ለይለት አልቀድር
- የመወሰኛው ሌሊት ተብሎ ለምን ተሰየመ?
- የለይለት አልቀድር ትሩፋትና የላቀ ደረጃው
- ለይለቱል ቀድር የትኛው ሌሊት ነው?
- በለይለቱል ቀድር ምሽት የሚወደዱ ሥራዎች
- የለይለቱል ቀድር ምልክቶች
- መመሪያዎች
የመወሰኛው ሌሊት ተብሎ ለምን ተሰየመ?
1 - በዚህ የተሰየመው ‹‹አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም፡፡›› [አል-አንዓም፡91] እንዳለው ዓይነት ክቡርነቱን ለማመልከት ነው ተብሏል፡፡ሌሊቱ ቁርኣን የወረደበት (የተላለፈበት)፣መላእኮች፣ የአላህ ረሕመት፣በረከቱና ምሕረቱ የሚወርድበት ሌሊት በመሆኑ ምክንያት ከበሬታን የተጎናጸፈ ነው ማለት ነው፡፡ ሌሊቱን በዕባዳ ሕያው የሚያደርግ ሰው የተከበረ ነው ማለትም ይሆናል ተብሏል፡፡
2 - ቀደር የሚለው ቃል መጣበብ በሚለው ትርጉሙ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ይህም ቁርኣን ውስጥ እንደተመለከተው ‹‹በርሱም ላይ ሲሳዩ የተጠበበበት ሰው፣›› [አል-ጦላቅ፡7]
እንዳለው ዓይነት ሌሊቱ በግልጽ ተለይቶ ያልታወቀ ድብቅ መሆኑን ወይም በዚያ ሌሊት ምድር ወደ መሬት በወረዱ መላእኮች ብዛት የሚጣበብ መሆኑን ለማመልከት ነውም ተብሏል፡፡
3 - ቀድር ማለት መወሰን በሚለው ትርጉሙ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ይህም በዚያ ሌሊት ዓመቱን የሚመለከቱ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ አላህ አንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹በውስጧ የተወሰነው ነገር ሁሉ ይለያል፡፡›› [አል-ዱኻን፡4] [ፈትሕ አልባሪ ቅጽ 4 ገጽ 255]
የለይለት አልቀድር ትሩፋትና የላቀ ደረጃው
1 - ቁርኣን የወረደበት ሌሊት ነው
አላህ ፡- ‹‹እኛ (ቁርኣንን) በመወሰኛይቱ (በከበረችው) ሌሊት አወረድነው፡፡›› [አል- ቀድር፡1] ብሏል፡፡2 - ሌሊቱ ከአንድ ሺሕ ሌሊት በላጭ ነው
አላህ ፡- ‹‹መወሰኛይቱ ሌሊት ከሺሕ ወር በላጭ ናት፡፡›› [አል- ቀድር፡3] ብሏል፡3 - በዚያ ሌሊት መላእክትና ሩሕ (መንፈስ) ይወርዳሉ
አላህ ፡- ‹‹በርሷ ውስጥ መላእክትና መንፈሱ በጌታቸው ፈቃድ በነገሩ ሁሉ ይወርዳሉ፡፡›› [አል- ቀድር፡4] ብሏል፡፡ከአቡ ሁረይራ በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ፡- ‹‹የመወሰኛው ሌሊት (ለይለቱል ቀድር) ሃያ ሰባተኛው ሌሊት፣ወይም ሃያ ዘጠነኛው ሌሊት ነው፤በዚያ ሌሊት በመሬት ላይ የመላእኮች ቁጥር ከአሸዋ ቁጥር የበለጠ ነው፡፡›› [በእብን ኹዘይማ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
4 - የሰላም ሌሊት ነው
እንዲህ ብሏል ፡- አላህ ‹‹እርስዋ እስከ ጎህ መቅደድ ድረስ ሰላም ብቻ ናት፡፡›› [አል- ቀድር፡5] ይህም ሌሊቱ ሙሉ በሙሉ እስከ ጎህ መቅደድ ድረስ በጎ ነገር ብቻ እንጂ ምንም ክፉ ነገር የሌለበት ሌሊት ነው ማለት ነው፡፡5 - ሌሊቱ ብሩክ ሌሊት ነው
‹‹እኛ (ቁርኣንን) በተባረከች ሌሊት ውስጥ አወረድነው፤ እኛ አስፈራሪዎች ነበርንና፡፡›› [አል- ዱኻን፡3]6 - የዓመቱ ጉዳዮች ተወስነው ይለዩበታል
አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹በውስጧ የተወሰነው ነገር ሁሉ ይለያል፡፡›› [አል-ዱኻን፡4]7 - የአላህን ቃል በማመንና ምንዳውን በማሰብ ሌሊቱን (በሶላትና በዕባዳ) ያሳለፈ ሰው ላለፈው ኃጢአቱ ምሕረት ያገኛል
የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹ የአላህን ቃል በማመንና ምንዳውን በማሰብ የመወሰኛውን ሌሊት (ለይለቱል ቀድርን በሶላትና በዕባዳ) የቆመ ሰው ላለፈው ኃጢኣቱ ምሕረት ይደረግለታል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡ለይለቱል ቀድር የትኛው ሌሊት ነው?
