጥና ከልቡ ላይ ይነሳል” የሚለው የኢማም አሕመድ ኢብኑ ሲናን ንግግር አስደንጋጭ ደወል ነው-ልቡ ላልታወረ፡፡
ዛሬ ትእዛዝ ጥሰን፣ ሱናን አርክሰን፣ ቢድዐን አንግሰን የውርደት ካባ ተከናንበናል፡፡ ሸሪዐው ባስቀመጠው ሳይሆን እኛ በቀየስነው ውሽልሽል እቅድ ካለንበት ውርደት እንወጣለን ብለን እንገምታለን፡፡ በግምትም እንለፋለን፡፡ እየለፋንም ፈውስ በመዘግየቱ እንቆዝማለን፡፡ ውስጣችን ቆስሎ ከላይ እብጠት ቢያስከትል እብጠቱን ብቻ ለማጥፋት መጣር ሞኝነት ነው፡፡ ከውስጥ ሆዱ በተፈጠረ ህመም ሳቢያ ከንፈሩ ነፍሮ ከንፈሩን ቫስሊን በመቀባት ከህመሙ ፈውስ የሚጠብቅ የለም፡፡ እኛ ግን ከቫስሊንም አልፈን አደገኛ አሲዶችን ሳይቀር እንደ መድሃኒት እንጠቀማለን፡፡ ከዚያም ፈውስ እንጠብቃለን፡፡ በመጀመሪያ ህመማችንን እንለይ፡፡ ህክምናውም ከስሩ ይጀምር፡፡ በሽታው ካልታወቀ ህክምናው በሽታ ነው የሚጨምረው፡፡ ያለነው ለውርደታችን ሰበብ የሆነን ቢድዐ ላይ ነው፡፡ በብዛት ካለንበት ውርደት ለመውጣት ስንለፋም በቢድዐ ነው፡፡ ከቢድዐ በቢድዐ አይወጣም፡፡ ቢወጣም መልሶ ወደ ቢድዐ ነው፡፡ “እሾህን በእሾህ” እዚህ ጋር አይሰራም፡፡ ያለበለዚያ “ታጥቦ ጭቃ” አይነት ነገር ነው፡፡ እውነተኛ መፍተሄ የሚሻ ከሱናው ጀልባ ላይ ይሳፈር፡፡ የሶሐቦችን መንገድም ይምረጥ፡፡ ኢማሙ ማሊክን አላህ ይማራቸው፡፡ ሰሚ ጆሮ ካለ መሬት ጠብ የማይል ምክር መክረውናል፡፡ እንዲህ ሲሉ፡
“የዚህ ህዝብ መጨረሻ የሚስተካከለው የመጀመሪያው በተስተካከለበት ብቻ ነው፡፡” የመጀመሪያው በምን ተስተካከለ? በሱናና በሱና ብቻ!! ቢድዐ ስንዝር ታክል ለሙስሊሞች በጎ ውለታ የለውም፡፡ የሚመስለው ካለ መነፀሩን ይቀይር፡፡ እይታ ከተንሸዋረረ ተኩላም በግ ትመስላለች፡፡ አሁንም ኢማሙ ማሊክ እንዲህ ይላሉ፡- “ሱና የኑሕ መርከብ ነች፡፡ የተሳፈረባት ይተርፋል፡፡ ከሷ ወደ ኋላ የቀረ ይሰጥማል::” አዎ! የኑሕ መርከብ ዐለም በማዕበል በምትናጥበት አማራጭ ባልነበረበት ቀውጢ ጊዜ ብቸኛ አማራጭ ነበረች፡፡ “ልጄ ሆይ ከኛ ጋር ተሳፈር” በሚለው የሱና ጥሪ ላይ እምነት ባለመጣሉ ወደ ተራራ የወጣው የኑሕ ልጅ እንኳ የውሃ እራት ሆኗል፡፡ ልክ እንዲሁ ዛሬ የሙስሊሙ ዓለም በቢድዐ ማዕበል እየተናጠ ነው፡፡ ታዲያ አንዳንዱ በአስተማማኙ የሱና መድህን ላይ ያለው እምነት በመቅለሉ ከነፍስያ ተራራ ላይ ተንጠላጥሎ ከማዕበሉ ለመትረፍ እየቧጨረ ነው፡፡
መዳንን ፈልገህ መንገዱን ካልለየህ
እባክህ አትልፋ
ጀልባ በየብስ ላይ መቼ ሲጓዝ አየህ?
“ጌታችን ሆይ! የእውነትን እውነትነት አሳየን፡፡ መከተሉንም አድለን፡፡ የሀሰትንም ሀሰትነት አሳየን፡፡ መራቁንም አድለን”

https://www.facebook.com/IbnuMunewor