Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ፋቲሐን ቀርተው ሲጨርሱ “ኣሚን” ማለት


ፋቲሐን ቀርተው ሲጨርሱ “ኣሚን” ማለት

ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ፋቲሐን ቀርተው ሲጨርሱ “ኣሚን” ይሉ ነበር፡፡ “ኣሚን” ማለት እራሱን የቻለ ዱዓእ ነው፡፡ ስለሆነም ቂራኣት ድምፅ ከፍ ተደርጎ በሚቀራበት ጊዜ ከሆነ ድምፃችንን ከፍ አድርገን “ኣሚን” ማለት የሚወደድ ሲሆን ድምፃችንን ዝቅ አድርገን በምንቀራበት ጊዜ ከሆነ ደግሞ ዝቅ አድርገን “ኣሚን” እንላለን፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከኢማም ኋላ ተከትለው የሚሰግዱትንም በዚህ ያዙ ነበር፣ እንዲህ በማለት ፡- “ኢማሙ ገይሪልመግዱቢ ዐለይሂም ወለዷሊን” ሲል ኣሚን በሉ፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
የኣሚን ጥቅሞቹ
1. “ኣሚን” ማለት ወንጀልን ያስምራል፡- ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “የሱ ኣሚን ከመላእክት ኣሚን ጋር የገጠመለት ከወንጀሉ ያለፈው ይማርለታል፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
2. “ኣሚን” ማለት ዱዓችንን ተቀባይነት ያስገኛል፡- ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ኣሚን በሉ አላህ ይቀበላችኋል” ብለዋል፡፡ [ሙስሊም]
3. ጠላትን ያስቆጫል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡- “የሁዶች በሰላምታችሁ እና በተእሚን (አሚን) የተመቃኟችሁን ያክል አልተመቃኟችሁም፡፡” [ቡኻሪ]
ባይሆን እነዚህን ፋይዳዎች ለማገኘት “ኣሚን” ስንል ባግባቡ ሊሆን ይገባል፡፡ እሱም ኢማሙ “ኣሚን” ማለት ሲጀምር ወዲያው ተከትለነው አብረን ነው ማለት ያለብን፡፡ ብዙ ሰዎች ግን ኢማሙ ገና “ኣሚን” ማለት ሳይጀምር ነው ቀድመውት የሚሉት፡፡ ሐዲሡ ላይ ግን “ኢማሙ ኣሚን ሲል ኣሚን በሉ ነው” የሚለው፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] እንዳውም ብዙዎቹ ሰዎች የኢማሙ “ኣሚን” ማለት አለማለት ደንታቸውም አይደለም፡፡ የራሳቸውን ነው እንደፈለጉ የሚሉት፡፡ አንዳንድ ኢማሞች ደግሞ ከናካቴው ወይ “ኣሚን” አይሉም ወይ ደግሞ ድምፃቸውን አያሰሙም ወይ ደግሞ በሱናው መሰረት ሳብ አድርገው ሳይሆን ቁርጥ አድርገው ነው የሚሉት፡፡
ስለዚህ ስርኣቱን በጠበቀ መልኩ “ኣሚን” በማለት ተጠቃሚ ልንሆን ይገባል፡፡
በነገራችን ላይ 1
“ኣሚን” ማለት “ጌታችን ሆይ! ዱዓችንን ተቀበለን” ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ 2
ፋቲሐን የቀራ ሰው ከሶላት ውጭ እንኳን ቢሆን “ኣሚን” ማለቱ የተወደደ እንደሆነ ዑለማዎች ይገልፃሉ፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሐምሌ 29/2007)