ሙስሊሙ በረመዷን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት በተለይም በኢተጋማሽ (ውትር) ቀኖች ማለትም በ21፣በ23፣በ25፣በ27ና በ29 ውስጥ ለዕባዳ ልዩ ጥረት እንዲያደርግ ለማነሳሳት አላህ ይህን ሌሊት በነዚህ ቀናት ውስጥ ደብቆታል፡፡ነቢዩ ﷺ ‹‹ለይለት አልቀድርን ኢተጋማሽ (ውትር) በሆኑ የመጨረሻዎቹ የረመዷን አስር ቀናት ውስጥ ተጠባብቃችሁ ፈልጉ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡
አንዳንድ የዕውቀት ባለቤቶች ማስረጃዎቹን አንድ ላይ በማጣመር ሌሊቱ በነዚህ ሌሊቶች መካከል የሚዘዋወር መሆኑን አውስተዋል፡፡
በለይለቱል ቀድር ምሽት የሚወደዱ ሥራዎች
1 - እዕትካፍ
እዕትካፍ ማለትም ለዕባዳ በመስጊድ ውስጥ መቀመጥ ለይለት አልቀድር በሚጠበቅባቸው ውትር ቀናት ብቻ ሳይሆን በአስሩም ቀናት በሙሉ ነው፡፡ ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከረመዷን የመጨረሻዎቹን አስር ቀናት እዕትካፍ ያደርጉ ነበር፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡2 - የአላህን ቃል በማመንና አጅሩን በማሰብ ሌሊቶቹን በዕባዳ ማሳለፍ
የአላህ መልእክተኛ ﷺ፡- ‹‹የአላህን ቃል በማመንና ምንዳውን በማሰብ የመወሰኛውን ሌሊት (ለይለቱል ቀድርን በሶላትና በዕባዳ) የቆመ ሰው ላለፈው ኃጢኣቱ ምሕረት ይደረግለታል፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡3 - ዱዓእ ማድረግ
ዓእሻ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ‹‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ለይለቱል ቀድር ቢገጥመኝ ምን ብዬ ዱዓእ ላድርግ? ስላቸው፣‹አል’ሏሁምመ እን’ነከ ዐፉው’ዉን ቱሕቡል ዐፍወ ፈዕፉ ዐን’ኒ› (አላህ ሆይ! አንተ በጣም ይቅር ባይ ነህ፣ይቅርባይነትን ትወዳለህና ይቅር በለኝ) በይ አሉኝ፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡4 - ለዕባዳ ጥረት ያደርጉ ዘንድ ቤተሰብን ከእንቅልፍ መቀስቀስ
ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት፡- ‹‹ነቢዩ ﷺ የረመዷን የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ሲጀመር ሽርጣቸውን (መቀነታቸውን) ያጠብቁ፣ሌሊቶቹን (በዕባዳ) ሕያው ያደርጉና ቤተሰባቸውንም (ለዕባዳ ከእንቅልፍ) ይቀሰቅሱ ነበር፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡የለይለቱል ቀድር ምልክቶች
1 - ሞቃታማም ቀዝቃዛም ያልሆነ ብሩህ ሌሊት ነው
ከጃቢር ብን ዐብደላህ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል ፡- ‹‹ለይለቱል ቀድርን እንዳይ ተደርጎ ነበር፣ከዚያ እንዲረሳው ተደረገ፤ በመጨራሻዎቹ አስር ቀናት ሌሊቶች ውስጥ ሲሆን፣ የማይከብድ ለቀቅ ያለ፣ብርሃናማ፣ሞቃታማም ቀዝቃዛም ያልሆነ ሌሊት ነው፡፡›› [በእብን ኹዘይማህ የተዘገበ] ብለዋል፡፡2 - በነጋታው ጸሐይ ነጭና ውጋገን የሌላት ሆና ትወጣለች
ኡበይ ብን ከዕብ (ረዐ) ስለ ምልክቶቹ ሲጠየቁ ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ በነገሩን ምልክት መሰረት በዚያ ቀን ጸሐይ ወጋገን የሌላት ሆና ትወጣለች፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋል፡፡መመሪያዎች
1 - የዓመቱ ምርጥ ሌሊቶች በመሆናቸው፣አንድ ሙስሊም በመጨረሻዎቹ አስር ሌሊቶች ውስጥ የዕባዳ ዓይነቶችን ማብዛት ይኖርበታል፡፡2 - አንድ ሙስሊም ተመራጭ የሆኑ ወቅቶችን፣የዕባዳና የመልካም ሥራዎች አዝመራን በአልባሌ ነገር፣በዋዛ ፈዛዛ፣አስፈላጊ ባልሆነ የበዛ ሸመታና ዙረት ማባከን የለበትም፡፡
http://www.amharicfiqh.com/elm/Fasting/The_Night_of_Qadr.aspx
0 Comments