Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጥያቄ፦ ዘካን ለመውሰድ እጁን የዘረጋ ሁሉ ዘካ ይገባዋልን?



ጥያቄ፦ ዘካን ለመውሰድ እጁን የዘረጋ ሁሉ ዘካ ይገባዋልን?
መልስ፦ ዘካን ለመውሰድ እጁን የዘረጋ ሁሉ ዘካ አይገባውም። ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ሀብታምም ሆነው ገንዘብ ለመውሰድ እጃቸውን ይዘረጋሉና። የዚህ አይነቱ ሰው በቂያማ ቀን ተቀስቅሶ ሲመጣ ፊቱ ላይ ቁራጭ ስጋ እንኳ አይኖረውም። አላህ ይጠብቀን። ሕዝብ በሚቆምበት በቂያማ ቀን የዚህ አይነቱ ሰው የፊት አጥንቶቹ በቆዳ ሳይሸፈኑ በግልፅ እየታዩ ይመጣል። ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) << ገንዘብ ለማብዛት ፈልጎ ሰዎችን ገንዘብ እንዲሰጡት የሚጠይቅ ሰው የእሳት ፍም ነው የሚጠይቀው ያብዛው ወይም ያሳንሰው።>> ብለዋል (ሙስሊም ዘግበውታል)
በዚህ አጋጣሚ ሀብታም ሆነው ሳሉ ችክ ብለው ሰውን የሚለምኑትንና የዘካ ባለመብት ሳይሆኑ ዘካ የሚቀበሉትን ሰዎች ሐራም እየበሉ መሆናቸውን አስጠነቅቃቸዋለሁ። አላህን ሊፈሩ ይገባል። ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) << የተብቃቃ ሰው አላህ እንዲብቃቃ ያደርገዋል (ከመጠየቅ) የተቆጠበም ሰው አላህ ቁጥብ ያደርገዋል። >> ብለዋል (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል) ነገር ግን አንድ ሰው ዘካ ስጠኝ ብሎ እጁን ቢዘረጋልህና የዘካ ባለመብት መስሎህ ብትሰጠው አንተ ግዴታህን ተወጥተሃል። ተጠያቂነት የለብህም። ከሰጠህ በሗላ ዘካ እንደማይገባው ብታውቅ እንኳ እንደገና የመስጠት ግዴታ የለብህም። የዚህም ማስረጃ የሚከተለው የነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሐዲስ ነው፦
<< ሰውየው መጀመሪያ ዝሙተኛ ለሆነች ሴት ሰደቃ ሰጠና ሰዎች በማግስቱ ሌሊት ለዝሙተኛ ሴት ሰደቃ ተሰጠ ብለው አወሩ። ሰውየውም <<አልሐምዱሊላህ>>አለ። ከዚያም በሚቀጥለው ሌሊት ሰውየው ሰደቃ ሰጠና። ሰደቃው ሌባ እጅ ገባ። በነጋታው ሰዎቹ ሌሊቱን ለሌባ ሰደቃ ተሰጠ ብለው አወሩ። ሰውየው በሦስተኛው ሌሊትም ሰደቃ ሲሰጥ ሰደቃውን ሀብታም ወሰደው። ሰዎች አሁንም አሁንም በጧት ተነስተው ማታ ደግሞ ለሀብታም ሰደቃ ተሰጠ ብለው አወሩ። ከዚያም ሰውየው << አልሐምዱሊላህ ለዝሙተኛ ፣ ለሌባ ፣ ለሀብታም ሰደቃ ሰጠሁ >> አለ። ከዚያም ሰውየው (አላህ ዘንድ) እንዲህ ተባለ፦
<< የአንተ ሰደቃ (ምፅዋት) ተቀባይነት አግኝታለች፤ ዝሙተኛዋ አንተ በሰጠሃት ሰደቃ ምክንያት ከዝሙት ትቆጠብ ይሆናል። ሌባውም ተብቃቅቶ ከሌብነት ሊታቀብ ይችላል። ሀብታሙም ነገሩን በማገናዘብ ራሱም ሰደቃ ሊሰጥ ይችላል። >> (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ወንድሜ ሆይ! እውነተኛና ልባዊ ኒያ ምን ያክል ጥቅም እንደሚሰጥ ተመልከት። ስለዚህ ዘካ እንድትሰጠው የጠየቀህን ሰው ብትሰጠውና ከዚያ በሗላ ሰውየው ሀብታም መሆኑ ቢገለፅልህ አንተ ድሃ መሆኑን በመገመት ስለሰጠኽው እንደገና ዘካ የማውጣት ግዳታ የለብህም።
(ሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን ረሒመሁላህ)

Taju Nasir